ሰው ለዓለም አቀፍ ደህንነት ያወጣቸው ዕቅዶች
“ይህ ሁሉ ካለፈ በኋል ፈዋሾች ለመሆን እንፈልጋለን። አዲስ የዓለም ሥርዓት ብዬ በልበ ሙሉነት የምጠራውን ሁኔታ ለማፋጠን የተቻለንን ሁሉ ለማድረግ እንፈልጋለን።”—የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ጥር 1991 ከኢራቅ ጋር የተደረገው ጦርነት ከጀመረ በኋላ የተናገሩት።
“የፕሬዚዳንት ቡሽ የአዲስ ዓለም ሥርዓት ጽንሰ-ሐሳብ ለሕግ የበላይነት ተገዥ የመሆንን አስፈላጊነትና መንግሥታት ነፃነትና ፍትሕ ለማስፈን የጋራ ሐላፊነት ያለባቸው መሆኑን ማመን እንዳለባቸው አጥብቆ ያሳስባል። ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ጋር አዲስ ዘመን እየመጣ ነው።”—በአውስትራሊያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ነሐሴ 1991 የተናገሩት
“ዛሬ ማታ በምድር ዙሪያ እየተስፋፋ ያለውን የዲሞክራሲ ድራማ ስመለከት ምናልባት፣—ምናልባት—ወደ አዲሱ የዓለም ሥርዓት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየቀረብን ሳይሆን እንደማይቀር ይሰማኛል።”—የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ መስከረም 1991 የተናገሩት
ቡዙዎቹ የዓለም መሪዎች እንደ ፕሬዚዳንት ቡሽ ስለወደፊቱ ጊዜ በልበ ሙሉነት እየተናገሩ ነው። ይህን ያህል ልበ ሙሉ ለመሆናቸው በቂ ምክንያት አለን? ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የተፈጸሙ ሁኔታዎች ይህን የመሰለ ብሩሕ ተስፋ እንዲኖረን የሚያስችሉ ናቸውን? የፖለቲካ ሰዎች ዓለም አቀፍ ደህነት ለማምጣት ይችላሉ ብለህ ታስባለህን?
የሰው ልጅ ያወጣው ታላቅ ዕቅድ
ጦርነት ደህና ሁን የሚል በቴሌቪዥን ላይ የቀረበ ጥናታዊ ፊልም “በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የመጨረሻዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ በየወሩ ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች የገደሉ ነበር” በማለት ገልጿል። በወቅቱ የነበሩ መንግሥታት እንደዚህ ዓይነት ጦርነት ዳግመኛ እንዳይደርስ የሚያግድ ዕቅድ እንደሚያስፈልግ ተሰማቸው። ጦርነቱ ገና በመካሄድ ላይ እያለ የ50 መንግሥታት ተወካዮች ከዚያ በፊት ታቅዶ የማያውቅ የዓለም አቀፍ ደህንነት ዕቅድ አወጡ። ይህም እቅድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ነበር። የቻርተሩ መቅድም “ተከታዮቹን ትውልዶች ከጦርነት መቅሠፍት ለማዳን” ቁርጥ ውሳኔ መደረጉን ይገልጻል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል የሚሆኑ መንግሥታት ሁሉ “ዓለም አቀፍ ሰላምና ደህነት ለማስከበር [ኃይላቸውን ሁሉ] ማስተባበር” ነበረባቸው።
ከአርባ አንድ ቀናት በኋላ በጃፓን አገር በሂሮሽማ ከተማ ላይ አቶሚክ ቦምብ በአይሮፕላን ተጣለ። ቦምቡ ከከተማዋ እምብርት ከፍ ብሎ በመፈንዳት ከ70,000 የሚበልጡ ሰዎችን ገድሏል። ይህ ቦምብና ሦስት ቀናት ቆይቶ በናጋሳኪ ላይ የተጣለው ፍንዳታ ከጃፓን ጋር ይደረግ የነበረውን ጦርነት በተቀላጠፈ መንገድ ወደ ፍጻሜ አምጥቶታል። የጃፓን ተባባሪ የነበረችው ጀርመንም ግንቦት 7, 1945 እጅ ሰጥታ ስለነበር ሁለተኛው የዓለም ጦርነትም አበቃ። ይሁን እንጂ ይህ ጦርነት የጦርነቶች ሁሉ ፍጻሜ ሆኖአልን?
አልሆነም። የሰው ዘር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከ19 ሚሊዮን በላይ ሕይወት ያጠፋ 150 አነስተኛ ጦርነቶችን አይቷል። ታላቁ የተባበሩት መንግሥታት ዕቅድ ዓለም አቀፍ ደህንነት እንዳላመጣ ግልጽ ነው። ዕቅዱ የከሸፈው ለምንድን ነው?
ቀዝቃዛው ጦርነት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕቅድ አውጭዎች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ተባባሪዎች በነበሩት መንግሥታት መካከል ትልቅ ፉክክር ይፈጠራል ብለው አላሰቡም ነበር። ብዙ መንግሥታት ቀዝቃዛው ጦርነት በተባለውና በከፊልም በኮሙኒዝምና በካፒታሊዝም መሃል በነበረው የኃያልነት ትግል ውስጥ አንደኛውን ወገን ደግፈው ይታገሉ ነበር። በሁለቱም ጎራዎች የሚገኙ መንግሥታት ኃይላቸውን አስተባብረው ጦርነት ከማጥፋት ይልቅ በአካባቢ ግጭቶች ወይም ውጊያዎች ላይ ተቃራኒ ወገኖችን ደግፈዋል። ይህን በማድረጋቸውም በእስያ፣ በአፍሪካና በአሜሪካ አገሮች እርስ በርሳቸው ተዋግተዋል።
በ1960ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይ ቀዝቃዛው ጦርነት ረገብ ማለት ጀመረ፤ በ1975 35 መንግሥታት የሄልስንኪ ስምምነት በመባል የሚጠራውን ውል በተፈራረሙ ጊዜ ቀዝቃዛው ጦርነት በከፍተኛ ደረጃ ረገበ። በስምምነቱ ከተሳተፉት አገሮች መሃል ሶቪየት ኅብረትና ዩናይትድ ስቴትስ እንዲሁም የእነዚህ አገሮች ተባባሪዎች የሆኑ የአውሮፓ መንግሥታት ይገኛሉ። ሁሉም “ለሰላምና ደህንነት” አብረው ለመሥራትና “የማንኛውንም አገር የግዛት አንድነት ወይም የፖለቲካዊ ነፃነት ወይም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በመጋፋት ወይም ከተባበሩት መንግሥታት ዓላማዎች ጋር በሚጋጭ በማንኛውም መንገድ ከማስፈራራትና በኃይል ከመጠቀም . . . ለመቆጠብ” እንደሚጥሩ ቃል ገብተዋል።
ይሁን እንጂ እነዚህም ሐሳቦች ቢሆኑ ምንም ፍሬ አላስገኙም። በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ በልዕለ ኃያላኑ መንግሥታት መሃል የነበረው ትግል እንደገና ተፋፋመ። ነገሮች በጣም ከመበላሸታቸው የተነሣ በ1982 አዲስ ተመርጠው የነበሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ዶክተር ያቪየር ፔሪዝ ዴ ኩዌላ የድርጅታቸው ጥረት አለመሳካቱን አምነው በመቀበል “አዲስ ዓይነት ዓለም አቀፍ ብጥብጥ” እንደሚነሳ አስጠንቅቀው ነበር።
ሆኖም ዛሬ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊም ሆነ ሌሎች መሪዎች ብሩህ ተስፋ እንዳለ ይገልጻሉ። የዜና ዘገባዎች ስለ “ድሕረ-ቀዝቃዛ ጦርነት ዘመን” ማውሳት ጀምረዋል። ታዲያ ይህ ለውጥ የመጣው እንዴት ነው?
“የድሕረ-ቀዝቃዛ ጦርነት ዘመን”
ለቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ 35 መንግሥታት ያደረጉት የአውሮፓ የደህንነትና የትብብር ጉባዔ ነበር። እነዚህ መንግሥታት መስከረም 1986 የስቶክሆልም ሰነድ የተባለውን ውል ተፈራረሙና የ1975ቱን የሄልስንኪ ስምምነት በፊርማቸው እንደገና አጸደቁ።a የስቶክሆልሙ ሰነድ የወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ብዙ ደንቦችን ይዟል። ሲፕሪ የተባለው ድርጅት (Stockholm International Peace Research Institute- የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም) በ1990 የዓመት መጽሐፉ ላይ “ያለፉት ሦስት ዓመታት ውጤቶች የሚያበረታቱ ናቸው። አፈጻጸሙም የስቶክሆልሙ ሰነድ የሚያዝዘውን የጽሑፍ ግዴታ መብለጥ ጀምሯል” ብሎአል።
ከዚያም በ1987 ልዕለ ኃይላን መንግሥታቱ ከ500 እስከ 5000 ኪሎ ሜትር ርቀት ሊመቱ የሚችሉትን ከምድር የሚተኮሱ ሚሳይሎች ለማጥፋት ተስማሙ። “ሚሳይሎችንና ሚሳይል ተኳሾችን የማጥፋቱ ሥራ በወጣለት ፕሮግራም መሠረት በመካሄድ ላይ ነው። ስምምነቱ የሚጠይቃቸው ግዴታዎች በሁለቱም ወገኖች እየተከበሩ ነው” ይላል ሲፕሪ
የኒውክሌር ጦርነትን አደጋ ለመቀነስ ሌሎች እርምጃዎችም ተወስደዋል። ለምሳሌ ያህል በ1988 ልዕለ ኃያላኑ መንግሥታት “አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይሎችንና ከባሕር ሰርጓጅ መርከቦች የሚወነጨፉ ባለስቲክ ሚሳይሎችን” የሚመለከት ስምምነት ተፈራርመዋል። እያንዳንዱ ወገን እነዚህን መሣሪያዎች ከመተኮሱ በፊት “ሊተኩስ ስላሰበበት ቀን፣ ከየትና ወዴት እንደሚተኩስ ከሃያ አራት ሰዓት ከማያንስ ጊዜ በፊት” ለሌላው ወገን ማስታወቅ ይኖርበታል። ሲፕሪ እንደሚገልጸው ከሆነ እንደነዚህ ያሉት ውሎች “የአካባቢ ግጭቶች ተባብሰው ዓለም አቀፍ የኒውክሌር ጦርነት ወደመሆን እንዳይደርሱ የሚከላከሉ ናቸው።”
በዚህ ጊዜ ዓለም አቀፍ ደህንነትን የሚያሻሽሉ ዕቅዶች ተፋጥነዋል። ግንቦት 1990 በዋሽንግተን ዲ ሲ በተደረገው የልዕለ ኃያላን መንግሥታት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የሶቪየቱ ፕሬዚዳንት ሚክሃይል ጎርባቾብ በሁለቱ ጎራዎች የተሰለፉት የአውሮፓ አገሮች የሰላም ውል እንዲፈራረሙ ሐሳብ አቅርበው ነበር። በሐምሌ ወር 16ቱ የናቶ (NATO North Atlantic Treaty Organization)- የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት) ምዕራባውያን አገሮች በለንደን ከተማ ተሰበሰቡ። ሚክሃይል ጎርባቾቭ ላቀረቡት ረቂቅ ሐሳብ “ሁለቱም ወገኖች ከእንግዲህ ባላንጣዎች ስለአይደሉ ከማስፈራራት ወይም ኃይል ከመጠቀም የመቆጠብ ዓላማ እንዳላቸው የሚያረጋግጥ የጋራ መግለጫ እንዲፈራረሙ” ሐሳብ እናቀርባለን የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የአንድ አፍሪካዊ ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ ይህን እርምጃ “ወደ ዓለም ሰላም የሚያደርስ ታላቅ እርምጃ” ሲል ገልጾታል።
ከዚያም በሄልስንኪ ፊንላንድ የልዕለ ኃያላን መሪዎች ጉባኤ በሚደረግበት ዋዜማ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ቃል አቀባይ “[በመካከለኛው ምሥራቅ] የተፈጠረው የጦርነት ስጋት ለዓለም ሰላም የሚበጅ አዲስ የጋራ ጥረት እንድናደርግ እያስገደደን ነው” ብሏል። ኢራቅ ኩዌትን በወረረችና መካከለኛው ምሥራቅ በጦርነት እሳት የሚቀጣጠል በመሰለበት ጊዜ ሰላም ለማምጣት የሚደረገው ጥረት የተሰናከለ መስሎ ነበር። ነገር ግን በዩናይትድ ስቴትስ የተመራው ዓለም አቀፉ ኃይል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰጠው ሥልጣን ተጠቅሞ ወራሪዎቹን ወደ ገዛ አገራቸው መልሶአቸዋል። በዚህ ጦርነት ላይ የታየው ዓለም አቀፍ የዓላማ አንድነት አንዳንድ ሰዎች አዲስ የትብብር ዘመን መባቻ እንደቀረበ ተስፋ እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል።
ከዚያ ጊዜ ወዲህም ቢሆን የዓለም ሁኔታዎች ተጨማሪ ለውጥ አሳይተዋል። በተለይም ሶቪየት ህብረት ትባል የነበረችው አገር በአስደናቂ ሁኔታ ተለዋውጣለች። የቦልቲክ አገሮች ነፃነታቸውን እንዲያውጁ ተፈቀደላቸው። በሶቪየት ህብረት ውስጥ የነበሩ ሪፐብሊኮችም የእነዚህ አገሮች ምሳሌ በመከተል ነፃነታቸውን አውጁ። በኮሙኒስት ማዕከላዊ ቁጥጥር ፍጹም አንድነት ያላቸው ይመስሉ በነበሩ አገሮች የብሔረሰቦች ግጭት መታየት ጀመረ። በ1991 ማብቂያ ላይ ሶቪየት ኅብረት የተባለች አገር መኖርዋ በይፋ አከተመ።
በዓለም የፖለቲካ መድረክ ላይ የደረሱት እነዚህ ሥር ነቀል ለውጦች ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥሩ የአጋጣሚ በር ከፈቱለት። ይህን በሚመለከት ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “የዓለም አቀፍ ውጥረቶች መላላታቸውና በዩናይትድ ስቴትስና በሶቪየት ህብረት መሃል አዲስ የትብብር መንፈስ መፈጠሩ የመንግሥታቱ ድርጅት በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ አዲስና ይበልጥ የጎላ ሚና እንዲጫወት አስችሎታል” ብሏል።
ይህ የ47 ዓመት ዕድሜ ያለው ድርጅት የተቋቋመበትን ዓላማ ፈጽሞ ይገኝ ይሆንን? ዩናይትድ ስቴትስ “አዲስ የሰላም፣ የነፃነት፣ የብልጽግና ምዕተ-ዓመትና ሺህ ዓመት” ብሎ ወደጠራው ዘመን በእርግጥ እየገባን ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህ ስምምነት ካናዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሶቪየት ኅብረትና ሌሎች 32 አገሮች በሄሊስንኪ ከተፈራረሙአቸው ተከታታይ ስምምነቶች ሁሉ የመጀመሪያውና ዋናው ነው። የዋናው ስምምነት የይፋ ስሙ የአውሮፓ የደህንነትና የትብብር ጉባዔ የመጨረሻ ድንጋጌ የሚል ነበር። ተቀዳሚ ግቡም በምሥራቅና በምዕራብ መሃል ያለውን ዓለም አቀፍ ውጥረት መቀነስ ነበር። —ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ