ጦርነት የማይኖርበት ዓለም የሚመጣው መቼ ነው?
የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር የጸደቀው ጥቅምት 24, 1945 ነው። የተባበሩት መንግሥታት ሰዎች ለዓለም ሰላም ለማምጣት ከዚህ በፊት ከቀየሷቸው ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ስትራቴጂዎች ሁሉ የላቀ ነው። በወቅቱ 51 አባላት የነበሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለም ታሪክ ውስጥ ከተቋቋሙት ድርጅቶች ሁሉ ትልቁ ድርጅት ሆነ። በተጨማሪም በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰላምና ደኅንነት የሚያስከብር ሠራዊት ያለውና ጦርነት የሌለበት ዓለም ለማምጣት የታለመ አንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ተቋቋመ።
ዛሬ የተባበሩት መንግሥታት 185 አባል አገራት ስላሉት ከመቼውም ጊዜ በላይ ኃይል ያለው ሆኗል። ታዲያ በታሪክ ውስጥ ከታዩት ሁሉ ይበልጥ ኃይለኛ የሆነው ይህ ዓለም አቀፍ ድርጅት ታላላቅ ዓላማዎቹን ሙሉ በሙሉ መፈጸም የተሳነው ለምንድን ነው?
ሃይማኖት ትልቅ እንቅፋት ሆኗል
አንዱ ዐቢይ ችግር ሃይማኖት በዓለም ጉዳዮች ውስጥ የሚጫወተው ሚና ነው። እርግጥ የተባበሩት መንግሥታት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ይህን ድርጅት የዓለም ታላላቅ ሃይማኖቶች ሲደግፉት ቆይተዋል። ዳግማዊ ፖፕ ጆን ፓል የተባበሩት መንግሥታትን 50ኛ ዓመት ጠቅሰው ሲናገሩ የተባበሩት መንግሥታት “ሰላምን ለማምጣትና ለማስከበር የላቀ መሣሪያ ነው” ብለዋል። በመላው ዓለም ያሉ የሃይማኖት መሪዎች ከእርሳቸው ሐሳብ ጋር ይስማማሉ። ይሁን እንጂ ይህ በሃይማኖትና በመንግሥታት መካከል በዘዴ የሚደረግ ግንኙነት ሃይማኖት ለተባበሩት መንግሥታት እንቅፋትና ጎጂ የመሆኑን ሐቅ ሊሸሽግ አይችልም።
ለብዙ መቶ ዘመናት ሃይማኖት ብሔረተኝነት የሚንጸባረቅበትን ጥላቻ፣ ጦርነቶችና የዘር ጭፍጨፋዎች በማስፋፋት ወይም በመደገፍ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውቷል። በቅርብ ዓመታት በሃይማኖት አክራሪነት ሽፋን ጎረቤታሞች እርስ በርሳቸው ተገዳድለዋል። “የጎሣ ምንጠራ” የሚለው ቃል በባልካን ግዛቶች ውስጥ ከሚካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ መንገድ በሰፊው ተሠርቶበታል። ይሁን እንጂ በዚያ ጦርነት ውስጥ የተካፈሉ ብዙ ሰዎች በጣም እንዲጠላሉ ያደረጋቸው ከዘር ይልቅ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነገር ነው፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ ተመሳሳይ ዘር አላቸው። አዎን፣ ሃይማኖት በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ውስጥ እንደ ጎርፍ ለፈሰሰው ደም በአብዛኛው ተጠያቂ መሆን ይኖርበታል፤ እስካሁን ድረስም ይህን ደም መፋሰስ የተባበሩት መንግሥታት ሊያስቆመው አል ቻለም።
በቅርቡ አንድ የሃይማኖት ኮሌጅ ፕሮፌሰር “ምንም እንኳን ስሜትን የሚረብሽ ቢሆንም ቀዝቃዛው ጦርነት ባከተመበትና ሃይማኖታዊ ጦርነቶች እየጨመሩ በመጡበት ዓለም ውስጥ ከሁሉ የበለጠ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ተግባሮች አንዱ ስለ ሃይማኖትና ስለ ዘር ጭፍጨፋ ጉዳይ መመርመር ነው” ብለዋል። ሃይማኖት በዛሬው ጊዜ ለዓለም ሰላም የሚደረጉ ጥረቶችን ምን ያህል እያጨናገፈ እንዳለ እየታወቀ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት በ1981 ያወጣው የአቋም መግለጫ እንዲህ ይላል፦ “በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች አሁንም ቢሆን በሃይማኖት ወይም በእምነት ሳቢያ አለመግባባቶችና ልዩነቶች መኖራቸው በጣም አሳሳቢ በመሆኑ እንደነዚህ ያሉትን በተለያዩ መልኮች የሚገለጹ አለመግባባቶች ለማስወገድ እና በሃይማኖት ወይም በእምነት ሳቢያ ልዩነቶች እንዳይፈጠሩ ለመከላከልና ለመዋጋት ማናቸውንም አስፈላጊ እርምጃዎች በፍጥነት ለመውሰድ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።”
የተባበሩት መንግሥታት ከዚህ የአቋም መግለጫ ጋር በመስማማት 1995 የመቻቻል ዓመት እንዲሆን አውጅዋል። ሆኖም ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ለመናገር በሃይማኖት በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ሰላምና ደኅንነት ለማምጣት ይቻላልን?
የሃይማኖት የወደፊት ሁኔታ
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ አንድ ትንቢት ለዚህ ምላሽ ይሰጠናል። ትንቢቱ እንደ ‘ንግሥት’ ሆና ስለ ተቀመጠችና ‘በምድር ነገሥታት ላይ ስለ ነገሠች’ አንዲት ምሳሌያዊት ‘ታላቅ ጋለሞታ’ ይናገራል። ይህች ጋለሞታ ‘ተቀማጥላ’ ትኖራለች፤ ከዓለም መንግሥታትም ጋር ግንኙነት አላት። እነዚህ መንግሥታት ጋለሞታይቱ ተመችቷት በምትጋልብበት ‘አንድ ቀይ አውሬ’ ተመስለዋል። (ራእይ 17:1–5, 18፤ 18:7) “ታላቂቱ ባቢሎን” በመባል የምትታወቀው ይህች ኃይለኛ የሆነችና ሥነ ምግባር የጎደላት ሴት ይህን ስም ያገኘችው የጣዖት አምልኮ ምንጭ ከሆነችው ከጥንቷ ባቢሎን ነው። በአሁኑ ወቅት ጋለሞታይቱ የምታመለክተው በመንግሥታት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ የሚገቡትን ሁሉንም የዓለም ሃይማኖቶች ነው።
አምላክ ከጊዜ በኋላ በአውሬው ወታደራዊ ኃይሎች ልብ ውስጥ እርምጃ እንዲወስዱ ሐሳብ እንደሚያስገባ በመናገር ታሪኩ ይቀጥላል። እነዚህ “ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፣ ሥጋዋንም ይበላሉ፣ በእሳትም ያቃጥሉአታል።” (ራእይ 17:16)a በዚህ መንገድ ኃያላን መንግሥታት ሐሰተኛ ሃይማኖትን የማስወገድ ዘመቻ እንዲያደርጉ በማንቀሳቀስ ይሖዋ አምላክ ራሱ ቀዳሚ ሆኖ እርምጃ ይወስዳል። ዓለም አቀፉ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ከተዋቡ ቤተ መቅደሶቹና የጸሎት ቤቶቹ ጋር ሙሉ በሙሉ ይደመሰሳል። በዚያን ወቅት ሃይማኖት ፖለቲከኞች ሰላምና ደኅንነት ለማምጣት ለሚያደርጉት ጥረት እንቅፋት መሆኑ ይቀራል። ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜም ቢሆን በምድር ላይ እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት ይኖር ይሆን?
ሰብዓዊ አለፍጽምና
የሃይማኖት መጥፋት ጦርነት የሌለበት ዓለም ለማምጣት ጥርጊያ መንገድ እንደሚሆን በእርግጥ ዋስትና ይሆናልን? በፍጹም አይሆንም። የተባበሩት መንግሥታት የሚያጋጥመው አንድ መጥፎ ሁኔታ እንዳለ ይቀጥላል። በአንድ በኩል ሰዎች ሰላምና ደኅንነት ይፈልጋሉ። በሌላ በኩል ግን ለሰላምና ደኅንነት ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥሩት ራሳቸው ሰዎች ናቸው። ጥላቻ፣ ኩራት፣ ለሌሎች ጥቅም አለማሰብ፣ ራስ ወዳድነት እና ድንቁርና የግጭቶችና የጦርነቶች መንሥኤ የሆኑ ሰብዓዊ ባሕርያት ናቸው።—ያዕቆብ 4:1–4
መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በዘመናችን “ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ” ይሆናሉ በማለት አስቀድሞ ተናግሯል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1–4
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ “ዓለም በብዙ ማኅበረሰቦች ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በተስፋፋ ማኅበራዊና ሥነ ምግባራዊ ቀውስ ውስጥ ገብቷል” ሲሉ አምነዋል። የቱንም ያህል የዲፕሎማሲ ጥረቶች ቢደረጉም በሰብዓዊው አለፍጽምና ምክንያት የሚመጡትን መጥፎ ባሕርያት ሊከላከሉ አልቻሉም።—ከዘፍጥረት 8:21 እና ከኤርምያስ 17:9 ጋር አወዳድር።
የሰላም መስፍን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ
የተባበሩት መንግሥታት ለዓለም ሰላም የማምጣት ችሎታ እንደሌለው ግልጽ ነው። ምንም እንኳ ከፍተኛ ዓላማዎች ቢኖሯቸውም የተባበሩት መንግሥታት አባላትና ደጋፊዎች በሙሉ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” ይላል። (ኤርምያስ 10:23) ከዚህም በላይ አምላክ “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ” ብሏል።—መዝሙር 146:3
መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ በልጁ ‘በሰላሙ መስፍን’ አማካኝነት ምን እንደሚያደርግ ይናገራል። ኢሳይያስ 9:6, 7 እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ [“መስፍን” አዓት] ተብሎ ይጠራል። . . . [“ለመስፍናዊ አገዛዙና” አዓት] ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም።”
የዓለም ብሔራት ለ50 ዓመታት ያልተሳኩ ጥረቶችን በማድረግ ሲደክሙ ቆይተዋል። በጣም ቅርብ በሆነ ጊዜ ውስጥ ጋለሞታ መሰል ሃይማኖታዊ ድርጅቶችን ያጠፋሉ። ከዚያ በኋላ “የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እና የሰማይ ተዋጊ ሠራዊቱ ሰብዓዊ መንግሥታትን በጠቅላላ ጠራርገው ያጠፏቸዋል፤ በተጨማሪም የአምላክን ሉዓላዊነት የማይቀበሉትን ሰዎች በሙሉ ከሕልውና ውጪ ያደርጓቸዋል። (ራእይ 19:11–21፤ ከዳንኤል 2:44 ጋር አወዳድር።) በዚህ መንገድ ይሖዋ አምላክ ጦርነት የሌለበት ዓለም ያመጣል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ታላቂቱ ባቢሎንን በተመለከተ ጠለቅ ያለ ጥናት ለማድረግ ከፈለግህ በ1988 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ከምዕራፍ 33 እስከ 37 ተመልከት።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ክርስቲያኖች ለተባበሩት መንግሥታት ያላቸው አመለካከት
በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ ሰብዓዊ መንግሥታት ብዙውን ጊዜ በአራዊት ተመስለዋል። (ዳንኤል 7:6, 12, 23፤ 8:20–22) ስለዚህ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ለብዙ አሥርተ ዓመታት ከራእይ ምዕራፍ 13 እስከ 17 ድረስ ያሉት አራዊት በአሁኑ ወቅት ያሉትን መንግሥታት እንደሚያመለክቱ ሲያሳውቅ ቆይቷል። ይህም በራእይ ምዕራፍ 17 ላይ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ባሉት ቀይ አውሬ የተመሰለውን የተባበሩት መንግሥታትን ይጨ ምራል።
ሆኖም ይህ ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋም ለመንግሥታት ወይም ለባለ ሥልጣናት ማናቸውንም ዓይነት ንቀት እንድናሳይ ሰበብ አይሆነንም። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ።”—ሮሜ 13:1, 2
በዚህ ምክንያት በፖለቲካ ረገድ ጥብቅ የገለልተኝነት አቋም ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች በሰብዓዊ መንግሥታት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አይገቡም። የለውጥ እንቅስቃሴ በጭራሽ አያነሣሱም ወይም ደግሞ በሕዝብ ዓመፅ ውስጥ አይሳተፉም። ከዚህ ይልቅ በሰብዓዊው ኅብረተሰብ ውስጥ ሕግና ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ አንድ ዓይነት መንግሥት እንደሚያስፈልግ ያውቃሉ።—ሮሜ 13:1–7፤ ቲቶ 3:1
የይሖዋ ምሥክሮች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የሚመለከቱት እንደ ሌሎች የዓለም መንግሥታዊ መዋቅሮች አድርገው ነው። የተባበሩት መንግሥታት አምላክ እስከ ፈቀደ ድረስ እንደሚቆይ ያምናሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በመስማማት ለሁሉም መንግሥታት ተገቢውን አክብሮት ከማሳየታቸውም በተጨማሪ ከአምላክ ሕግ ጋር የሚጻረር እስካልሆነ ድረስ ይታዘዟቸዋል።—ሥራ 5:29