ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
የወላጆቼን አድሎአዊነት እንዴት መቋቋም እችላለሁ?
“ታናሽ እህቴን በሁለት ዓመት እበልጣታለሁ፣ ወላጆቼ ሙሉ ትኩረት የሚሰጡት ግን ለእርስዋ ነው። . . . እንዲህ ማድረጋቸው ትክክል መስሎ አይታየኝም።”—ሪቤካa
ወንድምህ ወይም እህትህ የበለጠ ትኩረት በተሰጣቸው መጠን አንተ የተጣልክ እንደሆንክ ይሰማሃል። በተለይ ወንድምህ ወይም እህትህ ልዩ የሆነ ተሰጥኦ ያላቸው ከሆኑ ወይም ከባድ ችግር ካለባቸው ወይም ከወላጆችህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ባሕርይ ወይም ፍላጎት ያላቸው ከሆኑ የወላጆችህን ትኩረት ቅንጣት ያህል እንኳ ለማግኘት ከባድ ትግል ሊጠይቅብህ ይችላል! ስለጉዳዩ ባሰብክ መጠን ይበልጥ ትከፋለህ፣ ትናደዳለህ።b
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ተቆጡ፣ ነገር ግን ኃጢአትን አታድርጉ። በመኝታችሁ ሳላችሁ በልባችሁ አስቡ፣ ዝም በሉ” በማለት ያስጠነቅቃል። (መዝሙር 4:4) በምትበሳጭበትና በምትቆጣበት ጊዜ የኋላ ኋላ የምትጸጸትበት ነገር ማድረግህ ወይም መናገርህ አይቀርም። ቃየን ወንድሙ አቤል የአምላክን ሞገስ በማግኘቱ እንዴት እንደተቆጣ አስታውስ። አምላክ “ኃጢአት በደጅ ታደባለች፣ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፣ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት” ሲል አስጠንቅቆት ነበር። (ዘፍጥረት 4:3-16) ቃየን ስሜቱን መቆጣጠር አልቻለም። በዚህም ምክንያት ከባድ ውድቀት ደረሰበት!
እንደ ቃየን ነፍስ ለመግደል አትነሳ ይሆናል። ቢሆንም አድልዎ እንደተደረገብህ ሲሰማህ መጥፎ የሆኑ ስሜቶችና ግፊቶች ሊነሳሱብህ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት አደጋዎች በደጅህ ሊያደቡብህ ይችላሉ! ከእነዚህ አደጋዎች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? እንዲህ ያለውንስ ሁኔታ እንዴት ልታሸንፍ ትችላለህ?
ምላስህን ግታ!
ቤት 13 ዓመት በሆናት ጊዜ ወላጆችዋ ለወንድምዋ የሚያዳሉና እርስዋን የሚበድሉ መሰላት። እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “እኔና እማዬ ብዙ ጊዜ እርስ በርሳችን እንጯጯህ ነበር። ይሁን እንጂ ምንም ያስገኘልን ፋይዳ አልነበረም። እኔ እርስዋ የምትለውን አልሰማም፣ እርስዋም እኔ የምለውን አትሰማም ነበር። ስለዚህ የትም ለመድረስ አልቻልንም።” አንተም መጯጯህ ሁኔታውን ከማባባስ ሌላ የሚያስገኘው ፋይዳ እንደሌለ ሳትገነዘብ አትቀርም። ኤፌሶን 4:31 “መራርነትና ንዴት ቊጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ” ይላል።
ሐሳብህንና አመላካከትህን ሰዎች እንዲረዱልህ ለማድረግ መጮህ አያስፈልግህም። አብዛኛውን ጊዜ በእርጋታ መንፈስ መነጋገር የተሻለ ውጤት ያስገኛል። ምሳሌ 25:15 “በትዕግሥት አለቃ ይለዝባል፣ የገራም ምላስ አጥንትን ይሰብራል” ይላል። ስለዚህ ወላጆችህ አድልዎ የሚፈጽሙብህ መስሎ ከተሰማህ አትጩህባቸው ወይም አትወንጅላቸው። ተስማሚ ጊዜ ጠብቅና በአክብሮት ረጋ ብለህ አነጋግራቸው።—ከምሳሌ 15:23 ጋር አወዳድር።
በወላጆችህ ጉድለት ላይ ብቻ ብታተኩር ወይም ምን ያህል አድሎኛ እንደሆኑ በመናገር ብትወቅሳቸው ይበልጥ ታርቃቸዋለህ ወይም የከረረ አቋም እንዲይዙ ታደርጋለህ። ከዚህ ይልቅ ድርጊታቸው ምን ዓይነት ስሜት እንዲያድርብህ እንዳደረገ አስረዳቸው። ለምሳሌ ‘ችላ ስትሉኝ በጣም ይከፋኛል’ ለማለት ትችላለህ። እንዲህ ስታደርግ ስሜትህን አክብደው መመልከታቸው አይቀርም። በተጨማሪም ‘ለመስማት የፈጠንክ ሁን።’ (ያዕቆብ 1:19) ወላጆች ለወንድምህ ወይም ለእህትህ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ ያደረጋቸው ተገቢ ምክንያት ይኖር ይሆናል። ምናልባት አንተ የማታውቃቸው ችግሮች ይኖሩበት ይሆናል።
በምትቆጣበት ጊዜ ስሜትህን መቆጣጠር የማትችልና በግልፍተኝነት የምትናገር ከሆንክስ? ምሳሌ 25:28 ‘መንፈሱን የማይቆጣጠር ሰው ቅጥር እንደሌላት ከተማ’ እንደሆነ ይናገራል። በገዛ ራሱ ፍጽምና የጎደለው ስሜት ተሸንፎ ሳይወድቅ አይቀርም። በሌላው በኩል ግን ስሜትህን መቆጣጠር መቻልህ በእርግጥ ጠንካራ ሰው መሆንህን ያሳያል! (ምሳሌ 16:32) ስለዚህ ለምን ቆየት ብለህ፣ ምናልባትም እስከ ማግስቱ ቆይተህ ቁጣህ በረድ ሲልልህ የተሰማህን አትናገርም? በተጨማሪም ብድግ ብለህ ወጥተህ ወዲያ ወዲህ መንሸራሸር ወይም አንድ ዓይነት አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ሊጠቅምህ ይችላል። (ምሳሌ 17:14 NW) አንደበትህን ብትቆጣጠር የሚያስከፋ ወይም የቂልነት ንግግር ከመናገር ልትጠበቅ ትችላለህ።—ምሳሌ 10:19፤ 13:3፤ 17:27
የእምቢተኝነት መንፈስ ማሳየት
ሌላው ልታስወግደው የሚገባ ዝንባሌ የእምቢተኝነት መንፈስ ነው። አሥራ ስድስት ዓመት የሆናት ማሪ ታናሽ ወንድምዋ በቤተሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት ሲረብሽ ምንም ዓይነት ቅጣት እንደማይሰጠው ታስተውላለች። ወላጆችዋ ለወንድምዋ ያዳሉ መስሏት በመበሳጨትዋ ዓምፃ በጥናቱ ለመካፈል እምቢተኛ ሆነች። አንተስ ተገቢ ያልሆነ ነገር እንደተፈጸመብህ ሲሰማህ ታኮርፋለህ ወይም ያለመተባበር መንፈስ ለማሳየት ትወስናለህ?
እንዲህ የምታደርግ ከሆነ እንዲህ ያለው የረቀቀ ዘዴ ወላጆችህን እንድታከብርና እንድትታዘዝ ከሚያዘው የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ጋር እንደሚቃረን ተገንዘብ። (ኤፌሶን 6:1, 2) ከዚህም በላይ አለመታዘዝ ከወላጆችህ ጋር ያለህን ዝምድና ያበላሽብሃል። ችግሩን ከወላጆችህ ጋር ግልጥልጥ አድርገህ ብትወያይ የተሻለ ይሆናል። ምሳሌ 24:26 “በቀና ነገር የሚመልስ” የሌሎችን አክብሮት እንደሚያተርፍ ይገልጻል። ማሪ ችግሩን ከእናትዋ ጋር ስትወያይ ወደ መግባባት ደረሱ፣ ሁኔታዎችም መሻሻል ጀመሩ።
ራስን ማግለል የሚያስከትለው አደጋ
አድልዎ እንደተፈጸመብህ ሲሰማህ ማድረግ የማይገባህ ሌላው አደገኛ ነገር ደግሞ ከቤተሰብህ መራቅ ወይም የማያምኑ ሰዎችን ባልንጀርነት መፈለግ ነው። ካሳንድራ እንዲህ አድርጋ ነበር:- “ራሴን ከቤተሰቦቼ አገለልኩና በትምህርት ቤት ካገኘኋቸው ዓለማዊ ጓደኞች ጋር መወዳጀት ጀመርኩ” ትላለች። “የወንድ ጓደኞች ሳይቀር አበጀሁ። ወላጆቼ ግን ይህን አያውቁም ነበር። ከዚያ በኋላ የማደርገው ሁሉ ትክክል እንዳልሆነ ስላወቅኩ ከባድ ጭንቀትና የበደለኛነት ስሜት ይሰማኝ ጀመር። ካለሁበት ሁኔታ ለመውጣት ፈለግኩ፣ ግን ለወላጆቼ እንዴት ብዬ እንደምናገር ግራ ገባኝ።”
በተለይ በምትበሳጭበትና በትክክል ማሰብ በማትችልበት ወቅት ራስህን ከቤተሰብህና ከእምነት ባልደረቦችህ ማግለል በጣም አደገኛ ነው። ምሳሌ 18:1 “መለየት የሚወድ ምኞቱን ይከተላል፣ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል” በማለት ያስጠነቅቃል። በዚህ ወቅት ወላጆችህን ቀርበህ ማነጋገር የሚከብድህ ከሆነ ምሳሌ 17:17 “እውነተኛ ወዳጅ ሁልጊዜ ይወድዳል፣ ለመከራ ጊዜም እንደተወለደ ወንድም ነው” የሚለውን ዓይነት ክርስቲያን ጓደኛ ፈልግ። እንዲህ ያለውን “እውነተኛ ወንድም” ከጎለመሱ የጉባኤ አባላት መካከል ማግኘት አያስቸግርም።
ካሳንድራ በችግሯ ጊዜ “እውነተኛ ወዳጅ” አግኝታለች። “የወረዳ የበላይ ተመልካቹ [ተጓዥ አገልጋይ] ጉባኤያችንን በሚጎበኝበት ጊዜ ወላጆቼ አብሬው እንዳገለግል አበረታቱኝ። እርሱና ባለቤቱ የሰው ስሜት የሚገባቸው በመሆናቸው ልባዊ የሆነ አሳቢነት አሳዩኝ። የልቤን ሁሉ አውጥቼ ላዋያቸው ቻልኩ። ይኮንኑኛል የሚል ስሜት አልነበረኝም። በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ማደግ ብቻ ፍጹም መሆን እንደማያስችል የሚገነዘቡ ሰዎች ነበሩ።” ካሳንድራ ያስፈልጋት የነበረው የእነርሱ ማበረታቻና የጉልምስና ምክር ነበር።—ምሳሌ 13:20
ምቀኝነት የሚያስከትለው አደጋ
ምሳሌ 27:4 “ቁጣ ምሕረት የሌለው ነው፣ መዓትም እንደ ጎርፍ ነው፣ በቅንዓት ፊት ግን ማን ይቆማል?” በማለት ያስጠነቅቃል። አንዳንድ ወጣቶች የተለየ ፍቅርና እንክብካቤ በሚደረግላቸው ወንድሞቻቸው ወይም እህቶቻቸው በመመቅኘታቸውና በመቅናታቸው ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ፈጽመዋል። አንዲት ሴት እንዲህ ስትል የሠራችውን ስህተት ገልጻለች:- “ትንሽ ልጅ ሳለሁ ስስና አጭር የሆነ ቡናማ ፀጉር ነበረኝ። እህቴ ግን እስከ ወገብዋ ድረስ የሚደርስ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ወርቃማ ፀጉር ነበራት። አባቴ ሁልጊዜ ስለ ፀጉሯ ያወድሳት ነበር። የኔ ‘ራፑንዘል’ እያለ ይጠራት ነበር። አንድ ቀን ሌሊት እንደተኛች የእናቴን መቀስ ያዝኩና ቀስ ብዬ ወደ አልጋዋ በመጠጋት የቻልኩትን ያህል ፀጉሯን ቆረጥኩ።”—ሲብሊንግስ ዊዝአውት ራይቨልሪ፣ በአደል ፋብር እና ኢሌን ማዝሊሽ።
ስለዚህ ምቀኝነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከመጥፎ ‘ሥጋ ሥራዎች’ አንዱ እንደሆነ መገለጹ የሚያስደንቅ አይደለም። (ገላትያ 5:19-21፤ ሮሜ 1:28-32) ይሁን እንጂ “የምቀኝነት ዝንባሌ” በሁላችንም ውስጥ ይገኛል። (ያዕቆብ 4:5) ስለዚህ ወንድምህን ወይም እህትህን ለማስቀጣት የምትችልበትን ወይም አስቀያሚ የሚሆንበትን ወይም የሚዋረድበትን የተንኮል ዘዴ በመሸረብ ላይ ከሆንክ ምቀኝነት “በደጅህ እያደባ” በአንተ ላይ ሊነግሥብህ እየሞከረ ነው!
እንዲህ ያለ ጎጂ ስሜት እንዳለብህ ከተገነዘብክ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? በመጀመሪያ አምላክ መንፈሱን እንዲሰጥህ ለመጸለይ ሞክር። ገላትያ 5:16 “በመንፈስ ተመላለሱ፣ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ” ይላል። (ከቲቶ 3:3-5 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም ለወንድምህ ወይም ለእህትህ ያለህን እውነተኛ ስሜት ማሰላሰል ሊረዳህ ይችላል። ምንም ያህል ቅሬታ ቢሰማህ ለወንድምህ ወይም ለእህትህ ምንም ዓይነት ፍቅር የለኝም ልትል ትችላለህን? ታዲያ ቅዱሳን ጽሑፎች “ፍቅር አይቀናም” ይሉ የለምን? (1 ቆሮንቶስ 13:4) ስለዚህ አፍራሽ የሆኑትንና ቅናት አነሳሽ የሆኑትን ሐሳቦች አስወግድ። ወንድምህ ወይም እህትህ የወላጆችህን ልዩ እንክብካቤና ትኩረት የሚያገኙ ከሆነ ከእነርሱ ጋር አብረህ ለመደሰት ሞክር።—ከሮሜ 12:15 ጋር አወዳድር።
ከወላጆችህ ጋር የምታደርገውም ውይይት በዚህ ረገድ በጣም ሊረዳህ ይችላል። ለአንተ የበለጠ ትኩረትና እንክብካቤ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ካመኑ በወንድምህ ወይም በእህትህ ላይ የተሰማህን የምቀኝነት ስሜት ለማሸነፍ በጣም ቀላል ይሆንልሃል። ሆኖም ሁኔታው ካልተሻሻለና አድልዎ ማድረጋቸውን ከቀጠሉስ? በወላጆችህ ላይ አትቆጣ፣ አትጩህ ወይም አታምፅ። እነርሱን የመርዳትና የመታዘዝ ዝንባሌህን ይዘህ ለመቀጠል ጥረት አድርግ። አስፈላጊ ከሆነ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ የጎለመሱ ወንድሞች እንዲረዱህ ጠይቅ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ወደ ይሖዋ አምላክ የበለጠ ቅረብ። “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፣ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ” የሚሉትን የመዝሙራዊውን ቃላት አስታውስ።—መዝሙር 27:10
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።
b በጥቅምት 22, 1997 የእንግሊዝኛ ንቁ! እትም ላይ የወጣውን “ወንድሜ ይህን ያህል ትኩረት የሚሰጠው ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ችላ መባልህን መግለጽህ ለችግሩ መፍትሔ ያስገኝ ይሆናል