የሃይማኖት የወደፊት ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንፃር ሲታይ
ክፍል 22:- ከ1900 ጀምሮ የሐሰት ሃይማኖት የቀድሞ ታሪኩን እየደገመ ነው!
“የአንድ ብሔር የወደፊት ዕጣ የሚወሰነው በቀድሞ ታሪኩ ነው።” አርተር ብርያንት፣ የ20ኛው መቶ ዘመን እንግሊዛዊ የታሪክ ሊቅ
መጽሐፍ ቅዱስ የሐሰት ሃይማኖትን ግዛት በጥንትዋ የባቢሎን ግዛት በመመሰል ታላቂቱ ባቢሎን በማለት ይጠራታል። (ራእይ 18:2) በዚህች ጥንታዊት መንግሥት ላይ የደረሰው ሁኔታ ዘመናዊት ሞክሼዋ ጥሩ ሁኔታ እንደሚጠብቃት አያመለክትም። ባቢሎን በ539 ከዘአበ በአንድ ሌሊት በታላቁ ቂሮስ ይመራ በነበረው በሜዶናውያንና በፋርሳውያን ሠራዊት እጅ ወደቀች። ወራሪዎቹ ጭፍሮች ከተማዋን መሐል ለመሐል ሰንጥቆ ያልፍ የነበረውን የኤፍራጥስ ወንዝ ወደ ሌላ አቅጣጫ ካዞሩ በኋላ ማንም ሳያያቸው በደረቀው ወንዝ በኩል ገቡ።
ይሖዋ አምላክና ከቂሮስ የሚበልጠው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስም በከዳተኛይቱ ታላቂቱ ባቢሎን ላይ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ድል ይቀዳጃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ታላቂቱ ባቢሎንን በብዙ ውኃዎች ላይ በተቀመጠች ታላቅ ጋለሞታ ይመስላታል። ይህም ድጋፍ የሚሰጧትን “ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም” ያመለክታል። ከመጥፋትዋ በፊት ግን ይህ እንደ ‘ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ያለ’ ድጋፍ “ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው” ይደርቃል።—ራእይ 16:12፤ 17:1, 15
እንዲህ ያለው የመድረቅ ሂደት በአሁኑ ጊዜ እየተከናወነ መሆኑን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች የሐሰት ሃይማኖትን ማንነት ለይቶ በማወቅ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው። ታዲያ በቂ ማስረጃ እናገኝ ይሆን?
ብሩሕ ሆኖ ይታይ የነበረው የወደፊት ተስፋ ጨለመ
በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ከዓለም ጠቅላላ ሕዝብ መካከል ሲሶ የሚሆነው ክርስቲያን ነኝ ይል ነበር። የሕዝበ ክርስትና የወደፊት ሁኔታ በጣም ብሩሕ ሆኖ ይታይ ነበር። ወንጌላዊና የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ጆን አር ሞት በ1900 ባሳተሙት ዚ ኤቫንጀላይዘሽን ኦቭ ዘ ወርልድ ኢን ዚስ ጀነረሽን በተባለ መጽሐፋቸው የነበራቸውን ብሩሕ ተስፋ አንጸባርቀዋል።
ይሁን እንጂ “20ኛው መቶ ዘመን ከእነዚህ ተስፋዎች ፈጽሞ የተለየ ሆኖ ተገኝቷል” ይላል ወርልድ ክርስቺያን ኢንሳይክሎፔድያ። ይህንንም ሲያብራራ “በ1900 በምዕራብ አውሮፓ በዓለማዊነት መስፋፋት፣ በሩስያና ቆየት ብሎም በምሥራቅ አውሮፓ በኮሙኒዝም፣ በአሜሪካ በፍቅረ ንዋይ ምክንያት በጣም ብዙ ሰዎች ከክርስትና ይርቃሉ ብሎ የጠበቀ አንድም ሰው አልነበረም። እነዚህና ሌሎች “አስመሳይ ሃይማኖቶች” በ1900 ከነበሩበት የ0.2 በመቶ አነስተኛ መጠን ተነስተው እንደ እንጉዳይ በመፍላት በ1980 ወደ 20.8 በመቶ ከፍ ብለዋል” ይላል።
ብዙ ሰዎች ከሃይማኖት በመራቃቸው ምክንያት የምዕራብ አውሮፓ አብያተ ክርስቲያናት ፈጽሞ ወና ሆነዋል። በጀርመን ፌዴራላዊ ሪፑብሊክ የምትገኘው የሉተራን ቤተ ክርስቲያን ከ1970 ወዲህ ከአባሎችዋ መካከል 12 በመቶ የሚሆኑትን አጥታለች። በኔዘርላንድስ ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት አብያተ ክርስቲያናት ሲዘጉ አንዳንዶቹ መጋዘኖች፣ ምግብ ቤቶች፣ የመኖሪያ አፓርተማዎች ሌላው ቀርቶ ዳንስ ቤቶች ሆነዋል። በብሪታንያ ከ30 ዓመት በፊት ከነበሩ የእንግሊዝ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንድ ስምንተኛ የሚሆኑት አገልግሎታቸውን አቁመዋል። አንድ ቄስ በአንድ የአውሮፓ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት መሪዎችና ቀሳውስት ጉባኤ ላይ “ክርስቲያን ይባል የነበረው የምዕራቡ ዓለም አሁን ራሱን ክርስቲያን ነኝ ብሎ ሊጠራ አይችልም። . . . አውሮፓ ሚስዮናውያን የሚያስፈልጓት መስክ ሆናለች” በማለት በምሬት መናገራቸው አያስደንቅም።
ይሁን እንጂ ችግሩ በሕዝበ ክርስትናና በአውሮፓ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ለምሳሌ ያህል በመላው ዓለም በየዓመቱ 900,000 የሚያክሉ ቡድሂስቶች እምነታቸውን በመተው ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም ወደሚል ፍልስፍና እንደሚያመሩ ተገምቷል።
የአገልጋዮች እጥረት
አንድ የጃፓናውያን ምሳሌ “አንድን መንደር ለማነሳሳት ከፈለግህ ቀድመህ ቄሶቿን አነሳሳ” ይላል። ነገር ግን እንዲህ የተባለላቸው ቄሶች የት አሉ? ከ1983 በፊት በነበረው አሥር ዓመት በመላው ዓለም የነበረው የካቶሊክ ቄሶች ቁጥር 7 በመቶ ቀንሶ ነበር። በ15 ዓመት ጊዜ ውስጥ የሴት መነኮሳት ቁጥር 33 በመቶ ቀንሷል። እነዚህን የሚተኩ ሰዎች የመገኘታቸው ተስፋ በጣም የጨለመ ነው። ከ20 ዓመት በሚያንስ ጊዜ ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ወደ ካቶሊክ የሃይማኖት ትምህርት ቤቶች የገቡ ሰዎች ቁጥር ከ48,992 ወደ 11,262 ዝቅ ብሏል።
በተጨማሪም የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ማኅበራት ቁጥር በጣም እየቀነሰ መጥቷል። በ1534 በፓሪስ፣ ኢግናሺየስ ኦቭ ሎያላ በተባለ ሰው የተቋቋመው የኢየሱስ ማኅበር በአንድ ወቅት በበርካታ አገሮች የነበረውን የትምህርት ሥርዓት ሙሉ በሙሉ እስከመቆጣጠር ደርሶ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ጀስዊት ተብለው ይጠሩ የነበሩት የማኅበሩ አባላት በሚሲዮናዊ እንቅስቃሴዎች በግንባር ቀደምትነት ይሰለፉ ነበር። ከ1965 ወዲህ ግን የአባሎቹ ቁጥር ከአንድ አራተኛ በሚበልጥ መጠን ቀንሷል።
የሠራተኞች ቁጥር እየተመናመነ መሄዱ የሚያስከትለው ችግር እንዳይበቃ ያሉትም ቢሆኑ እምነት የማይጣልባቸው እየሆኑ መጥተዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱ ስለ ብህትውና፣ ስለ ወሊድ ቁጥጥርና ሴቶች ስላላቸው ሃይማኖታዊ የሥራ ድርሻ ያላትን አቋም የሚቃወሙ ቄሶችና ሴት መነኮሳት ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን በጥር ወር 1989 መቶ ስልሳ ሦስት የሚያክሉ የአውሮፓ ካቶሊካውያን የሃይማኖት መሪዎች ያወጡት መግለጫ ነው። ይህ መግለጫ እስከ ግንቦት 1 ድረስ ከ500 በሚበልጡ ቫቲካንን በአምባገነንነትና በሥልጣን ብልግና በሚወነጅሉ ተጨማሪ የሃይማኖት ሰዎች ተፈርሟል።
በሚልዮን የሚቆጠሩ የሕዝበ ክርስትና አባላት መንፈሳዊ ጠኔ ይዟቸው በመንፈሳዊ በድኖች ሆነዋል። አንድ የዩናይትድ ስቴትስ የቤተ ክርስቲያን ሰው ይህን በማመን እንዲህ ብለዋል:- “ቤተ ክርስቲያን ለአላፊ አግዳሚው መናኛ ምግብ የምታድል የገበያ ማዕከል ሆናለች። የሰባኪው መልእክት ለደንበኞች በቅናሽ ከሚቀርበው ‘የሳምንቱ ልዩ ሸቀጥ’ የተሻለ አልሆነም።”
ከ1965 ወዲህ በዩናይትድ ስቴትስ የአምስቱ ዋነኛ የፕሮቴስታንት ሃይማኖታዊ ክፍሎች አባላት ቁጥር 20 በመቶ ሲቀንስ የሰንበት ተማሪዎች ቁጥር ደግሞ ከ50 በመቶ በላይ ቀንሷል። ታይም መጽሔት “ዋነኞቹ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች መልእክታቸውን ለሕዝብ ማድረስ የተሳናቸው ከመሆኑም በላይ መልእክታቸው ራሱ ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅ እያቃታቸው መጥቷል” ሲል ጽፏል። እንዲህ ያለው መንፈሳዊ ችጋር በተስፋፋበት ሁኔታ ብዙ የቤተ ክርስቲያን መጽሔቶች ከኅትመት ውጭ መሆናቸው የሚያስደንቅ አይሆንም። ገና በ1970ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ከእነዚህ መጽሔቶች አንዱ “የቤተ ክርስቲያን መጽሔት በሰፊው ይታተም የነበረበት ዘመን . . . አልፏል” ሲል አማርሮ ነበር።
ግድየለሽና አንገተ ደንዳና የሆነ መንጋ
በአሥራ ስምንተኛው መቶ ዘመን የእንግሊዝ ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣን የነበሩት ኤድመንድ ቡርክ “የግድየለሽነትን ያህል ሃይማኖትን የሚገድል ክፉ ጠላት የለም” ብለው ነበር። በሕይወት ቆይተው የዛሬውን ሁኔታ ቢመለከቱ ኖሮ ግድ የለሽ የሆኑ ሃይማኖተኞች በእጅጉ ተስፋፍተው ይመለከቱ ነበር።
ለምሳሌ ያህል ከጥቂት ዓመታት በፊት ለዩናይትድ ስቴትስ ሉተራውያን ቃለ መጠይቅ ሲደረግ 44 በመቶ የሚያክሉት የቤተ ክርስቲያናቸው አባሎች ላልሆኑ ቤተሰቦች ስለ እምነታቸው እንዲናገሩ ቄሶቻቸው ቢጠይቋቸው እንደማይናገሩ ገልጸዋል። ከዩናይትድ ስቴትስ ካቶሊኮች መካከል ከሦስት አራተኛ በላይ የሚሆኑት በሥነ ምግባር ጥያቄዎች ላይ ሳይቀር ከሊቀ ጳጳሱ ጋር የማይስማሙ መሆናቸው ጥሩ ካቶሊኮች መሆናቸውን እንደማይቀንስባቸው ተናግረዋል። በቅርቡ የተደረገ አንድ የሕዝብ አስተያየት ጥናት አሳይቷል።
በጃፓን አገር ከጠቅላላዎቹ ሕዝቦች መካከል 79 በመቶ የሚሆኑት ሃይማኖተኛ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ሪልጅንስ ኦቭ ሞደርን ማን እንዳለው ከእነዚህ መካከል ሃይማኖት አለኝ ያሉት አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ብቻ በመሆናቸው ለሃይማኖት ግድየለሽ የሆኑ ሰዎች በጣም ብዙ መሆናቸው ግልጽ ነው።
ለሃይማኖት ግድየለሽ የሆኑ ወላጆች አብዛኛውን ጊዜ ለሃይማኖት ጥሩ ዝንባሌና ቅንዓት ያላቸው ልጆች አይኖሯቸውም። በጀርመን አገር የቦን ዩኒቨርሲቲ የስነ ልቦና ተቋም ዳይሬክተር ከ11 እስከ 16 ዕድሜ ላይ በሚገኙ ልጆች ላይ ባደረጉት ጥናት ልጆች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አርዓያ የሚሆኗቸውን ሰዎች በመፈለግ ላይ መሆናቸውን ተገንዝበዋል። በአርዓያነት የሚመለከቷቸው እነማን እንደሆኑ በተጠየቁ ጊዜ ግን ልጆቹ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን አንድ ጊዜ እንኳን ሳይጠቅሱ ቀርተዋል።
ፖለቲካዊ ተደማጭነት ማጣት
የተደራጀ ሃይማኖት ከዚህ በፊት የነበረውን ፖለቲካዊ ተደማጭነት እያጣ መጥቷል። ለምሳሌ ያህል ቫቲካን በዋነኞቹ የካቶሊክ አገሮች እንኳን ውርጃን፣ ፍቺንና የአምልኮ ነጻነትን የሚደግፉ ሕጎች እንዳይወጡ ለማገድ ሳትችል ቀርታለች። በተመሳሳይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የኢጣሊያ መንግሥታዊ ሃይማኖት የመሆን መብቷን የነጠቃትን የ1984 ውል በሁኔታዎች አስገዳጅነት ተቀብላለች!
የሐሰት ሃይማኖት ከዚህ በፊት መሰሪ በሆኑ የፖለቲካ ተጽእኖዎች አማካኝነት ታገኝ የነበረውን መብት በአሁኑ ጊዜ፣ እንደ ደቡብ አፍሪካው የአንግሊካን ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ በመሰሉ እውቅ ቀሳውስት በሚመሩ የሕዝባዊ ተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ለማግኘት ትሞክራለች።
አንድ ብንሆን እንቆማለን፣ ብንነጣጠል ግን እንወድቃለን
የዘመናችን የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት እንቅስቃሴ የተወለደው በ1910 በኤድንበርግ፣ ስኮትላንድ ከተደረገው የፕሮቴስታንት ሚስዮናውያን ማኅበራት ጉባኤ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህ እንቅስቃሴ በመፋፋም “የክርስቲያን ሃይማኖት” በአንድ ድምፅ ለመናገር እንዲችል ሃይማኖታዊ ትብብርና መግባባት እንዲኖር እየተጣጣረ ይገኛል።
የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት እንቅስቃሴ ብዙ ፈርጆች አሉት። በ1948 በአምስተርዳም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ መቋቋሙ አንድ ዓቢይ እርምጃ ሆኖ ተቆጥሯል። ጉባኤው በመጀመሪያ ሲቋቋም የነበሩት አባሎች 150 የሚያክሉ የፕሮቴስታንት፣ የአንግሊካንና የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ቢሆኑም በአሁኑ ጊዜ ይህ የአባላት ቁጥር በእጥፍ እንዳደገ በጉራ ይናገራል።
የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ አባል ባትሆንም በአሁኑ ጊዜ ወደዚያው አቅጣጫ እያመራች ያለ ይመስላል። በ1984 ጉባኤው በስዊዘርላንድ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ባደረገው ስብሰባ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጆን ፖል የሥራ ዘመናቸውን ከፈጸሙት የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ጋር ሆነው ሥርዓተ ጸሎቱን መርተዋል። በግንቦት 1989 ደግሞ በባዝል፣ ስዊዘርላንድ አንድ ጋዜጣ “ከተሐድሶ ዘመን ወዲህ ታይቶ የማያውቅ ትልቅ የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጉባኤ” ባለው ስብሰባ ላይ ከተገኙት 700 የሚያክሉ የአውሮፓ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች መካከል ካቶሊኮች ተገኝተው ነበር።
ከ1930ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ወዲህ ሁሉም “ክርስቲያን” ሃይማኖቶች ከአምላክ የተሰጠ የአንድነት ባሕርይ አላቸው የሚለው አስተሳሰብ ያለው ተቀባይነት እየጨመረ በመምጣቱ ይህ ዓይነቱ የስምምነት መንፈስ ይበልጥ ግልጽ ሆኖ መታየት ጀምሯል። የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ “ክርስቲያን” ሃይማኖቶች የአንድነት ባሕርይ እንዳላቸው “ማስረጃ” አድርጎ የሚያቀርበው የጉባኤው አባል አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት የሚቀበሉና “ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርና አዳኝ” መሆኑን የሚያምኑ መሆናቸውን ነው።
ከዚህም በላይ ሕዝበ ክርስትና ክርስቲያን ካልሆኑ ሃይማኖቶች ጋር የመወያየት ፍላጎት አሳይታለች። ይህ የሆነው ዚ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪልጅን እንደሚለው “እውነተኛው ሃይማኖት አንድ ብቻ ከሆነ ሌሎቹ ሃይማኖቶች የመኖር መብት ሊኖራቸው አይገባም የሚል አንድምታ ካለው ሃይማኖታዊ ኢምፔሪያሊዝምና በሃይማኖቶች መካከል ግጭት ሊያስነሳ የሚችል በቂ ልዩነት ባለመኖሩ ሁሉም ሃይማኖቶች ተዋህደው አዲስ የሆነ የወደፊቱ ዘመን ሃይማኖት ሊመሠርቱ ይችላሉ የሚል አንድምታ ካለው የሲንክሬቲዝም አስተሳሰብ መካከል” አንድ አስታራቂ ሐሳብ ለማግኘት ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ የሐሰት ሃይማኖት እያንዳንዳቸው ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች በሚሳቡ በርካታ ክሮች የተገመደ ሲባጎ መስሏል። እስከ ዛሬ ድረስ “እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፣ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም” የሚለውን የኢየሱስ ቃል ሊያስተባብል የቻለ ሰው ስላልተገኘ ለከፋ ጥፋት ተዘጋጅቷል።”—ማቴዎስ 12:25
ሐሰቱን ትተህ እውነቱን ተቀበል!
አንዳንድ ሰዎች ዐይናቸውን ጨፍነው ማስረጃውን ላለማየት ይመርጡ ይሆናል። ይሁን እንጂ መሠረት በሌለው ነገር ላይ ተስፋ ማድረግ አደገኛ ነው። የለንደኑ ዘ ታይምስ በጥቅምት ወር 1988 እትሙ “አብያተ ክርስቲያናት ከአንድ ትውልድ ለሚበልጥ ዘመን ሁኔታዎች በራሳቸው ይሻሻላሉ በሚል ተስፋ ኖረዋል” ብሏል። በማከልም “በብሪታንያ የአብያተ ክርስቲያናት አባሎች ቁጥር ሳያቋርጥ ማሽቆልቆል ከጀመረ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም አብያተ ክርስቲያናት ምክንያቱን ለማወቅ ወይም ሁኔታውን ለመለወጥ ወይም ከዚህ ጋር የሚጣጣም የፖሊሲ ለውጥ ለማምጣት ያደረጉት ጥረት የለም” ካለ በኋላ “ሽያጩ ከዕለት ወደ ዕለት እየቀነሰበት እንደሄደ የተገነዘበ ማንኛውም የንግድ ድርጅት ራሱን ለመጨረሻ ክስተት ያዘጋጃል ወይም ምርቱንና የሽያጭ ዘዴውን የሚያሻሽልባቸውን እርምጃዎች ይወስዳል” በማለት ደምድሟል።
የሐሰት ሃይማኖት “ምርቱንና የሽያጭ ዘዴውን የሚያሻሽልባቸውን እርምጃዎች” እንደሚወስድ የሚያመለክት አንድም ማስረጃ የለም። ፈሪሐ አምላክ ያላቸው ሰዎች ያላቸው ብቸኛ ተስፋ የመንፈሳዊ ውኃ ምንጩ የመድረቅ አንዳች አደጋ ወደማይደርስበት እውነተኛ ሃይማኖት ዘወር ማለት ነው። የሐሰት ሃይማኖት ግን “ዋጋውን የሚያገኝበት ጊዜ ቀርቧል።” በሚቀጥለው እትማችን ከሚወጣው ከዚህ ርዕስ ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ጥረት አድርግ።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የይሖዋ ምሥክሮች:- የውኃ ምንጫቸው አልደረቀም
“የታወቁት ሃይማኖቶች ቀስ በቀስ እያሽቆለቆሉ በሄዱና አብያተ ክርስቲያናትና አብያተ መቅደሶች ወና እየሆኑ በሄዱ መጠን የይሖዋ ምሥክሮች የአባሎቻቸውን ቁጥር በመጨመር አልፎ ተርፎም ከዚህ በፊት አብያተ ክርስቲያናትና ሌሎች ድርጅቶች የነበሩባቸውን ሕንጻዎች ተረክበው ለአዳዲስ አባሎቻቸው መሰብሰቢያነት በመገልገል ላይ ናቸው።”—ለ ፐቲት ዦርናል፣ የካናዳ ጋዜጣ
“በኢጣሊያ 45 ሺህ የሚያክሉ አሉ . . . ዛሬ ይህ ሃይማኖታዊ ድርጅት በጣም ጥሩ የሆኑና የሚነበቡ (ከመላው ዓለም የተውጣጡ ዜናዎችንና ርዕሶችን ይዘው የሚወጡ) መጽሔቶች አሉት፤ በጣም ወቅታዊ የሆኑና ሊቃውንት ናቸው ለሚባሉ የካቶሊክ ምሁራን እንኳን ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎቻቸው መልስ የሚያስገኙ ትናንሽ መጻሕፍት ያትማሉ፤ በቀጥታ ከዕብራይስጥ የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶችን ያሰራጫሉ። . . . ምሥክሮቹ በእነዚህ ዘዴዎች በጣም ከፍተኛ የሆነ ውጤት አግኝተዋል።”—ፋሚግልያ ሜዘ፣ የኢጣሊያ ካቶሊክ መጽሔት (የተጻፈው በ1975 ሲሆን በ1996 በኢጣልያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር 221,229 ደርሷል።)
“[የይሖዋ ምሥክሮች] በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሲያጠምቁ እኛ ግን የምናጠምቃቸው ከሁለት ወይም ከሦስት አያልፉም።”—ዚ ኢቫንጀሊስት፤ የኤቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን ትራክት አሰራጮች ኦፊሴልያዊ መጽሔት። (የይሖዋ ምሥክሮች ይህ ጽሑፍ በወጣበት በ1962 ያጠመቋቸው ሰዎች ቁጥር 69,649 ሲሆን በ1996 የተጠመቁ ሰዎች ቁጥር 366,579 ደርሷል።)
“በ1962 በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ያደረግኩትን ጥናት ‘የአዲሱ ዓለም ማኅበር በድንገት መዳከም ይጀምራል ብሎ ማሰብ በጣም አጠራጣሪ ነው’ በሚል አስተያየት ደምድሜ ነበር። . . . በአሁኑ ጊዜ [1979] ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በዚያ ጊዜ ከነበረው በእጥፍ ይበልጣል። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት እንደገና በእጥፍ ሊያድግ የሚችል መሆኑን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች በርካታ ናቸው።”—ዊልያም ጄ ዋለን በዩ ኤስ ካቶሊክ። (በ1962 የነበሩት 989,192 ምሥክሮች በ1996 ወደ 5,167,258 ደርሰዋል።)
ከ1970 ወዲህ በጀርመን ፌዴራል ሪፑብሊክ (እና በቀድሞዋ ምዕራብ በርሊን) የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር 38 በመቶ አድጓል። ባለፉት 30 ዓመታት በኔዘርላንድስ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ቁጥር ከ161 ወደ 420፣ በብሪታንያ ደግሞ ከ825 ወደ 1,430 ከፍ በማለቱ ምክንያት በሁለቱም አገሮች ብዙ አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾችን መገንባት ግድ ሆኗል።—“ብሩህ ሆኖ ይታይ የነበረው የወደፊት ተስፋ ጨለመ” ከሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ያለውን አንቀጽ 3ን ከዚህ ጋር አወዳድር።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሩጫና ትርምስ በበዛበት በዛሬው ዓለም ሃይማኖት በአብዛኛው በቸልታ ይታለፋል