አንድ ንብ እውነተኛ ንብ የማይሆነው መቼ ነው?
ንቦች በየቀኑ በመቶ የሚቆጠሩ አበቦችን በመቅሰምና የአበባ ወለላ ወደ ቀፏቸው በማመላለስ በሥራ የተጠመደ ሕይወት ይመራሉ። የጸደይ ወቅት ሲደርስ ወንዶቹ ንቦች ተጓዳኝ ፍለጋ ይዞራሉ። ይህን የሚያደርጉት በማየትና በማሽተት ነው። በአጭር ርቀት ላይ ያለን ነገር ብቻ ማየት የሚችሉት ንቦች እንግዳ በሆነ በአንድ ሌላ ጓደኛ ፈላጊም ይማረካሉ። እርሱም ኦርኪድ የሚባለው አበባ ነው።
በደቡብ አውሮፓ የተለያዩ የዱር ኦርኪዶች ይገኛሉ። የእነዚህ አበቦች መራባት እንስት ንቦችን በመምሰላቸው ላይ የተመካ ነው። እነዚህ ኦርኪዶች የወንዴ ዘር የያዙ “ጥቅሎችን” ለሌሎች መሰል ኦርኪዶች ለመላክ ይፈልጋሉ። እነዚህን ጥቅሎች ለማድረስ ተስማሚ ሆነው ያገኟቸው ንቦችን ነው። ይሁን እንጂ ኦርኪዶች ጣፋጭ የሆነ የአበባ ወለላ ስለሌላቸው ንቦችን ወደ ራሳቸው ለመሳብ የማታለያ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ለማታለል የሚጠቀሙበት ዘዴ የእንስት ንቦችን መልክና ሽታ መያዝ ነው። ስለዚህም ወንዱ ንብ ኦርኪዱ እንስት ንብ ስለሚመስለው ግንኙነት ለማድረግ ይሞክራል! እያንዳንዱ የኦርኪድ ዘር የየራሱ ዓይነት የማስመሰያ መልክና ሽታ አለው።
ንቡ ስህተቱን የሚገነዘበው ኦርኪዱ በአካሉ ላይ የሚያጣብቅ የወንዴ ዘር ጥቅል ከለጠፈበት በኋላ ነው። በመጨረሻም ንቡ ይበራል፤ ይሁንና ብዙም ሳይቆይ የተሸከመውን የአበባ የወንዴ ዘር በምትቀበለው በአንድ ሌላ የኦርኪድ ተክል ይታለላል። ንቡ በዚህ ዓይነት ለብዙ ጊዜ ከተታለለ በኋላ እነዚህ ኦርኪዶች የማይታመኑ መሆናቸውን ይገነዘባል። በዚህን ጊዜ ግን ጥቂት አበባዎች እንዲራቡ ምክንያት ሆኗል።
እነዚህ የማሰብ ችሎታ የሌላቸው ኦርኪዶች ንቦችን ለማታለል የሚያስችል ትክክለኛ ሽታና መልክ ለመያዝ የቻሉት እንዴት ነው? ይህን የመሰለው ግሩም አሠራር የፍጥረት ሥራው አስገራሚነትና ማራኪነት ማለቂያ የሌለው አንድ ብልህ ንድፍ አውጪ መኖሩን ያሳያል።