ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ...
የትምህርት ውጤቴን ማሻሻል እችላለሁን?
“ወላጆቼ በትምህርት ለማግኘው ውጤት ያላቸው ግምት በጣም ከፍ ያለ ነው። ‘በሂሳብ ያገኘኸው ውጤት ስንት ነው? በእንግሊዝኛስ?’ እንዲህ ብለው ሲጠይቁኝ በጣም እናደዳለሁ!”—የ13 ዓመቱ ሳም
እንዲህ ዓይነት ችግር ያለበት ሳም ብቻ አይደለም። “ኩድ ዱ ቤተር” የተባለው መጽሐፍ ደራሲዎች “ልጃቸው በትምህርት ቤት ያቅሙን ያህል እየጣረ እንዳለ የሚሰማቸው ወላጆች እስካሁን አላጋጠሙንም” በማለት ጽፈዋል። ሆኖም ሳምን የመሰሉ በርካታ ወጣቶች በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ እንዲያውም ከሁሉም የበለጡ እንዲሆኑ ወላጆቻቸው ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩባቸው ይሰማቸዋል። በክፍላቸው ውስጥም ተጨማሪ ተጽዕኖ ይገጥማቸው ይሆናል። “መምህራን ትዕግሥት የላቸውም” በማለት አንድ ወጣት ያማርራል። “መልሱን ወዲያው አስታውሳችሁ እንድትነግሯቸው ይፈልጋሉ። ማስታወስ ካቃታችሁ ሰነፍ እንደሆናችሁ ሆኖ እንዲሰማችሁ ያደርጋሉ። ስለዚህ ጨርሶ ለመመለስ እንኳ ጥረት አላደርግም።”
ወላጆቻቸውና አስተማሪዎቻቸው እንደጠበቋቸው ሆነው የማይገኙ ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ዝቅተኛ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች በመባል ይታወቃሉ። በመሠረቱ ሁሉም ተማሪዎች ማለት ይቻላል፣ በሆነ ወቅት ላይ ዝቅተኛ ውጤት ያመጣሉ። ለምን? ለዚህ ምክንያቱ ስንፍና ወይም የመማር ችሎታ ማነስ ብቻ አለመሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።a
አንዳንዶች ዝቅተኛ ውጤት የሚያመጡት ለምንድን ነው?
ብዙም ጥረት ሳያደርጉ በሚያገኙት ውጤት ብቻ የሚረኩ አንዳንድ ወጣት ተማሪዎች መኖራቸው እሙን ነው። “ተንጠልጥዬ ካለፍኩ መቼ አነሰኝ” በማለት ሄርመን የተባለ አንድ የ15 ዓመት ወጣት ሳይሸሽግ ተናግሯል። እርግጥ ነው እንዲህ ዓይነቶቹ ወጣቶች በሙሉ ለትምህርት ግዴለሾች ናቸው ብሎ መደምደም አይቻልም። የማይማርኳቸው አንዳንድ የትምህርት ዓይነቶች ይኖሩ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ የሚማሯቸው ትምህርቶች የሚሰጡት ተግባራዊ ጠቀሜታ ግልጽ ሆኖ አይታያቸውም። ሮቤል የተባለ አንድ የ17 ዓመት ወጣት እንዲህ በማለት ሁኔታውን ይገልጻል:- “ትምህርት ከጨረስኩ በኋላ ምንም የማልጠቀምባቸው የትምህርት ዓይነቶች እንዳሉ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ።” አንድ ተማሪ ፍላጎት ካጣ ወይም ስሜቱን ሊቀሰቅስ የሚችል ነገር ከሌለ በቀላሉ ዝቅተኛ ውጤት ሊያመጣ ይችላል።
ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። ለምሳሌ ያህል አስተማሪህ ፈጣን እንደሆነ ከተሰማህ ተስፋ ሊያስቆርጥህ ይችላል። ዝግተኛ ከሆነ ደግሞ ሊሰለችህ ይችላል። የዕድሜ እኩዮችህም በትምህርት ቤት ውጤትህ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። ኪድስ ሁ አንደርአቺቭ የተባለው መጽሐፍ “ጥሩ የመማር ችሎታ ያለው አንድ ጎበዝ ተማሪ ለትምህርት ምንም ግድ በሌላቸው ሰነፍ ተማሪዎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲል ዝቅተኛ ውጤት ማምጣት እንዳለበት ይሰማው ይሆናል” ሲል ይገልጻል። በአሥራዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ አንድ ወጣት በትምህርት ቤት ጥሩ ይሠራባቸው በነበሩት በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ላይ ሌሎች ይቀኑበትና ይቀልዱበት እንደነበር በምሬት ተናግሯል። አዎን፣ አንድ ወጣት “አስተዋይ ሰው በሌሎች ዘንድ ይጠላል” የሚለውን በምሳሌ 14:17 [NW] ላይ የሠፈረውን መሠረታዊ ሥርዓት እውነተኝነት መቀበል ይኖርበታል።
አንዳንድ ጊዜ ለዝቅተኛ ውጤት ምክንያት የሚሆኑት ነገሮች የተወሳሰቡ ናቸው። የሚያሳዝነው አንዳንድ ወጣቶች ለራሳቸው አፍራሽ አስተሳሰብ ይዘው ያድጋሉ። አንድ ልጅ ኤሊ፣ ደደብ ወይም ሰነፍ የሚሉትን የመሰሉ መጥፎ ቅጽል ስሞች ያለ ማቋረጥ የሚዥጎደጎዱበት ከሆነ ይህ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። የሚያሳዝነው ደግሞ አንድ ሰው በወጡለት የቅጽል ስሞች ተቀርጾ ሊወጣ የሚችል መሆኑ ነው። አንድ ሐኪም እንደተናገሩት “ሞኝ እንደሆንክ ቢነገርህና አንተም ብታምንበት የሞኝነት ተግባር መፈጸም ትጀምራለህ።”
ብዙውን ጊዜ ወላጆችና አስተማሪዎች የሚጎተጉቱት በቅን ልቦና ተነሳስተው ነው። ሆኖም ወጣቶች ከአቅማቸው በላይ እንደሚጠብቁባቸው ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። አንተም እንደዚያ የሚሰማህ ከሆነ ወላጆችህና አስተማሪዎችህ አንተን ለማበሳጨት እየሞከሩ እንዳልሆኑ እርግጠኛ ሁን። ምናልባት የሚፈልጉት ነገር ቢኖር የአቅምህን ያክል እንድትሠራ ሊሆን ይችላል። እንደሚፈልጉት ሆነህ ለመገኘት ስትል የምታደርገው ጥረት የሚያሳድርብህ ጭንቀት ተስፋ ቆርጠህ ሁሉን እርግፍ አድርገህ እንድትተወው ሊያደርግህ ይችላል። ይሁን እንጂ ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጥ። የትምህርት ውጤትህን ማሻሻል ትችላለህ።
መነሳሳት
የመጀመሪያው እርምጃ በራስህ መነሳሳት መቻል ነው! ይህን ለማድረግ የምትማርበትን ዓላማ ማወቅ ይኖርብሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያርስ በተስፋ ሊያርስ የሚያበራይም እንዲካፈል በተስፋ ሊያበራይ [ይገባዋል]” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 9:10) በአንዳንድ የትምህርት ዓይነቶች ላይ ሳይታክቱ “ማረስ” ያለው ጥቅም በቀላሉ ላይታየን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ‘እኔ የኮምፒዩተር ፕሮግራም አዘጋጅ መሆን ነው የምፈልገው፤ ታዲያ ታሪክ የምማርበት ምን ምክንያት አለ?’ ትል ይሆናል።
እርግጥ ነው፣ በትምህርት ቤትህ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የተካተተው እያንዳንዱ ትምህርት የሚሰጠው ጥቅም ቢያንስ በአሁኑ ጊዜ ግልጽ ሆኖ ላይታይህ ይችላል። ይሁን እንጂ አርቀህ ለመመልከት ሞክር። ከተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች የምታገኘው አጠቃላይ እውቀት በአካባቢህ ስላለው ዓለም ያለህን ግንዛቤ እንድታሰፋ ይረዳሃል። በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚገኙ በርካታ ወጣቶች አጠቃላይ የሆነ እውቀት ማግኘታቸው ከተለያዩ ማኅበረሰብ ለመጡ ሰዎች “ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ” በመሆን የመንግሥቱን መልእክት ከሰዎቹ ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ ማቅረብ እንዲችሉ እንደረዳቸው ተናግረዋል። (1 ቆሮንቶስ 9:22) አንድ የትምህርት ዓይነት የሚሰጠው ተግባራዊ ጠቀሜታ አነስተኛ ቢመስልም እንኳ ትምህርቱን ጠንቅቀህ በማወቅህ ጥቅም ልታገኝበት ትችላለህ። ቢያንስ ቢያንስ የኋላ ኋላ ከፍተኛ ጥቅም የሚያበረክትልህን “የማሰብ ችሎታህን [NW]” ያዳብርልሃል።—ምሳሌ 1:1-4
ከዚህም በተጨማሪ ትምህርት የተሰወሩ ተሰጥኦዎችህ እንዲገለጡ በማድረግም ሊረዳህ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እሳት እንደሚያቀጣጥል ሰው . . . በአንተ ያለውን የእግዚአብሔርን ስጦታ [አነሳሳ]” በማለት ለጢሞቴዎስ ጽፎለታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:6) ጢሞቴዎስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አንድ ዓይነት ልዩ ኃላፊነት ተሰጥቶት እንደነበረ ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ ከአምላክ ያገኘው ችሎታ ማለትም “ስጦታ” ተዳፍኖ እንዳይጠፋ ሊኮተኩተው ይገባ ነበር። እርግጥ ነው፣ የአንተ የመማር ችሎታ ለጢሞቴዎስ እንደተሰጠው ዓይነት ስጦታ ከአምላክ በቀጥታ ያገኘኸው አይደለም። የሆነ ሆኖ በሥነ ጥበብም ይሁን በሙዚቃ፣ በሒሳብም ይሁን በሳይንስ ወይም በሌላ መስክ ያለህ ችሎታ ለአንተ ልዩ ሲሆን ትምህርት ቤት ደግሞ እንደነዚህ ያሉትን ስጦታዎች እንድታውቃቸውና እንድታሳድጋቸው ሊረዳህ ይችላል።
ጥሩ የጥናት ልማድ
ይሁን እንጂ ከትምህርት ቤት የተቻለውን ያክል ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት ጥሩ የጥናት ልማድ ሊኖራችሁ ይገባል። (ከፊልጵስዩስ 3:16 ጋር አወዳድሩ።) የተወሰነ የትምህርት ክፍል ለመሸፈን የሚያስችል በቂ ጊዜ መድብ። ሆኖም ራስህን ዘና ማድረግ ትችል ዘንድ አልፎ አልፎ እረፍት አድርግ። ጥናትህ ንባብን የሚጨምር ከሆነ የምታጠናውን ጽሑፍ አጠቃላይ መንፈስ ማግኘት ትችል ዘንድ በመጀመሪያ ጽሑፉን ቃኘት አድርግ። ከዚያም በምዕራፉ ርዕስ ወይም በዋና ዋና ርዕሶች ላይ በመመሥረት ጥያቄ አዘጋጅ። ከዚያም ላወጣሃቸው ጥያቄዎች መልስ የሚሆኑትን እየፈለግህ ማንበብህን ቀጥል። በመጨረሻም ካጠናኸው ውስጥ ምን ያህሉን እንደምታስታውስ ለማረጋገጥ በቃልህ ለመድገም ሞክር።
የተማርከውን ነገር ቀድሞ ከምታውቀው ነገር ጋር አዛምድ። ለምሳሌ ያህል የምትከታተለው የሳይንስ ትምህርት ‘የማይታየውን የአምላክ ባሕርይ . . . በግልጥ የምትመለከትበት’ መስኮት ሊሆንልህ ይችላል። (ሮሜ 1:20) ያለፉ ታሪኮችን ማጥናትህ ደግሞ “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” የሚለውን አባባል እውነተኝነት እንድትገነዘብ ሊረዳህ ይችላል። (ኤርምያስ 10:23) በትጋት ባጠናህ መጠን ትምህርት ይበልጥ ቀላል እንዲያውም አስደሳች እየሆነልህ ይሄዳል! ሰሎሞን “ለአስተዋይ ግን እውቀትን ማግኘት አያስቸግረውም” በማለት ተናግሯል።—ምሳሌ 14:6
አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ
አንዳንድ ጊዜ ግን አንድ ተማሪ ዝቅተኛ ውጤት የሚያመጣው በጓደኛ ምርጫው ምክንያት ሊሆን ይችላል። ጓደኞችህ ጥሩ ውጤት ማምጣትን የሚያበረታቱ ናቸው ወይስ እነርሱ ራሳቸው ዝቅተኛ ውጤት የሚያመጡ ናቸው? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 13:20) ስለዚህ ጓደኞችህን በጥበብ ምረጥ። ለትምህርት አዎንታዊ አመለካከት ካላቸው ጋር ተቀራረብ። የትምህርት ውጤትህን ለማሻሻል ያለህን ግብ ለአስተማሪህ ለመንገር ወደኋላ አትበል። እዚህ ግብህ ላይ መድረስ ትችል ዘንድ አንተን ለመርዳት አስተማሪህ ተጨማሪ ጥረት እንደሚያደርግ ጥርጥር የለውም።
ችሎታህን በሚመለከት አፍራሽ አመለካከት የሚሰማህ ከሆነ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ አስታውስ። የመናገር ችሎታውን አስመልክተው ሰዎች በተቹት ጊዜ “በአነጋገሬ ያልተማርሁ ብሆን እንኳ፣ በእውቀት ግን እንዲህ አይደለሁም” በማለት መልስ ሰጥቷል። (2 ቆሮንቶስ 10:10፤ 11:6) አዎን፣ ጳውሎስ በደካማ ጎኑ ላይ ሳይሆን በጠንካራ ጎኑ ላይ ትኩረት አድርጓል። አንተስ ያሉህ ጠንካራ ጎኖች ምንድን ናቸው? ለይተህ ማወቅ የምትቸገር ከሆነ ሊረዳህ የሚችል አንድ ትልቅ ሰው ለምን አታነጋግርም? እንዲህ ያለው ወዳጅ ጠንካራ ጎኖችህን ለይተህ እንድታውቅና ጥሩ አድርገህ እንድትጠቀምባቸው ሊረዳህ ይችላል።
ችግሮች ቢኖሩም እድገት ማድረግ
“እድገትህ ለሁሉም ግልጽ ሆኖ እንዲታይ መላውን ትኩረትህንና መላውን ኃይልን በእነዚህ ነገሮች ላይ አድርግ።” (1 ጢሞቴዎስ 4:15፣ ፊሊፕስ) ጢሞቴዎስ ቀደም ሲል ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም በአገልግሎቱ ተጨማሪ እድገት እንዲያደርግ ጳውሎስ ልክ ልጁን እንደሚያነጋግር አንድ አባት በመሆን አበረታቶታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን “እድገት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግሥ ቃል በቃል ሲተረጎም “እየመነጠሩ ወደፊት መግፋት” ማለት ሲሆን ይህም መንገድ እያወጣ በዱር ውስጥ የሚያልፍን ሰው ያስታውሰናል። አንዳንድ ጊዜ የትምህርት ቤት ሕይወትም ከዚያ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይሁን እንጂ መጨረሻ ላይ ስለሚገኘው ወሮታ አሻግረህ የምታስብ ከሆነ በትምህርት ቤት የምታሳልፈው ሕይወት ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል።
ጥረት፣ ውስጣዊ ግፊትና ትምህርት የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል የሙዚቃ መሣሪያ ስለሚጫወት አንድ ሰው ለአንድ አፍታ አስብ። መሣሪያውን መጫወት የሚያስደስተው ከሆነ ደጋግሞ መጫወቱን ይቀጥላል። ይበልጥ እየተጫወተ በሄደ መጠን ደግሞ ችሎታው ያድጋል፤ ይህም ደስታውን ይጨምርለታል። እኛም ይበልጥ በተማርን መጠን የመማሩ ሂደት ይበልጥ እየቀለለን ይሄዳል። ስለዚህ ተስፋ አትቁረጥ። አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ አድርግ። ጥሩ ውጤት እንድታመጣ ከሚረዱህ ሰዎች ጋር ተወዳጅ። በተጨማሪም “እናንተ ግን ለሥራችሁ ብድራት ይሆንላችኋልና በርቱ፣ እጃችሁም አይላላ” በማለት ዓዛርያስ ለጥንቱ ንጉሥ አሳ የተናገራቸውን ቃላት ምንጊዜም አትዘንጋ።—2 ዜና መዋዕል 15:7
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የመማር ችሎታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ወጣቶች በዚህ ረገድ ለየት ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊገጥሟቸው ይችላሉ። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የሰኔ 22, 1996 የእንግሊዝኛ ንቁ! ገጽ 11-13ን ተመልከቱ።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የትምህርት ውጤትህን ለማሻሻል ያለህን ግብ ለአስተማሪህ ከመንገር ወደኋላ አትበል
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ የትምህርት ዓይነት የሚሰጠው ተግባራዊ ጠቀሜታ አነስተኛ ቢመስልም እንኳ ጠንቅቀህ ማወቅህ በእጅጉ ይጠቅምሃል