የፊት ላይ ምልክት እየቀረ የመጣው የናይጄሪያውያን ‘መታወቂያ’
ናይጄሪያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
በ1960ዎቹ ዓመታት ማብቂያ ላይ አንድ ቀን ጠዋት የስድስት ዓመቱ ዳንጁማ የኢጋላ ተወላጆች የሚኮሩበትን የፊት ላይ ሽንትፍ ለእሱም እንዲያደርግለት አባቱን አጥብቆ ጠየቀ። ዳንጁማ የፊት ላይ ምልክት የሌለው እየተባለ የክፍል ጓደኞቹ መቀለጃ መሆን ሰልችቶት ነበር። አብዛኛውን ጊዜ በኢጋላ ጎሳ ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ፊታቸውን የሚሸነተፉት ገና ነፍስ ሳያውቁ ቢሆንም ልጆቹ ደፋር መሆናቸውን የሚያሳይ ምልክት አድርገው ይቆጥሩታል። ምልክት የሌላቸውን ልጆች የቢለዋ ስለት መጋፈጥ የማይችሉ ፈሪዎች አድርገው ይመለከቷቸዋል።
የዳንጁማ አባት እስከዚያን ጊዜ ድረስ የልጁን ፊት መሸንተፍ አልፈለገም ነበር። ሆኖም የዚያን ዕለት ጠዋት ደፋር መሆኑን ለማስመስከር ቆርጦ በተነሳው ልጁ ገፋፊነት ቢለዋ ወስዶ በልጁ ፊት ላይ በሁለቱም ጎን ከአፉ ትንሽ ከፍ ብሎ አግድም ሦስት ቦታ ላይ ሸነተፈው።
የዳንጁማ አባት እነዚያ ሽንትፎች ደፋር መሆንን የሚያሳዩ እንዳልሆኑ ያውቅ ነበር። ከዚያ ይልቅ ሽንትፎቹ ይደርቁና ለምልክት የሚሆን ጠባሳ ትተው ያልፋሉ። ሊጠፉም ሆነ ሊለወጡ የማይችሉ ቋሚ ‘መታወቂያ’ ይሆናሉ። ልጁን ዘመዶቹ ያለ ምንም ችግር ወዲያውኑ እንዲለዩት በማስቻል አንድ የኢንጋላ ተወላጅ ላሉት ሕጋዊና ሌሎች መብቶች ብቁ ያደርጉታል። ይሁን እንጂ ምልክቶቹ በናይጄሪያ ከሚገኙት ከ250 በላይ ከሚሆኑት ሌሎች የጎሳ ቡድኖች የተለየ መሆኑንም የሚያሳዩ ናቸው።
አካልን መብጣትም ሆነ መሸንተፍ በአፍሪካ ብቻ የተወሰነ ልማድ ባይሆንም በአህጉሩ ውስጥ የረዥም ጊዜ ታሪክ አለው። የግሪኩ ታሪክ ጸሐፊ ሂሮደተስ በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በግብጽ ይኖሩ ስለነበሩት ካሪያናውያን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ግምባራቸውን በቢለዋ በመሸንተፍ ግብጻውያን አለመሆናቸውን ያሳውቁ ነበር።” ከሰባት መቶ ዓመታት በፊት በናይጄሪያ ኢፊ ከተማ ውስጥ ከነሐስ የተሠሩ የአንገት በላይ ምስሎች የፊት ላይ መስመሮች ያሏቸው ሲሆን ብዙ ሰዎች እነዚህ መስመሮች የጎሣ ምልክቶች ናቸው የሚል እምነት አላቸው። በተጨማሪም በጥንታዊው የናይጄሪያ ግዛት በቤኒን ውስጥ በሚገኙ ቅርጻ ቅርጾች ላይም የፊት ላይ ምልክት ይደረግ እንደነበር ተረጋግጧል።
በፊት ላይ ምልክት የሚደረገው ጎሳን ለማመልከት ብቻ አይደለም። አንዳንድ ምልክቶች ከመናፍስታዊና ሃይማኖታዊ ልማዶች ጋር ግንኙነት የነበራቸውና አሁንም ያላቸው ናቸው። አንድ ሰው በባህላዊው ማኅበረሰብ ውስጥ ያለውን ቦታ የሚጠቁሙ ምልክቶችም አሉ። ሌሎቹ ደግሞ ለውበት ሲባል የሚደረጉ ናቸው።
ሽንተፋው የሚከናወነው በማኅበረሰቡ ውስጥ በሚገኙ ዐዋቂዎች ሲሆን የፊት ላይ ምልክቶቹም የተለያየ ዓይነት አላቸው። አንዳንዶቹ ቆዳን በትንሹ በመብጣት የሚደረጉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በጣት እንዲሰፉ የተደረጉ ጥልቅ ስንጥቆች ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ምልክቶቹን ለማቅለም በቁስሉ ላይ በአካባቢው የሚሠራ ቀለም ይደረግበታል። እያንዳንዱ ጎሳ የራሱ የሆነ የተለየ ምልክት አለው። ለምሳሌ ያህል የኦንዶ ወንዶችና ሴቶች በሁለቱም ጉንጮቻቸው ላይ አንድ ቀጥ ያለ ምልክት ያደርጋሉ። በእያንዳንዱ ጉንጭ ላይ የሚደረጉ ሦስት አግድም ምልክቶች የኦዮ ሰዎችን ለይተው የሚያሳውቁ ናቸው። ምልክቶቹን ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰዎች የአንድን ሰው ፊት በማየት ብቻ የሰውየውን ጎሳ፣ መንደርና ቤተሰቡን ሳይቀር መናገር ይችላሉ።
የተለያዩ አመለካከቶች
ምልክቶቹም ሆኑ ምልክቶቹ የሚደረጉባቸው ምክንያቶች የተለያዩ እንደሆኑ ሁሉ ሰዎች ለምልክቶቹ ያላቸው አመለካከትም የዚያኑ ያህል የተለያየ ነው። ብዙዎች ባሏቸው ምልክቶች ይኮራሉ። የናይጄሪያው ዴይሊ ታይምስ መጽሔት አዘጋጅ እንዲህ ብሏል:- “አንዳንዶች ምልክቶቹን የሚመለከቷቸው ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ አርማ አድርገው ነው። የቀድሞ አባቶቻችን ትክክለኛ ልጆች ነን የሚል ስሜት እንዲያድርባቸው ያደርጋቸዋል።”
ጂሞ የሚባል አንድ ናይጄሪያዊ እንደሚከተለው ይላል:- “የኦዮ ምልክቶቼ ከአላፊን መንደር የመጣሁ ትክክለኛ የዮሩባ ተወላጅ መሆኔን የሚያሳውቁ በመሆናቸው የሃፍረት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም።” በመቀጠልም በ1967 በናይጄሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ጊዜ ምልክቶቹ ሕይወቱን እንዴት እንዳተረፉለት ተናግሯል:- “እኖርበት የነበረበት ቤት . . . ተከብቦ [ከእኔ በስተቀር] ሁሉም ተገደሉ። ነፍሰ ገዳዮቹ በፊቴ ላይ ባሉት ምልክቶች ምክንያት ምንም ጉዳት አላደረሱብኝም።”
ሌሎች ደግሞ ለምልክቶቹ ከፍተኛ ጥላቻ አላቸው። ታጁዲን በፊቱ ላይ ስላለው ምልክት ሲናገር “ምልክቱን እጠላዋለሁ፤ በፊቴ ላይ የተደረገበትንም ቀን እረግማለሁ” ብሏል። አንዲት በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ ልጃገረድ ትንሽ ልጅ እያለች እናቷ ምልክቱ እንዲደረግባት ባለመፍቀዷ ታመሰግናታለች። “ምልክቶቹ ቢኖሩኝ ኖሮ ራሴን አጠፋ ነበር” ብላለች።
ፌዝን መቋቋም
በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ዳንጁማ ይፌዝበት የነበረው ምልክቶቹ ስለሌሉት ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ግን ሁኔታው ተቃራኒ ነው። ከ45 ዓመታት በፊት ጂ ቲ ባስደን ኒጀር ኢቦስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “አካልን መብጣትና ንቅሳት ጊዜ ያለፈባቸው ነገሮች እየሆኑ መጥተዋል። ብዙ ወጣቶች ... [ምልክቶቻቸው] ቢጠፉላቸው ይወዳሉ። ከወገኖቹ ጋር በሚሆንበት ጊዜ የሚኮራበት ነገር በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ሰዎች ዘንድ ስለሚፌዝበትና ስለሚናቅ የሚያሳፍር ነገር ይሆናል።”
በተለይ ዛሬ የእነዚህ ቃላት እውነታ ጎልቶ ይታያል። ከሌጎስ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቡና ዲግሪዋን የተቀበለችው አጃይ በናይጄሪያ በሚደረገው የፊት ምልክት ላይ በቅርቡ አንድ ጥናት አካሂዳ ነበር። የታዘበችውን ስትናገር እንዲህ ብላለች:- “በአሁኑ ጊዜ በተለይ እንደ ሌጎስ ባሉ ከተማዎች ውስጥ የፊት ላይ ምልክት ያላቸው ሰዎች ቁጥራቸው በጣም አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ሰዎች ያፌዙባቸዋል። ለምሳሌ ያህል ሰዎች አንድን ግለሰብ ኮሎኔል ብለው ሲጠሩት መስማት የተለመደ ነው፤ ሰውየው የጦር ሠራዊት አባል ሆኖ ሳይሆን በጉንጮቹ ላይ የሚገኙት ሦስት መስመሮችና አንድ የጦር ሠራዊት ኮሎኔል በሚለብሰው ዩኒፎርም ላይ ያሉት መስመሮች ቁጥር ተመሳሳይ ስለሆነ ብቻ ነው። አንዳንዶች ጉንጫቸው ላይ ባለው መስመር ምክንያት ነብር ሲባሉ ሌሎች ደግሞ የእንባ ጅረት ተብለው ይጠራሉ። . . . ይህ ግለሰቡ ለራሱ በሚኖረው ግምት ላይ ምን ያህል ተጽእኖ እንደሚያሳድር ልትገምቱት ትችላላችሁ።”
ምናልባትም ይበልጥ ከባድ ፈተና የሚሆነው በትምህርት ቤት የሚያጋጥመው ሳይሆን አይቀርም። ሳምዌል በክፍሉ ውስጥ የፊት ላይ ምልክት ያለው እሱ ብቻ ነበር። እንዲህ ይላል:- “በትምህርት ቤት ውስጥ መቀለጃ ነበርኩ። የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ‘የባቡር ሐዲድ’ እና ‘የባቡር ሐዲድ ያለው ልጅ’ እያሉ ይጠሩኝ ነበር። ሁልጊዜ ያሾፉብኝ የነበረ ሲሆን ሦስት ጣቶቻቸውንም ይቀስሩብኝ ነበር። ይህ የበታችነት ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል።”
ይህን ሁኔታ ሊወጣው የቻለው እንዴት ነው? ሳሙዌል በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “አንድ ቀን በፌዛቸው በጣም በመማረሬ ወደ ባዮሎጂ መምህሬ ሄድኩና ምልክቶቹን ማጥፋት ይቻል እንደሆነና እንዳልሆነ ጠየቅሁት። ፕላስቲክ ሰርጀሪ በተባለ የቀዶ ሕክምና አማካኝነት ምልክቶቹን ማጥፋት እንደሚቻል ነገረኝ፤ ይሁን እንጂ በናይጄሪያ የሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ምልክት ያላቸው በመሆኑ ምንም መጨነቅ እንደሌለብኝ ነገረኝ። እኩዮቼ የሚያሾፉብኝ የአእምሮ ብስለት ስለሌላቸው መሆኑንና ትልቅ ሰው በምንሆንበት ጊዜ ግን የሚያፌዝብኝ እንደማይኖር ነገረኝ። በተጨማሪም ምልክቶቹ ምን ዓይነት ሰው እንደሆንኩ ወይም ወደፊት ምን ዓይነት ሰው እንደምሆን እንደማይወስኑ ነገረኝ።
“ይህ ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ ያደረገ ሲሆን ስለ ምልክቶቹ የነበረኝ መጥፎ ስሜትም ጠፋ። በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ስላሉኝ ምልክቶች የሚናገሩት ከስንት አንዴ ነው። ስለ ምልክቶቹ በሚጠቅሱበት ጊዜም ስቄ አሳልፈዋለሁ። ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ። ሰዎች የሚያከብሩኝ በእኔነቴ እንጂ ባለኝ ምልክት አይደለም።”
እየቀረ የመጣ ባህል
አብዛኛውን ጊዜ ምልክት የሚደረገው በትናንሽ ልጆች ላይ በመሆኑ በፊታቸው ላይ የጎሳ ምልክት ያላቸው አብዛኞቹ ናይጄሪያውያን በጉዳዩ ላይ ምንም የመምረጥ መብት አልነበራቸውም ለማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ እነሱ በተራቸው ወላጆች በሚሆኑበት ጊዜ ልጆቻቸው ላይ ምልክት ለማድረግ ወይም ላለማድረግ መወሰን አለባቸው።
አንዳንዶች ምልክቱን በልጆቻቸውም ላይ ማድረግ መርጠዋል። በሌጎስ የሚታተመው ታይምስ ኢንተርናሽናል የተባለው መጽሔት ለዚህ ውሳኔ ያበቋቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሏቸው ተናግሯል። መጽሔቱ እንዲህ ይላል:- “አሁንም እንኳ አንዳንዶች ምልክቶቹ መልክ ለማሳመር ይረዳሉ ብለው ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ ምልክቱ ያለበትን ሰው ጎሳ ለመለየትና ለአድልዎ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል የሚል እምነት አላቸው። ሌላው ጥቅም በባህላዊው አሠራር መሠረት የአንድን ልጅ ሕጋዊነት ለይቶ ማሳወቅ የሚያስችል መሆኑ ነው።”
ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ብዙ ወላጆች እነዚህ ምክንያቶች የሚዋጡላቸው አልሆኑም። በምልክቶቻቸው ከሚኮሩት መካከል እንኳን የባህል ሐኪሙ ቢለዋ በልጆቻቸው ፊት ላይ እንዲያርፍ የሚፈቅዱት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በጣም ጥቂቶች ናቸው። በተለይ ይህ በከተማዎች ውስጥ በሰፊው የሚታይ ነገር ነው። ሕመሙ እንዲሁም ቁስሉ ያለው የመመረዝ አደጋ፣ ልጁ በኋለኛው የሕይወት ዘመኑ ሊደርስበት ከሚችለው ንቀትና መድሎ ጋር ተዳምሮ ወላጆች የፊት ላይ ምልክቶችን እንዲቃወሙ ያደርጋቸዋል።
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የፊት ላይ ምልክት የነበረውን ተወዳጅነትና ተቀባይነት በፍጥነት እያጣ ነው። ወደፊት በናይጄሪያ ውስጥ የሰዎች ‘መታወቂያ’ በፊት ላይ ሳይሆን በቦርሳ ውስጥ የሚያዝ ነገር የሚሆን ይመስላል።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የፊት ላይ ምልክቶች ጎሳን ለይተው ያሳውቃሉ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፊት ላይ ምልክት ማድረግ እየቀረ የመጣ ባህል ነው