ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ...
ጓደኛዬ መፈናፈኛ አሳጣችኝ—ምን ባደርግ ይሻለኛል?
“ጓደኛዬ ልክ እንደ ግል ንብረቷ ነው የምትመለከተኝ። ምንም አታፈናፍነኝም።”—ሃሊ
ጥበብ ያለበት አንድ ምሳሌ “ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ” ይላል። (ምሳሌ 18:24) እናንተ በምታምኑበት ነገር የሚያምን፣ በምትደሰቱበት ነገር የሚደሰት ወይም የምትወዱትን ነገር የሚወድ ጓደኛ ካላችሁ አብራችሁት መሆን እንደምትፈልጉ የታወቀ ነው። ካረሊን የተባለች አንዲት ወጣት “በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ካሉ ከአንዳንዶች ጋር በጓደኝነት ያቀራረበኝ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች አብሬ መካፈሌ ነው” ብላለች። ካረሊን የይሖዋ ምሥክር ስለሆነች በወንጌላዊነቱ ሥራ 60 ሰዓት ለማሳለፍ አንድ ወር መድባ ነበር። ጓደኞቿ በዚህ ሥራ እሷን ለማገዝ ፕሮግራማቸውን አስተካከሉ!
ሆኖም አንድ ላይ መሆን የራሱ ጥቅሞች ቢኖሩትም አንዳንድ ጊዜ ከልክ ሊያልፍ ይችላል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ሃሊ አንድ ጓደኛዋ መፈናፈኛ እንዳሳጣቻት ሆኖ ተሰምቷታል። እንዲህ የሚሰማት እሷ ብቻ አይደለችም። ሃሊ እንዲህ በማለት የታዘበችውን ተናግራለች:- “ሌሎች ልጆችም እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ይመስላል። እፍ እፍ ሲሉ ይከርሙና ድንገት ይናቆራሉ። ከዚያም ተኮራርፈው ሳምንታት ያልፋሉ።”
ችግሩ ግን፣ መፈናፈኛ እንዳሳጣችሁ ሆኖ እንደሚሰማችሁና ለብቻችሁ የምትሆኑበት ጊዜ እንደምትፈልጉ ለራሱ ለጓደኛችሁ መንገር ቀላል አይደለም። ስሜቱን እጎዳዋለሁ ብላችሁ ልትፈሩ ትችላላችሁ። ግንኙነታችሁ አደጋ ላይ እንዳይወድቅም ትፈሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ጓደኛሞች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መራራቃቸው ይጠቅም ይሆናል እንጂ አይጎዳም።
በምሳሌ ለማስረዳት:- በአውስትራሊያ ሲድኒ በአንድ የሕዝብ መናፈሻ ውስጥ የሚገኝ ትልቅ ዛፍ በሽቦ መታጠር አስፈልጎታል። ለምን? ምክንያቱም በሺህ የሚቆጠሩ ጎብኚዎች አፈሩን በመደምደም ሥሮቹን መፈናፈኛ ስላሳጧቸው ነው። ይህ ዛፍ በአጥር ባይከለል ኖሮ ይደርቅ ነበር። ጓደኝነትን በተመለከተም ተመሳሳይ ነገር ሊከሰት ይችላል። ሙጭጭ ብሎ አብሮ ጊዜ ማሳለፍ ግንኙነቱን መፈናፈኛ የሌለው ሊያደርገው ይችላል። ንጉሥ ሰሎሞን “እንዳይሰለችህ እንዳይጠላህም እግርህን ወደ ባልንጀራህ ቤት አታዘውትር” ሲል ጽፏል።—ምሳሌ 25:17
ለብቻችን የምንሆንበት ጊዜ ማግኘት አስፈላጊ ነው
ሰሎሞን እንዲህ ያለው ለምን ነበር? በመጀመሪያ ደረጃ ሁላችንም ብንሆን ለብቻችን የምንሆንበት ጊዜ ማግኘት እንፈልጋለን። ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ ለብቻው የሚሆንበት ጊዜ ፈልጎ ነበር። ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በጣም ይቀራረብ የነበረ ቢሆንም በየጊዜው “ይጸልይ ዘንድ ብቻውን” ይሆን ነበር። (ማቴዎስ 14:23፤ ማርቆስ 1:35) በተመሳሳይም ፈሪሃ አምላክ የነበረው ይስሐቅ ብቻውን የሚሆንበት ጊዜ አግኝቶ ነበር። (ዘፍጥረት 24:63) እናንተም የቤት ሥራችሁን የምትሠሩበት፣ ቤት ውስጥ ወላጆቻችሁን የምትረዱበት እንዲሁም የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችሁን የምታካሂዱበት የራሳችሁ የሆነ የተወሰነ ጊዜ ያስፈልጋችኋል። በዚህ ረገድ ጓደኞቻችሁ የእናንተን ፍላጎት የማይረዱና አሳቢነት የማያሳዩ ከሆነ በመካከላችሁ በቀላሉ ቅሬታ ሊፈጠር ይችላል።
ስለዚህ ለብቻችሁ የምትሆኑበት ጊዜ እንደሚያስፈልጋችሁ ሲሰማችሁ ለጓደኛችሁ መንገር አትፍሩ። ክርስቲያናዊ ፍቅር “የራሱን ጥቅም ብቻ ፈላጊ” ስላልሆነ አብዛኛውን ጊዜ እውነተኛ ጓደኛ የሌላውን ሐሳብ ለመረዳት ይጥራል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5 የ1980 ትርጉም፤ ምሳሌ 17:17) አንዲት ወጣት እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “የመጨረሻ ፈተናዬን የምወስድበት ጊዜ ሲቃረብ ጓደኞቼ ድጋፍ ይሰጡኝ ነበረ፤ ሐሳቤንም ይረዱልኝ ነበር። ማጥናት በሚያስፈልገኝ ጊዜ እንዲሄዱልኝ ለመጠየቅ ምንም አይጨንቀኝም ነበር። ከጓደኞቼ ጋር ሐቀኛ መሆን ቀላል ነበር፤ ሁላችንም ኃላፊነቶች እንዳሉብን ያውቃሉ።”
እንዲያውም ወርቃማው ሕግ ለጓደኛችሁ እንዲህ ያለውን አሳቢነት እንድታሳዩ ይጠብቅባችኋል። (ማቴዎስ 7:12) ታማር የምትባል አንዲት ወጣት “ብዙ ኃላፊነቶች ያለኝ መሆኔ ጓደኛዬ ለብቻዋ የምትሆንበት ጊዜ እንደሚያስፈልጋት ይበልጥ እንድገነዘብ አድርጎኛል” ስትል ጽፋለች። እንዲሁም ታማር የቤት ውስጥ ሥራ ሲኖራት ጓደኞቿ ሥራዋን በጥድፊያ እንደነገሩ ሠርታ እንድትጨርስ ወይም ለሌላ ጊዜ እንድታስተላልፈውና ከእነሱ ጋር እንድትሆን አይጨቀጭቋትም። ከዚህ ይልቅ ታማር እንዲህ ትላለች:- “ከዚያ በኋላ አብረን አንዳንድ ነገሮች እንድናደርግ ሥራዬን እንድጨርስ ያግዙኛል።” ራስ ወዳድ ያልሆኑ እንዲህ ያሉ ጓደኞች ማግኘት ምንኛ መታደል ነው! ጊዜን በጥሩ ሁኔታ አብሮ ማሳለፍ ማለት ይህ ነው!
“ተስፋፉ”
ጓደኛሞች በተወሰነ መጠን መራራቃቸው ጥበብ የሚሆንበት ሌላም ምክንያት አለ። ጊዜያችንንና ስሜታችንን የምንጋራው ከአንድ ጓደኛችን ጋር ብቻ ከሆነ ከወላጆቻችን፣ ከሥጋ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ያለንን አስፈላጊ ግንኙነት ችላ ወደ ማለት እናዘነብል ይሆናል። በተጨማሪም ስሜታዊና መንፈሳዊ እድገታችንን በእጅጉ እንገድባለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ብረት ብረትን ይስለዋል፣ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል” ይላል። (ምሳሌ 27:17) ከአንድ ሰው ጋር፣ በተለይ ደግሞ በዕድሜ እኩያችሁ ከሆነ ሰው ጋር ብቻ የምትወዳጁ ከሆነ ‘ለመሳል’ ያላችሁ አጋጣሚ የዚያኑ ያክል ውስን ይሆናል።
በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ በጓደኛ ምርጫችን ረገድ ጠባቦች መሆንን ወይም ሌሎችን ማግለልን አያበረታታም። ‘እንድንስፋፋ’ አጥብቆ ይመክረናል። (2 ቆሮንቶስ 6:13) ሙድስ ኤንድ ፊሊንግስ የተባለው መጽሐፍ “ከአንድ ሰው ጋር ልዩ ቅርርብ ያለህ ብትሆንም እንኳ ከሌሎች ጓደኞችህ ጋር ለመሆንም ጊዜ መዋጀቱ አስፈላጊ ነው” ሲል ምክር ይለግሳል።
እንዲህ ያለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም። ማይክል የተባለ አንድ ክርስቲያን ወጣት እንዲህ ብሏል:- “እኔና ትሮይ በጉባኤም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ማንኛውንም ነገር የምንሠራው አንድ ላይ ነበር። በፍጹም አንለያይም ነበር። ከዚያም አንድ ሌላ ወጣት ወንድም ወደ ጉባኤያችን ተዛወረ። ከዚህ ወንድም ጋር በሙሉ ጊዜ ወንጌላዊነት አንድ ላይ ለማገልገል ስለፈለግን አብረን ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ጀመርን።” ከዚያስ? “ከዚያ ትሮይ ጨርሶ አኮረፈኝ፤ ሁኔታውን ለማስተካከል ሞክሬ አልሳካልኝ ቢለኝ እኔም ማነጋገሬን አቆምኩ። እንደ ተኮራረፍን አንድ ዓመት አለፈ” ይላል ማይክል። ወዳጅነታቸውን “የኔ ብቻ ይሁን የሚል የቅንዓት መንፈስ የሚንጸባረቅበት” ሲል ገልጾታል።
ይሁን እንጂ ጓደኛሞች ጤናማ የሆነ ወዳጅነት ካላቸው አንዳቸው ሌላውን እንደ ግል ንብረታቸው አድርገው አይመለከቱም። ስለዚህ አንድ ጓደኛችሁ ወዳጅነታችሁን ለማስፋት የምታደርጉት ጥረት የሚያስከፋው ከሆነ በግልጽ መወያየት ያስፈልጋችኋል። ምናልባት ጓደኛችሁ የሚፈልገው ከእሱ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ምንጊዜም ከፍ አድርጋችሁ እንደምትመለከቱት የሚያሳይ ማረጋገጫ ይሆናል። በጓደኝነት አብራችሁ የምታደርጓቸውን ነገሮች ወደፊትም እንደሚቀጥሉ ግልጽ አድርጉለት።
ጓደኛችሁ ይህን ሐሳብ ለመቀበል ትንሽ ጊዜ ሊወስድበት እንደሚችል አይካድም። ለምሳሌ ያህል የአሥራ ስድስት ዓመቷ ዛኔታ የቅርብ ጓደኛዋ ከሌሎች ልጆች ጋር ጊዜ ማሳለፍ መጀመሯን ስትመለከት የቅናት ስሜት አድሮባት ነበር። ሆኖም ዛኔታ “በጸሎትና የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግ” ይህን ስሜት ማሸነፍ እንደቻለች ተናግራለች። በዚህ መንገድ ከጓደኛዋ ጋር የነበራትን የቅርብ ወዳጅነት ጠብቃ ለማቆየት ችላለች። የማይክል ጓደኛ የሆነው ትሮይም በመጀመሪያ የተሰማውን የቅናት ስሜት በማሸነፍ እንደገና ጥሩ ጓደኛሞች ሊሆኑ ችለዋል። ምናልባት የእናንተም ጓደኛ እንዲህ ያደርግ ይሆናል። በእርግጥም ወዳጅነትን ማስፋት የኋላ ኋላ ለሁሉም ይጠቅማል። የአሥራ ሰባት ዓመቷ ዴቢ ጓደኞቿ የሚያፈሯቸው አዳዲስ ጓደኞች “አብዛኛውን ጊዜ የእኔም ጓደኞች ይሆናሉ” በማለት ተናግራለች።
ይሁንና ጓደኛችሁ በወዳጅነታችሁ ላይ የተፈጠሩትን እነዚህን ለውጦች ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆንስ? ከመለያየት ሌላ ምንም አማራጭ ላይኖራችሁ ይችላል። ይሁን እንጂ ጓደኝነታችን አብቅቶለታል ብላችሁ ከመደምደማችሁ በፊት ለምን ወላጆቻችሁን አታማክሯቸውም? እንዲያውም ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች ከማንም ይበልጥ የሚቀርቡ ወዳጆች መሆናቸው የተረጋገጠ ነው። በግል ማሳለፍ የምትፈልጉት ጊዜ እንደተጠበቀ ሆኖ ወዳጅነታችሁን ጠብቃችሁ ማቆየት የሚያስችሏችሁን አንዳንድ ተግባራዊ ምክሮች ሊለግሷችሁ ይችላሉ።
ጥሩ ከሆኑ ጓደኞች ጋር ጊዜ አሳልፉ
አንድ ልብ ልንለው የሚገባ ነገር:- ወዳጅነትን ማስፋት ማለት በጓደኛ ምርጫችሁ ረገድ እገሌ ከገሌ ሳትሉ ማንንም ጓደኛ ማድረግ ትችላላችሁ ማለት አይደለም። ስለ ጓደኝነት የሚናገር አንድ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ብዙ ጊዜ አብረሃቸው ከምትውላቸው ሰዎች ጋር መመሳሰል ያለ ነገር ነው። አንዳንድ ጊዜ እነሱን እየመሰልክ የምትሄደው ሳይታወቅህ ነው። የሚሰማህ ስሜት ምንም ይሁን ምን እንደ እኩዮችህ ማሰብና እንደነሱ መሆን ትጀምራለህ። የምትገኝበት የእኩዮችህ ቡድን በዚህ መንገድ እየተቆጣጠረህ ይሆናል።” መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” በማለት በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ተመሳሳይ ነገር ተናግሯል።—ምሳሌ 13:20
ይሖዋን ማገልገል ከማይፈልጉ ሰዎች ጋር በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ አብራችሁ ጊዜ ማሳለፍ ትገደዱ ይሆናል። ሆኖም የቅርብ ጓደኞችን በምትመርጡበት ጊዜ “መጥፎ ጓደኛ ጥሩውን ጠባይ ያበላሻል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አስታውሱ። (1 ቆሮንቶስ 15:33 የ1980 ትርጉም)
በተጨማሪም ከማንኛውም ሰብዓዊ ወዳጅነት ይልቅ ከፈጣሪያችን ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለን ወዳጅነት እንደሚበልጥብን አትርሱ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ዴቢ በርካታ ጥሩ ጓደኞች አላት። ሆኖም “ሁልጊዜ ለይሖዋ ቅድሚያ ስጡ” በማለት ትመክራለች። ታማኝ የነበረው የጥንቱ ሰው አብርሃም ይህን አድርጓል፤ ይሖዋም ‘ወዳጄ’ ብሎ ጠርቶታል። (ኢሳይያስ 41:8) እንዲሁም ይህን አስቡ:- ይሖዋ እሱን ከሚወዱት ጓደኞቻችሁ ጋር ጊዜ በማሳለፋችሁ ቅር አይሰኝም፤ እንዲያውም እንዲህ ማድረግን ያበረታታል። እንዴት ያለ እውነተኛ ጓደኛ ነው!
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ ጓደኛሞች እያንዳንዳቸው ለብቻቸው የሚሆኑበት ጊዜ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸው ይገነዘባሉ