የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 7/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ድህነትና አካባቢ
  • ተስፋ መቁረጥ የሚያስከትለው አደጋ
  • በጉዞ የሚጠፉ ዓመታት
  • ማጨስ የማይሽር ጉዳት ያስከትላል!
  • የፈረንሳይኛ ቋንቋ የተደቀነበት ሥጋት
  • ጉቦ ለማስቀረት የሚደረግ ጥረት
  • የአባጨጓሬ ወረት
  • ዓለም አቀፍ የደኖች መመናመን
  • የተረሳ ሕግ
  • የእሳት እራት ለእራት
    ንቁ!—2007
  • ከሲጋራ ትርቃለህን?
    ንቁ!—1997
  • በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ሕይወት እንደ ጭስ እየበነነ ነው
    ንቁ!—1999
  • ማጨስ ኃጢአት ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 7/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

ድህነትና አካባቢ

በመላው ዓለም የኢኮኖሚ እድገት ቢኖርም አሁንም 1.3 ቢልዮን የሚያክሉ ሰዎች የሚተዳደሩት ከሁለት ዶላር ባነሰ የቀን ገቢ ነው። አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚለው ድህነትን ማስወገድ ቀርቶ እየተባባሰ እንዳይሄድ ማድረግ እንኳን አልተቻለም። በአሁኑ ጊዜ ከአንድ ቢልዮን የሚበልጡ ሰዎች የሚያገኙት ገቢ ከ20፣ ከ30 ወይም ከ40 ዓመት በፊት ያገኙት ከነበረው በጣም ያነሰ ነው። ይህ ደግሞ ለአካባቢ ጥፋት አስተዋጽኦ አድርጓል። ምክንያቱም ዩኔስኮ ሶርስ መጽሔት እንዳለው “ድህነት የአካባቢ ጥበቃን በሚጻረር መንገድ የተፈጥሮ ሀብቶችን አሟጥጦ ለመጠቀም ያስገድዳል። በአሁኑ ፍጥነት ከቀጠለ በካሪብያን አገሮች የሚገኙ ደኖች ከ50 ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ፈጽመው ይወድማሉ። . . . በብሔራዊ ደረጃ ከታየ ሁኔታው እንዲያውም ከዚህ የባሰ ነው። ፊሊፒንስ ያላት ደን ለ30 ዓመት ብቻ የሚያቆያት ሲሆን አፍጋኒስታን 16 ዓመት፣ ሊባኖስ 15 ዓመት ብቻ የሚያቆይ ደን አላቸው።”

ተስፋ መቁረጥ የሚያስከትለው አደጋ

“ተስፋ መቁረጥ በልብ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በቀን 20 ሲጋራ ማጨስ ከሚያስከትለው ጉዳት ጋር እንደማይተናነስ . . . ሳይንቲስቶች ይናገራሉ” ሲል የለንደኑ ዘ ታይምስ ሪፖርት አድርጓል። “በመካከለኛ ዕድሜ ላይ በሚገኙ 1,000 ፊንላንዳውያን ላይ የተደረገ የአራት ዓመት ጥናት እንዳመለከተው ተስፋ መቁረጥ አቴሮስክሌሮሲስ ወይም በደም ቅዳ ቧንቧዎች የመደንደንን ዕድል ከፍ እንደሚያደርግ አረጋግጧል።” የአንድ ሰው የአእምሮ ወይም የአስተሳሰብ ሁኔታ በጤንነቱ ላይ በቀላሉ የማይገመት ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል ጥናቱ አመልክቷል። ጥናቱን የመሩት ዶክተር ሱዛን ኤቨርስን “ሥነ ልቦናዊና ስሜታዊ ሁኔታዎች በጤንነት ላይ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ የማያሻማ ማስረጃ እያገኘን ነው” ብለዋል። አክለውም “ሐኪሞች ተስፋ ቢስ መሆን በጤንነት ላይ ጉዳት እንደሚያስከትልና ተጨማሪ ጭነት እንደሚያስከትል ማወቅ ይኖርባቸዋል። ሰዎች ተስፋ የመቁረጥና ተስፋ ቢስ የመሆን ስሜት ሲሰማቸው እርዳታ ለማግኘት ጥረት ማድረግ እንደሚኖርባቸው መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል” ብለዋል።

በጉዞ የሚጠፉ ዓመታት

የትላልቆቹ የኢጣሊያ ከተሞች ነዋሪዎች ከቤት ወደ ሥራ ወይም ከቤት ወደ ትምህርት ቤት ሲመላለሱ ረዥም ሰዓት ያጠፋሉ። ምን ያህል ጊዜ ያሳልፋሉ? ለጋምቢዬንቴ የተባለው የኢጣሊያ የአካባቢ ጥበቃ ማኅበር እንዳለው የኔፕልስ ነዋሪዎች በየቀኑ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ 140 ደቂቃ ያሳልፋሉ። የአንድ ሰው በሕይወት የመቆያ ዘመን በአማካይ 74 ዓመት ቢሆን አንድ የኔፕልስ ነዋሪ ከዕድሜው ላይ ለጉዞ የሚያጠፋው ጊዜ 7.2 ዓመት ይሆናል ማለት ነው። በየቀኑ 135 ደቂቃ በጉዞ የሚያሳልፍ የሮም ነዋሪ ደግሞ 6.9 ዓመት ያባክናል። በሌሎች ከተሞች ያለው ሁኔታም ከዚህ የሚሻል አይደለም። በቦሎኛ የሚኖሩ ሰዎች 5.9 ዓመት፣ በሚላን የሚኖሩ ደግሞ 5.3 ዓመት በመንገድ ላይ እንደሚያጠፉ ላ ሪፑብሊካ የተባለው ጋዜጣ ሪፖርት አድርጓል።

ማጨስ የማይሽር ጉዳት ያስከትላል!

አንድ በቅርቡ የተደረገ ጥናት በማጨስ ምክንያት በደም ቅዳ ቧንቧዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ሊሽር የማይችል እንደሆነ አመልክቷል። ተመራማሪዎች ሲጋራ ማጨስም ሆነ ሌሎች ለሚያጨሱት የሲጋራ ጭስ መጋለጥ በደም ቅዳ ቧንቧዎች ላይ ሊሽር የማይችል ጉዳት እንደሚያስከትል ዘ ጆርናል አቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን ላይ ሪፖርት አድርገዋል። ጥናቱ ከ45 እስከ 65 ዓመት ዕድሜ በሚገኙ 10,914 ወንዶችና ሴቶች ላይ ክትትል አድርጎ ነበር። ጥናት ከተደረገባቸው ሰዎች መካከል አጫሾች፣ የቀድሞ አጫሾች፣ አጫሾች ባይሆኑም ሁልጊዜ ለሲጋራ ጭስ የተጋለጡ፣ የማያጨሱና ለሲጋራ ጭስ የማይጋለጡ ሰዎች ይገኙበት ነበር። ተመራማሪዎቹ በአልትራሳውንድ መሣሪያ በመጠቀም በአንገት ላይ የሚገኘውን የካሮቲድ ደም ቅዳ ቧንቧ ውፍረት ለኩ። ከሦስት ዓመትም በኋላ ደግመው ለኩ።

ውጤቱ እንደተጠበቀው ነበር። በዘወትር አጫሾች ላይ የደም ቅዳ ቧንቧ መደንደን ታይቷል። በየቀኑ አንድ ፓኮ ሲጋራ ለ33 ዓመት ባጨሱት ሰዎች ላይ የ50 በመቶ ጭማሪ ታይቷል። ማጨስ ያቆሙ የቀድሞ አጫሾች የደም ሥር ከማያጨሱ ሰዎች ከ25 በመቶ በሚበልጥ ፍጥነት እየጠበበ የሄደ ሲሆን የአንዳንዶቹ ጥበት በዚህ ፍጥነት የቀጠለው ማጨስ ካቆሙ ከ20 ዓመት በኋላ ጭምር ነበር። አጫሾች ሳይሆኑ ሌሎች ለሚያጨሱት ጭስ የተጋለጡ ሰዎች ለጭሱ ካልተጋለጡት በ20 በመቶ የሚበልጥ የደም ሥር ድንዳኔ ታይቶባቸዋል። በተጨማሪም ጥናቱ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ሌሎች የሚያጨሱትን የትንባሆ ጭስ በመተንፈሳቸው ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች በዓመት ከ30,000 እስከ 60,000 እንደሚደርስ ገምቷል።

የፈረንሳይኛ ቋንቋ የተደቀነበት ሥጋት

በቅርቡ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ከሆነው ዓለም የተውጣጡ ተወካዮች በቬትናም፣ ሃኖይ “የፈረንሳይኛን ዓለም አቀፋዊነት” ለማክበር የሦስት ቀን ጉባኤ አድርገው እንደነበረ ለ ፊጋሮ የተባለው የፓሪስ ዕለታዊ ጋዜጣ ዘግቧል። ፈረንሳይኛን ዕለታዊ መነጋገሪያቸው ያደረጉ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሚልዮን ይበልጣሉ። ፈረንሳይኛ እጅግ ገንኖ በነበረበት በ17ኛው መቶ ዘመን የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ቋንቋ እስከመሆን ደርሶ ነበር። “ተከፋፍላ በነበረችው አውሮፓ ጦርነቶችና ግጭቶች እልባት ያገኙ የነበረው በፈረንሳይኛ በተጻፉ የሰላም ውሎች ነበር” ይላል ጋዜጣው። አሁን ግን ፈረንሳይኛ “በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን እውቅና ለማስጠበቅ የሚንገታገት ይመስላል።” የፈረንሳይኛ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየቀነሰ የሄደው እንግሊዝኛ በተለይ በንግድ ቋንቋነቱ ይበልጥ ተወዳጅ እየሆነ በመምጣቱ ሊሆን ይችላል። ይህን አዝማሚያ ለመግታት የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት በኮምፒዩተር መገናኛዎች አማካኝነት ሰዎች የፈረንሳይኛ ፍቅር እንዲያድርባቸው ቅስቀሳ እንዲደረግ ሐሳብ አቅርበዋል። ይሁን እንጂ የፈረንሳይኛ የወደፊት ዕጣ ያሳሰባቸው አንድ የፖለቲካ ሰው ሲናገሩ “ፈረንሳይኛ የዓለም ቋንቋ መሆኑ የብዙ ሰዎችን ወይም የመገናኛ ብዙሐንንና የፖለቲከኞችን ትኩረት ሊስብ አልቻለም። ከሌሎች አገሮች ይልቅ ይህ የግድየለሽነት ባሕርይ በይበልጥ አይሎ የሚታየው በፈረንሳይ አገር ነው” ብለዋል።

ጉቦ ለማስቀረት የሚደረግ ጥረት

በቻይና ሁዌሉ፣ በኬንያ ኪቱ ኪዶጎ ይባላል። በሜክሲኮ ኡና ሞርዲዳ፣ በራሽያ ፍስያትክ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ባክሺሽ ይባላል። ጉቦ በብዙ አገሮች በጣም የተለመደ ዕለታዊ ጉዳይ ከመሆኑም በላይ ጉቦ ሳይሰጡ ንግድ ነክ ጉዳዮችን ማስፈጸም ወይም አንዳንድ ነገሮች ማግኘት ወይም ሌላው ቀርቶ ፍትሕ ማግኘት የማይቻልባቸው አገሮች አሉ። ይሁን እንጂ በቅርቡ 34 አገሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚከናወኑ የንግድ እንቅስቃሴዎች ዘንድ ጉቦን ያስወግዳል ተብሎ የታሰበ አንድ ውል ተፈራርመዋል። እነዚህ አገሮች አርጀንቲናን፣ ብራዚልን፣ ቡልጋርያን፣ ቺሊንና ስሎቫኪያን ጨምሮ 29ኙ የኢኮኖሚ ትብብርና የእድገት ድርጅት አባል አገሮች ናቸው። በተጨማሪም የዓለም ዋነኛ የገንዘብ ድርጅቶች የሆኑት የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት በሙስና ላይ እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል። እነዚህ እርምጃዎች ሊወሰዱ የቻሉት በ69 አገሮች ከሚገኙ የንግድ ድርጅቶች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ጉቦ እንደሚሰጡ የዓለም ባንክ ባደረገው ጥናት ከተረጋገጠ በኋላ ነው። በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ሙስናን በዝምታ ለሚመለከቱ አገሮች የገንዘብ እርዳታ ላለመስጠት አቅደዋል።

የአባጨጓሬ ወረት

ሞፔን የሚባሉት የአባጨጓሬ ዝርያዎች በደቡብ አፍሪካ ገጠራማ አካባቢዎች ለሚኖሩ ድሆች በምግብነት ማገልገል ከጀመሩ ብዙ ዘመናት አልፈዋል። በዚህ አካባቢ ኑሯቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች የፕሮቲን ፍላጎታቸውን የሚያሟሉት እነዚህን አባጨጓሬዎች በመመገብ ነበር። እነዚህ ኢምፐረር ሞዝ ከሚባለው የእሳት እራት ዝርያ የሚወለዱ አባ ጨጓሬዎች ሞፔን የሚለውን ስያሜ ያገኙት ምግባቸው ከሆነው ሞፔ ከተባለው ዛፍ ነው። ሴቶች በሚያዝያና በታኅሣሥ ወራት አባጨጓሬዎቹን ሰብስበው ሆድ ዕቃቸውን ካወጡ በኋላ ይቀቅሏቸውና ፀሐይ ላይ አስጥተው ያደርቋቸዋል። ያላቸው የፕሮቲን፣ የስብ፣ የቪታሚንና የካሎሪ መጠን ከሥጋና ከዓሣ አይተናነስም። በአሁኑ ጊዜ ግን የሞፔን አባጨጓሬዎች በደቡብ አፍሪካ ምግብ ቤቶች በወረት የሚበሉ ምግቦች ሆነዋል። ይህ ወረት በዚህ አካባቢ ብቻ ሳይወሰን ወደ አውሮፓና ዩናይትድ ስቴትስ ጭምር ተዛምቷል። ይህም በአፍሪካ የገጠር ነዋሪዎች ላይ ትልቅ ሥጋት አስከትሎባቸዋል። ለምን? የለንደኑ ዘ ታይምስ “የፈላጊዎቹ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ እነዚህ ዝርያዎች ጨርሰው እስከ መጥፋት ሊደርሱ ይችላሉ” ብሏል። እስከ አሁን እንኳን “ጎረቤት አገር ከሆኑት ከቦትስዋናና ከዚምባብዌ ሰፊ አካባቢዎች ጠፍተዋል።”

ዓለም አቀፍ የደኖች መመናመን

“ከዓለማችን የደን ሽፋን ሁለት ሦስተኛው ወድሟል” ሲል ዦርናል ዳ ታርድ ዘግቧል። 80 ሚልዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ከሚያክለው የምድር የተፈጥሮ ደን ውስጥ አሁን የቀረው 30 ሚልዮን ካሬ ኪሎ ሜትር የሚያክለው ብቻ ነው። ከሁሉም አሕጉሮች የባሰ ደኖች የተመናመኑት በእስያ ሲሆን 88 በመቶ የሚያክለው የተፈጥሮ ደን እንደወደመ የዓለም የዱር አራዊት ፈንድ ገልጿል። በአውሮፓ 62 በመቶ፣ በአፍሪካ 45 በመቶ፣ በላቲን አሜሪካ 41 በመቶ፣ በሰሜን አሜሪካ 39 በመቶ የሚሆነው ደን ወድሟል። ከዓለም በትልቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው የሐሩር መስመር አካባቢ ደን የሚገኝባት አማዞንያ ከተፈጥሮ ደንዋ 85 በመቶ የሚሆነው አሁንም አልጠፋም። ኦ ኤስታዶ ደ ሳኦ ፓውሎ የዓለም ዱር አራዊት ፈንድ ባልደረባ የሆኑት ጋሮ ባትማንያን “ብራዚል በሌሎች ደኖች የተፈጸመውን ስህተት ያለመድገም አጋጣሚ አላት” እንዳሉ ጠቅሷል።

የተረሳ ሕግ

ከአሥሩ ትእዛዛት ስንቶቹን በቃልህ መጥራት ትችላለህ? በሪዮ ደ ጃኔይሮ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው ጥያቄ ከቀረበላቸው 4 ብራዚላውያን መካከል ከአንድ የሚበልጡት አንዳቸውንም ለማስታወስ አልቻሉም! ቢያንስ አንዱን ሕግ እንኳን ካወቁት መካከል 42 በመቶ የሚሆኑት የጠቀሱት “አትግደል” ወይም “አትስረቅ” የሚለውን ሕግ ነው። ሌሎች ደግሞ “የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ” (38 በመቶ)፣ “እናትህንና አባትህን አክብር” (22 በመቶ)፣ “በሐሰት አትመስክር” (14 በመቶ) የሚሉትን አስታውሰዋል ሲል ቬጃ ዘግቧል። “የአምላክን ስም በከንቱ አትጥራ” የሚለውን ሦስተኛ ሕግ ያስታወሱት 13 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ