የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 1/8 ገጽ 18-20
  • የዊልያም ሼክስፒር ምሥጢራዊነት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የዊልያም ሼክስፒር ምሥጢራዊነት
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መሠረታዊ ችግሮች
  • የተማረ ሰው ነበር?
  • መጻሕፍትና የእጅ ጽሑፍ ቅጂዎች
  • ወደ ለንደን መሄድና ከፍተኛ ዝና ማግኘት
  • በሼክስፒር ስም ተጠቅመዋል የሚባሉ ሰዎች
  • ማን በሰጠው ተስፋ መተማመን ይቻላል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • እምነት ሊጣልበት ይችላል?
    ንቁ!—2007
  • የወደፊት ዕጣህን የሚወስነው ምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ሐቀኝነት—በአጋጣሚ ወይስ በምርጫ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 1/8 ገጽ 18-20

የዊልያም ሼክስፒር ምሥጢራዊነት

ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

ዊልያም ሼክስፒር በታሪክ ዘመናት ከተነሱት ጸሐፌ ተውኔቶች በሙሉ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት እንደሆነ ይነገራል። ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ “ብዙዎች በዘመናት ሁሉ አቻ ያልተገኘለት የቲያትር ሰው እንደሆነ አድርገው ይገልጹታል። በአሁኑ ጊዜ ቲያትሮቹ . . . ከማንኛውም ጸሐፌ ተውኔት ድርሰቶች የበለጠ ብዙ ጊዜና በብዙ አገሮች ይታያሉ” ይላል። ከ70 ወደሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል።

ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክለፒዲያ ሥራዎቹ ናቸው የሚባሉት በርካታ ድርሰቶች የማን እንደሆኑ ሲናገር “ቲያትሮቹንና ግጥሞቹን የጻፈው ሼክስፒር መሆኑን የሚጠራጠር በሼክስፒር ሥራዎች ላይ ጥናት ያደረገ ምሁር ይኖራል ለማለት አይቻልም” ይላል። ይሁን እንጂ በዚህ አባባል የማይስማሙ ሰዎች አሉ። ለምን?

ሼክስፒር ስትራትፎርድ-አፖን-አቮን በተባለ ሥፍራ በ1564 ተወልዶ ከ52 ዓመታት በኋላ፣ በ1616 በዚችው መንደር ሞተ። ስለ ሼክስፒር ለቁጥር የሚያታክቱ በርካታ መጻሕፍት የታተሙ ሲሆን ብዙዎቹ በሼክስፒር ስም የሚጠሩትን የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች በእርግጥ የጻፈው ሼክስፒር ራሱ ነውን? ለሚለው መሠረታዊና ሞጋች ለሆነው ጥያቄ ምላሽ ለማስገኘት በርካታ ዓመታት የፈጁ ጥናቶች ከተደረጉ በኋላ የተጻፉ ናቸው።

መሠረታዊ ችግሮች

በሼክስፒር ቲያትሮች ውስጥ በጣም ሰፊ የሆነ ዓለማዊ እውቀትና ተሞክሮ ተንጸባርቋል። ለምሳሌ ያህል ስለ ሕግ ነክ ጉዳዮች ጥሩ ግንዛቤ ያለው ሲሆን ሕግ ነክ በሆኑ ቃላትና ሁነቶች በአስደናቂ ሁኔታ ተጠቅሟል። ሰር ጆን በክኒል በ1860 ሜዲካል ኖውሌጅ ኦቭ ሼክስፒር በተባለው መጽሐፋቸው ሼክስፒር የነበረው የሕክምና እውቀት በጣም የጠለቀ እንደሆነ አመልክተዋል። ስለ አደን፣ አዕዋፍን ለአደን ስለ ማሰልጠንና ስለ ሌሎች ስፖርቶች እንዲሁም ስለ ቤተ መንግሥት ሥርዓት ስለ ነበረው እውቀትም እንዲሁ ለማለት ይቻላል። በሼክስፒር ታሪክ ላይ ጥናት ያደረጉት ጆን ሚቸል “ሁሉን አወቅ የሆነው ደራሲ” ብለውታል።

በሼክስፒር ሥራዎች ውስጥ ስለ መርከብ አደጋ አምስት ጊዜ ተገልጿል። ስለ መርከብ ጉዞ የተሰጠው ገለጻ ጸሐፊው በቂ ተሞክሮ ያለው መርከበኛ እንደነበረ ያመለክታል። ሼክስፒር ወደ ውጭ አገር ተጉዞ ያውቅ ነበር? በግዳጅ የባሕር ኃይል አባል እንዲሆን ተደርጎ ነበር? በ1588 የስፓንሽ አርማዳን ድል ለማድረግ በተደረገው ውጊያ ተካፍሎ ይሆን? እነዚህ ሁሉ የሼክስፒርን ደራሲነት ይበልጥ አሳማኝ የሚያደርጉ ቢሆኑም ለአንዳቸውም በቂ ማስረጃ ማቅረብ አልተቻለም። ስለ ወታደራዊ ጉዳዮች ስላለው እውቀትና እግረኛ ወታደሮችን በሚመለከት ስለ ተጠቀመባቸው ቃላትም ተመሳሳይ አስተያየት መስጠት ይቻላል።

በሼክስፒር ሥራዎች ውስጥ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቷል። እነዚህን ጥቅሶች ከእናቱ ተምሮ ሊሆን ቢችልም እናቱ ማንበብና መጻፍ ስለ መቻሏ የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የነበረው እውቀት ስለ ትምህርት ደረጃው ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል።

የተማረ ሰው ነበር?

የዊልያም አባት ጆን የእጅ ጓንት ሠራተኛ፣ የሱፍ ነጋዴና ምናልባትም ሥጋ ሻጭ ነበር። መሐይም የነበረ ቢሆንም የተከበረ ዜጋ ነበር። የስትራትፎርድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ተማሪዎች ዝርዝር የያዘ መዝገብ ባይኖርም ብዙ ምሁራን ሼክስፒር እዚህ ትምህርት ቤት ገብቶ እንደነበረ ያምናሉ። ከዓመታት በኋላ የዊልያም ጓደኛና ጸሐፌ ተውኔት የነበረው ቤን ጆንሰን “መጠነኛ ላቲንና በጣም ትንሽ ግሪክኛ ይችል” እንደነበረ ገልጿል። ይህም ዊልያም በትምህርቱ ብዙም ያልገፋ መሆኑን ያመለክታል።

የቲያትሮቹ ጸሐፊ ግን የግሪክንና የሮማን ክላሲክ ጽሑፎች እንዲሁም የፈረንሳይን፣ የኢጣሊያንና የስፔይን ሥነ ጽሑፍና ቋንቋ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነበር። ከዚህም በላይ በጣም ሰፊ የሆነ የቃላት እውቀት ነበረው። በዛሬው ጊዜ በጣም የተማረ ነው የሚባል ሰው በዕለታዊ ንግግሩ የሚጠቀምባቸው ቃላት ብዛት 4,000 ይደርሳል። ጆን ሚልተን የተባለው የ17ኛው መቶ ዘመን እንግሊዛዊ ባለ ቅኔ በሥራዎቹ ውስጥ የተጠቀመባቸው ቃላት ብዛት 8,000 ነው። ሼክስፒር ግን አንድ ምሁር እንዳሉት ከ21,000 በማያንሱ ቃላት ተጠቅሟል!

መጻሕፍትና የእጅ ጽሑፍ ቅጂዎች

የሼክስፒር ንብረቶች በሙሉ ሦስት ገጽ በፈጀው የኑዛዜ ቃሉ ውስጥ በጥንቃቄ የተዘረዘሩ ሲሆን ስለ መጻሕፍቱና ስለ እጅ ጽሑፍ ግልባጮች ግን የተጠቀሰ ነገር የለም። ለታላቅ ልጁ ለሱዛን ሰጥቷት ይሆን? ሰጥቷት ከነበረ ወደ ዘር ዘሮችዋ ተላልፈው ይገኙ ነበር። ይህ ሁኔታ እንቆቅልሽ የሆነባቸው አንድ የ18ኛው መቶ ዘመን የቤተ ክህነት ሰው በስትራትፎርድ-አፖን-አቮን ዙሪያ በ80 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኙትን የግል ቤተ መጻሕፍት በሙሉ ፈትሸው የሼክስፒር ንብረት የሆነ አንድ መጽሐፍ እንኳን ለማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።

የእጅ ጽሑፍ ሥራዎቹም ቢሆኑ ግራ የሚያጋቡ ናቸው። በእጅ ጽሑፍ ከተዘጋጁት ሥራዎቹ መካከል በአሁን ጊዜ አንዱም የለም። ሼክስፒር ከሞተ ከሰባት ዓመት በኋላ በ1623 በታተመው የመጀመሪያ ጥራዝ ሠላሳ ስድስት የሚሆኑ ቲያትሮች ታትመው ወጥተዋል። በሕይወት ዘመኑም ቢሆን የእሱን ፈቃድ ያላገኙ ብዙ እትሞች ወጥተዋል። ከፍተኛ የንግድ ችሎታ የነበረው ሼክስፒር ግን እነዚህን ሕትመቶች ለማስቆም ምንም ዓይነት ሕጋዊ እርምጃ አልወሰደም።

ወደ ለንደን መሄድና ከፍተኛ ዝና ማግኘት

በቀዳማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ዘመን ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩ የቲያትር ቡድኖችን ማግኘት የተለመደ ነገር ነበር። አንዳንዶቹም በ1587 ስትራትፎርድ-አፖን-አቮንን ጎብኝተው ነበር። ሼክስፒር ከነዚህ የቲያትር ቡድኖች ጋር አብሮ ሠርቶ ከነበረ በዚያው ዓመት የበልግ ወራት ለንደን ደርሶ ነበር ማለት ነው። የሎርድ ቻምበርለይን ሰዎች ይባል የነበረውና በኋላ ደግሞ የንጉሡ ሰዎች የሚል ስያሜ የተሰጠው የለንደን እውቅ የቲያትር ኩባንያ አባል ሆኖ እንደነበር እናውቃለን። ዋናው ከተማ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ መበልጸግ ጀመረ። በቀጣዮቹ ዓመታትም በለንደንና በስትራትፎርድ-አፖን-አቮን ንብረት ለመያዝ በቃ። ከ1583 እስከ 1592 ድረስ ባሉት ዓመታት ግን የት እንደነበረና ምን እንዳደረገ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም።

በ1599 ዘ ግሎብ የተባለው ቲያትር ቤት በሳውዝዋርክ ተሠራ። ከዚያ ጊዜ በፊት በሼክስፒር የሚጠሩ ቲያትሮች በለንደን ታዋቂ ሆነው ነበር። ሆኖም በደራሲነቱ ገንኖ አልታወቀም ነበር። እንደ ቤን ጆንሰንና እንደ ፍራንሲስ ቦሞንት ለመሰሉ ጸሐፌ ተውኔቶች በለንደን ዌስትሚኒስተር አቤ ከፍተኛ የቀብር ሥነ ሥርዓት የተደረገ ቢሆንም ሼክስፒር በሞተ ጊዜ ግን ትልቅ የቀብር ሥነ ሥርዓት አልተደረገለትም።

በሼክስፒር ስም ተጠቅመዋል የሚባሉ ሰዎች

ሼክስፒር የሚለው ስም እውነተኛውን ደራሲ ወይም እውነተኞቹን ደራሲዎች ለመደበቅ ያገለገለ ስም ይሆን? በዚህ ስም ተጠቅመው ይሆናል የሚባሉ ከ60 የሚበልጡ ግለሰቦች ተጠቁመዋል። ጸሐፌ ተውኔት ክርስቶፈር ማርሎውa እና እንደ ካርዲናል ዎልሲ፣ ሰር ዎልተር ራሌይና ቀዳማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ያሉ ብዙም ትኩረት ያልተሰጣቸው ሰዎች፣ ሳይቀሩ ተጠቁመዋል። ይበልጥ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡት እነማን ናቸው?

የመጀመሪያው ተጠቋሚ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የተማረው ፍራንሲስ ቤከን ነው። ሼክስፒርን በሦስት ዓመት የሚበልጠው ሲሆን የታወቀ ጠበቃና የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣን ሊሆን ችሏል። በርካታ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችም አበርክቷል። የሼክስፒር ሥራዎች የቤከን ናቸው የሚለው ንድፈ ሐሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰነዘረው በ1769 ሲሆን ለ80 ዓመታት ያህል ችላ ተብሎ ቆይቷል። ለጉዳዩ እልባት እንዲያገኝለት በ1885 የቤከን ማኅበር የተቋቋመ ሲሆን ንድፈ ሐሳቡን የሚደግፉ ብዙ ጭብጦች ተገኝተዋል። ለምሳሌ ያህል ቤከን ከለንደን በስተ ሰሜን 32 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው የሴንት አልባንስ ከተማ የኖረ ሲሆን ይህች ከተማ በሼክስፒር ሥራዎች ውስጥ 15 ጊዜ ተጠቅሳለች። ሼክስፒር የተወለደባት ስትራትፎርድ-አፖን-አቮን ግን አንድ ጊዜ እንኳን አልተጠቀሰችም።

የሩትላንድ አምስተኛ መስፍን የነበረው ሮጀር ማነርስና የደርቢ ስድስተኛ መስፍን የነበረው ዊልያም ስታንሊም የየራሳቸው ደጋፊዎች አሏቸው። ጥሩ ትምህርት ያላቸውና በቤተ መንግሥት ሥርዓት ከፍተኛ ተሞክሮ ያካበቱ ሰዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ሥራቸው እንዳይታወቅ የሚፈልጉበት ምን ምክንያት ነበራቸው? ፕሮፌሰር ፒ ኤስ ፖሮሆፍሼኮፍ በ1939 ሩትላንድን በመደገፍ ባቀረቡት ክርክር “የመጀመሪያ ድርሰቶቹ የታተሙት አለ ደራሲ ስም ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በብዕር ስም ነበር። ይህን ያደረገው ከመሳፍንት ወገን የሚቆጠር ሰው በተራ ሰዎች ቲያትር ቤቶች የሚታዩ ተውኔቶች መጻፉ አግባብ ስላልነበረ ነው” ብለዋል።

አንዳንዶች የሼክስፒር ተውኔቶች በተለያዩ ግለሰቦች የተጻፉ ተውኔቶች ስብስብ ናቸው ይላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሼክስፒር የተዋጣለት ተዋናይ እንደመሆኑ የሌሎች ደራሲዎችን ተውኔቶች ለመድረክ እንደሚስማማ አድርጎ አዘጋጅቶ ይሆን? በረቂቅ ጽሑፎቹ ላይ ‘አንድ ስርዝ’ እንኳን እንደማይገኝ ይነገራል። የቀረቡለትን የሌሎች ጸሐፌ ተውኔቶች ጽሑፍ ብዙ እርማት ሳያደርግ የአርትኦት ሥራ ብቻ ይሠራ ከነበረ ይህ እውነት ሊሆን ይችላል።

አንዳንዶች የሼክስፒርን ደራሲነት እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸው ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው? ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክለፒዲያ እንደሚለው ሰዎች “ከስትራትፎርድ-አፖን-አቮን የመጣ ተራ ተዋናይ ተውኔቶቹን ደረሰ ብለው ሊያምኑ አልቻሉም። የሼክስፒር ገጠሬነትና ተራ አስተዳደግ በድርሰቶቹ ላይ ከተንጸባረቀው ከፍተኛ የአእምሮ ብስለት ጋር ሊጣጣምላቸው አልቻለም።” በመቀጠልም የተውኔቶቹ ደራሲዎች ናቸው ተብለው የተጠቆሙት ሰዎች በሙሉ ለማለት ይቻላል፣ “የመሳፍንት ወገን ናቸው” ይላል። በዚህ መሠረት የሼክስፒርን ደራሲነት ከሚጠራጠሩት ሰዎች ብዙዎቹ “ተውኔቶቹን ሊጽፍ የሚችለው ከፍተኛ ትምህርት ያለው፣ በከፍተኛ የማህበራዊ ኑሮ ደረጃ የሚገኝ ሰው ብቻ እንደሆነ ያምናሉ።” ይሁን እንጂ ቀደም ብለን በዚህ ጽሑፍ መጀመሪያ ላይ እንደተመለከትነው በእርግጥ ደራሲው ሼክስፒር እንደነበረ የሚያምኑ ብዙ ምሁራን አሉ።

ታዲያ ይህ ክርክር በቅርብ ጊዜ ውስጥ እልባት ያገኝ ይሆን? የሚያገኝ አይመስልም። የመጀመሪያዎቹ ረቂቅ የእጅ ጽሑፎች ተገኝተው ተጨማሪ ማስረጃዎች ብቅ እስኪሉና ስለ ዊልያም ሼክስፒር የሕይወት ታሪክ የተሟላ እውቀት እስኪገኝ ድረስ “ይህ ታላቅ የሥነ ጽሑፍ ሰው” ምሥጢር እንደሆነ ይኖራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በመጀመሪያዎቹ የሼክስፒር ሥራዎች ውስጥ የክርስቶፈር ማርሎው እጅ እንደነበረ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ማርሎው በ1593 በ29 ዓመቱ በለንደን ከተማ ሞተ። አንዳንዶች ማርሎው በአንድ መጠጥ ቤት ውስጥ በተነሣ አምባ ጓሮ ምክንያት ሞቷል የተባለው በውሸት ሲሆን ወደ ኢጣሊያ ሄዶ የሥነ ጽሑፍ ሥራውን ቀጥሏል ይላሉ። ስለ መቀበሩም ሆነ ስለ ተደረገለት የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚታወቅ ነገር የለም።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የማንበብና የመጻፍ ችሎታና ስሙ

ዊልያም ሼክስፒር እስከ ጊዜያችን ተጠብቀው በቆዩ አራት ሰነዶች ላይ ስድስት ጊዜ ያህል የጽሑፍ ፊርማውን አኑሯል። ስሙን ሙሉ በሙሉ ማንበብ የማይቻል ሲሆን ፊደላቱም አንድ ዓይነት አይደሉም። በሼክስፒር የኑዛዜ ቃል ላይ ስለ እርሱ ሆነው የፈረሙት ጠበቆቹ ሳይሆኑ አይቀሩም የሚሉ ሊቃውንት አሉ። ይህም ዊልያም ሼክስፒር በእርግጥ መጻፍና ማንበብ ይችል ኖሯል? የሚል ጥንቃቄ የሚጠይቅ ጥያቄ አስነስቷል። ሼክስፒር ራሱ የጻፈው የእጅ ጽሑፍ እስከዛሬ ድረስ አልተገኘም። ሴት ልጁ ሱዛና ስሟን ለመጻፍ እንደምትችል ቢታወቅም ከዚህ ያለፈ ችሎታ እንደነበራት ግን የሚታወቅ ነገር የለም። ሌላዋ ለአባቷ ቅርበት የነበራት የሼክስፒር ሴት ልጅ ጁዲት ትፈርም የነበረው በማኅተም አማካኝነት ነበር። መሐይም ነበረች። ሼክስፒር ልጆቹ በዋጋ ሊተመን የማይችለው የሥነ ጽሑፍ ጠቀሜታ ተጋሪዎች እንዲሆኑ ማድረግ የተሳነው ለምን እንደነበረ ማንም ሰው አያውቅም።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሼክስፒርን መልክ በእርግጠኝነት የሚያውቅ ሰው ባይኖርም የሼክስፒርን ፊት የሚያሳዩ የጥንት ሥዕሎች

[ምንጭ]

ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ 11ኛ እትም (1911)

Culver Pictures

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ