የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 4/8 ገጽ 4-7
  • ኢየሱስ ምን ይመስል ነበር?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኢየሱስ ምን ይመስል ነበር?
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዓለማዊ ታሪክ ምን ይላል?
  • መጽሐፍ ቅዱስና የኢየሱስ መልክ
  • ኢየሱስ አቅመ ደካማ አልነበረም
  • አካላዊ ቁመናው ይህን ያህል አስፈላጊ ነውን?
  • ኢየሱስ ምን ይመስል ነበር?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017
  • ኢየሱስ ምን ይመስል ነበር?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነበር?
    ንቁ!—1999
  • “እነሆ! ሰውዬው!”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 4/8 ገጽ 4-7

ኢየሱስ ምን ይመስል ነበር?

ኢየሱስ ምን ይመስል እንደነበረ ዓለማዊ ታሪክ በሚሰጠው ምሥክርነት ላይ ተጽእኖ ያሳደሩ በርካታ ነገሮች አሉ። የተለያዩ ሠዓሊዎች በሳሏቸው ሥዕሎች መካከል ሰፊ ልዩነት ሊኖር የቻለው በዚህ ምክንያት ነው።

ሥዕሉ የተሣለበት አገር ባሕልና የተሣለበት ዘመን ልዩነት ይፈጥራሉ። በተጨማሪም የሠዓሊዎቹና ሠዓሊዎቹን የቀጠሯቸው ሰዎች ሃይማኖታዊ እምነት በኢየሱስ ቁመና አሳሳል ላይ ተጽእኖ አሳድሯል።

ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ እንደ ማይክልአንጀሎ፣ ሬምብራንትና ሩበንዝ የመሰሉ ዝነኛ የሥነ ጥበብ ሰዎች ለክርስቶስ ቁመና ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተዋል። ሥዕሎቻቸው አብዛኛውን ጊዜ ምሥጢራዊና ረቂቅ ቢሆኑም በኢየሱስ ቁመናና መልክ ረገድ ያስተላለፉት አጠቃላይ የሆነ ግንዛቤ ነበር። ይሁን እንጂ የእነዚህ ሠዓሊዎች አተረጓጎም በምን ላይ የተመሠረተ ነበር?

ዓለማዊ ታሪክ ምን ይላል?

ከ280 ገደማ እስከ 337 እዘአ ከኖረው ከሮማዊው አጼ ቆስጠንጢኖስ ዘመን በፊት የተሠሩ የሥነ ጥበብ ሥራዎች ኢየሱስ አጭር ወይም ረዘም ያለ የሚጠቀለል ፀጉር እንዳለውና ወጣት የሆነ “መልካም እረኛ” እንደሆነ የሚያሳዩ ናቸው። ስለዚህ ሁኔታ ግን አርት ስሩ ዘ ኤጅስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “መልካሙ እረኛ የሥነ ጥበብ ርዕስ መሆን የጀመረው ከጥንታዊው የግሪክ [አረማውያንና] የግብጽ ሥነ ጥበብ ዘመን አንስቶ ነው። እዚህ ላይ ግን የክርስቲያን መንጋ ታማኝ ጠባቂ ምሳሌ ሆኗል።”

ከጊዜ በኋላ ይህ የአረማውያን ተጽእኖ ይበልጥ በግልጽ ታይቷል። መጽሐፉ በማከል “ኢየሱስ ከሜዲትራንያን ዓለም አማልክት፣ በተለይ የፀሐይ አምላክ ከሆነው ከሄልዮስ (አፖሎ) [በአናቱ ላይ ይሳል የነበረው አክሊለ ብርሃን ከጊዜ በኋላ ለኢየሱስና ቆየት ብሎም ለሌሎች ቅዱሳን ተሰጥቷል] ወይም የምሥራቁ የሮማ ዓለም አቻ ከሆነው ሶል ኢንቪክቱስ (ድል የማይነሳው ፀሐይ) ጋር እንደሚመሳሰል መደረጉን ለመገንዘብ አያዳግትም።” እንዲያውም ኢየሱስ ሮም በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተገኘ መቃብር ቤት ውስጥ ልክ እንደ አፖሎ ሆኖ “የፀሐይን ሠረገላ በሰማይ ሲጋልብ” ተስሏል።

ይሁን እንጂ ይህ ወጣት አስመስሎ የመሳሉ ሂደት ለረዥም ጊዜ አልዘለቀም። አዶልፍ ዲድሮ ክርስቺያን አይከኖግራፊ በተባለ መጽሐፋቸው የሆነውን ነገር ይገልጹልናል:- “በመጀመሪያ ወጣት መስሎ ይሳል የነበረው የክርስቶስ መልክ የክርስትና ዕድሜ እየጨመረ በሄደ መጠን . . . ከዘመን ወደ ዘመን እያረጀ መጣ።”

ፑብልዩስ ለንቱሉስ የተባለ አንድ ሰው ለሮማ መንግሥት ምክር ቤት የጻፈው ነው በተባለ አንድ የ13ኛው መቶ ዘመን ጽሑፍ ላይ የኢየሱስ መልክና ቁመና እንደሚከተለው ተገልጿል:- “ነጣ ያለ ቡናማ ቀለም ያለውና እስከ ጆሮው የሚደርስ ዞማ ፀጉር ሲኖረው ከጆሮው ጀምሮ ግን ጠቆር ያለና የሚያብረቀርቅ ሆኖ እየተጠቀለለ ወደ ትከሻው ይወርዳል። በመሐል አናቱ ላይ ለሁለት ተከፍሏል። . . . ፊቱ በሙሉ በጺም የተሸፈነ ሲሆን የጺሙ ቀለም ከፀጉሩ ያልተለየ፣ ረዥም ያልሆነ፣ ግን አገጩ ላይ የተከፈለ ነው። . . . ዓይኖቹ ግራጫና . . . ጥርት ያሉ ናቸው።” ይህ ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ መግለጫ ከዚያ በኋላ በተነሱ ሠዓሊዎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክለፒዲያ “እያንዳንዱ ዘመን የየራሱን ክርስቶስ እንደፈለገ ፈጥሯል” ይላል።

እያንዳንዱ ዘርና ሃይማኖትም እንደ እያንዳንዱ ዘመን የራሱን ክርስቶስ ፈጥሯል። በአፍሪካ፣ በአሜሪካና በእስያ ሚስዮናዊ መስኮች ክርስቶስ እንደ ምዕራቡ ዓለም ረዥም ፀጉር እንዳለው ሆኖ ቢሳልም አንዳንድ ጊዜ “የየአገሮቹ ልዩ ባሕርያት” እንደታከሉበት ኢንሳይክለፒዲያው ይገልጻል።

ፕሮቴስታንቶችም የራሳቸው የሥነ ጥበብ ሰዎች ሲኖሯቸው የክርስቶስን ቁመናና መልክ በራሳቸው መንገድ ተርጉመዋል። ኤፍ ኤም ጎድፍሬ ክራይስት ኤንድ ዚ አፖስትልስ—ዘ ቼንጂንግ ፎርምስ ኦቭ ሪሊጅየስ ኢማጀሪ በተባለው መጽሐፋቸው “ሬምብራንት ክርስቶስን የሚያሳዝን አድርጎ መሳሉ የፕሮቴስታንትን አስተያየት ማለትም ኮሳሳ፣ ሐዘንተኛና ጭምት የሆነውን እንዲሁም . . . ውስጣዊ ማንነቱን የሚመረምረውንና የራሱን ፍላጎትና ስሜት የሚገታውን የፕሮቴስታንት ነፍስ የሚያንጸባርቅ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ይህም “የክርስትናን መሥራች ከሲታ፣ ጎስቋላ፣ ‘ራሱን ዝቅ የሚያደርግ፣ አሳዛኝና ጭምት’ ሰው አድርጎ በመሳሉ ታይቷል” ይላሉ።

ይሁን እንጂ ቀጥለን እንደምንመለከተው አቅመ ደካማ የሆነ፣ በአናቱ ላይ አክሊለ ብርሃን ያለበት፣ የሴት መልክ ያለው፣ ሐዘንተኛ ፊትና ረዥም ፀጉር እንዳለው ሆኖ የሚሳለው የሕዝበ ክርስትና ክርስቶስ ትክክለኛውን የክርስቶስ መልክ አያሳይም። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጸው ኢየሱስ ጋር ፈጽሞ የማይመሳሰል ነው።

መጽሐፍ ቅዱስና የኢየሱስ መልክ

ኢየሱስ “የእግዚአብሔር በግ” እንደመሆኑ ምንም ዓይነት ጉድለት ስላልነበረበት መልከ ቀና ሰው እንደነበረ አያጠራጥርም። (ዮሐንስ 1:29፤ ዕብራውያን 7:26) በተጨማሪም በብዙ ሥዕሎች እንደሚታየው ሁልጊዜ ሐዘንተኛ ሊሆን አይችልም። እርግጥ ነው፣ በሕይወቱ ውስጥ ብዙ አስጨናቂ ሁኔታዎች አጋጥመውታል። ይሁን እንጂ በአጠቃላይ ባሕርዩ “ደስተኛ አምላክ” የሆነው የአባቱ ትክክለኛ ነጸብራቅ ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW፤ ሉቃስ 10:21፤ ዕብራውያን 1:3

የኢየሱስ ፀጉር ረዥም ነበር? ፀጉራቸውን የማይቆረጡትና ወይን ጠጅ የማይጠጡት ናዝራውያን ብቻ ነበሩ። ኢየሱስ ደግሞ ናዝራዊ አልነበረም። ስለዚህ እንደ ማንኛውም አይሁዳዊ ወንድ ፀጉሩን አሳምሮ ይቆረጥ እንደነበረ አያጠራጥርም። (ዘኁልቁ 6:2-7) በተጨማሪም ከሰዎች ጋር በሚሆንባቸው ጊዜያት የወይን ጠጅ በመጠኑ ይጠጣ ነበር። ይህም ደስተኛ ሰው እንደነበረ ያረጋግጣል። (ሉቃስ 7:34) እንዲያውም በቃና በገሊላ በተደረገ የሠርግ ድግስ ላይ ውኃውን በተአምር ወደ ወይን ጠጅ ለውጧል። (ዮሐንስ 2:1-11) ጺም የነበረው ስለመሆኑም ስለሚቀበለው መከራ በተነገረ አንድ ትንቢት ላይ ተረጋግጧል።—ኢሳይያስ 50:6

ስለ ኢየሱስ የቆዳ ቀለምና መልክስ ምን ለማለት ይቻላል? ሴማዊ ቀለምና መልክ የነበረው ይመስላል። ይህን መልኩን አይሁዳዊት ከነበረች እናቱ ከማርያም መውረሱ አይቀርም። የማርያም ዘሮች ከዕብራውያን የተወለዱ አይሁዳውያን ነበሩ። ስለዚህ ኢየሱስ አይሁዳውያንን የሚመስል ቀለምና መልክ ሳይኖረው አይቀርም።

ኢየሱስ ከሐዋርያቱ እንኳን ልዩ ሆኖ እንዲታይ የሚያደርግ መልክና አካላዊ ቁመና አልነበረውም። ይሁዳ አሳልፎ በሰጠው ጊዜ ኢየሱስን ለይቶ ለማሳወቅ መሳም ያስፈለገው በዚህ ምክንያት ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በአካባቢው ከነበሩ ሰዎች ጋር በቀላሉ ሊቀላቀልና ሊመሳሰል ይችል ነበር ማለት ነው። ቢያንስ በአንድ ወቅት ማንነቱ ሳይታወቅ ከገሊላ እስከ ኢየሩሳሌም ሊጓዝ ችሎ ነበር።—ማርቆስ 14:44፤ ዮሐንስ 7:10, 11

ይሁን እንጂ አንዳንዶች ኢየሱስ አቅመ ደካማ ሰው ነበር ይላሉ። እንዲህ የሚሉት ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ የመከራውን እንጨት ለመሸከም የሌላ ሰው እርዳታ አስፈልጎት ነበር። በተጨማሪም ከተሰቀሉት ሦስት ሰዎች መካከል አስቀድሞ የሞተው እርሱ ነበር።—ሉቃስ 23:26፤ ዮሐንስ 19:17, 32, 33

ኢየሱስ አቅመ ደካማ አልነበረም

መጽሐፍ ቅዱስ በአንዳንድ አፈ ታሪኮች እንደሚባለው ኢየሱስ አቅመ ደካማ ወይም ሴታ ሴት እንደነበረ አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ ገና ወጣት ሳለ እንኳን “በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ” እንደነበረ ይናገራል። (ሉቃስ 2:52፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ከመጀመሪያዎቹ 30 ዓመታት የዕድሜ ዘመኑ መካከል አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፈው በአናጢነት ሥራ ነው። አናጢነት፣ በተለይ የዘመናችን ድካም ቀናሽ መሣሪያዎች ባልነበሩበት በዚያ ዘመን ኮሳሳ ወይም አቅመ ደካማ የሆነ ሰው የሚሠራው ሥራ አልነበረም። (ማርቆስ 6:3) በተጨማሪም ኢየሱስ ከብቶችን፣ በጎችንና ገንዘብ ለዋጮችን ከቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ አባሯል። የገንዘብ ለዋጮቹንም ጠረጴዛ ገልብጧል። (ዮሐንስ 2:14, 15) ይህም ፈርጠም ያለ ቁመናና ጥሩ ጉልበት የነበረው ሰው መሆኑን ያመለክታል።

በምድር ላይ ባሳለፋቸው የመጨረሻ ሦስት ተኩል ዓመታት በስብከት ሥራው በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች በእግሩ ተጉዟል። ቢሆንም ደቀ መዛሙርቱ አንድም ጊዜ ‘እስቲ ጥቂት አረፍ በል’ አላሉትም። ይልቁንም አንዳንዶቹ ጠንካራ ዓሣ አጥማጆች ለነበሩ ደቀ መዛሙርቱ “እናንት ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ” ያለው ኢየሱስ ነበር።—ማርቆስ 6:31

በእርግጥ “መላው የወንጌል ትረካ” ይላል የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፒዲያ “[ኢየሱስ] የተሟላና ብርቱ አካላዊ ጤንነት እንደነበረው ያመለክታል።” ታዲያ የመከራውን እንጨት ለመሸከም እርዳታ ያስፈለገውና አብረውት ከተሰቀሉት ሰዎች ቀድሞ የሞተው ለምንድን ነው?

አንደኛውና ዋነኛው ምክንያት ከፍተኛ ጭንቀት ነው። ኢየሱስ የሚገደልበት ጊዜ ሲቀርብ “ነገር ግን የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ፣ እስክትፈጸምም ድረስ እንዴት እጨነቃለሁ?” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 12:50) ይህ ጭንቀት በመጨረሻው ምሽት ላይ አድጎ እስከ ‘ማጣጣር’ አድርሶት ነበር። “በፍርሃትም ሲጣጣር አጽንቶ ይጸልይ ነበር፤ ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ።” (ሉቃስ 22:44) የሰው ልጅ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ እስከ ሞት ድረስ የጸና አቋም ጠብቆ በመገኘቱ ላይ የተመካ እንደሆነ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። እንዴት ያለ ከባድ ሸክም ተጭኖበት ነበር! (ማቴዎስ 20:18, 19, 28) በተጨማሪም በአምላክ ሕዝቦች ‘የተረገመ’ ወንጀለኛ እንደሆነ ተቆጥሮ እንደሚገደል ያውቅ ነበር። ይህ በአባቱ ላይ ነቀፌታ ሊያመጣ የሚችል መሆኑ በጣም አሳስቦት ነበር።—ገላትያ 3:13፤ መዝሙር 40:6, 7፤ ሥራ 8:32

አልፎ ከተሰጠ በኋላም ብዙ የጭካኔ ድርጊቶች ተፈጽመውበታል። ከእኩለ ሌሊት በኋላ በተደረገ የማስመሰያ ችሎት ላይ በአገሩ የነበሩ ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች ሰድበውታል፣ ተፍተውበታል፣ በጡጫ መትተውታል። ሌሊት ተደርጎ ለነበረው ዳኝነት ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት ሲባል በማግስቱ በማለዳ ሌላ ችሎት ተሰየመ። በዚያም ኢየሱስ በመጀመሪያ በጲላጦስ ቀጥሎ ከወታደሮቹ ጋር ተሳልቆበት በነበረው በሄሮድስ ከዚያም በጲላጦስ በድጋሚ ተመርምሯል። በመጨረሻም ጲላጦስ አስገረፈው። ይህ ተራ የሆነ ቀላል ግርፋት አልነበረም። ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን ስለ ሮማውያን አገራረፍ የሚከተለውን ብሏል:-

“አብዛኛውን ጊዜ ይጠቀሙበት የነበረው መሣሪያ የተለያየ ርዝመት ያላቸው ነጠላ የሆኑ ወይም ደግሞ የተገመዱ የቆዳ ጠፍሮች ያሉትና በየመሐሉ ትናንሽ የብረት ብዮች ወይም ሹል የበግ አጥንቶች የተሰገሰጉበት አጠር ያለ አለንጋ . . . ነው። . . . ሮማውያኑ ወታደሮች የሰውየውን ጀርባ ባለ በሌለ ኃይላቸው ደጋግመው ሲገርፉት የብረት ብዮቹ ትልልቅ ሰንበር ያወጣሉ። የቆዳ ጠፍሮቹና የበግ አጥንት ቁርጥራጮቹ ደግሞ ቆዳውንና ከቆዳው ሥር ያሉትን ሕብረ ሕዋሳት ይቆራርጧቸዋል። ግርፋቱ እየቀጠለ ሲሄድ ከቆዳው ሥር ያለው ሥጋ ስለሚቆራረጥ ደም ማዠት ይጀምራል።”

የኢየሱስ አቅም የተዳከመው በመከራው እንጨት ክብደት ፈጽሞ ዝሎ ከመውደቁ በፊት እንደነበረ ግልጽ ነው። እንዲያውም ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን እንዲህ ሲል ገልጿል:- “በተጨማሪም አይሁዳውያኑና ሮማውያኑ ያደረሱበት የአካልና የአእምሮ ሥቃይ፣ እንዲሁም ምግብ፣ ውኃና እንቅልፍ ሳያገኝ መቆየቱ ለአቅሙ መመናመን አስተዋጽኦ አድርገዋል። ስለዚህ ኢየሱስ ገና ከመሰቀሉ በፊት አካላዊ ሁኔታው አሳሳቢ ሁኔታ ላይ፣ ምናልባትም አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።”

አካላዊ ቁመናው ይህን ያህል አስፈላጊ ነውን?

ከለንቱለስ ሐሰተኛ የጽሑፍ መግለጫ ጀምሮ እስከ ዝነኞቹ ሠዓሊዎች የሥነ ጥበብ ሥራና ዘመናዊ የመስታወት ሥዕሎች ድረስ ሕዝበ ክርስትናን ይበልጥ ያስጨነቃት በዓይን የሚታየው ነገር ብቻ ይመስላል። ቱሪን የሚገኘው የኢየሱስ አወዛጋቢ መግነዝ ጠባቂ የሆኑት የቱሪን ሊቀ ጳጳስ “የኢየሱስ ክርስቶስ ምስል ልብን የመማረክ ኃይል ተጠብቆ መኖር ይገባዋል” ብለዋል።

የአምላክ ቃል ግን ይህን ‘ልብ ይማርካል’ የተባለውን የኢየሱስ መልክ በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥቧል። ለምን? ሰዎች የዘላለም ሕይወት ከሚያስገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲዘናጉ ስለሚያደርግ ነው። (ዮሐንስ 17:3) ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ ራሱ የሰዎችን ውጪያዊ መልክ አያይም ወይም አስፈላጊ እንደሆነ ነገር አይቆጥርም። (ማቴዎስ 22:16፤ ከገላትያ 2:6 ጋር አወዳድር።) በመንፈስ በተጻፉት ወንጌሎች ውስጥ ተጠቅሶ ለማይገኘው የኢየሱስ አካላዊ ቁመናና መልክ ትልቅ ትኩረት መስጠት የወንጌሎቹን መንፈስ መቃወም ነው። እንዲያውም በሚቀጥለው ርዕስ እንደምንመለከተው ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ የሰው መልክ የለውም።a

[የግርጌ ማስታወሻ]

a እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ በሚጠናበት ጊዜ የኢየሱስን ምስል በያዙ ሥዕሎች መጠቀም ምንም ጉዳት የለውም። እነዚህ ሥዕሎች በመጠበቂያ ግንብ ማህበር ጽሑፎች ውስጥ ብዙ ጊዜ ይወጣሉ። ይሁን እንጂ ምሥጢራዊ ኃይል ለማስተላለፍ ወይም የተመልካቹን አድናቆት ለመማረክ ወይም ደግሞ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ጽንሰ ሐሳቦችንና ምልክቶችን ለማስፋፋት ወይም የተለየ ቅድስና ለመስጠት የሚደረግ ጥረት የለም።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አቅመ ደካማና የገረጣ ሆኖ በሕዝበ ክርስትና ሠዓሊዎች የሚሳለው ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ ከተሳለው ሥዕል ጋር ሲነጻጸር

[ምንጭ]

ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ሲሰብክ፣ በጉስታቭ ዶሬ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ