ኢየሱስ ሕይወቱና አገልግሎቱ
“እነሆ! ሰውዬው!”
ጲላጦስ በኢየሱስ እርጋታ ተገርሞና ምንም ወንጀል የሌለበት መሆኑን ተገንዝቦ የሚፈታበትን ሌላ ዘዴ ሞከረ። ለተሰበሰቡት ሰዎች “በፋሲካ አንድ ልፈታላችሁ ልማድ አላችሁ”አላቸው።
በርባን የተባለ መጥፎ ወንጀለኛ በእሥራት ላይ ይገኝ ስለነበረ ጲላጦስ “በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
ሕዝቡ ግን ቀስቅሰው ባነሳሱአቸው ሊቀካህናት ተገፋፍተው በርባን እንዲፈታና ኢየሱስ ግን እንዲገደል ጠየቁ። አሁንም ጲላጦስ ተስፋ ሳይቆርጥ “ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
“በርባንን” ሲሉ በአንድ ድምጽ ጮሁ።
ጲላጦስም ግራ ተጋብቶ “ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው?” ብሎ ጠየቃቸው።
እነርሱ ግን በአንድ ላይ “ይሰቀል፣ ስቀለው” እያሉ በጩኸት አደነቆሩት።
ጲላጦስ ሕዝቡ እንዲገደልላቸው የሚጠይቁት ሰው ምንም ወንጀል የሌለበት መሆኑን ተገንዝቦ “ምነው? ያደረገውስ ክፋት ምንድን ነው? ለሞት የሚያደርሰው ክፋት አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ” አላቸው።
ምንም ዓይነት ሙከራ ቢያደርግ ሕዝቡ በሃይማኖታዊ መሪዎቻቸው እየተጎተጎቱ “ስቀለው ስቀለው” እያሉ መጮሃቸውን አላቆም አሉ። ካህናቱ በጣም ስላነሳሱአቸው ደም ለማፍሰስ አጥብቀው ፈለጉ። በዚያ ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ከአምስት ቀናት በፊት የኢየሱስን ንግሥና በደስታ ከተቀበሉት ሰዎች መካከል እንደነበሩ ስናስታውስ በጣም ያስገርመናል። ይህ ሁሉ ሲሆን የኢየሱስ ደቀመዛሙርት በአካባቢው ቢኖሩም እንኳን አንድ ቃል እንኳን አልተናገሩም ነበር።
ጲላጦስ ሙከራው ሁሉ ረብሻ ከማስነሳት አልፎ ምንም ውጤት እንዳላስገኘለት ስለተመለከተ ውሃ አንስቶ በሕዝቡ ፊት እጁን ከታጠበ በኋላ “እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ” አላቸው። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ መልሰው “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” አሉ።
ስለዚህ ጲላጦስ ትክክል እንደሆነ ያወቀውን ነገር ከማድረግ ይልቅ ሕዝቡን ለማስደሰት ሲል በርባንን ፈታላቸው። ኢየሱስንም ወሰደ ልብሱን አስወልቆ አስገረፈው። ይህ ተራ ግርፋት አልነበረም። የአሜሪካ ሕክምና ማህበር መጽሔት ሮማውያን ሰዎችን የሚገርፉበትን ሁኔታ ይገልጻል።
“የተለመደው መሣሪያ የተቆጣጠሩ የቆዳ ዘርፎች ያሉት አጭር አለንጋ ነበር። በቋጠሮዎቹ ላይ ትናንሽ የብረት እንክብሎች ወይም የሾሉ የበግ አጥንቶች ይታሠሩ ነበር። . . . ሮማውያን ወታደሮች የሚገረፈውን ሰው ጀርባ በሙሉ ኃይላቸው በሚመቱበት ጊዜ የብረት እንክብሎቹ ጠልቀው በመግባት በሰውነቱ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ የተቆጣጠሩት ቆዳዎችና ሹል አጥንቶች ደግሞ ቆዳውንና በቆዳው አካባቢ ያሉትን የሰውነት ክፍሎች ይቆራርጣሉ። ግርፋቱ በቀጠለ መጠን የቆዳው ስንጥቅ እየጠለቀ ይሄድና ከሥር ያሉትን ጡንቻዎች እየቆራረጠ ወደ ውጭ ያወጣል።”
ከዚህ አሰቃቂ ግርፋት በኋላ ኢየሱስ ወደ ገዥው ቤተ መንግሥት ተወሰደ። መላው የወታደሮች ጭፍራ ተጠራ። እዚህም ወታደሮቹ የእሾህ አክሊል ሠርተው በአናቱ ላይ በመድፋትና የእሾኽ አክሊሉን ወደ ታች በመጫን ተጨማሪ ውርደት አደረሱበት። በቀኝ እጁም መቃ አስያዙትና ነገሥታት የሚለብሱትን ዓይነት ሐምራዊ ጨርቅ አለበሱት። እየተዘባበቱበትም “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን“ አሉት። ተፉበትም፣ በጥፊም መቱት። በእጁም የነበረውን መቃ ወስደው ራሱን እየመቱ በአናቱ ላይ የተደፋው የእሾህ አክሊል ወደራሱ ጠልቆ እንዲገባ አደረጉት።
ኢየሱስ ይህ ሁሉ መከራና ውርደት ሲደርስበት ያሳየው ጥንካሬ ጲላጦስን በጣም ስላስደነቀው እርሱን ለማዳን አንድ የመጨረሻ ሙከራ ለማድረግ ፈለገ። ለሕዝቡ “እነሆ፣ አንዲት በደል ስንኳ እንዳላገኘሁበት ታውቁ ዘንድ እርሱን ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ“ አላቸው። ኢየሱስ ምን የሚያክል ሥቃይ እንደደረሰበት ሲመለከቱ ልባቸው ይለሰልሳል ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ በጨካኞቹ ሕዝቦች ፊት የእሾህ አክሊል አጥልቆ፣ ሐምራዊ መጎናጸፊያ ለብሶና በደም የራሰው ፊቱ በደረሰበት ሥቃይ ተቆጣጥሮ ሲቆም ጲላጦስ “እነሆ! ሰውዬው!”አለ።
በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የበለጠው ሰው ተደብድቦና ቆስሎ ከፊታቸው ቆሟል! አዎ፣ ኢየሱስ ታላቅነቱን የሚያስመሰክርለት ግርማና እርጋታ ነበረው። ጲላጦስም የአክብሮትና የሐዘኔታ ስሜት የተቀላቀለበት ቃል የተናገረው ለዚህ ነበር። ዮሐንስ 18:39–19:5፤ ማቴዎስ 27:15-17, 20-30፤ ማርቆስ 15:6-19፤ ሉቃስ 23:18-25
◆ ጲላጦስ ኢየሱስን ለመፍታት የሞከረው እንዴት ነው?
◆ ጲላጦስ ራሱን ከኃላፊነት ነፃ ለማድረግ የሞከረው እንዴት ነው?
◆ ግርፋት ምን ዓይነት ስቃይ ያስከትል ነበር?
◆ ኢየሱስ ከተገረፈ በኋላ የተዘባበቱበት እንዴት ነው?
◆ ጲላጦስ ኢየሱስን ለማስፈታት ምን ተጨማሪ ሙከራ አደረገ?