የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • jy ምዕ. 129 ገጽ 294-ገጽ 295 አን. 2
  • ጲላጦስ “እነሆ፣ ሰውየው!” አለ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጲላጦስ “እነሆ፣ ሰውየው!” አለ
  • ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “እነሆ! ሰውዬው!”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • “እነሆ ሰውዬው!”
    እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
  • ጳንጥዮስ ጲላጦስ ማን ነበረ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ጲላጦስም ሆነ ሄሮድስ ምንም ጥፋት አላገኙበትም
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
ለተጨማሪ መረጃ
ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
jy ምዕ. 129 ገጽ 294-ገጽ 295 አን. 2
ኢየሱስን የእሾህ አክሊል ከደፉለትና ሐምራዊ ልብስ ካለበሱት በኋላ ጲላጦስ ወደ ውጭ አወጣው

ምዕራፍ 129

ጲላጦስ “እነሆ፣ ሰውየው!” አለ

ማቴዎስ 27:15-17, 20-30 ማርቆስ 15:6-19 ሉቃስ 23:18-25 ዮሐንስ 18:39–19:5

  • ጲላጦስ ኢየሱስን ለመፍታት ሞከረ

  • አይሁዳውያን በርባን እንዲፈታላቸው ጠየቁ

  • ኢየሱስን አሾፉበት እንዲሁም አንገላቱት

ጲላጦስ፣ ኢየሱስ እንዲገደል ለሚፈልገው ሕዝብ “በእሱ ላይ ያቀረባችሁትን ክስ የሚደግፍ ምንም ነገር አላገኘሁም” አላቸው። አክሎም ‘ሄሮድስም ቢሆን ምንም ጥፋት አላገኘበትም’ አለ። (ሉቃስ 23:14, 15) ከዚያም ጲላጦስ ኢየሱስን ለማዳን ሌላ ዘዴ ለመጠቀም ሞከረ፤ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “በልማዳችሁ መሠረት በፋሲካ አንድ ሰው ለእናንተ መፍታቴ አይቀርም። ስለዚህ የአይሁዳውያንን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?”—ዮሐንስ 18:39

ጲላጦስ በዝርፊያ፣ ዓመፅ በማነሳሳትና በነፍስ ግድያ የሚታወቅ በርባን የተባለ እስረኛ እንዳለ ያውቃል። ስለዚህ ጲላጦስ “ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ? በርባንን ወይስ ክርስቶስ የሚባለውን ኢየሱስን?” ሲል ጠየቃቸው። ሕዝቡም የካህናት አለቆች ስላግባቧቸው ኢየሱስ ሳይሆን በርባን እንዲፈታ ጠየቁ። ጲላጦስም “ከሁለቱ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” በማለት በድጋሚ ጠየቀ። ሕዝቡ “በርባንን” ብለው ጮኹ!—ማቴዎስ 27:17, 21

ጉዳዩ ያስጨነቀው ጲላጦስ “እንግዲያው ክርስቶስ የሚባለውን ኢየሱስን ምን ባደርገው ይሻላል?” አላቸው። ሕዝቡም “ይሰቀል!” ብለው ጮኹ። (ማቴዎስ 27:22) ንጹሕ ሰው እንዲሞት እየጠየቁ መሆናቸው በጣም ያሳፍራል። ጲላጦስ “ለምን? ይህ ሰው ምን ያጠፋው ነገር አለ? ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ” አላቸው።—ሉቃስ 23:22

ጲላጦስ በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ክፉኛ የተቆጣው ሕዝብ “ይሰቀል!” እያለ በአንድነት መጮኹን ቀጠለ። (ማቴዎስ 27:23) የሃይማኖት መሪዎቹ የተሰበሰቡትን ሰዎች በማነሳሳት ስሜታዊ እንዲሆኑ ስላደረጓቸው ደም ለማፍሰስ ቆርጠዋል! ማስገደል የፈለጉት ደግሞ አንድን ወንጀለኛ ወይም ነፍሰ ገዳይ አይደለም። ከአምስት ቀናት በፊት እንደ ንጉሥ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ጥሩ አቀባበል የተደረገለትን ንጹሕ ሰው ነው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በቦታው ተገኝተው ከሆነ ማንነታቸው እንዳይታወቅ ድምፃቸውን አጥፍተዋል።

ጲላጦስ ሕዝቡን ለማግባባት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ ተገነዘበ። ሁከት እየተነሳ መሆኑን ስላስተዋለ ውኃ አምጥቶ በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። ከዚያም “ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ። ከዚህ በኋላ ተጠያቂ የምትሆኑት እናንተ ናችሁ” አላቸው። ሕዝቡ ይህን ሲሰሙ እንኳ አመለካከታቸውን አልቀየሩም። እንዲያውም “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” አሉ።—ማቴዎስ 27:24, 25

አገረ ገዢው ትክክል እንደሆነ የሚያውቀውን ነገር ከማድረግ ይልቅ የሕዝቡን ፍላጎት ማሟላትን መረጠ። በመሆኑም ጲላጦስ በርባንን በመፍታት እንደ ፍላጎታቸው አደረገላቸው። ኢየሱስንም ልብሱን አስወልቆ አስገረፈው።

ኢየሱስ በጣም በሚያሠቃይ ሁኔታ ከተገረፈ በኋላ ወታደሮቹ ወደ አገረ ገዢው ቤተ መንግሥት ወሰዱት። በዚያም የሠራዊቱ አባላት ሁሉ ተሰብስበው ይበልጥ አዋረዱት። የእሾህ አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ ደፉበት። በተጨማሪም ወታደሮቹ በቀኝ እጁ የመቃ ዘንግ አስያዙት፤ እንዲሁም ነገሥታት የሚለብሱት ዓይነት ቀይ መጎናጸፊያ አለበሱት። ከዚያም “የአይሁዳውያን ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ አሾፉበት። (ማቴዎስ 27:28, 29) ይባስ ብለውም ምራቃቸውን ተፉበት፤ በጥፊም መቱት። እንዲሁም ጠንካራውን መቃ ከእጁ ወስደው ጭንቅላቱን ይመቱት ጀመር፤ እሱን ለማዋረድ ብለው ራሱ ላይ በደፉት “አክሊል” ላይ ያሉት ሹል እሾኾች በዚህ ጊዜ ጭንቅላቱ ላይ ይበልጥ ተሰኩ።

ኢየሱስ፣ ይህን ሁሉ ቁም ስቅል ክብሩን ጠብቆ መቋቋሙና ጥንካሬው ጲላጦስን በጣም ስላስደነቀው ራሱን ከኃላፊነት ነፃ ለማውጣት ሌላ ሙከራ አደረገ። ሕዝቡን “ምንም ጥፋት እንዳላገኘሁበት ታውቁ ዘንድ እነሆ ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ” አላቸው። ጲላጦስ፣ ሕዝቡ የኢየሱስ ሰውነት በልዞና ደም በደም ሆኖ መመልከታቸው ልባቸውን እንደሚያራራው አስቦ ይሆን? ኢየሱስ ጨካኝ በሆነው ሕዝብ ፊት ቆሞ እያለ ጲላጦስ “እነሆ፣ ሰውየው!” አላቸው።—ዮሐንስ 19:4, 5

ኢየሱስ የተደበደበና የቆሳሰለ ቢሆንም የመንፈስ ጥንካሬና መረጋጋት ይነበብበታል። ጲላጦስም እንኳ ይህን እንዳስተዋለ አክብሮትና ሐዘን ከተቀላቀለበት ንግግሩ መረዳት ይቻላል።

ግርፋት

መግረፊያ ጅራፍ

ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን በተባለው መጽሔት ላይ ዶክተር ዊልያም ኤድዋርድስ ሮማውያን እንዴት እንደሚገርፉ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦

“ለመግረፍ ይጠቀሙበት የነበረው የተለመደው መሣሪያ የተለያየ ርዝመት ባላቸው ነጠላ የሆኑ ወይም ደግሞ የተገመዱ የቆዳ ጠፍሮች የተሠራና ትናንሽ የብረት እንክብሎች ወይም ሹል የበግ አጥንቶች አለፍ አለፍ ብለው የተሰኩበት አጠር ያለ አለንጋ (ፍላግሩም ወይም ፍላጀለም ይባላል) ነው። . . . ሮማውያን ወታደሮች የሰውየውን ጀርባ ባለ በሌለ ኃይላቸው ደጋግመው ሲገርፉት የብረት እንክብሎቹ ትላልቅ ሰንበር ያወጣሉ፤ ጠፍሮቹና የበግ አጥንቶቹ ደግሞ ቆዳውንና ከቆዳው ሥር ያሉትን ሕብረ ሕዋሳት ይቆራርጧቸዋል። ከዚያም ግርፋቱ ሲቀጥል የቆዳው ስንጥቅ ጥልቅ እየሆነ ስለሚሄድ ከሥር ያሉት ጡንቻዎች ድረስ ይደርሳል፤ ይህም ሥጋው እንዲተለተልና ደም በደም እንዲሆን ያደርገዋል።”

  • ጲላጦስ ኢየሱስን በመፍታት ራሱን ከኃላፊነት ነፃ ለማድረግ የሞከረው እንዴት ነው?

  • የሮማውያን ግርፋት ምን ይመስላል?

  • ኢየሱስን ከገረፉት በኋላ የዘበቱበት እንዴት ነው?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ