ንዑሳን ፕላኔቶችና ጅራታም ኮከቦች፣ ከምድር ጋር መላተም በመገስገስ ላይ ናቸው?
‘ሰኔ 30 ቀን ማለዳ ላይ በዚህ በሳይቤሪያ መንደር አንድ ፈጽሞ እንግዳ የሆነ ነገር ተከሰተ። ገበሬዎች ከአድማስ በላይ አንድ በጣም የሚያበራ ነገር ተመለከቱ፤ እጅግ የሚያንጸባርቅ ከመሆኑ የተነሣ በዓይን ለማየት አዳጋች ነበር። ከአድማስ በታች ደግሞ የሚያንጸባርቀው አካል ባለበት በዚያው አቅጣጫ አንድ አነስተኛ የሆነ ጥቁር ደመና ይታያል። ከፍተኛ ብርሃን የሚያመነጨው አካል ወደ መሬት እየቀረበ ሲመጣ ብትንትኑ የወጣ መሰለ። በምትኩ መጠነ ሰፊ የሆነ እንደ ደመና ያለ ጥቁር ጭስ ተተካ። በተጨማሪም እንደ ድንጋይ ናዳ ያለ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ ተሰማ። ሕንፃዎች ተናጡ፤ የእሳት ነበልባል ደመናውን ሰንጥቆ ወደ ላይ ወጣ። መንደርተኞቹ በፍርሃት ተውጠው ወደ ጎዳና ፈረጠጡ። አሮጊቶች ዋይታውን አቀለጡት፤ ሁሉም ሰው የዓለም ፍጻሜ የደረሰ መስሎት ነበር።’—ሐምሌ 2, 1908 በሩስያ ኢርኩትስክ በታተመው ሰቢር የተባለ ጋዜጣ ላይ ከወጣው ዘገባ የተወሰደ።
መንደርተኞቹ ከሰማይ የወረደ አንድ አካል ከአናታቸው በላይ መፈንዳቱን የተገነዘቡ አይመስሉም። ይህ ከሆነ ከ90 ዓመት በላይ የተቆጠረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የፕላኔታችንን ፍጻሜ በተመለከተ ከሚነገሩት እጅግ ግራ የሚያጋቡ ትንበያዎች አንዱ በንዑስ ፕላኔት ወይም በጅራታም ኮከብ አማካኝነት ይደርሳል የሚባለው እልቂት ነው። እንደ ኤን ኢ ኦ (በመሬት አቅራቢያ የሚገኙ አካላት) እና ፒ ኤች ኦ (አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ አካላት) ያሉ ምህፃረ ቃላት ምድር ከሰማያዊ አካላት ጋር በመላተም ልትጠፋ ትችላለች ከሚሉት የመዓት ቀን ትንበያዎች ጋር ተያይዘው ሲጠቀሱ ይሰማል። ሆሊውድ ይህን ስጋት ዲፕ ኢምፓክት እና አርማጌዶን በተባሉት ፊልሞች ላይ በመጠቀም ከፍተኛ ትርፍ ማጋበስ ችሏል።
አንተ ወይም ልጆችህ ከሰማይ ተምዘግዝጎ በመጣ ኳስ እሳት (fireball) የመሞታችሁ አጋጣሚ ምን ያህል ነው? በቅርቡ የብረትና የበረዶ ስብርባሪ ግቢዬ ውስጥ ይዥጎደጎዳል ብለህ መጠበቅ ይኖርብህ ይሆን? በባሕር ዳርቻ አቅራቢያ የምትኖር ከሆንክ ቤትህ ባሕር ውስጥ የሚወድቅ ንዑስ ፕላኔት በሚያስከትለው ከባድ መውጃዊ ሞገድ (tidal wave) ድምጥማጡ ይጠፋ ይሆን?
በፕላኔቶች ግባሶ መካከል መዞር
እኛ ባለንበት ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ የሚገኙት ፀሐይ፣ ዘጠኙ ፕላኔቶችና ጨረቃዎቻቸው ብቻ አይደሉም። ጅራታም ኮከቦች (ከበረዶና ከአቧራ የተሠሩ አካላት)፣ ንዑሳን ፕላኔቶች (ትንንሽ ወይም አነስተኛ ፕላኔቶች) እና ሰማይ ወረዶች (አብዛኞቹ የንዑሳን ፕላኔቶች ስብርባሪዎች ናቸው) እኛ ባለንበት ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ይዞራሉ። ሳይንቲስቶች ምድር ከጠፈር ለሚወረወሩ አካላት የተጋለጠች እንደሆነች ከተረዱ ረጅም ጊዜ ሆኗቸዋል። በተደጋጋሚ የተደበደበውን የጨረቃ ገጽታ በመመልከት ብቻ ዝብርቅ ባለበት አካባቢ እንደምንኖር መገንዘብ እንችላለን። ከባቢ አየር እንዲሁም በስፍሃን ቴክቶኒካ (plate tectonics) እና በመሬት መሸርሸር አማካኝነት በምድር ገጽ ላይ የሚካሄደው የማያቋርጥ ድግመ ኡደት ባይኖር ኖሮ የፕላኔታችን ገጽ ልክ እንደ ጨረቃ ገጽ በስርጉደ መሬት የተሞላ ይሆን ነበር።
በመሬት ከባቢ አየር ውስጥ በየዕለቱ እስከ 200 ሚልዮን የሚደርሱ ተወርዋሪ ኮከቦች እንደሚታዩ ሳይንቲስቶች ይገምታሉ። ወደ ከባቢ አየር ከሚገቡት አካላት መካከል ብዙዎቹ ትንንሾች ከመሆናቸውም በላይ ማንም ልብ ሳይላቸው እንደ ጧፍ ቀልጠው ይጠፋሉ። ይሁን እንጂ ከእነዚህ አካላት መካከል አንዳንዶቹ የማቃጠል ኃይል ያለውን ከፍተኛ ሙቀት አልፈው ወደ ከባቢ አየር ዘልቀው በመግባት ከአየር ጋር በሚፈጥሩት ሰበቃ ፍጥነታቸው በሰዓት ወደ 320 ኪሎ ሜትር ዝቅ ይላል። የተረፈው አካላቸው ዱቤ በረቅ (meteorites) ሆኖ ምድርን ይመታል። አብዛኞቹ የሚወድቁት ውቅያኖሶች ላይ ወይም ሰው በማይኖርባቸው የምድር ክፍሎች በመሆኑ እምብዛም በሰው ላይ ጉዳት አያደርሱም። ወደ ከባቢ አየራችን የሚገቡት አካላት በየዕለቱ የመሬትን ክብደት በመቶዎች በሚቆጠር ቶን እንደሚያሳድጉት ይገመታል።
በተጨማሪም የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች ከመሬት ምህዋር ጋር የሚሳበሩ ወይም ወደ መሬት ምህዋር የተጠጉ ከአንድ ኪሎ ሜትር ስድስት አሥረኛ በላይ የሆነ ዲያሜትር ያላቸው 2,000 ገደማ የሚሆኑ ንዑሳን ፕላኔቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገምታሉ። ሳይንቲስቶቹ ያገኟቸውና የእንቅስቃሴያቸውን አቅጣጫ መከታተል የቻሉት 200 የሚሆኑትን ብቻ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከ50 ሜትር የሚበልጥ ዲያሜትር ያላቸውና ወደ መሬት ምህዋር በአደገኛ ሁኔታ የተጠጉ አንድ ሚልዮን ንዑሳን ፕላኔቶች እንዳሉ ይገመታል። ይህን የሚያክል መጠን ያላቸው ንዑሳን ፕላኔቶች መሬት ሊደርሱና ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ የሚባለው እንዲህ ዓይነቱ አረር አሥር ሜጋቶን ገደማ የሚሆን ጉልበት ያለው ሲሆን ይህም ከአንድ ትልቅ የኑክሊየር ቦምብ ጋር የሚተካከል ነው። የመሬት ከባቢ አየር አነስተኛ ከሆኑ ልተማዎች ሊጠብቀን ቢችልም እንኳ አሥር ሜጋቶን ወይም ከዚያ በላይ ጉልበት ያላቸውን ግን ሊያቆማቸው አይችልም። አንዳንድ ተመራማሪዎች ከአኃዛዊ መረጃዎች አንጻር ሲታይ በአንድ መቶ ዘመን ውስጥ በአማካይ አሥር ሜጋቶን ጉልበት ያለው አንድ ልተማ ሊከሰት ይችላል ይላሉ። አንዳንድ ግምታዊ አኃዞች እንደሚያሳዩት ከሆነ አንድ ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሆን ዲያሜትር ያላቸው አካላት በ100,000 ዓመታት ጊዜ ውስጥ መሬትን አንድ ጊዜ ይለትማሉ።
ስርጉደ መሬትን፣ ፍንዳታዎችንና ግጭቶችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል
በቀደምት ዘመናት ፕላኔታችን ከሰማይ በዘነቡ ትልልቅ አካላት ተመትታ እንደነበረ ለማመን አዳጋች አይደለም። በምድር ገጽ ላይ የሚታዩ ይህን የሚያረጋግጡ ከ150 በላይ የተሰረጎዱ ቦታዎች ተገኝተዋል። አንዳንዶቹ በግልጽ የሚታዩ ሲሆኑ ሌሎቹን ማየት የሚቻለው ከአውሮፕላን ወይም ከሳተላይት ላይ ብቻ ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ ለረጅም ጊዜ ተቀብረው የቆዩ ወይም በውቅያኖስ ወለል ላይ የሚገኙ ናቸው።
ከእነዚህ በጣም የታወቁ ስርጉደ መሬቶች መካከል አንዱ ቺክሱሉብ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በምድር ገጽ ላይ 180 ኪሎ ሜትር የሚሆን ዲያሜትር ያለው ስርጉድ ፈጥሯል። በሜክሲኮ ዩከታን ባሕር ሰርጥ ሰሜናዊ ጫፍ አቅራቢያ የሚገኘው ይህ በጣም ሰፊ የሆነ ስርጉደ መሬት አሥር ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ጅራታም ኮከብ ወይም ንዑስ ፕላኔት የተለተመ እንደሆነ ይታመናል። አንዳንዶች ይህ ልተማ ያስከተለው የአየር ንብረት ለውጥ ለዳይኖሶርና ለሌሎች የየብስና የባሕር እንስሳት ጨርሶ መጥፋት ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ።
አሪዞና ዩ ኤስ ኤ ውስጥ አንድ ብረት ዱቤ በረቅ 1,200 ሜትር ገደማ የሚሆን ዲያሜትርና 200 ሜትር ጥልቀት ያለው ሚትዮር ክሬተር የተባለ እጅግ አስደናቂ ጉድጓድ ፈጥሯል። እንዲህ ያለ ዱቤ በረቅ አንዲትን ከተማ ቢመታ ምን ዓይነት ጉዳት ይከሰት ነበር? ኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም የቀረበ አንድ ብዙ ሰው የጎበኘው ትዕይንት እንዲህ ዓይነቱ አካል ማንሃተንን ቢመታ ይህ በሰዎች የተጨናነቀ አውራጃ ሙሉ በሙሉ እንደሚወድም አመልክቷል።
ሰኔ 30, 1908 ላይ በግምት ከ100 ሜትር ያነሰ ዲያሜትር ያለው አንድ ንዑስ ኮከብ ወይም የአንድ ጅራታም ኮከብ ስባሪ በከባቢ አየር ላይ እያስገመገመ በመግቢያችን ላይ እንደተጠቀሰው በአብዛኛው ሰው በማይኖርበት ሳይቤሪያ ውስጥ በሚገኘው የቱንጉስካ ክልል ከመሬት 10 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ ፈነዳ። ፍንዳታው 15 ሜጋቶን ጉልበት እንደነበረው የተገመተ ሲሆን ዛፎችን በመጣል፣ እሳት በማስነሳትና አጋዘኖችን በመፍጀት 2,000 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሆን ቦታን አውድሟል። ፍንዳታው ሰው በብዛት በሚኖርበት አካባቢ ላይ ተከስቶ ቢሆን ኖሮ ምን ያህል ሰዎች ያልቁ ነበር?
በሐምሌ ወር 1994 ሹማከር ሊቪ 9 የተባለችው ጅራታም ኮከብ ስብርባሪዎች ጁፒተር ላይ ሲዥጎደጎዱ ለመመልከት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አቅርበው የሚያሳዩ መሣሪያዎች ወደዚህች ፕላኔት አነጣጥረው ነበር። በጁፒተር ላይ የተፈጠሩት ጊዜያዊ ስርጉዶች ግጭቱን በዓይናቸው በተመለከቱት ሰዎች አእምሮ ውስጥ በማይፋቅ ሁኔታ ተቀርጸው እንደሚቀሩ የታወቀ ነው። ጁፒተር በተደጋጋሚ ስትለተም የተመለከቱ ጠበብትና ተራ ሰዎች ጅራታም ኮከቧ ምድርን ለትማ ቢሆን ኖሮ ምን ሁኔታ ሊከሰት ይችል እንደነበረ ራሳቸውን ለመጠየቅ ተገድደዋል።
ሊከሰት ይችላል ተብሎ የሚታሰበው አደጋ
ሳይንቲስቶች በፍርሃት ተውጠው አንድ ጅራታም ኮከብ ወይም ንዑስ ፕላኔት እኛ የምንኖርባትን ፕላኔት ብትለትም የሚከተለውን አስከፊ መዘዝ ቆም ብለው ለማሰብ ሞክረዋል። አንድ ከባድ ግጭት ቢፈጠር ወዲያውኑ ሊከሰት የሚችለውን ነገር በሚከተለው ሁኔታ በምናባቸው ሥለዋል። መጀመሪያ ፈንጂ የሆነ የአለትና የአቧራ ሙቅ ዘለቅ (plume) ይከሰታል። ወደ ታች የሚዘንበው ግባሶ ሰማዩን ፍም የሚያስመስልና ደኖችንና የሳር መሬቶችን እሳት በማያያዝ አብዛኛውን የየብስ ሕይወት የሚያጠፋ የተወርዋሪ ኮከብ ክፈት (meteor shower) ይፈጥራል። ከባቢ አየሩ ላይ ተንጠልጥሎ ለረጅም ጊዜ የሚቆየው አቧራ የፀሐይ ብርሃንን በመጋረድ የሙቀት መጠን ወዲያውኑ እንዲያሽቆለቁልና በጨለመው የምድር ገጽ ላይ የሚካሄደው ብርሃን አስተጻምሮ (photosynthesis) እንዲስተጓጎል ያደርጋል። በተጨማሪም ብርሃን አስተጻምሮው ሲስተጓጎል በውቅያኖስ ውስጥ ያለው የምግብ ሰንሰለት ይቋረጥና በባሕር ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ፍጥረታት ይሞታሉ። በዚህ ንድፈ ሐሳብ መሠረት አካባቢያዊው አደጋ ዓለም አቀፋዊ በሆነ አሲድ ዝናብና በኦዞን ንብር ላይ በሚደርስ ጥፋት ይደመደማል።
እንዲህ ያለ ንዑስ ፕላኔት ውቅያኖስን ቢመታ ከፍተኛ ውድመት ሊያስከትል የሚችል መውጃዊ ሞገድ ይፈጥራል። መውጃዊ ሞገዶች መጀመሪያ ላይ ከሚከሰተው ክውታዊ ሞገድ (shock wave) የበለጠ ረጅም ርቀት መጓዝ የሚችሉ በመሆናቸው በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀው የሚገኙ የባሕር ዳርቻዎችን ያወድማሉ። የስነ ፈለክ ተመራማሪ የሆኑት ጃክ ሂልስ “ቀደም ሲል ከተሞች የነበሩባቸው ቦታዎች ሁሉ ጭቃ የተቆለለባቸው ባድማዎች ይሆናሉ” ብለዋል።
ይሁን እንጂ አንድ ሰው በእነዚህ አስተያየቶች ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። ከዚህ ንድፈ ሐሳብ ውስጥ አብዛኛው በመላ ምት ላይ የተመሠረተ ነው። አንድ ንዑስ ፕላኔት ከመሬት ጋር ሲጋጭ ያየ ወይም ግጭት ተከስቶ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያካሄደ ሰው እንደሌለ የታወቀ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በዛሬው ጊዜ ያሉ የሰዎችን ስሜት የመግዛት ሱስ የተጠናወታቸው መገናኛ ብዙሃን ባልተሟላ አልፎ ተርፎም በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሠረቱ ትኩረት የሚስቡ ርዕሰ ዜናዎች ለማቅረብ ፈጣኖች ናቸው። (ከላይ ያለውን ሳጥን ተመልከት።) አንድ ሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከሰማይ በወደቀ አካል የመሞቱ አጋጣሚ ከ16,700,000,000 ውስጥ አንድ ሲሆን በመኪና አደጋ ሊሞት የሚችልበት አጋጣሚ ግን ከ2,400,000 ውስጥ አንድ ነው።
መደረግ ያለበት ነገር ምንድን ነው?
ወደ መሬት እየቀረበ ያለ ጅራታም ኮከብ ወይም ንዑስ ፕላኔት የሚያስከትለውን አደጋ ማስወገድ የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለ ስልት ሮኬት በመተኮስ መሀል ላይ ማስቀረትና ቢያንስ ቢያንስ አቅጣጫውን ማስቀየር እንደሆነ ብዙዎቹ ጠበብት ያምናሉ። ንዑስ ፕላኔቱ ትንሽ ከሆነና ወደ መሬት እየመጣ መሆኑ ከብዙ ዓመታት በፊት ከታወቀ በሮኬት መምታቱ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል።
ይሁን እንጂ ከመሬት ጋር ሊጋጭ የሚችልን ትልቅ አካል በኑክሊየር መሣሪያ መምታቱ የተሻለ እንደሚሆን አንዳንድ ሳይንቲስቶች ይናገራሉ። በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በትክክል የተነጣጠረ የኑክሊየር መሣሪያ ንዑስ ፕላኔቱን ከአደጋ ዞን በማስወጣት ከመሬት ጋር እንዳይጋጭ ያደርገዋል። የኑክሊየር ፍንዳታው መጠን የሚወሰነው በንዑስ ፕላኔቱ መጠንና ቅርበት ነው።
ችግሩ ግን በበቂ ሁኔታ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ካልተሰጠ ከእነዚህ የመከላከያ መንገዶች መካከል የትኛውም ቢሆን ውጤታማ ሊሆን አይችልም። እንደ ስፔስዎች እና ኒር ኧርዝ አስቴሮይድ ትራኪንግ ያሉ የስነ ፈለክ ምርምር ቡድኖች ሙሉ በሙሉ በንዑስ ፕላኔት ፍለጋ ላይ የተሠማሩ ናቸው። ብዙ ሰዎች በዚህ ረገድ ገና ብዙ መሠራት እንዳለበት ይሰማቸዋል።
ፍጽምና የሌላቸው የሰው ልጆች እነዚህ ሰማያዊ አካላት ያሉበትን ቦታና የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በተመለከተ ያላቸው እውቀት ውስን እንደሆነ እሙን ነው። ሆኖም በምድር ላይ ያለው ሕይወት የወደፊት ዕጣ አደጋ ላይ ወድቋል በሚል ስጋት ከልክ በላይ መጨነቅ ወይም መሸበር አያስፈልግም። ከሁሉ ይበልጥ አስተማማኝ የሆነው ዋስትና የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ይሖዋ አምላክ የትኛውም ንዑስ ፕላኔት ወይም ጅራታም ኮከብ በምድር ላይ ያለውን ሕይወት ጠራርጎ እንዲያጠፋ የማይፈቅድ መሆኑ ነው።a መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” ሲል ያረጋግጥልናል።—መዝሙር 37:29፤ ኢሳይያስ 45:18
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያለውን አመለካከት በይበልጥ ለመረዳት የታኅሣሥ 8, 1998 ንቁ! መጽሔት (እንግሊዝኛ) ገጽ 22-3 ተመልከት።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የ1997 ኤክስ ኤፍ 11 (XF11) ጉዳይ
መጋቢት 12, 1998 ላይ አንድ መጥፎ ዜና በዓለም ዙሪያ ተሠራጨ:- 1.5 ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት አንዲት ንዑስ ፕላኔት ወደ መሬት እየገሰገሰች እንደሆነና ጥቅምት 26, 2028 “ዕለተ ሐሙስ” ላይ እንደምትደርስ ተነገረ። ይህች 1997 ኤክስ ኤፍ 11 ተብላ የተሰየመችው ንዑስ ፕላኔት የአሪዞና ዩኒቨርሲቲ ስፔስዎች ቡድን ባልደረባ በሆኑት የስነ ፈለክ ተመራማሪ ጂም ስኮቲ የተገኘችው ታኅሣሥ 6, 1997 ላይ ነበር። ከሃርቫርድ-ስሚዝሶኒያን የአስትሮፊዚክስ ማዕከል ጋር የሚሠሩ ሳይንቲስቶች ቀደም ሲል የነበሩ መረጃዎችንና አዳዲስ የምርምር ውጤቶችን በመጠቀም የሰጡትን ትንተና መሠረት በማድረግ አንዳንዶች ንዑስ ፕላኔቷ የምትሽከረከርበት ምህዋር ከመሬት ያለው ርቀት 80,000 ኪሎ ሜትር ገደማ እንደሚሆን ተንብየዋል። ይህ ከስነ ፈለክ መስፈርቶች አንጻር ሲታይ በጣም ቅርብ ነው። በሌላ አባባል “ንዑስ ፕላኔቷ ከምድር ጋር መጋጨቷ አይቀሬ ይሆናል።” የቴሌቪዥን መስኮቶች አንድ ንዑስ ፕላኔት ከምድር ጋር ስትጋጭ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን በሚያሳዩ አስፈሪ ትዕይንቶች ተሞሉ። ይሁንና አደጋው በአንድ ቀን ጊዜ ውስጥ ተወገደ። አዳዲስ መረጃዎችና ስሌቶች ንዑስ ፕላኔቷ ምድርን በ1,500,000 ኪሎ ሜትር ርቀት አልፋት እንደምትሄድ አመለከቱ። ይህም ቢሆን ከዚህ ቀደም ከታዩት ይህን የሚያክል መጠን ያላቸው ንዑስ ፕላኔቶች አንጻር ሲታይ በጣም ቅርብ ርቀት ነው። ሆኖም ለአደጋ የሚያጋልጥ አይደለም። ወዲያውኑ መገናኛ ብዙሃን “መረጃዎቹና ስሌቶቹ ትንሽ የተዛቡ ነበሩ” እንደሚለው ያሉ ርዕሰ ዜናዎችን ይዘው ብቅ አሉ።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
1. ሃሊ ኮሜት
2. ኢኬያ-ሴኪ የተሰኘችው ጅራታም ኮከብ
3. አስቴሮይድ 951 ጋስፕራ ተብላ የምትጠራው ንዑስ ፕላኔት
4. ወደ 1,200 ሜትር የሚጠጋ ስፋትና 200 ሜትር ጥልቀት ያለው በተወርዋሪ ኮከብ የተፈጠረ ስርጉድ
[ምንጮች]
Courtesy of ROE/Anglo-Australian Observatory, photograph by David Malin
NASA photo
NASA/JPL/Caltech
Photo by D. J. Roddy and K. Zeller, U.S. Geological Survey
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
NASA photo