የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 3/8 ገጽ 22-25
  • ምንስ ዓይነት ልብስ ብንለብስ ምን ለውጥ አለው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ምንስ ዓይነት ልብስ ብንለብስ ምን ለውጥ አለው?
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ፋሽን የምን መግለጫ ነው?
  • የአለባበስ ደንብ ምን እየሆነ ነው?
  • ይህን ያህል ስለ ራስና ስለ ማንነት መጨነቅ የበዛው ለምንድን ነው?
  • አለባበሴ ጥሩ ነው?
  • “ባለ አእምሮ” መሆንን በሚያሳይ ሁኔታ መልበስ
  • አለባበሳችሁ አምላክን ያስከብራል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • አለባበሴ ስለ እኔ እውነተኛ ማንነት ይናገራልን?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች
  • አለባበሳችንና ውጫዊ ገጽታችን ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
  • በአለባበስና በፀጉር አያያዝ ልከኛ መሆን
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2002
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 3/8 ገጽ 22-25

ምንስ ዓይነት ልብስ ብንለብስ ምን ለውጥ አለው?

“ምን ልልበስ?” እንዲህ ያለ ጥያቄ ቀርቦልህ አያውቅም? የዘመናችን የፋሽን ሱቆች በቅርቡ ያወጡትን ፋሽን በማሳየት ሊረዱህ ወይም የባሰውን ግራ ሊያጋቡህ ይችላሉ።

በተለይ በአሁኑ ጊዜ የጨዋ ልብስ ሳይሆን ቅጥ ያጣ ልብስ እንድትለብስ ግፊት ስለሚደረግብህ የልብስ ምርጫ ማድረግ የበለጠ አስቸጋሪ ይሆንብሃል። በ1990ዎቹ ዓመታት ስለተስፋፋው ስለዚህ ዓይነቱ አለባበስ አንድ የፋሽን ርዕሰ አንቀጽ እንዲህ ብሏል:- “የተጎሳቆለ፣ ያረጀ፣ የተጨማደደና የወየበ ልብስ መልበስ ተቀባይነት ያለው ብቻ ሳይሆን የሚፈለግ ነገር መሆኑን ማወቅ ያስደስታል።”

አዎን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ የማሳመን ችሎታ ያላቸው ማስታወቂያዎች፣ የቴሌቪዥን ኮከቦች ምሳሌነት፣ የእኩዮች ተጽእኖ፣ እድገት የማግኘት ፍላጎትና ማንነትን የማሳወቅ ጥማት በአለባበስ ላይ፣ በተለይ በወጣቶች አለባበስ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ፋሽን ለመከተል ሲሉ እስከ መስረቅ ደርሰዋል።

በእነዚህ በ1990ዎቹ ዓመታት ከተስፋፉት ፋሽኖች ብዙዎቹ በ1960ዎቹ ዓመታት በምዕራቡ ዓለም ተስፋፍቶ እንደነበረው የሂፒዎች እንቅስቃሴ ካሉ ቀደምት አጉል ባሕሎች ያቆጠቆጡ ናቸው። ጺም ማሳደግ፣ ፀጉር ማንጨብረርና የተጨረማመተ ልብስ መልበስ ቀደም ሲል ተቀባይነት በነበረው ባሕል ላይ ማመፅን ያመለክታል። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ የዓመፅ አለባበስ አዲስ ዓይነት በእኩዮች ተጽእኖ የመሸነፍ አዝማሚያ አስፋፍቷል።

አለባበስ ሰፋ ያለና ይበልጥ ግልጽ የሆነ የማንነት ማሳወቂያ መሣሪያ ሆኗል። ልብሶች፣ በተለይም ቲ-ሸርቶች እውቅ ስፖርቶችንና ስፖርተኞችን፣ ቀልዶችን፣ ቅሬታን፣ ጠብ አጫሪነትን፣ የንግድ ሸቀጦችን፣ የሞራል መጥበቅ ወይም መላላትን የሚያሳውቁ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ሆነዋል። ተመልካቾችን የሚያስደነግጡም ሊሆኑ ይችላሉ። በቅርቡ የወጣ አንድ የኒውስዊክ አምድ ርዕስ “ጨካኝነት በወጣቶች ፋሽን ሲገለጽ” ይላል። ይህ ጽሑፍ አንድ የ21 ዓመት ወጣት ስለ ቲ-ሸርቱ የተናገረውን ጠቅሷል:- “ይህን ቲ-ሸርት የምለብሰው የሚሰማኝን ስሜት ለሰዎች ስለሚያሳውቅልኝ ነው። ማንም ሰው እንዲህ አድርግ እንዲለኝ ወይም እንዲያስቸግረኝ አልፈልግም።”

በደረትና በጀርባ ላይ የሚነገቡት መፈክሮች እንደየሰዉ የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ከአንድ ቡድን ወይም ተስፋፍቶ ከሚገኝ ከአንድ የዓመፅ መንፈስ ጋር የመስማማት፣ ስለ ራስ ብቻ የማሰብ፣ የጭካኔና የዓመፅ መንፈስ በሁሉም ላይ ጎልቶ ይታያል። አንድ የልብስ ሞድ አውጪ እንደ ደንበኞቹ ጥያቄ ልብሳቸውን በጥይት የተበሳሳ አስመስሎ ዲዛይን ያወጣላቸዋል። “በሽጉጥ፣ ወይም በጠመንጃ ወይም በመትረየስ ጥይቶች የተበሳሳ አስመስሎ እንዲሠራላቸው ሊጠይቁ ይችላሉ። ሐሳባቸውን በፋሽን አማካኝነት የሚገልጹበት መንገድ ነው” ይላል።

ፋሽን የምን መግለጫ ነው?

ሲድኒ፣ አውስትራሊያ በሚገኘው ፓወርሃውስ ሙዚየም የፋሽን አስጎብኚና ጠባቂ የሆኑት ጄን ደ ቴሊጋ “ልብስ በአጠቃላይ የአንድ ነገድ አባል መሆናችንን የምናሳውቅበት መሣሪያ ነው” ካሉ በኋላ በማከል “አባል ለመሆን የምትፈልገውን ነገድ ከመረጥክ በኋላ እንደዚያ ነገድ መልበስ ትጀምራለህ” ብለዋል። በሲድኒ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና መምህር የሆኑት ዶክተር ዳያና ኬኒ ሰዎችን በቡድን በመከፋፈል ረገድ አለባበስ ከሃይማኖት፣ ከሀብት፣ ከሥራ፣ ከነገድ፣ ከትምህርትና ከመኖሪያ ሥፍራ ያላነሰ አስፈላጊነት እንዳለው ተናግረዋል። ጄት መጽሔት እንዳለው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኝ አንድ የነጮች ትምህርት ቤት “ነጭ ሴት ተማሪዎች እንደ ጥቁሮች ፀጉራቸውን ሹሩባ በመሠራታቸው፣ ባጊ ሱሪዎችን በመልበሳቸውና በጥቁሮችና የስፓኝ ዝርያ ባላቸው ሰዎች የሚዘወተረውን የሂፕ-ሆፕ ሙዚቃ አቀንቃኞች ፋሽን በመከተላቸው ትልቅ ረብሻ ተነስቷል።”

እንደ ሙዚቃው ዓለም ባሉ አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ወገናዊነት በአለባበስ ላይ ጎልቶ ይታያል። ማክሊንዝ መጽሔት እንደሚለው “አብዛኛውን ጊዜ የሚለበሰው ልብስ ከሙዚቃ ምርጫ ጋር ይቀናጃል። የሬጌ አቀንቃኞች የጃማይካን ደማቅ ቀለሞችና ኮፍያ ይለብሳሉ። ግሩንጅ ሮክ ሙዚቃ የሚመርጡ ደግሞ ወፍራም ካልሲና ባለሽንትር ሸሚዝ ይለብሳሉ።” ይሁን እንጂ የግሩንጅ ሙዚቃ አቀንቃኞች የሚለብሱት ልብስ ምንም ያህል ቡቱቶና የተጨረማመተ ቢሆን በቀላል ገንዘብ የሚገዛ አይደለም።

የአለባበስ ደንብ ምን እየሆነ ነው?

“ሁሉም ነገር ከምታስቡት ተቃራኒ ነው” ይላሉ የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ የሆኑት ዉዲ ሆክስዌንደር። “በአንድ ወቅት ጠንካራ በሆኑ ደንቦች ይገዛ የነበረው የወንዶች አለባበስ ከደንብ ውጭ እየሆነ መጥቷል። . . . ሁሉም ነገር ዶሮ እንደጫረው ምስቅልቅል ማለት አለበት።” ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ በአንዳንድ ሁኔታዎች ግድየለሽ መሆንን ሊያመለክት ይችላል። አለበለዚያም ለራስ ወይም ለሌሎች አክብሮት አለማሳየትን ሊያንጸባርቅ ይችላል።

ፐርሴፕችዋል ኤንድ ሞተር ስኪልስ የተባለው መጽሔት ተማሪዎች ለአስተማሪዎቻቸው ስለሚኖራቸው ግምት ባወጣው ጽሑፍ “ጂንስ የለበሰ አስተማሪ ቀልደኛ እንደሚሆን ቢታሰብም ለአስተያየቶቹ የሚሰጠው ከበሬታ አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ምንም ነገር እንደማያውቅ ሆኖ ይታያል” ብሏል። ይኸው መጽሔት “ጂንስ የለበሰች ሴት መምህር ቀልደኛና በቀላሉ የምትቀረብ ሆና ትታይ እንጂ እውቀት እንዳላት፣ ልትከበር እንደሚገባት፣ በአጠቃላይ እንደ መምህር ሆና የምትታይና ተመራጭነት ያላት አትሆንም።”

በሥራው ዓለም ደግሞ በአለባበስ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር ሌላ ነገር አለ። ልብስ የሌሎችን ትኩረት ለመሳብና እድገት ለማግኘት መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመሥሪያ ቤቶቻቸው ከፍተኛ ቦታ ላይ ለመድረስ የሚጣጣሩ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። የአንድ ማተሚያ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የሆነችው ማሪ “የምለብሰው ሌሎችን ለማጥቃት ነው። ከሌሎች በልጬ መታየት እፈልጋለሁ። በጣም አምሬ መታየት እፈልጋለሁ” ብላለች። ማሪ ትኩረቷ በሙሉ በራሷ ላይ መሆኑን በሐቀኝነት ተናግራለች።

ተወዳጅ ፋሽኖች ወደ ቤተ ክርስቲያናትም ገብተዋል። አንዳንድ ፋሽን አሳዳጆች ቤተ ክርስቲያናቸውን የልብሳቸው ማሳያ አድርገው እስከ መጠቀም ደርሰዋል። በአሁኑ ጊዜ ቀሳውስት ዘርፋፋ ልብሶቻቸውን ተጎናጽፈው ቢታዩም ከመድረክ ሆነው የሚመለከቷቸው የጉባኤዎቻቸው አባሎች በአብዛኛው ጂንስና ስኒከር ጫማዎች ያደረጉ ወይም ከሥርዓት ውጭ የሆነ ልብስ የለበሱ ናቸው።

ይህን ያህል ስለ ራስና ስለ ማንነት መጨነቅ የበዛው ለምንድን ነው?

ጊዜ አመጣሽ ፋሽን መልበስ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት በተለይ በወጣቶች ዘንድ አድማጭ የማግኘት ፍላጎት መግለጫ በመሆኑ ስለራስ ብቻ የማሰብ ባሕርይ አንዱ ገጽታ ነው። ስለዚህ ባሕርይ ምንነት ሲያብራሩ “በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያለው ወጣት የሚያሳየው የሌሎችን ትኩረት የማግኘት ሥር የሰደደ ፍላጎት ነው” ይላሉ። “እኔ ስለ ራሴ የማስበውንና የምጨነቀውን ያህል እናንተም እንድታስቡልኝና እንድትጨነቁልኝ እፈልጋለሁ” ይላል ማለት ነው።—አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ኦርቶሳይኪያትሪ

ለአምላክ ምንም ቦታ ሳይሰጡ ለሰው ልጅ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጡ ፍልስፍናዎችም በዚህ ጽንፈ ዓለም ከራሴ የበለጠ ነገር የለም የሚለው አስተሳሰብ (የንግዱ ዓለም የሚያራምደው አስተሳሰብ) እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ችግሩ ግን በአሁኑ ጊዜ ‘ከእኔ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ማንም የለም’ የሚሉ ወደ ስድስት ቢልዮን የሚጠጉ ሰዎች በዓለማችን መኖራቸው ነው። በሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “አሁን ያለውን ጥሩ ኑሮ” ለማግኘት ሲፍጨረጨሩ ለዚህ ቁሳዊ አስተሳሰብ ተንበርክከዋል። (ከ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ጋር አወዳድር።) በዚህ ሁሉ ላይ የቤተሰብ አንድነትና የእውነተኛ ፍቅር መሸርሸር ሲጨመርበት ብዙዎች፣ በተለይም ወጣቶች፣ ለሚነሳባቸው የማንነት ጥያቄና ሥጋት ምላሽ ለማግኘት ባገኙት ማንኛውም ነገር ላይ ቢንጠላጠሉ የሚያስደንቅ አይሆንም።

ይሁን እንጂ ስለ አለባበሳቸውና በአምላክ ዘንድ ስላላቸው አቋም የሚያስቡ ሰዎች በየጊዜው ከሚለዋወጠው የአለባበስ ሥርዓት ጋር አብሬ መሄድ የሚኖርብኝ እስከ ምን ድረስ ነው? አለባበሴ ጥሩ መሆኑንና አለመሆኑን የማውቀው እንዴት ነው? ስለ ማንነቴ የተሳሳተ ወይም አደናጋሪ መልእክት ያስተላልፋል? ብለው ቢጠይቁ ተገቢ ይሆናል።

አለባበሴ ጥሩ ነው?

በመሠረቱ የምንለብሰው ልብስ እንደየግል ምርጫችን የሚወሰን ነው። የገንዘብ አቅማችንም ሆነ ምርጫችን ይለያያል። በተጨማሪም የአለባበስ ልማዶች ከቦታ ወደ ቦታ፣ ከአገር ወደ አገርና እንደ አየሩ ጠባይ ይለያያሉ። ይሁን እንጂ በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ብትኖር የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት ልብ ማለት ይኖርብሃል:- “ለሁሉ ዘመን አለው፣ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:1) በሌላ አነጋገር ለሁኔታው የሚስማማ ልብስ ልበስ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ‘ቦታህንና አቅምህን ጠብቀህ ከአምላክህ ጋር ተመላለስ።’—ሚክያስ 6:8 NW

ይህ ማለት አለባበስን በተመለከተ ከመጠን በላይ ፅንፈኛ መሆን አለብህ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘ጤናማ አስተሳሰብ’ ያለህ መሆንህን የሚያንጸባርቅ ‘ተገቢ ልብስ’ መልበስ አለብህ ማለት ነው። (1ጢሞቴዎስ 2:9, 10) ይህን ለማድረግ ብዙውን ጊዜ የሚጠይቀው ራስን መግታትን ነው። ይህ ራስን የመግታት ባሕርይ ጥሩ ምርጫ ከማድረግና አምሮ ከመታየት ጋር ዝምድና እንዳለው ወርኪንግ ውመን የተባለው መጽሔት ገልጿል። በዚህ ረገድ፣ ወደ አንድ ክፍል ስትገቡ የሰዎችን ትኩረት በመጀመሪያ የሚስበው ልብሳችሁ አይሁን የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ሕግ ጥሩ መመሪያ ይሆናል። ወርኪንግ ውመን እንዲህ ይላል:- “ልብሳችሁ ... ሰዎች በውጫዊ ቁመናችሁ ሳይደናገሩ ውስጣዊ ማንነታችሁን እንዲመለከቱ የሚያስችል ይሁን።”

ፐርሴፕቹዋል ኤንድ ሞተር ስኪልስ የተባለው መጽሔት እንዲህ ይላል:- “ልብስ በተመልካቾች ላይ የሚያሳድረውን ግንዛቤና የሚያስተላልፈውን መልእክት የመረመሩ በርካታ ጽሑፎች ልብስ ስለ አንድ ሰው ማንነት የመጀመሪያ ግንዛቤ የሚሰጥ አስፈላጊ ፍንጭ እንደሚገኝበት ያመለክታሉ።” በዚህ ረገድ አንዲት በ40ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ የምትገኝና ከዚህ በፊት አለባበሷ በነበረው ሰዎችን የመማረክ ኃይል ትኩራራ የነበረች ሴት “በሥራዬና በግል ሕይወቴ መካከል ያለውን ልዩነት ስላደበዘዘው ብዙ ችግር አጋጥሞኛል። በሥራ አጋጣሚ የማገኛቸው በርካታ ወንዶች ራት ሊጋብዙኝ ይፈልጋሉ።” ከዚህ ተቃራኒ የሆነ አለባበስ ደግሞ ምን ዓይነት ውጤት እንደሚያስከትል አንዲት የሂሣብ ሠራተኛ እንዲህ ስትል ትገልጻለች:- “ወንዶች ዝርክርክ ልብስ የለበሱ ወይም የወንድ አለባበስ ያላቸውን ሴቶች እንዴት እንደሚመለከቱ ታዝቤያለሁ። ጉልበተኞችና ሁልጊዜ በወንዶች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የተዘጋጁ እንደሆኑ ተደርገው ስለሚታዩ ወንዶች በጣም ያስቸግሯቸዋል።”

ጄፊ የምትባል አንዲት ወጣት ፀጉሯን እንደ ጊዜው ፋሽን በመቆረጧ የተሳሳተ መልእክት ማስተላለፏን ተገንዝባለች። “‘ልዩ’ ሆኜ ከመታየት በቀር ምንም ክፋት ያለው ሆኖ አልታየኝም ነበር” ትላለች። “ይሁን እንጂ ሰዎች ‘እውነት አንቺ የይሖዋ ምሥክር ነሽ?’ እያሉ ይጠይቁኝ ጀመር። ይህ ደግሞ በጣም የሚያሳፍር ነበር።” ጄፊ ራስዋን አሳሳቢ የሆኑ ጥያቄዎች ለመጠየቅ ተገድዳ ነበር። በእርግጥም፣ አፋችን ብቻ ሳይሆን አለባበሳችንና ቁመናችንም የሚናገረው “በልብ ሞልቶ ከተረፈው” አይደለም? (ማቴዎስ 12:34) አለባበስህ የሚያሳየው ምን ዓይነት ልብ እንዳለህ ነው? የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ የሚፈልግ ልብ ነው ያለህ ወይስ ፈጣሪህን ለማስከበር የሚፈልግ?

“ባለ አእምሮ” መሆንን በሚያሳይ ሁኔታ መልበስ

በተጨማሪም አለባበስህ በአንተ በራስህ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽእኖ አስብ። ከመጠን በላይ መዘነጥ ለራስህ ከልክ ያለፈ ግምት እንድትሰጥ ሊያደርግህ፣ ዝርክርክ ልብስ መልበስ ስለ ራስህ ያለህን አሉታዊ አመለካከት ሊያጠናክርብህ፣ እንዲሁም እውቅ የሲኒማ ወይም የስፖርት ኮከቦችን ወይም ደግሞ ሌሎች ታዋቂ ሰዎችን የሚያስተዋውቅ ቲ-ሸርት መልበስ ሰዎችን ወደ ማምለክ ማለትም ወደ ጣዖት አምልኮ ሊገፋፋህ ይችላል። አዎን፣ ልብሶችህ ስለ ማንነትህ ይናገራሉ።

በጣም ዝንጥ ብለህ ለመታየት ወይም ሌሎችን ለመማረክ ብለህ ብትለብስ ልብሶችህ ስለ አንተ ምን ይናገራሉ? ለማሸነፍ መታገል የሚኖርብህን ባሕርይ ማጠንከር አይሆንብህም? ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ልትማርክ የምትፈልገው እንዴት ያለውን ሰው ነው? በሮሜ 12:3 ላይ የሚገኘው ምክር ስለ ራስ ብቻ የማሰብን፣ ከልክ በላይ መኩራራትንና አፍራሽ አስተሳሰብ የማዳበርን መንፈስ እንድናሸንፍ ሊረዳን ይችላል። እዚህ ጥቅስ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ማንም “እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ” ይመክራል። “ባለ አእምሮ” መሆን ማለት አሳቢ ሰው መሆን ማለት ነው።

በተለይ ይህ ባሕርይ ኃላፊነት ለተሰጣቸው ሁሉ በጣም አስፈላጊ ነው። የሚያሳዩት ምሳሌነት በሌሎች ላይ ጠንካራ ተጽእኖ ያሳድራል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለሚሰጡ የአገልግሎት መብቶች ለመብቃት የሚጣጣሩ ሁሉና ክርስቲያን ሚስቶቻቸውም በተመሳሳይ በአለባበሳቸውና በአጋጌጣቸው ላላቸው ኃላፊነት የአክብሮትና ቦታቸውን የመጠበቅ ዝንባሌ እንዳላቸው ማሳየት ይኖርባቸዋል። ማናችንም ብንሆን ኢየሱስ ስለ አንድ ሠርግ በሰጠው ምሳሌ ላይ እንደገለጸው ሰው መሆን አንፈልግም:- “ንጉሡም የተቀመጡትን ለማየት በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያለበሰ አንድ ሰው አየ።” ሰውየው እንዲህ ያለ አክብሮት የጎደለው ልብስ የለበሰበት ምንም ዓይነት በቂ ምክንያት እንዳልነበረው ሲረዳ “ንጉሡ አገልጋዮቹን:- እጁንና እግሩን አስራችሁ ... አውጡት” አላቸው።—ማቴዎስ 22:11-13

ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ስለ አለባበስ ጤናማ የሆነ አመለካከት እንዲያዳብሩና ጥሩ ምርጫ እንዲያደርጉ በቃልም ሆነ በተግባር ሊያስተምሯቸው ይገባል። ከወንድ ወይም ሴት ልጃቸው ጋር ስለ አለባበስ በሚነጋገሩበት ጊዜ አንዳንዴ ጥብቅ መሆን ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ሰዎች በራሳቸው ተነሳስተው ስለ ወጣቶቻችንም ሆነ ስለ ራሳችን አለባበስ ጥሩ አስተያየት ሲሰጡ መስማት ምንኛ ያበረታታል!

አዎን፣ የይሖዋ አገልጋዮች ከንቱ ውዳሴ ከመፈለግ፣ ብዙ ወጪ የሚጠይቁ ፋሽኖችን ከመከተልና ስለራሳቸው ብቻ ከማሰብ ነጻ ወጥተዋል። የሚመሩት መለኮታዊ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንጂ በዓለም መንፈስ አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 2:12) እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች የምታከብር ከሆነ የምትለብሰውን ልብስ መምረጥ አስቸጋሪ አይሆንብህም። ከዚህም በላይ ልብሶችህ እንደ ጥሩ የሥዕል ፍሬም እውነተኛ ባሕርይህን የሚያሳዩና የማያስነቅፉህ ይሆናሉ። አምላክን ለመምሰል በጣርክ መጠን በልብስ ከሚገኘው ውበት በጣም የላቀ መንፈሳዊ ውበት ታገኛለህ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ