በአለባበስና በፀጉር አያያዝ ልከኛ መሆን
1 አንድ የዜና ዘገባ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ትናንሽ ልጆችን ጨምሮ ሁሉም ወንዶች ከረባት አድርገዋል። በአሥራዎቹ እድሜ የሚገኙትንና ትናንሽ ሴቶች ልጆችን ጨምሮ ሁሉም ሴቶች የለበሱት ቀሚስ ነው። ጂንስ የለበሰ ወይም ከረባት ያላሰረ ሰው በመካከላቸው አይታይም። በሁሉም ፊት ላይ የደስታ ስሜት ይታያል።” እየተናገረ ያለው ስለ እነማን ነው? ባለፈው ዓመት በተደረገ አንድ ትልቅ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ስለተገኙ ወንድሞችና እህቶች መናገሩ ነበር። አንድ የጥበቃ ሠራተኛ ደግሞ “ጨዋ፣ የተከበራችሁና ንጹሕ ናችሁ። በጣም ደስ የምትሉ ናችሁ። በዚህ በቆሻሻ በተሞላ ዓለም ውስጥ ንጹሕ ሆናችሁ ለመገኘት ችላችኋል!” ብሏል። እነዚህ እኛን የሚያሞግሱ እንዴት ያሉ ግሩም ምሥክርነቶች ናቸው! የወንድማማች ኅብረታችንን በተመለከተ እንዲህ ያለ ውዳሴ በማግኘታችን ደስ አንሰኝም? እርግጥ ነው እንዲህ ያለውን ምሥክርነት ልናገኝ የቻልነው ሁሉም በአለባበሳቸውና በፀጉር አያያዛቸው ጥሩ ምሳሌ በማሳየታቸው ነው።
2 በአለባበሳችንና በፀጉር አያያዛችን የተለየን መሆናችን በዓለም ዙሪያ በሰፊው የሚታወቅ ነው። (ሚል. 3:18) ለምን? ይህ የሆነበት ምክንያት ‘በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳችንን ከመግዛት ጋር እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት እንደሚገባ ሰውነታችንን እንድንሸልም’ የተሰጠንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ስለምንከተል ነው።—1 ጢሞ. 2:9, 10
3 አለባበሳችሁና የፀጉር አያያዛችሁ ምን መልእክት ያስተላልፋል? የምንለብሰው የልብስ ዓይነትና የምንለብስበት መንገድ ስለ እኛ ማለትም ስለ እምነታችን፣ ስለ አስተሳሰባችንና ስለ ዝንባሌያችን ግልጽ መልእክት ያስተላልፋሉ። የምንከተለው ፋሽን ስለ ማንነታችንና የማን ደጋፊ እንደሆንን ይናገራል። በዓለም እንደ ትልቅ ተደርጎ የሚታየውን ወራዳ አስተሳሰብና ሥነ ምግባር ፈጽሞ መከተል አይኖርብንም። ግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን አንዱ ዓይነት ፋሽን ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈ መሆን አለመሆኑ ሳይሆን የአምላክ አገልጋይ ነኝ ለሚል ሰው ተስማሚ መሆን አለመሆኑ ነው። (ሮሜ 12:2) ቁመናችን በራስ የመመራት መንፈስ ወይም ምግባረ ብልሹነት የሚያንጸባርቅ እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ ‘እግዚአብሔርን የምናስከብር’ መሆናችንን ማሳየት እንፈልጋለን።—1 ጴጥ. 2:12
4 አንዳንድ ጊዜ አዲስ የሆነ፣ ተሞክሮ የሌለውና በመንፈሳዊ ደካማ የሆነ ሰው በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ምን ነቀፋ ሊያስከትል እንደሚችል ግምት ውስጥ ሳያስገባ ዓለም የሚያስፋፋውን ማንኛውንም የአለባበስና የፀጉር አያያዝ ፋሽን ሊከተል ይችላል። ሁላችንም የዓለም አስተሳሰብ ተጽዕኖ አሳድሮብን እንደሆነና እንዳልሆነ ራሳችንን ልንመረምር እንችላለን። በመንፈሳዊ ወደጎለመሰና ወደተከበረ አንድ ወንድም (ወይም እህት) ዘንድ ቀርበን ስለ አለባበሳችንና ስለ ፀጉር አያያዛችን የታዘቡትን በሐቀኝነት እንዲነግሩን ልንጠይቃቸውና የሚሰጡንን ሐሳብ አክብደን በመመልከት ማስተካከያ ልናደርግ እንችላለን።
5 አንዳንዶች በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ሲገኙ ለአለባበሳቸው ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ይስማማሉ። ይሁን እንጂ ከስብሰባ በኋላ ባለው ትርፍ ጊዜ ለአለባበሳቸው እምብዛም ትኩረት አይሰጡ ይሆናል። ለክርስቲያን አገልጋይ የሚስማማ ዓይነት አለባበስ ይኑራችሁ። (2 ቆሮ. 6:3, 4) ደረት ላይ የምንለጥፈው ካርድ ተስማሚ ከሆነው አለባበሳችንና የፀጉር አበጣጠራችን ጋር ተዳምሮ በምንሄድበት ቦታ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ያሳውቃል። በመሆኑም አለባበሳችን ምንጊዜም ሥርዓታማና ልከኛ ሆኖ ‘ከዓለም እንዳይደለን’ የሚያሳይ መሆን አለበት።—ዮሐ. 15:19
6 በዚህ ዓመት በሚደረገው “ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ‘ለአምላካችን ለይሖዋ የተቀደስን ሕዝብ መሆናችንን’ ለማሳየት የሚቻለንን ሁሉ እናድርግ። በውጤቱም ሰዎች የሚሰነዝሩት መልካም አስተያየት ለይሖዋ ‘ምስጋና፣ መልካም ስምና ክብር’ ያመጣለታል።—ዘዳ. 26:19
[ገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ይሖዋን ማስከበር የምንችልባቸው መንገዶች:-
■ ለአንድ የአምላክ አገልጋይ በሚስማማ መንገድ ልበሱ።
■ የዓለም መንፈስ የሚንጸባረቅባቸው ፋሽኖችን አስወግዱ።
■ ከጤናማ አስተሳሰብ የሚመነጨውን ልከኝነትን አሳዩ።