የጥያቄ ሣጥን
◼ ለይሖዋ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ስንጎበኝ ምን ዓይነት አለባበስ ሊኖረን ይገባል?
በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የመንግሥት አዳራሾች፣ ትላልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የቤቴል ቤቶችና ቢሮዎች ለይሖዋ አገልግሎት የተወሰኑ ልዩ ቦታዎች ናቸው። እነዚህ ቦታዎች ልከኛ፣ ንጹሕና በሚገባ የተያዙ መሆናቸው ክብርን የሚያንጸባርቁ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይህም በሰይጣን ሥርዓት ውስጥ በአብዛኛው ከሚታየው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር ፈጽሞ የተለየ ነው። ለይሖዋ አምልኮ የምንጠቀምባቸውን እነዚህን ቦታዎች የሚጎበኙ ወንድሞችና እህቶችም የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉ የእሱ ሕዝቦች እንደሆኑ ተደርገው መታየት ይገባቸዋል።
ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ተገቢ የሆነ አለባበስንና አጋጌጥን ጨምሮ በምናደርገው ነገር ሁሉ “ራሳችንን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች እናቀርባለን።” (2 ቆሮ. 6:3, 4) ከዚህም በተጨማሪ ጥሩ ጠባይ እንድናሳይ ይጠበቅብናል። በማንኛውም ጊዜም ቢሆን አለባበሳችንና አጋጌጣችን ከይሖዋ አገልጋዮች የሚጠበቀውን ጨዋነትና ክብር የሚያንጸባርቅ ሊሆን ይገባል። በተለይ በኒው ዮርክ የሚገኘውን ዋና መሥሪያ ቤትም ሆነ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ስንጎበኝ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት መስጠታችን አስፈላጊ ነው።
የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ የተባለው መጽሐፍ፣ ሥርዓታማ አለባበስና አጋጌጥ አስፈላጊ መሆኑን አስመልክቶ ሲናገር በመስክ አገልግሎት ስንሳተፍም ሆነ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ስንሄድ አካላዊ ንጽሕና፣ ልከኛ አለባበስና አጋጌጥ አስፈላጊ መሆኑን ሐሳብ ሰጥቷል። በመቀጠልም በገጽ 138 አንቀጽ 3 ላይ እንዲህ ብሏል:- “ቤቴል የሚለው ቃል ‘የአምላክ ቤት’ ማለት መሆኑን አስታውስ። ስለዚህ ወደ ቤቴል ስንሄድ አለባበሳችን፣ አጋጌጣችንና ምግባራችን በመንግሥት አዳራሽ ወደሚደረገው ስብሰባ ለአምልኮ ስንሄድ ሊኖረን ከሚገባው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ መሆን ይኖርበታል።” ከቅርብም ሆነ ራቅ ካለ አካባቢ ቤቴልን ለመጎብኘት የሚመጡ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይህን የላቀ የአቋም ደረጃ ማሟላት ይገባቸዋል። በዚህ መንገድ ጎብኚዎቹ ለቦታው ተገቢ አድናቆትና አክብሮት እንዳላቸው ያሳያሉ።—መዝ. 29:2
አለባበሳችን ‘አምላክን የምናመልክ’ መሆናችንን ለይቶ የሚያሳውቅ ሊሆን ይገባል። (1 ጢሞ. 2:10) ተገቢ የሆነ አለባበስና አጋጌጥ ሌሎች ለእውነተኛው የይሖዋ አምልኮ በሚኖራቸው አመለካከት ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይሁን እንጂ ጥቂት ወንድሞችና እህቶች ለይሖዋ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ሲጎበኙ ከመጠን በላይ ግድየለሽነት የሚንጸባረቅበት፣ ዝርክርክና ሰውነትን የሚያሳይ ልብስ እንደሚለብሱ ተስተውሏል። ክርስቲያኖች በማንኛውም ጊዜ ቢሆን እንዲህ ያሉ ልብሶችን መልበሳቸው ተገቢ አይደለም። እንደ ሌሎቹ ክርስቲያናዊ የሕይወታችን ዘርፎች ሁሉ በዚህ ጉዳይም ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር በሚያመጣ መንገድ በማድረግ የአምላክን ሕዝቦች ከዓለም ልዩ የሚያደርጋቸውን ከፍተኛ የአቋም ደረጃ ለመጠበቅ እንፈልጋለን።—ሮሜ 12:2፤ 1 ቆሮ. 10:31
ዋናውን መሥሪያ ቤት እንዲሁም በኒው ዮርክም ሆነ በሌሎች አገሮች የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ስትጎበኝ፣ ጉብኝትህ የታሰበበትም ይሁን አሊያም እግረ መንገድህን እንዲህ በማለት ራስህን ጠይቅ:- ‘አለባበሴና አጋጌጤ የምጎበኘውን ቦታ የሚመጥን፣ ንጹሕና ክቡር መሆኑን የሚያንጸባርቅ ነው? ምን ዓይነት አምላክ እንደማመልክ በትክክል ያንጸባርቃል? ሌሎች በእኔ አለባበስና አጋጌጥ ሊሰናከሉ ወይም ቅር ሊሰኙ ይችላሉ?’ ምንጊዜም በአለባበሳችንም ሆነ በአጋጌጣችን ‘አዳኛች የሆነው አምላክ የሰጠንን ትምህርት በሁሉም ነገር የሚያስውብ’ እንዲሆን እናድርግ!—ቲቶ 2:10 NW