ከዓለም አካባቢ
የእናት ጡት ወተት ብልጫ አለው
ኒውስዊክ መጽሔት “የእናት ጡት ወተት የመድኃኒቶች ሁሉ ቁንጮ ነው” ይላል። “ጡት የሚጠቡ ሕፃናት ለተስተካከለ የአንጎል እድገት የሚያስፈልጉትን ንጥረ ምግቦች ለማግኘት ከመቻላቸውም በላይ ከአለርጂና ከኢንፌክሽን አንስቶ እስከ ተቅማጥ፣ ችፌና ሳንባ ምች ባሉ የተለያዩ በሽታዎች የመያዝ ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው።” በዚህ ምክንያት የአሜሪካ የሕፃናት ሕክምና አካዳሚና የአሜሪካ የሥርዓተ ምግብ ማህበር እናቶች ቢያንስ ለአንድ ዓመት ያህል ልጆቻቸውን እንዲያጠቡ ይመክራሉ። “ይሁን እንጂ ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ንብረት በአግባቡ ጥቅም ላይ አልዋለም” ይላል ኒውስዊክ። ለምን? አብዛኛውን ጊዜ በተሳሳቱ መረጃዎች ምክንያት ነው። አንዳንድ እናቶች ለልጃቸው ጤናማ እድገት የሚበቃ ወተት እንደሌላቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ ምግቦች ቀደም ብለው መሰጠት የሚያስፈልጋቸው ይመስላቸዋል። “እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አብዛኞቹ እናቶች ሕፃኑ 6 ወር እስኪሞላው ድረስ የሚኖረውን የምግብ ፍላጎት ማሟላት ይችላሉ። ከዚያ በኋላ ደረቅ ምግቦችን ቀስ በቀስ ማስለመድ ይቻላል” ይላል ይኸው ጽሑፍ። “ከዚህም በላይ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ምግብ ቢሰጣቸው ሕፃናት 2 ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ ከእናታቸው ጡት ከሚያገኟቸው ፀረ እንግዳ አካላትና (antibodies) ፋቲ አሲዶች ጥቅም ያገኛሉ።” እናቲቱም ብትሆን በማጥባቷ የምታገኘው ጥቅም አለ። ማጥባት በጡት ካንሰር የመያዝን ዕድል ሲቀንስ የአራስነት ውፍረቷን ደግሞ ቶሎ ለመቀነስ ያስችላታል።
ድህነት አገር አይመርጥም
ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪብዩን እንደሚለው በቅርቡ የወጣ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት በጣም ባለጠጋ ናቸው በሚባሉት አገሮች ሳይቀር ድህነት እየጨመረ መሄዱን ገልጿል። በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች የሚኖሩ በርካታ ሰዎች እንደ ሥራ፣ ትምህርትና ሕክምና ያሉትን “የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች” አያገኙም። በዚህ ሪፖርት መሠረት ከመላው የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝቦች መካከል 16.5 በመቶ የሚሆኑት በድህነት ይማቅቃሉ። በብሪታንያ ቁጥሩ 15 በመቶ ይደርሳል። በኢንዱስትሪ በበለጸገው ዓለም ክፍል 100 ሚልዮን የሚያክሉ ቤት አጦች ሲኖሩ 37 ሚልዮን የሚሆኑት ሥራ የላቸውም። 200 ሚልዮን የሚያክሉ ደግሞ “ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት አያልፍም።”
እንደሚታሰበው ለማዳ አይደለም
“ከአፍሪካ አራዊት ሁሉ አደገኛው አንበሳ ወይም ጎሽ ነው ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ ሐሳባችሁን መለወጥ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል” ይላል ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል። “እጅግ አደገኛው ጉማሬ ነው።” የሕፃናት ሥዕሎችና ተረቶች ጉማሬዎች ለማዳና ሰው ወዳድ እንደሆኑ አድርገው ቢያሳዩና የጉማሬ አሻንጉሊቶችም በጣም ተወዳጅ ቢሆኑም በአፍሪካ ውስጥ የጉማሬን ያህል ለብዙ ሰዎች መሞት ምክንያት የሆነ አውሬ የለም። አስጎብኚዎች በአሕጉሪቱ ውስጥ ወደ ውኃ የሚያስገባውን የጉማሬ መንገድ ያህል አደገኛ ቦታ የለም ይላሉ። “በአደገኛነቱ ሁለተኛ የሚሆነው ምናልባት በእናት ጉማሬና በግልገሏ መካከል ያለው ቦታ ነው።” ጉማሬዎች ጥልቀት ባላቸው ወንዞች ሲዝናኑ በጣም ሰላማውያን ይምሰሉ እንጂ አካባቢያቸው እንዲደፈር አይፈልጉም። የሚያስደነግጥ ወይም ኃይላቸውን የሚፈታተን ነገር ሲያጋጥማቸውም በጣም ቁጡዎች ይሆናሉ። በጣም ጉልበተኞች ናቸው። “አንድ ያበደ ጉማሬ አንድን አዞ ለሁለት ሊቆርጠው ይችላል። አንድን ጀልባ ደግሞ በቀላሉ ያደቅቃል” ሲል አንድ አስጎብኚ ገልጿል። ታዲያ ሰዎች ጉማሬዎች በሚገኙባቸው ወንዞች በጀልባ ለመጓዝ የሚደፍሩት ለምንድን ነው? ወንዙንና በወንዞች ዳርቻ የሚገኙትን እንስሳት ለማየት ስለሚያመችና “ምናልባትም ጎብኚዎች በዚህ የዓለም ክፍል የሚካፈሉባቸውን ሌሎች እንቅስቃሴዎች፣ ለምሳሌ ያህል 110 ሜትር ከፍታ ካለው የቪክቶሪያ ፏፏቴ ድልድይ የመዝለልን ያህል አደገኛ ስላልሆነ ሊሆን ይችላል” ይላሉ አስጎብኚዎች።
የቅድመ ሆሎኮስት ማስጠንቀቂያ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል
በመክጊል ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰርና በካናዳ የሚገኘው የሄልሲንኪው የሰብዓዊ መብት አስጠባቂ ቡድን ተባባሪ ሊቀ መንበር የሆኑት ኧርውን ኮትለር “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሆሎኮስት መንገድ ጠራጊ የሆኑት ክስተቶች ከታዩባቸው የ1930 የጨለማ ዓመታት ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች እየታዩ ነው” ሲሉ መናገራቸውን ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል። የሄልሲንኪ የሰብዓዊ መብቶች ፌደሬሽን በ41 አገሮች ያደረገው ጥናት በአናሳ የማህበረ ሰብ ክፍሎች ላይ የሚሰነዘረው የጥላቻ ንግግር እየጨመረ መምጣቱንና አደገኛ የሆነ አዝማሚያ መታየት መጀመሩን ጎላ አድርጎ ያሳያል። የጥላቻ ስሜት የሚቀሰቅሱ የራዲዮ ስርጭቶችና የመንግሥት የሕትመት ውጤቶች ብዙውን ጊዜ በአናሳ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ስደት ያስነሳሉ። ኮትለር ስለዚህ አዝማሚያ ሲናገሩ “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግኘት ይገባን የነበረውን ትምህርት አላገኘንም” ብለዋል። ሌላው የዘነጋነው ትምህርት “የሰብዓዊ መብቶች ረገጣን በግድየለሽነትና በዝምታ ማለፍ በጣም ከፍተኛ ወንጀል መሆኑን ነው” ይላሉ።
የጦርነት ሰለባ የሚሆኑ ልጆች
የጀርመን ዕለታዊ ጋዜጣ የሆነው ግሪቬነ ሳይቱንግ በዘገበው መሠረት “የተመድ ልዩ ተወካይ የሆኑት ኦላራ ኦቱኑ ባለፉት አሥር ዓመታት በጦርነቶችና በግጭቶች ምክንያት ሁለት ሚልዮን ልጆች ሕይወታቸውን ሲያጡ አንድ ሚልዮን የሚያክሉት እናትና አባታቸውን አጥተዋል። ስድስት ሚልዮን የሚያክሉት ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።” የተመድ ፀጥታ ምክር ቤት ልጆችን የጥቃት ዒላማ የሚያደርጉ ድርጊቶችን በሙሉ አውግዟል። በተለይ በጣም አሳሳቢ የሆነው በዓለም ዙሪያ ለውትድርና የተመለመሉት ከ300,000 የሚበልጡ ልጆች ጉዳይ ነው። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ወደ ውትድርና የገቡት ተገድደው ሲሆን አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ አጥፍቶ በመጥፋት ግዳጅ ላይ የሚሰማሩት ልጆች ናቸው። አንድ አዲስ የተቋቋመ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥምረት 18 ዓመት ያልሞላቸው ልጆች በውትድርና እንዳይሰማሩ የሚከለክል ዓለም አቀፍ ሕግ እንዲወጣ ግፊት ማድረግ ጀምሯል።
ቫቲካን በኢንተርኔት ላይ
ቫቲካን በ1994 በኢንተርኔት ላይ የራሷ ገጽ እንዲኖራት የሚያስችል ኮንትራት ተፈራርማለች። ባሁኑ ጊዜ በኢንተርኔት አማካኝነት ኃጢአት መናዘዝ ወይም ስለማንኛውም ሃይማኖት ነክ “ጥርጣሬዎች” ቀሳውስትን ማማከር እንደሚቻል ኤል ፊናንስዬሮ የተባለው ጋዜጣ ሪፖርት አድርጓል። “የኮምፒዩተር ተጠቃሚ የሆኑ ካቶሊኮች” ጸሎት እንዲደረግላቸው ሊጠይቁ ይችላሉ። በተጨማሪም ሊቀ ጳጳሱ የዕለተ እሁድ ቡራኬያቸውን ሲያስተላልፉ በቀጥታ መመልከት ይቻላል። ከዚህም ሌላ “የሃይማኖታዊ ዕቃዎችን ሽያጭና ግዥ የሚያስተዋውቅ ልዩ ክፍል አለው።” “ችግሩ ግን ከካቶሊክ የኢንተርኔት ሳይቶች መካከል አብዛኞቹ ጨርሶ የማይጎበኙ መሆናቸው ነው” ይላል ኤል ፊናንስዬሮ። “የቫቲካንን ሳይት በቀን ውስጥ የሚጎበኙት ከ25 የማይበልጡ ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ የካቶሊክ ፕሬስ ሠራተኞች ናቸው።”
ታማሚ ለመሆን መምረጥ
“አሁንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ሰዎችን በመግደል ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የያዘው ሳንባ ነቀርሳ ነው” ይላል ኬፕ ታይምስ የተባለው ጋዜጣ። በጣም ድሃ በሆኑ ደቡብ አፍሪካውያን መካከል እንደ ሰደድ እሳት በመዛመት ላይ የሚገኘው ይህ በሽታ በየዓመቱ 13,000 ሰዎች ሲገድል ብዙዎችን አቅመ ደካማ ያደርጋቸዋል። ለእነዚህ መሥራት የተሳናቸው አቅመ ደካሞች መንግሥት የገንዘብ ድጎማ የሚሰጣቸው ሲሆን የሳንባ ነቀርሳ ሕክምናም በነጻ ይሰጣቸዋል። ይሁን እንጂ ሥራ እንደልብ የማይገኝና ቢገኝም ክፍያው በጣም አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት አንዳንድ በሽተኞች የሚያገኙት ድጎማ እንዳይቋረጥባቸው ሲሉ የሳንባ ነቀርሳ ሕክምናቸውን ለማቋረጥ ይወስናሉ። ቲ ቢ ኬር የተባለው የደቡብ አፍሪካ ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ሪያ ግራንት “የሚያገኙት ድጎማ እዚያና እዚህ ተሯሩጠው ያገኙ ከነበረው ገቢ 10 እጥፍ ይበልጣል” ይላሉ። “ምን ያህል ገንዘብ ሊያገኙ እንደሚችሉ ከተገነዘቡ በኋላ ጤነኛ ከመሆን መታመም እንደሚሻላቸው ያምናሉ።”
እንቅልፍ የሚያሸልባቸው አሽከርካሪዎች
ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን መዲካል አሶሲዬሽን እንደዘገበው “እንቅልፋም አሽከርካሪዎች የሰካራም አሽከርካሪዎችን ያህል አደገኞች እንደሆኑ አንዳንድ ጠበብት ያምናሉ።” “[በተሽከርካሪዎች] ግጭት ረገድ እንቅልፍ የሚጫወተው ሚና አብዛኛውን ጊዜ ዝቅ ተደርጎ ይታያል። ሆኖም እንቅልፋም አሽከርካሪዎች በሕዝብ ጤናና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ስጋት ይፈጥራሉ።” ዘ ቶሮንቶ ስታር እንደሚለው ከሆነ ሰዎች መቼ እንደሚያንቀላፉ ወይም ሸለብ አድርጓቸው እንደሆነና እንዳልሆነ በእርግጠኝነት እንደማያውቁ ጥናቶች አረጋግጠዋል። የአሜሪካ አውቶሞቢል ማህበር የትራፊክ ደህንነት ድርጅት ቃል አቀባይ የሆኑት ስቴፋኒ ፎል “እንቅልፍ እንደመራብና እንደ መተንፈስ የተፈጥሮ ፍላጎት ነው። ሰውነትህ እንቅልፍ ሲፈልግ አለምንም ማስጠንቀቂያ ታሸልባለህ” ብለዋል። ታዲያ አሽከርካሪዎች ደጋግሞ ካዛጋቸው ወይም ዓይናቸውን መግለጥ ካስቸገራቸው ወይም መኪናቸውን ቀጥ አድርገው ማሽከርከር ካቃታቸው ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? “መስተዋት ዝቅ በማድረግ፣ ወይም ሙዚቃ በማስጮህ እንቅልፍ ለማባረር መሞከር ፈጽሞ አይሠራም” ይላል ዘ ቶሮንቶ ስታር። “ቡና ወይም ሻይ መውሰድ ለአጭር ጊዜ ሊያነቃ ቢችልም የአንድን ሰው የማንቀላፋት ፍላጎት ሊቀንስ አይችልም።” አሽከርካሪዎች እንቅልፍ ከተፈታተናቸው መኪናቸውን ዳር አስይዘው እንቅልፋቸውን እንዲያሳልፉ ይመከራሉ።
ምን ያህል ባክቴሪያዎች አሉ?
ባክቴሪያዎች በምድር ላይ በጣም ተስፋፍተው የሚገኙ ሕያዋን ፍጡሮች ናቸው። በጣም ጥልቅ በሆነ የውቅያኖስ ወለልም ሆነ እስከ 60 ኪሎ ሜትር በሚደርስ የከባቢ አየር ከፍታ ላይ ይኖራሉ። የባክቴሪያዎች ጠቅላላ መጠን ከማንኛውም ሕያው ነገር ይበልጣል። ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሚሆን በዩ ኤስ ኤ የጆርጅያ ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቶች በዓይነቱ የመጀመሪያ ነው ሊባል የሚችል ግምት ሰጥተዋል። ከአምስት በኋላ 30 ዜሮ የተከተለው አሀዝ እንደሚሆን ገምተዋል። “አብዛኞቹ ሰዎች ባክቴሪያዎች በሽታ አምጪዎች ብቻ እንደሆኑ ያስባሉ” ይላል የለንደኑ ዘ ታይምስ። “ይሁን እንጂ የጤና ጠንቅ የሆኑት ባክቴሪያዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው። በሁሉም እንስሳት ውስጥ ጥገኛ ሆነው የሚኖሩት ባክቴሪያዎች በሙሉ አንድ ላይ ቢደመሩ እንኳን ከጠቅላላዎቹ ባክቴሪያዎች ከ1 በመቶ አይበልጡም። አብዛኞቹ ምንም ዓይነት ጉዳት የሌላቸው ከመሆኑም በላይ እንደ ምግብ ማላም ባሉት ተግባሮች ጥሩ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።” ከ92 እስከ 94 በመቶ የሚያክሉት ባክቴሪያዎች የሚኖሩት ከባሕር በታች በሚገኘው መሬት ከ10 ሴንቲ ሜትር በላይ በሚደርስ ጥልቀትና በየብስ ላይ እስከ 9 ሜትር በሚደርስ ጥልቀት ነው። እነዚህ አካባቢዎች ፈጽሞ ሕይወት አልባ እንደሆኑ ይታሰብ ነበር። ከባክቴሪያዎች ደረቅ ክብደት ግማሽ ያህል የሚሆነው ካርቦን ሲሆን ካርቦን ደግሞ ለሕይወት እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ንጥረ ነገሮች አንዱ ነው። “በባክቴሪያዎች ውስጥ የተከማቸው ካርቦን በመላው ዓለም በሚገኙ እጽዋት ውስጥ ከተከማቸው ካርቦን ጋር እኩል ነው ማለት ይቻላል” ይላል ዘ ታይምስ።