በመሰላል ስትጠቀም የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች ታደርጋለህን?
በአየርላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ፖል የቤቱን የውጭ መብራት መቀየር ነበረበት። በተጨማሪም ሚስቱ ፎቅ ላይ ያለውን ክፍል መስኮቶች በውጪ በኩል እንዲያጸዳቸው ደጋግማ ነግራዋለች። ሆኖም ፖል እነዚህን ሥራዎች ለሌላ ጊዜ ያስተላልፋቸው ነበር። ለምን? ምክንያቱም መሰላል መጠቀም ስለነበረበት ነው።
መሰላል ለመጠቀም ስጋት ቢያድርበት ምንም አያስደንቅም። ከመሰላል ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ አደጋዎች ከባድ የአካል ጉዳት ሊያስከትሉ አልፎ ተርፎም ለኅልፈተ ሕይወት ሊዳርጉ እንደሚችሉ ያውቃል። አብዛኛውን ጊዜ ይህ የሚከሰተው ተጠቃሚው ትክክለኛው የመሰላል አጠቃቀም እንዴት እንደሆነ በደንብ ሳያስብበት ሲቀር ነው።
ፖል እነዚህን ተግባሮች ከማከናወኑ በፊት መሰላል መጠቀምን በተመለከተ ምን ነገሮችን ሊያጤን ይገባዋል? ተግባሮቹን ጉዳት በማያስከትል መንገድ ለማከናወን የረዱት አሥር ነጥቦች ቀጥለው ቀርበዋል።
መሰላሉ አስተማማኝ ነውን?
1 ተስማሚውን ዓይነት መሰላል ተጠቀም። መሰላሉ በጣም አጭር ከሆነ ከመጠን በላይ መንጠራራት ሊያስፈልግህ ይችላል። በጣም ረዥም ከሆነ ደግሞ አደገኛ በሆነ ሁኔታ አዝምመህ ታቆመው ይሆናል። ከኮርኒስ በላይ ወዳለው ትንሽ ክፍል (attic) ለመውጣት በደረጃ መሰላል (stepladder) አትጠቀም። ወደዚህ ክፍል መግቢያ ላይ የተገጠመ ተስማሚ መሰላል ይኑርህ፤ አሊያም ተደጋፊ መሰላል ተጠቀም።
2 የመሰላልህን ደህንነት በደንብ ፈትሽ። መሰላሉ ከቤት ውጭ ተቀምጦ ነበርን? የእንጨት መሰላል እርጥበት ሲነካው ይነፋል ሙቀት ሲሆን ደግሞ ይመለሳል። ከጊዜ በኋላ መወጣጫዎቹ ይላሉና መሰላሉ እንዲዋዥቅ ያደርጉታል። ከእንጨት መወጣጫዎቹ መካከል የመሰንጠቅ ወይም የመበስበስ ምልክት የሚታይበት ይኖር ይሆን? አብዛኛውን ጊዜ እያንዳንዱን እንጨት የሚደግፍ የብረት መቀተሪያ ይኖራል። እነዚህ መቀተሪያዎች ቦታቸው ላይ አሉ? ጥብቅ ናቸው? የብረት መወጣጫዎቹን ከቋሚዎቹ ጋር የሚያያይዙት ብሎኖችና ከምሱሮች ተሰብረዋል ወይም ዝገዋል? ትላልቅ የሆኑ ተቀጣይ መሰላሎች በከራዎችና ማስረዘሚያ ገመዶች ይኖሯቸው ይሆናል። በከራዎቹ ያለ ምንም ችግር ይሠራሉ? የማስረዘሚያ ገመዱ የማርጀት ምልክት ይታይበታል? አሁንም ቢሆን ርዝመቱ በቂ ነው? ሳትዘገይ አስፈላጊውን ጥገናና ለውጥ ሁሉ አድርግ።
አብዛኛውን ጊዜ መወጣጫዎች እንዳያንሸራትቱ ሲባል ሸንተር ሸንተር ይደረግላቸዋል። በእነዚህ ሸንተሮች መካከል የሚደገደገውን ማንኛውም ቆሻሻ አስወግድ። ሁሉም መሰላሎች ታች እግራቸው ላይ የማይንሸራተት መቆሚያ ሊኖራቸው ይገባል። እነዚህ መቆሚያዎች መኖራቸውንና አለመበላታቸውን ፈትሽ።
3 መሰላሎችን ስታጓጉዝ ጥንቃቄ አድርግ። በተሽከርካሪ ላይ ከሆነ ለመሰላል ማስቀመጫ በተዘጋጀው ቦታ ላይ አድርገው ወይም ተሳቢው ላይ ጭነህ ቢያንስ በሁለት ቦታዎች ላይ እሰረው። ረዥም መሰላል ከተሽከርካሪው ጀርባ ተርፎ ሊወጣ ይችላል፤ ስለዚህ ከኋላ የሚመጣ ሰው በቀላሉ እንዲያየው የሚውለበለብ ነገር ጫፉ ላይ እሰርበት።
አንድን ረዥም መሰላል ሁለት ሰዎች ቢሸከሙት የተሻለ ነው። ይሁንና ብቻህን መሸከም ካለብህና አግድም ልትሸከመው ከፈለግህ መሰላሉን በአንድ እጅህ ጥብቅ አድርገህ በመያዝ በሌላኛው እጅህ ደግሞ ሚዛኑን በመጠበቅ በትከሻህ ተሸከመው። ሰው እንዳትገጭ ከፊት በኩል ከሰው ቁመት በላይ ከፍ አድርገው። ሆኖም መሰላልህ ከፊት የምታየውን ያህል ርዝማኔ ከኋላም እንዳለው አትዘንጋ! ኮሜዲያኖች ሰዎችን በመሰላል መግጨትን አስቂኝ አስመስለው ያቀርቡታል። በገሃዱ ዓለም ግን በተለይ ጉዳቱ የደረሰው በራስህ ላይ ከሆነ ይህ ነገር በፍጹም አስቂኝ አይሆንም።
መሰላሉን በቁመቱ ስትሸከም፣ ክብደቱን በአንደኛው እጅህ ላይ አሳርፈህ ከትከሻህ በላይ በማንሳትና ሚዛኑን ለመጠበቅ ሌላኛውን እጅህን ከጭንቅላትህ በላይ በማድረግ ደገፍ አድርገህ ያዘው። ከላይህ ያሉ ሽቦዎችን፣ መብራቶችንና ምልክቶችን እንዳትነካ ተጠንቀቅ!
4 መሰላሉን በትክክል አቁም። ለጥንቃቄ ሲባል መሰላሉ ወደ አንድ ጎን ማዘንበል የሌለበት ሲሆን ከወለሉ በ75 ዲግሪ ርቀት ላይ ማረፍ አለበት።
5 ከላይና ከታች ድጋፍ አድርግ። የመሰላሉ የላይኛው ጫፍ የሚያርፍበትን ቦታ በጥንቃቄ ምረጥ። ላይኛው የመሳላሉ ክፍል የሚያርፍበት ቦታ ጥብቅና የማያንሸራትት መሆኑን አረጋግጥ። መሰላሉን በመስተዋት ወይም በፕላስቲክ ነገር ላይ አታስደግፍ። የሚቻል ሲሆን የመሰላሉ የላይኛው ጫፍ ከሚያርፍበት ቦታ አንድ ሜትር ያክል ወደ ላይ ከፍ ይበል፤ ከዚያም ጠንካራ ከሆነ ነገር ጋር በደንብ እሰረው።
በተለይ የመሰላሉን ላይኛ ክፍል ለማሰር በምትወጣበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርግ። ለመጀመሪያ ጊዜ ስትወጣም ሆነ በመጨረሻ ጫፉ ላይ ያለውን እስር ፈትተህ ስትወርድ ልትወድቅ ትችላለህ። ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ ስትወጣና ስትወርድ ለአደጋ እንዳትጋለጥ መሰላሉን በምትወጣበት ጊዜ አንድ ሰው ከታች እንዲይዝልህ አድርግ። ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው መሰላሉ ከ5 ሜትር የማይበልጥ ከሆነ ብቻ ነው።
ከሕንፃው አጠገብ ያለው መሬት እያጋደለ የሚሄድ ከሆነ ክብደት ያለው ነገር በመሰላሉ ሥር አስቀምጥ ወይም ታችኛውን መወጣቻ ከአንድ ጠንካራ ነገር ጋር እሰረው። መሬቱ ወጣ ገባ ቢሆንም ጠጣርነት ካለው በሽብልቅ ተጠቅመህ መቆሚያው የተደላደለ እንዲሆን አድርግ። መሬቱ ጠንካራ ካልሆነ ወይም የሚያንሸራትት ከሆነ ድጋፍ የሚሆን ጣውላ ወይም ተመሳሳይ የሆነ ሌላ ነገር አድርግ።
በደረጃ መሰላል ስትጠቀም አራቱም እግሮቹ መሬት ላይ በደንብ ማረፋቸውን እንዲሁም ሁለቱም ጥንድ እግሮች በደንብ መከፈታቸውንና መቆለፊያዎቹ በሙሉ መቆለፋቸውን አረጋግጥ።
የአንተስ ሁኔታ አስተማማኝ ነውን?
6 የጫማዎችህን ሁኔታ ተመልከት። መሰላል ላይ ከመውጣትህ በፊት የጫማህ ሶል ደረቅ መሆኑን አረጋግጥ። እንደ ጭቃ ያሉ ሊያንሸራትቱህ የሚችሉ ነገሮችን አስወግድ።
7 እቃዎችን ስትሸከም ጥንቃቄ አድርግ። በሁለቱም እጆችህ በመጠቀም መሰላሉን ለመውጣት እንድትችል መሣሪያዎችህን ቀበቶ ላይ በሚታሠር መያዣ ውስጥ ከትተህ ያዝ። አመቺ ያልሆኑ እቃዎችን ለማንሳት ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም ሞክር፤ ሆኖም የግድ በመሰላል መጠቀም ካለብህ ነፃ የሆነውን እጅህን ከመሰላሉ ሳታርቅ በቋሚው እንጨት ላይ እያንሸራተትክ ውጣ። ጥንቁቅና ዘዴኛ ሁን፤ አትጣደፍ።
በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ መሣሪያዎች የምትጠቀም ከሆነ መሣሪያዎቹን በፍጹም በሁለቱ እጆችህ ይዘህ አትጠቀም። ለምሳሌ ያህል መሰርሰሪያ ድንገት ሊነክስ ወይም ሊያፈነግጥና ሚዛንህን ስተህ እንድትወድቅ ሊያደርግህ ይችላል። መሣሪያዎቹ እየሠሩ ሊወድቁ ስለሚችሉ አስነሽ አጥፊውን መጫን ሳያስፈልግ ያለማቋረጥ እንዲሠራ የሚያደርገውን ቁልፍ አትጠቀም።
8 ለሌሎች አሳቢነት አሳይ። ብዙ ሰዎች ባሉበት ቦታ የምትሠራ ከሆነ መሰላሉን በቀላሉ ማየት በሚቻልበት ቦታ ላይ አድርገው፤ የሚቻል ከሆነ ደግሞ ዙሪያውን በሪባን ነገር እጠረው። መሰላሉን ይዘህ በአንድ ማዕዘን በኩል የምታልፍ ከሆነ ከወዲያ የሚመጡት ሰዎች ማን እየመጣ እንዳለ መገመት እንደማይችሉ አስታውስ። ጮክ ብለህ ወዳጃዊ ማስጠንቀቂያ ስጥ፤ እንዲሁም መንገዱ ነፃ መሆኑን አረጋግጥ።
መሣሪያዎችን ይዘህ መሰላል ላይ የምትወጣ ከሆነ ሌላው ቀርቶ ትንሿ መፍቻ እንኳ ከርቀት ከወደቀች ጉዳት ልታስከትል እንደምትችል አትዘንጋ። በአንድ በሆነ ምክንያት ከመሰላሉ ርቀህ መሄድ ካለብህና መሰላሉን በደንብ ለማሰር ካልቻልክ ሰው እንዲጠብቅልህ አድርግ ወይም እስክትመለስ ድረስ አደጋ በማያስከትል መንገድ መሰላሉን መሬት ላይ አጋድመው። እንዲሁ ትተኸው አትሂድ።
9 ጤንነትህን ግምት ውስጥ አስገባ። ከፍታን መውጣት በአብዛኛው ሚዛንን መጠበቅ የሚጠይቅ በመሆኑ የሕመም ስሜት ካለህ ወይም እያጥወለወለህና እያዞረህ ከሆነ መሰላል ላይ አትውጣ።
10 መሰላሉን ስትወጣ ጥንቃቄ አድርግ። ምንጊዜም የቅድሚያ ጥንቃቄ ለማድረግ ንቁ ሁን። ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች በአንድ ጊዜ መሰላሉ ላይ እንዲወጡ በፍጹም አትፍቀድ። ኃይለኛ ነፋስ በሚነፍስበት ጊዜ በፍጹም መሰላል ላይ አትውጣ። በደረጃ መሰላል የመጨረሻው መወጣጫ ላይ ወይም ረዥም በሆነ መሰላል ላይ ከላይ ሲቆጠር ከአራተኛው መወጣጫ በላይ ባሉት ላይ በፍጹም አትቁም። ተቀጣይ መሰላልን በፍጹም ከሚገባው በላይ አታስረዝም፤ ሁልጊዜ ቢያንስ ሦስት መወጣጫዎች እንዲደራረቡ አድርግ። በፍጹም ከመጠን በላይ አትንጠራራ። በመሰላል ላይ እያለህ ወደ አንድ በኩል በጣም ካጋደልህ በቀላሉ ሚዛንህን ስተህ ልትወድቅ ትችላለህ። ረዥም ጊዜ ሊወስድብህ ቢችልም ለአደጋ ከምትጋለጥ መሰላሉን ማዛወር ይሻልሃል። መሰላሉን ስትወጣ ቀና ብለህ ፊት ለፊትህ ተመልከት።
ማንኛውንም ዓይነት ጥንቃቄ ብታደርግም በመሰላል ስትጠቀም ሁልጊዜም ለአደጋ የተጋለጥህ ነህ። ምናልባት እነዚህን ሐሳቦች በመጠቀም አደጋዎቹን ለመቀነስ ትችል ይሆናል። ፖል ጠቃሚ ሆነው አግኝቷቸዋል። እነዚህን ሐሳቦች ተግባራዊ በማድረግ የውጭ መብራቱን ለመቀየር ችሏል። መስኮቶቹን ማጽዳቱስ ቀረ? እሱን ደግሞ ሌላ ጊዜ ያደርገው ይሆናል!
[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
1 ተስማሚውን ዓይነት መሰላል ተጠቀም
2 የመሰላልህን ደህንነት በደንብ ፈትሽ
3 መሰላሎችን ስታጓጉዝ ጥንቃቄ አድርግ
4 መሰላሉን በትክክል አቁም
5 ከላይና ከታች ድጋፍ አድርግ
6 የጫማዎችህን ሁኔታ ተመልከት
7 እቃዎችን ስትሸከም ጥንቃቄ አድርግ
8 ለሌሎች አሳቢነት አሳይ
9 ጤንነትህን ግምት ውስጥ አስገባ
10 መሰላሉን ስትወጣ ጥንቃቄ አድርግ