ሙዚቃ ስሜታችንን የሚነካው ለምንድን ነው?
ሙዚቃና ቋንቋ ለሰው ልጅ የተሰጡ ነገሮች ናቸው። ሙዚቃና ቋንቋ የሌለበት ዓለም ምን ሊመስል እንደሚችል ለመገመት እንኳ ያስቸግራል። ዘ ሚውዚካል ማይንድ የተባለው መጽሐፍ “ቋንቋም ሆነ ሙዚቃ የሰው ዘር የጋራ መለያ ባሕርያት ናቸው” ሲል ይገልጻል። ሁለቱም የሰው ልጅ የሐሳብ ልውውጥ የሚያደርግባቸው መንገዶች ናቸው። ስለዚህ ልክ እንደ ቋንቋ ሁሉ ሙዚቃ “ሲናገር” ስሜታችን “ያዳምጣል።”
ሙዚቃ ስሜታችንን የሚማርከው ለምንድን ነው? የሚማርከውስ እንዴት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት:- (1) የሙዚቃ መሠረታዊ ክፍሎችንና አንጎላችን እነዚህን ነገሮች የሚያስተናግድበትን መንገድ፣ (2) ለሙዚቃ በሚኖረን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩትን የራሳችንን ተፈጥሯዊ ስሜት፣ ያደግንበትን ባሕላዊ ሁኔታና (3) ቋንቋን መመርመር ይኖርብናል።
የሙዚቃ መሠረታዊ ክፍሎች
ሙዚቃ ያሉት ባሕርያት “የሙዚቃ መሠረታዊ ክፍሎች” በመባል ይታወቃሉ። እነዚህ መሠረታዊ ክፍሎች አንድ የሙዚቃ መሣሪያ የሚያወጣውን የድምፅ ቃና ወይም የድምፁን ጥራት ያጠቃልላሉ። ለምሳሌ ያህል ፍሬንች ሆርን የተባለው የሙዚቃ መሣሪያ “የሚያስተክዝ” ወይም የሚከብድ ድምፅ ያለው እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸ ሲሆን “የኩራት” ስሜት ከሚፈጥረው ከትራምፔት ድምፅ ፈጽሞ የተለየ ነው። ምንም እንኳ ሁለቱም የትንፋሽ መሣሪያዎች ተብለው በሚጠሩት የሙዚቃ መሣሪያዎች መደብ ውስጥ የሚካተቱ ቢሆንም የሚያወጡት የድምፅ ቃና ያለው ኃይል የተለያየ ነው። እያንዳንዱ መሣሪያ የራሱ የሆነ የተለየ “ድምፅ” እንዲኖረው የሚያደርገው ነገር ይህ ነው። የሙዚቃ ቀማሪዎች እነዚህን ባሕርያት በመጠቀም የአድማጭን ስሜት የሚኮረኩር ድምፅ ይፈጥራሉ።
መጀመሪያ ላይ ከምንለያቸው የሙዚቃ መሠረታዊ ክፍሎች አንዱ ምት ሊሆን ይችላል፤ ምናልባትም ገና በማኅፀን ውስጥ እያለን የእናታችንን የልብ ምት በመስማት ከዚህ ነገር ጋር ሳንተዋወቅ አልቀረንም። የልብ ምታችን አልፎ ተርፎም አተነፋፈሳችን ለሙዚቃ ምት በምንሰጠው ምላሽ ላይ ሳናውቀው ተጽዕኖ ሊያሳድርብን እንደሚችል ይነገራል። በመሆኑም አብዛኞቹ ሰዎች አንድ ጤናማ የሆነ ዐዋቂ ሰው በአማካይ ከሚኖረው የልብ ምት መጠን ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ በደቂቃ ከ70 እስከ 100 የሚደርስ ምት ያለው ሙዚቃ የሚመርጡት እንዲሁ የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ላይሆን ይችላል። ፐርሴፕችዋል ኤንድ ሞተር ስኪልስ የተባለው መጽሔት ሁኔታውን የገለጸው በዚህ መንገድ ነው።
የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎችንና መሣሪያዎቹ የሚያወጧቸውን ድምፆችና ጣዕመ ዜማዎች ስንመረምር ከእነዚህ የሙዚቃ መሠረታዊ ክፍሎች ሊወጡ የሚችሉትን የተለያዩ የሙዚቃ ዓይነቶች መረዳት እንችላለን። ሞዛርት ባዙን በተባለው የድምፅ መሣሪያ ባዘጋጀው ከንቼርቶ ሁለተኛ ክፍል ላይ የሚሰማው አእምሮ ውስጥ ተቀርፆ የሚቀር የባዙን ቃና ጥልቅ ስሜት ሊቀሰቅስ ይችላል። ከጃፓን ሻኩሃቺ ዋሽንት የሚወጣው አንጀት የሚበላ ድምፅ ልብ ውስጥ ዘልቆ ሊገባ ይችላል። የቴነር ሳክስፎን ጎርናና ድምፅ የብሉዝ ጣዕመ ዜማ በብዙዎች አእምሮ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲመላለስ ያደርጋል። በጀርመን ባንድ ውስጥ የሚሰማው ቱባ የተባለው የሙዚቃ መሣሪያ አጃቢ ድምፅ ልብን በሐሴት ይሞላል። ስትሮስ ባቀናበረው የዎልትስ ሙዚቃ ላይ የሚደመጠው ስሜትን የሚመስጥ የቫዮሊን ቃና ብዙ አድማጮች ወደ ዳንስ መድረኩ እንዲወጡ የሚያነሳሳ ነው። በኒው ዮርክ የሚገኘው የኖርዶፍ ሮቢንስ የሙዚቃ ሕክምና ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ክላይቭ ኢ ሮቢንስ እንዳሉት ከሆነ እንዲህ ዓይነት ተጽዕኖዎች የሚፈጠሩት “ሙዚቃ ለመላው የሰው ዘር የሚናገር” በመሆኑ ነው።
የኖታዎች ቅንብር፣ ቅንብር የሌላቸው ኖታዎችና ጣዕመ ዜማ
የኖታዎች ቅንብር ደስ የሚሉ ድምፆች ያሉት ሲሆን ቅንብር የሌላቸው ኖታዎች የሚፈጥሩት ድምፅ ግን ሸካራ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ መሠረታዊ የሙዚቃ ክፍሎች በአንዳንድ ሙዚቃዎች ላይ በጥምረት እንደሚሠራባቸው ታውቃለህ? የሚጥም ቅንብር ያለው አንድ ሙዚቃ አንተ ከምትገምተው በላይ በርከት ያሉ ያልተቀናበሩ ኖታዎችን ያቀፈ ሊሆን ይችላል። የኖታዎች ቅንብርና ቅንብር የሌላቸው ኖታዎች በጥምረት ሲሠራባቸው አብዛኛውን ጊዜ ልብ የማንለውን ስሜትን ወሰድ መለስ የሚያደርግ ሁኔታ በውስጣችን ይፈጥራሉ። ይህ ጉልህ ያልሆነ የስሜት መዋዠቅ መንፈስን የሚያረጋጋ ሲሆን ቅንብር በሌላቸው ኖታዎች ላይ ብቻ የተመሠረተ ሙዚቃ ግን ጥቁር ድንጋይን ወይም ሰሌዳን በጥፍር ሲጢጥ የማድረግ ያህል የሚረብሽ ወይም መጥፎ ስሜት የሚፈጥር ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሙዚቃ በኖታዎች ቅንብር ላይ ብቻ የተመሠረተ ከሆነ አሰልቺ ሊሆን ይችላል።
ጣዕመ ዜማ ተከታታይ የሆኑ ነጠላ ኖታዎች ጣዕም ባለው መንገድ ተቀናብረው የሚፈጥሩት የሙዚቃ ዓይነት ነው። አንዳንድ የመረጃ ጽሑፎች እንደሚሉት ከሆነ ጣዕመ ዜማ ተብሎ የተተረጎመው ሜሎዲ የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል “መዝሙር” የሚል ትርጉም ካለው ሜሎስ ከተባለው የግሪክኛ ቃል የመጣ ነው። መዝገበ ቃላት በሚሰጡት ፍቺ መሠረት ጣዕመ ዜማ የሚጥም ቃና ያለው ጣፋጭ ሙዚቃ ማለት ነው።
ይሁን እንጂ ተከታትለው የሚወጡ ድምፆች ሁሉ ጣፋጭ ዜማ ይፈጥራሉ ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል ተከታታይ በሆኑ ኖታዎች መካከል ሰፊ የሆኑ የርቀት በይኖች (intervals) ተደጋግመው በሚመጡበት ጊዜ ጣዕመ ዜማው የሚጥም ዓይነት ሳይሆን ስሜት የሚቀሰቅስ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ተከታታይ በሆኑ ኖታዎች መካከል ሰፊ የርቀት በይኖች እምብዛም በማይኖሩበት ጊዜ ደስ የሚል ጣዕመ ዜማ ሊፈጠር ይችላል። ኖታዎቹና የርቀት በይኖቹ የሚቀናበሩበት መንገድ የተለያየ መሆኑ አንድ ጣዕመ ዜማ ኀዘን ውስጥ የሚከት ወይም የሚያስደስት እንዲሆን ያደርገዋል። ልክ እንደ ኖታዎች ቅንብር ሁሉ ጣዕመ ዜማም ድምፁ ሲወጣና ሲወርድ ወይም ደግሞ የኖታው ድምፅ ከፍና ዝቅ ሲል በስሜታችን ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ስሜትን ውጥረት ውስጥ የመክተትና መልሶ ዘና የማድረግ ሁኔታ ይፈጥራል።
እነዚህ መሠረታዊ የሙዚቃ ክፍሎች በሙሉ በሚዋሃዱበት ጊዜ ስሜታችንን የሚያነቃቃ ወይም ደግሞ መንፈሳችንን የሚያረጋጋ ከፍተኛ ኃይል ይፈጥራሉ። ይህ የሚሆነው አንጎላችን ሙዚቃን የሚለይበትና የሚያስተናግድበት መንገድ የተለያየ በመሆኑ ነው።
ሙዚቃና አንጎል
አንዳንዶች ቋንቋና አስተሳሰብ በአብዛኛው ግንኙነት ያላቸው ከአንጎላችን የግራ ክፍል ጋር ሲሆን ሙዚቃ ግን የሚስተናገደው ብዙውን ጊዜ ከስሜት ጋር ግንኙነት ባለው በቀኝ የአንጎላችን ክፍል እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ትክክል ሆነም አልሆነ ሙዚቃ አድማጮች በደመ ነፍስ አንድ ዓይነት ምላሽ እንዲያሳዩ እንደሚያደርግ የታወቀ ነው። ፐርሴፕችዋል ኤንድ ሞተር ስኪልስ የተባለው መጽሔት ይህን ሁኔታ በዚህ መልኩ ገልጾታል:- “ሙዚቃ ፈጣንና ውጤታማ በሆነ መንገድ ስሜት የመቀስቀስ ኃይል አለው። ስሜትን በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ለመግለጽ ብዙ ዐረፍተ ነገሮች መጠቀም የሚያስፈልግ ሲሆን . . . በሙዚቃ ግን በአንድ የመክፈያ መስመር ውስጥ በሚገኙ ጥቂት የሙዚቃ ምቶች ወይም በአንድ ኅብረ ድምፅ ሊገለጽ ይችላል።”
በማየትና በመስማት መካከል ስላለው መስተጋብር እንዲሁም ለእያንዳንዳቸው የምንሰጠውን ምላሽ በተመለከተ ሚውዚክ ኤንድ ዘ ማይንድ የተባለው መጽሐፍ የሚከተለውን ትኩረት የሚስብ አስተያየት ሰጥቷል:- “መስማት ያለው ስሜት የመቀስቀስ ኃይል ማየት ካለው ስሜት የመቀስቀስ ኃይል የበለጠ ነው። . . . ምንም ድምፅ የማያሰማን የቆሰለ እንስሳ ወይም የታመመ ሰው መመልከት የተመልካቹን ስሜት ብዙም ላይነካ ይችላል። መጮህና ማቃሰት ከጀመሩ ግን ብዙውን ጊዜ የተመልካቹ ስሜት በእጅጉ ይነካል።”
ሙዚቃ፣ የዘፈን ግጥሞችና አንተ
አንዳንዶች አንድ ሙዚቃ በሁሉም አድማጮች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አንድ ዓይነት ነው የሚል እምነት አላቸው። ይሁን እንጂ ሌሎች ደግሞ አንድ ሰው ለአንድ ጣዕመ ዜማ ወይም ዘፈን የሚሰጠው ምላሽ ግለሰቡ በወቅቱ ያለውን ስሜት ወይም ደግሞ ቀደም ሲል የገጠመውን ነገር የሚጠቁም ነው ይላሉ። ለምሳሌ የሚወደውን ሰው በሞት ያጣ ግለሰብ በአንድ የአምልኮ ሥፍራ አንድ መዝሙር ይሰማ ይሆናል። መዝሙሩ ትዝታ ሊቀሰቅስበትና ሐዘን ውስጥ ሊከትተው አልፎ ተርፎም ዓይኖቹ እንባ ሊያቀርሩ ይችላሉ። ይህ ሁኔታ ያልገጠማቸው ሌሎች ሰዎች ግን ያንኑ መዝሙር ከልብ በመነጨ የደስታ ስሜት ሊዘምሩ ይችላሉ።
ቀደም ሲል ስለ ፍሬንች ሆርንና ስለ ትራምፔት የተሰጠውን መግለጫም ወደ አእምሮህ ልታመጣ ትችላለህ። ፍሬንች ሆርን የሚያስተክዝ ድምፅ ያለው መሣሪያ ነው በሚለው አባባል አትስማማ ይሆናል። ምናልባት ለአንተ ድምፁ በጣም ሞቅ ያለ ወይም ደግሞ የሚያስደስት ሊሆን ይችላል። በአንጻሩ ግን ትራምፔት ጥልቅ ስሜት ውስጥ የሚከት ሆኖ ሊታይህ ይችላል። ሙዚቃ በእያንዳንዳችን ውስጥ የራሳችን የሆነ የተለየ የስሜት ምንጭ እንዲፈልቅ ያደርጋል፤ በመሆኑም ሁላችንም በራሳችን መንገድ ምላሽ እንሰጣለን።
ሙዚቃ ቃላት ወይም ሐሳቦች ስሜትን እንዲነኩ ለማድረግ ይረዳል። ይህም በመሆኑ ያለ ሙዚቃ አጃቢነት የሚቀርብ የቴሌቪዥንም ሆነ የራዲዮ ማስታወቂያ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ብዙውን ጊዜ ቃላቱ ያን ያህል ትርጉም ያላቸው አይሆኑም። ይሁን እንጂ ማስታወቂያው ተስማሚ በሆነ ሙዚቃ ከታጀበ የአድማጮችን ስሜት በመሳብ የታለመውን ዒላማ ሊመታ ይችላል። የአብዛኛው ማስታወቂያ ዓላማ ሰዉ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ አስቦበት ሳይሆን በስሜት ተነሳስቶ እንዲገዛ ማድረግ እንደሆነ እሙን ነው!
ማስታወቂያ የሕዝቡን ኪስ ሊያራቁት የሚችል ቢሆንም እንኳ የዘፈን ግጥሞችና ሙዚቃ ያላቸው ኃይል ከዚህ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ጆርናል ኦቭ ዩዝ ኤንድ አዶለሰንስ የዘፈን ደራሲዎች በሚደጋገሙ የዘፈን ግጥሞች አማካኝነት በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የሌሎችን ሐሳብ ወደ ጎን ገሸሽ እንዲያደርጉና “ግትሮች እንዲሆኑ” ያስተምሯቸዋል ሲል ገልጿል። አንድ ሌላ ጽሑፍ እንዳለው ከሆነ “ከሄቪ ሜታል ግጥሞች ይበልጥ ግልጽ የሆኑት . . . አወዛጋቢ የሆኑ የራፕ ሙዚቃ ግጥሞች” የሚያስተላልፉት መልእክት የአድማጩን ስሜት ሊቆጣጠርና ፀረ ማኅበራዊ ምግባር እንዲያንጸባርቅ ሊያደርገው ይችላል።
አንድ ሰው ለግጥሞቹ ጆሮውን ሳይሰጥ ሙዚቃውን ብቻ ቢሰማ አፍራሽ ተጽዕኖዎቹን ማስወገድ ይችላል? በአብዛኛው የሄቪ ሜታልና የራፕ ሙዚቃ ግጥሞችን መስማት አስቸጋሪ እንደሆነ የታወቀ ነው። እንዲያውም ብዙውን ጊዜ ከልክ በላይ በሚጮኸው ሙዚቃ ይዋጣሉ። ሆኖም ቃላቱ ተሰሙም አልተሰሙ መልእክቱ በኃይለኛ ምቱና በሚደጋገመው ዜማ መስተጋባቱ አይቀርም!
እንዴት? አንዳንዶቹ የዘፈን ርዕሶች ራሳቸው ምናባዊ ምስል ይፈጥራሉ። ከዚህም በተጨማሪ ብዙውን ጊዜ የሙዚቃው ዓይነት የራሱ የሆነ መልእክት ይኖረዋል። የሚተላለፈው መልእክት ምንድን ነው? አንድ የወጣቶች መጽሔት “መልእክቱ በአእምሮ ውስጥ የበላይነትን፣ አንድ ነገር የማከናወን ብቃትንና ወሲባዊ ድልን የሚቀርጽ ይመስላል” ብሏል። አንድ ሌላ መጽሔት ደግሞ “መሠረታዊዎቹ ጭብጦች . . . ከባድ ዓመፅ፣ የኃይል ድርጊት፣ አደገኛ ዕፆችን መውሰድና የአልኮል መጠጦችን አላግባብ መጠቀም፣ ልቅ የሆነ ወሲብ፣ ሴሰኝነትና ሰይጣናዊ እምነት ናቸው” ሲል ገልጿል።
አንዳንድ ወጣቶች ይህ እውነት ሊሆን ቢችልም እንኳ በእነሱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደማያሳድር ይናገራሉ። እንዲህ ዓይነቱ ሙዚቃ ‘የራሳቸውን ማንነት እንዲያውቁ’ የሚረዳቸው በመሆኑ ጠቃሚ እንደሆነ አድርገው ይሟገቱ ይሆናል። በእርግጥ ሊረዳቸው ይችላል? ጆርናል ኦቭ ዩዝ ኤንድ አዶለሰንስ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በትምህርት ቤት ብቁ እንዳልሆኑ ሲነገራቸው የዋሉ ሰነፍ ልጆች ምሽት ላይ ቁጣ፣ የከረረ ተቃውሞና ኃይል የሚንጸባረቅባቸውን የሄቪ ሜታል ሙዚቃዎች መስማት ሊያስደስታቸው ይችላል።” አክሎም እንዲህ ይላል:- “የሚገርመውና እንቆቅልሽ የሆነው ነገር እነዚህ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ይበልጥ አስተማማኝና እውነተኛ የሆነውን ማንነታቸውን ለማወቅ የሚጥሩት ሕዝባዊና የጋራ ሐሳብ መግለጫ የሆነውን መሣሪያ በመጠቀም መሆኑ ነው። ብቻቸውን ሲሆኑ በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ገጠመኞችን እንደመሻት በንግዱ ኢንዱስትሪ ተቀርጸው የቀረቡ ጽንሰ ሐሳቦችን ለማግኘት ይጥራሉ።” በሌላ አነጋገር እነዚህ ወጣቶች ምን ማሰብ እንዳለባቸውና ምን ዓይነት ስሜት ሊሰማቸው እንደሚገባ የሚነግራቸው ሌላ ሰው ነው ማለት ነው።
እስቲ የሮክ ኮንሰርቶችን እንመልከት። በእነዚህ ኮንሰርቶች ላይ በሚገኙ በርካታ ሰዎች ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምንድን ነው? ሚውዚክ ኤንድ ዘ ማይንድ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል መልሱን ይሰጣል:- “ሙዚቃ የብዙ ሰዎችን ስሜት በከፍተኛ ሁኔታ በማቀጣጠልና ይህ ስሜት በተናጠል ሳይሆን በአንድነት እንዲጋጋል በማድረግ በሚገባ የማገናዘብ ችሎታን ሊያሳጣ ይችላል። እንዲሁ በጭፍን በወቅቱ ላለው ስሜት እጃቸውን ይሰጣሉ። ይህ ደግሞ ብዙ ሆነው አንድ ላይ በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ በአብዛኛው የሚንጸባረቅ አደገኛ ጠባይ ነው።” በሮክ ኮንሰርቶች ላይ የሚታዩት አንዳንድ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ምግባሮች የዚህን አባባል እውነተኛነት ያረጋግጣሉ።
እንግዲያው አእምሮንና ልብን ከብክለት ለመጠበቅ በሙዚቃ ምርጫችን ረገድ በጣም ጠንቃቆች መሆን አለብን። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የመደምደሚያው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙውን ጊዜ ሙዚቃ አድማጮችን ለጭፈራ ያነሳሳል