ለሙዚቃ ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ
በዛሬው ጊዜ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በብዙ ቢልዮን የሚቆጠር ዶላር የሚዛቅበት ንግድ ሆኗል። ዝነኛ ሙዚቀኞችና አጋፋሪዎቻቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ያፍሳሉ። ይሁንና እጅግ የተዋጣላቸው አንዳንድ ሙዚቀኞች ደስታ የሌላቸው ከመሆናቸውም በላይ ሕይወታቸው በአጭሩ ሲቀጠፍና የራሳቸውን ሕይወት በራሳቸው ሲያጠፉ ይታያሉ። በተጨማሪም አንዳንዶቹ ሙዚቃዎች ሥነ ምግባርን፣ ስሜትንና መንፈሳዊነትን የሚያቆሽሹ ከመሆናቸውም ሌላ የጠበኝነት መንፈስ ወደ ማንጸባረቅና ፀረ ማኅበራዊ ምግባር ወደ መፈጸም ሊመሩ እንደሚችሉ በሚገባ ታይቷል።
ይሁን እንጂ ለሙዚቃ ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። በዚህ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ከግብረ ገብ ውጪ የሆኑና ጎጂ የሆኑ በርካታ ነገሮች ቢኖሩም አንዳንዶቹ ሙዚቃዎች የአንድን ሰው ሕይወት ሊያበለጽጉና በተወሰነ ደረጃ ደስታና እርካታ ሊያስገኙለት ይችላሉ። በስሜትና በመንፈሳዊ ሊያነቃቃን ይችላል። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎች እንመልከት።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት 150 መዝሙራት ውስጣዊ ስሜትን የሚገልጹ ግጥሞችን፣ ቅዱስ መዝሙሮችንና ጸሎቶችን አካትተው የያዙ ምርጥ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ውጤቶች ናቸው። በዛሬው ጊዜ በመቶ በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ለሚያነቧቸው ሰዎች የደስታ ምንጭ ሆነዋል። ይሁን እንጂ የጥንቶቹ ዕብራውያን እነዚህን መዝሙራት ማንበብ ብቻ ሳይሆን ይዘምሯቸውም ነበር። ብዙውን ጊዜ እነዚህን መዝሙሮች ይዘምሩ የነበረው ጣዕም ባለው ሙዚቃ በመታጀብ ነበር። ይህም በቃሉ ውስጥ ያለውን የአምላካቸውን የይሖዋ ጥበብና የተካኑ ሙዚቀኞች በአድማጮቻቸው ላይ የሚያሳድሩትን ስሜት ለማጣመር የሚያስችል ነበር። መዝሙሮቹ በጣም ተራና ኋላ ቀር አልነበሩም። የዕብራይስጥ ሙዚቃ የነበረው ጥራትና ስልት በዘመኑ በአካባቢው አገሮች ከነበረው የሙዚቃ ደረጃ በእጅጉ የላቀ ነበር።
ከጊዜ በኋላ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችም አምላክን ለማወደስና የስሜት ውጥረትን ለማስወገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑትን መዝሙራትና ሌሎች ቅዱስ መዝሙሮችን ይዘምሩ ነበር። በዚህ መንገድ ሙዚቃ ሕይወታቸውን ሊያበለጽግላቸው ችሏል። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መዝሙሮችን በመዘመር ሕይወታቸውን ለመምራት በጣም አስፈላጊ የሆነው የአምላክ ቃል በልባቸው ውስጥ ይበልጥ ሥር እንዲሰድ ማድረግ ችለዋል።—ማቴዎስ 26:30፤ ሥራ 16:25
የጥንቶቹ ግሪኮች ሙዚቃ የሰውን ስብዕና እንደሚያዳብርና አንድን ወንድ ወይም አንዲትን ሴት ይበልጥ የተሟላ እንደሚያደርጋቸው ያምኑ ነበር። ሳይንስ፣ ኢኮኖሚክስና ሎጂክ መማርን አጥብቆ በሚያበረታታው በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ዓለም በኪነ ጥበብ ዘርፍ ስሜታዊውን የስብዕና ክፍል የማዳበሩ ጉዳይ ብዙውን ጊዜ ችላ ሲባል ይታያል።
ሚዛናዊ ሁን
አንድ ጥሩ ሙዚቃ መስማት ጠቃሚና አስደሳች ሊሆን ይችላል። ሆኖም አንድ ሰው የሙዚቃ መሣሪያ በመጫወት ወይም ደግሞ ከጓደኞቹ ጋር በቡድን ሆኖ በመዘመር የበለጠ ደስታ ሊያገኝ ይችላል። የሙዚቃ እውቀት እውነተኛ ደስታ የሚገኝበት ሰፊ መስክ ሊከፍት ይችላል።
እርግጥ ነው፣ እንደ ሌሎቹ ጥሩ የሕይወት ዘርፎች ሁሉ በዚህ የመዝናኛ መስክም ልከኛ መሆን፣ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መጠቀምና መራጭ መሆን ያስፈልጋል። ይህ በምንመርጠው የሙዚቃ ዓይነት ብቻ ሳይሆን ሙዚቃ በመስማት ወይም በመጫወት በምናሳልፈው ጊዜ መጠን ረገድም ይሠራል።
አንድ የሙዚቃ ዓይነት በስሜትህ፣ በድርጊቶችህና ከሌሎች ጋር ባለህ ዝምድና ረገድ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደር ከጀመረ ሌላ የሙዚቃ ስልት ምረጥ። ስሜትህን ብሎም ልብህንና አእምሮህን ለመጠበቅ ትችል ዘንድ ጆሮህን ጠብቅ!
በተለይ ግጥሞቹን በተመለከተ እንዲህ ማድረግህ በጣም አስፈላጊ ነው። ስለ ሕይወትና ስለ ሥነ ምግባር አቋም ከአንተ የተለየ አመለካከት ካላቸውና አምላካዊ ያልሆነና ብልሹ የአኗኗር ዘይቤ ከሚያራምዱ ሰዎች ምኞት ጋር በሚስማማ መንገድ ቀስ በቀስ ሊቀርጹህ ይችላሉ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የዘፈኑ ርዕስ እንኳ መጥፎ ዓይነት ስሜት ሊቀሰቅስ ይችላል።
የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉ ‘ሰውነታቸውን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት አድርገው እንዲያቀርቡ’ አጥብቆ የሚመክር ሲሆን ይህም ‘በማመዛዘን ችሎታቸው ተጠቅመው የሚያቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት’ እንደሆነ ይገልጻል። (ሮሜ 12:1 NW) ስሜታችን የዚህ ‘ሕያው መሥዋዕት’ ክፍል እንደሆነ የታወቀ ነው። ስለዚህ ሙዚቃ በሚያሳድረው ኃይል ሳቢያ ስሜታችን ጥንቃቄ የታከለበትን የማመዛዘንና የማሰብ ችሎታችንን ማዛባትና ድርጊታችን መስመሩን እንዲስት ማድረግ ከጀመረ ሙዚቃ በመስማት ልማዳችን ረገድ አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ ይኖርብናል። ሙዚቃ ያለው ኃይል በልብህና በአእምሮህ ላይ በጎም ሆነ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አትዘንጋ!
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የመማር ችሎታን ማጎልበት
“የኖታዎች ቅንብር ያለውን ሙዚቃ አዘውትሮ የሚሰማ ሕፃን የመማር ችሎታው ሊጎለብት እንደሚችል የተካሄደው ጥናት አመልክቷል። ሆኖም በብዙዎቹ ቤተሰቦች ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ለዚህ አልታደሉም።”—ኦዲዮ፣ መጋቢት 1999