የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 10/8 ገጽ 12-15
  • ከጠበቅሁት በላይ የሆኑ ነገሮች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከጠበቅሁት በላይ የሆኑ ነገሮች
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መና ያልቀረ ፍለጋ
  • በኔዘርላንድ ያከናወንነው አገልግሎት
  • በአዲሱ ምድባችን ማገልገል
  • ያገኘኋቸው ትምህርቶች
  • እንድንቀጥል የረዳን ነገር
  • “ይሖዋን ማገልገል እፈልግ ነበር”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • ብቸኛ ብሆንም ሕይወቴ ከንቱ አልነበረም
    ንቁ!—1998
  • በጥድፊያ ስሜት ማገልገል
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ይሖዋ ፈቃዱን እንዳደርግ አስተምሮኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 10/8 ገጽ 12-15

ከጠበቅሁት በላይ የሆኑ ነገሮች

ቫይለም ቫን ሴይል እንደተናገረው

ጊዜው 1942 ሲሆን አገራችን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ትታመስ ነበር። በኔዘርላንድ ግሮኒንገን ከተማ ውስጥ ከናዚዎች ተደብቀው ከነበሩት አምስት ወጣቶች መካከል አንዱ ነበርኩ። በአንዲት ትንሽ ክፍል ውስጥ ተቀምጠን በሕይወት መትረፍ የምንችልበት አጋጣሚ ምን ያህል እንደሆነ መወያየት ጀመርን።

በሕይወት ለመትረፍ የነበረን አጋጣሚ የተመናመነ መሆኑ ግልጽ ነበር። በኋላ እንደታየውም ከመካከላችን ሦስቱ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ። እንዲያውም የሽምግልና ዕድሜ ላይ ለመድረስ የበቃሁት እኔ ብቻ ነኝ። ይሁንና ይህ ከጠበቅሁት በላይ ሆነው ካገኘኋቸው ነገሮች መካከል አንዱ ብቻ ነው።

ከላይ የተጠቀሰው ሁኔታ በተፈጸመበት ወቅት ገና የ19 ዓመት ወጣት የነበርኩ ሲሆን ስለ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ስለ ሃይማኖት የማውቀው ነገር አልነበረም። እንዲያውም አባቴ ሃይማኖት የሚባል ነገር አይዋጥለትም ነበር። እናቴ ደግሞ እውነተኛውን ሃይማኖት ለማግኘት ያደረገችው ጥረት ወደ መናፍስት አምልኮ መርቷት ነበር። እኔ ምንም ተስፋ አልነበረኝም። በቦምብ ድብደባ ወቅት ወይም በአንድ በሆነ መንገድ ሕይወቴ ቢጠፋ አምላክ እኔን የሚያስብበት ምንም ምክንያት የለውም ብዬ አስብ ነበር። ሌላው ቢቀር ስለ እሱ ለመማር እንኳ አልሞከርኩም ነበር።

መና ያልቀረ ፍለጋ

ከአራቱ ወጣቶች ጋር ከላይ ያለውን ውይይት ካደረግን ከአጭር ጊዜ በኋላ በናዚዎች ተይዤ በጀርመን ኢመሪክ አቅራቢያ ወደሚገኝ አንድ የእስር ቤት ካምፕ ተወሰድኩ። ሥራችን በኅብረ ብሔሩ የቦምብ ድብደባ የፈራረሰውን ማጽዳትንና የደረሰውን ጉዳት መጠገንን ያካተተ ነበር። በ1943 ማብቂያ ላይ አመለጥኩና የተፋፋመ ጦርነት እየተካሄደ የነበረ ቢሆንም ወደ ኔዘርላንድ ተመለስኩ።

እንዴት እንደሆነ ባላውቅም በጥያቄዎችና በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተሞላች አንዲት ትንሽ ቡክሌት አገኘሁ። በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን መዳን (እንግሊዝኛ) የተሰኘውን መጽሐፍ ለማጥናት የተዘጋጀች ነበረች። ጥያቄዎቹን ካነበብኩና ጥቅሶቹን ከተመለከትሁ በኋላ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ የማወቅ ጥልቅ ፍላጎት አደረብኝ።

ስላነበብኩት ነገር ለእጮኛዬ ለክሬ ብነግራትም መጀመሪያ ላይ ብዙም ፍላጎት አልነበራትም። በሌላ በኩል ግን እናቴ በቡክሌቷ ተማርካ ነበር። “በሕይወቴ ሙሉ ስፈልገው የነበረው እውነት ይህ ነው!” ስትል በደስታ ተናገረች። ለወዳጆቼም ነግሬያቸው የነበረ ሲሆን አንዳንዶቹ የበለጠ የማወቅ ፍላጎት አድሮባቸው ነበር። እንዲያውም አንዱ የይሖዋ ምሥክር የሆነ ሲሆን በ1996 እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ደብዳቤ እንጻጻፍና እንጠያየቅ ነበር።

ከጊዜ በኋላ ክሬ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረችና ሁለታችንም የካቲት 1945 ላይ ተጠመቅን። ጦርነቱ ከጥቂት ወራት በኋላ አቆመ። ከተጋባን በኋላ አቅኚዎች ማለትም የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ለመሆን ፈለግን። ሆኖም የጤናና የገንዘብ ችግሮች ነበሩብን። በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ገንዘብ የምናገኝበት አጋጣሚም ተከፍቶልን ነበር። አቅኚነትን ከመጀመራችን በፊት የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ እናጠራቅም ወይስ አቅኚነቱን አሁኑኑ እንጀምር?

በኔዘርላንድ ያከናወንነው አገልግሎት

በቀጥታ ወደ አቅኚነት አገልግሎት ለመግባት በመወሰን መስከረም 1, 1945 ላይ አቅኚዎች ሆነን ማገልገል ጀመርን። በዚያን ዕለት ምሽት ላይ ወደ ቤት ስመለስ የሆነ ነገር ለመጠጣት ወደ አንድ ቡና ቤት ጎራ አልኩ። ለአስተናጋጁ የአንድ ጉልደን ኖት ነው ብዬ ያሰብኩትን አውጥቼ ሰጠሁትና “መልሱን ለራስህ አስቀረው” አልኩት። የሰጠሁት የ100 ጉልደን ኖት መሆኑን የተገነዘብኩት ወደ ቤት ከተመለስኩ በኋላ ነበር! በመሆኑም የአቅኚነት አገልግሎት ስንጀምር የነበረን አንድ ጉልደን ብቻ ነበር!

በ1946 መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሕዝብ ንግግሮች መስጠት ስጀምር የነበረኝ አንድ የቆዳ ጃኬት ብቻ ነበር። ከእኔ ጋር ብዙም የማንበላለጥ አንድ ጓደኛዬ የስብሰባው ሊቀ መንበር ሆኖ ነበር። የእኔን ንግግር ካስተዋወቀ በኋላ በፍጥነት ወደ መድረኩ ጀርባ ይመጣና ኮቱን ይሰጠኛል። ከዚያ ንግግሬን አቀርባለሁ። ንግግሩ ሲያበቃ ደግሞ መልሰን እንለዋወጥ ነበር!

በመጋቢት 1949 እኔ እና ክሬ የወረዳ ሥራ እንድንሠራ ጥሪ ቀረበልን፤ ይህም የተለያዩ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎችን በመጎብኘት የወንድሞችን መንፈሳዊነት ማጎልበት የሚጠይቅ ነበር። በጦርነቱ ወቅትም ሆነ ከዚያ በፊት በታማኝነት ያገለገለው ፍሪትስ ሃርትስታንግ ለወረዳ ሥራ ሥልጠና ሰጠኝ። ጥሩ ምክርም ለገሰኝ:- “ቪም፣ ምንም እንኳ መጀመሪያ ላይ የተሻለ መስሎ ባይታይህም በይሖዋ ድርጅት በኩል የሚሰጥህን መመሪያ ተከተል። በፍጹም አትጸጸትም።” ፍሪትስ ትክክል ነበር።

በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ናታን ኤች ኖር በ1951 ኔዘርላንድን ጎብኝቶ ነበር። በዚያን ጊዜ እኔ እና ክሬ በዩናይትድ ስቴትስ የሚሰጠውን የሚስዮናዊነት ሥልጠና ለማግኘት አመለከትን። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በ21ኛው ክፍል ገብተን እንድንሠለጥን ግብዣ ቀረበልን። በ1945 አቅኚነት ስንጀምር በኔዘርላንድ 2,000 የሚሆኑ ምሥክሮች የነበሩ ሲሆን በ1953 ግን ቁጥራቸው አድጎ ከ7,000 በላይ ሆኖ ነበር። ይህም ከጠበቅነው በላይ ሆነው ካገኘናቸው ነገሮች መካከል አንዱ ነው!

በአዲሱ ምድባችን ማገልገል

በአሁኑ ጊዜ የኢንዶኔዢያ ግዛት በሆነችው በደች ኒው ጊኒ እንድናገለግል ተመድበን የነበረ ቢሆንም የመግቢያ ፈቃድ በመከልከላችን ምድባችን ተቀይሮ በደቡብ አሜሪካ ወደምትገኘው ሱሪናም ወደምትባለው ሞቃታማ አገር ተላክን። እዚያም ታኅሣሥ 1955 ደረስን። በወቅቱ በሱሪናም የነበሩት ምሥክሮች ከመቶ የማይበልጡ ቢሆኑም ለመርዳት ዝግጁዎች ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ በጣም ተላመድን።

ከብዙ የተለያዩ ሁኔታዎች ጋር ራሳችንን ማለማመድ የነበረብን ከመሆኑም በላይ እንዲህ ማድረጉ አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል ክሬ እግርና ክንፍ ያሏቸው ፍጥረታት ሁሉ ያስፈሯት ነበር። ኔዘርላንድ በነበርንበት ጊዜ በመኝታ ቤታችን ውስጥ አንዲት ትንሽ ሸረሪት ካለች እኔ እስከምገድላት ድረስ አትተኛም ነበር። ይሁንና ሱሪናም ውስጥ በአሥር እጥፍ የሚበልጥ መጠን ያላቸውና መርዘኛ የሆኑ ሸረሪቶች አሉ! ከዚህም በላይ በሚስዮናውያን መኖሪያ ቤታችን በረሮዎች፣ አይጦች፣ ጉንዳኖች፣ የወባ ትንኞችና ፌንጣዎች ጭምር ነበሩ። እባቦች ሳይቀር ይጎበኙን ነበር። ክሬ እነዚህን ከመሳሰሉ ፍጥረታት ጋር ከመላመዷ የተነሳ እነሱን ለማጥፋት የምታደርገው ጥረት የዕለት ተለት ተግባሯ ሆኗል።

ከ43 ዓመታት ቆይታ በኋላ በአሁኑ ጊዜ ከብዙዎቹ የአገሬው ተወላጆች ይበልጥ እኛ አገሩን በደንብ እናውቀዋለን ለማለት ይቻላል። ለወንዞቹ፣ ለደኖቹና በባሕር ዳርቻ ለሚገኙት ረግረግ ቦታዎች ፍቅር አድሮብናል። በተጨማሪም በርካታ የእንስሳት ዓይነቶችን ማለትም ጃርቶችን፣ ስሎዝ የሚባሉ እንስሳትን፣ ጃግዋሮችንና ደስ የሚል ቀለም ያላቸውን የተለያዩ የእባብ ዘሮች ሳይቀር ማየት ችለናል። ሆኖም ይበልጥ አስደሳች ሆነው ያገኘናቸው የተለያየ ዘር ያላቸውን የአገሪቱን ነዋሪዎች ነው። የአንዳንዶቹ ቅድመ አያቶች ከአፍሪካ እንዲሁም ከሕንድ፣ ከኢንዶኔዥያ፣ ከቻይናና ከሌሎች አገሮች የመጡ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ነዋሪዎች ዝርያዎች የሆኑ የአሜሪካ ህንዶች ናቸው።

በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ወደ የቤታቸው ስንሄድ እነዚህን ከመሳሰሉ ሰዎች ጋር እንገናኛለን። በመንግሥት አዳራሾቻችንም ከተለያዩ ዘሮች የተውጣጡ ደስ የሚሉ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች አሉ። አንድ ደሳሳ የመንግሥት አዳራሽ ብቻ ከነበረበት ከ1953 አንስቶ ከ30 በላይ የሚሆኑ ማራኪ የመንግሥት አዳራሾች፣ አንድ ውብ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽና በየካቲት 1995 ለይሖዋ አገልግሎት የተወሰነ ግሩም የቅርንጫፍ ቢሮ እስከተገኘበት ጊዜ ድረስ የታየውን እድገት መመልከት ችለናል።

ያገኘኋቸው ትምህርቶች

በሱሪናም ውስጥ በባርነት ከሚሠሩባቸው የእርሻ ቦታዎች አምልጠው በወንዞች አካባቢ ኑሯቸውን የመሠረቱ የአፍሪካውያን ባሮች ዝርያዎች የሆኑ ቡሽ ኔግሮዎች የሚባሉ ሰዎች ያሉባቸው ጉባኤዎች አሉ። ችሎታቸውንና ጥንካሬያቸውን የሚያሳዩ አስገራሚ ነገሮች በተደጋጋሚ ተመልክቻለሁ። ለምሳሌ ያህል ወንዙን ለመጓጓዣነት የሚጠቀሙበት መንገድና ደኑን መኖሪያቸው ማድረጋቸው ያስገርመኛል። ዛፍ ይቆርጣሉ፣ ጀልባ ይሠራሉ፣ እንዲሁም በፏፏቴዎችና በፈረሰኛ ውኃ ላይ ይቀዝፋሉ። ምግባቸውን የሚያገኙት በማደንና ዓሣ በማጥመድ ሲሆን የሚያበስሉበት ዘመናዊ መሣሪያ የላቸውም። ለእኛ አስቸጋሪ የሚሆኑብንን ሌሎች በርካታ ነገሮችም ይሠራሉ።

ባለፉት ዓመታት በሱሪናም የሚኖሩ የሌሎች ሕዝቦችንም ባሕል፣ አስተሳሰብና የአኗኗር ሁኔታ ለማወቅ ችለናል። በ1950ዎቹ የአሜሪካ ህንዳውያን ወደሚኖሩበት አንድ መንደር የሄድኩበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። ወደ ሥፍራው ከሚወስደኝ አንድ ህንዳዊ ሰው ጋር በጀልባ ጉዞ ወደምንጀምርበት በደኑ መካከል ወደሚገኝ አንድ የተተወ ካምፕ የደረስነው እኩለ ሌሊት ላይ ነበር። እሳት አነደደ፣ የምንበላውን ምግብ አበሰለ፣ እንዲሁም ጫፍና ጫፉ ታስሮ በአየር ላይ የሚንጠለጠል እንደ አልጋ የሚያገለግል ጨርቅ አዘጋጀ። እኔ ምንም ማድረግ እንደማልችል ስለሚያውቅ ሁሉንም ነገር እሱ በማድረጉ ምንም አልተከፋም።

እኩለ ሌሊት ላይ ከተኛሁበት ስወድቅ ምንም አልሳቀም። ከዚያ ይልቅ ከልብሴ ላይ ቆሻሻውን አራገፈልኝና ጨርቁን እንደገና አሰረልኝ። ጠባብ በሆነ ወንዝ ላይ ስንጓዝ የገዛ እጆቼን መመልከት እስኪሳነኝ ድረስ በጣም ጨልሞ የነበረ ቢሆንም እሱ ግን በርካታ መታጠፊያዎችንና እንቅፋቶችን ያለ ምንም ችግር እየለየ ጀልባዋን ይቀዝፍ ነበር። እንደዚያ ሊያደርግ የቻለው እንዴት እንደሆነ በጠየቅሁት ጊዜ እንዲህ አለ:- “የምትመለከትበት አቅጣጫ ትክክል አይደለም። ቀና በልና በዛፎቹ ጫፍና በሰማዩ መካከል ያለውን ልዩነት ተመልከት። በወንዙ ላይ ያለውን መታጠፊያ ያመለክትሃል። ጎንበስ በልና ደግሞ ትናንሽ ሞገዶችን ተመልከት። ከፊት ለፊትህ አለት ወይም ሌላ እንቅፋት መኖሩን ይጠቁሙሃል። እንዲሁም አዳምጥ። የምትሰማቸው ድምፆችም ከፊትህ ምን እንዳለ ለማወቅ ሊረዱህ ይችላሉ።”

ከእንጨት ተቦርቡረው በተሠሩ ጀልባዎች መጓዝ፣ ፈረሰኛ ውኃን ማቋረጥና ፏፏቴዎችን ማለፍ አደገኛም አድካሚም ነው። ሆኖም ጉዞው አብቅቶ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሞቅ ባለ ወዳጅነት ሲቀበሉን መንፈሳችን ይታደስ ነበር። ለእንግዶች የሚሆን ምግብ ሌላው ቢቀር አንድ ሳህን ሾርባ አይጠፋም ነበር። ሚስዮናዊ ሕይወታችን ተፈታታኝና አስቸጋሪ የሆነባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ሚስዮናዊ በመሆናችን ተቆጭተን አናውቅም።

እንድንቀጥል የረዳን ነገር

የተሟላ ጤና ነበረን ማለት አንችልም። በተጨማሪም ከዘመዶቻችን መካከል ምሥክር የሆነችው እናቴ ብቻ ስለነበረች ከቤተሰባችን አባላት ብዙም ማበረታቻ አላገኘንም። ይሁንና የውድ ወዳጆቻችን እርዳታና ማበረታቻ በምድባችን ላይ ለመቀጠል የሚያስፈልገንን ነገር እንድናገኝ አስችሎናል። በተለይ እናቴ በጣም ታበረታታን ነበር።

በምድባችን ላይ ለስድስት ዓመታት ያህል ከቆየን በኋላ እናቴ በጠና ታመመች። ወዳጆቻችን ከመሞቷ በፊት እንድናያት ፈልገው የነበረ ቢሆንም እማማ ግን እንዲህ ስትል ጻፈችልን:- “እባካችሁ፣ እዚያው በምድብ ቦታችሁ ላይ ቆዩ። ጤነኛ እንደሆንኩ አድርጋችሁ አስቡ። በትንሣኤ እንደማያችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።” ጠንካራ እምነት ያላት ሴት ነበረች።

ለእረፍት ወደ ኔዘርላንድ መመለስ የቻልነው በ1966 ነበር። የቀድሞ ወዳጆቻችንን ለማየት በመቻላችን ብንደሰትም አሁን የትውልድ አገራችን ሱሪናም እንደሆነች ተሰምቶን ነበር። ሚስዮናውያን በምድባቸው ላይ ቢያንስ ለሦስት ዓመታት ያህል ከማገልገላቸው በፊት ለእረፍት ወደ አገራቸው እንዳይጓዙ ድርጅቱ የሚሰጠው ምክር ጥበብ ያለበት መሆኑን ከዚህ ለመገንዘብ ችለናል።

ምድባችንን እንድንወድደው ያደረገን ሌላው ነገር ደግሞ ተጫዋቾች መሆናችንና በራሳችንም ሆነ በተለያዩ ነገሮች ለመሳቅ መቻላችን ነው። ሌላው ቀርቶ በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ እንኳ ለደስታ ምክንያት የሚሆኑ አስገራሚ ነገሮች ይታያሉ። ዝንጀሮዎችና ኦተር የሚባሉ እንስሳት እንዲሁም የብዙ እንስሳት ግልገሎች የሚያደርጓቸው ነገሮች ፈገግ እንድትል ሊያደርጉህ ይችላሉ። በተጨማሪም የነገሮችን መልካም ጎን የመመልከትና ስለ ራሳችን ከልክ በላይ ከማሰብ የመራቅን አስፈላጊነት ከበርካታ ዓመታት ተሞክሮ ልንማር ችለናል።

በተለይ ፍሬያማ የሆነው የአገልግሎት ሥራችን በምድባችን ላይ እንድንቀጥል ረድቶናል። ክሬ በፓራማሪቦ በሚገኝ አንድ የአረጋውያን መጦሪያ የሚገኙ ዘጠኝ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠና ጀመር። ሁሉም ዕድሜያቸው ከ80 ዓመት በላይ ነበር። አረጋውያኑ ባላታብሊደር (ከጎማ ዛፍ ፈሳሹን የሚቀዱ) አሊያም ወርቅ ቆፋሪ ሆነው ይሠሩ የነበሩ ናቸው። ሁሉም ለተማሩት ነገር አድናቆት አድሮባቸው የተጠመቁ ሲሆን እስከ ዕለተ ሞታቸውም ድረስ በስብከቱ ሥራ በታማኝነት ተካፍለዋል።

የስዊድንቦርግ ኒው ቸርች ሰባኪ የነበሩ ሪቨርስ የሚባሉ አንድ ሽማግሌ ጥናቱን ራቅ ብለው በማዳመጥ አፍራሽ አስተያየቶች ይሰነዝሩ ነበር። ሆኖም በእያንዳንዱ ሳምንት ትንሽ ጠጋ ይሉ ነበር፤ የሚሰነዝሩትም ትችት እየቀነሰ መጣ። በመጨረሻ ከሌሎቹ ጋር ተቀምጠው መካፈል ጀመሩ። ዕድሜያቸው 92 ዓመት ነበር። ለማየትም ሆነ ለመስማት ይቸገሩ የነበረ ቢሆንም ቅዱሳን ጽሑፎችን ሲጠቅሱ ግን በቀጥታ የሚያነቡ ይመስሉ ነበር። በመጨረሻ ከእኛ ጋር በአገልግሎት በመካፈል መስማት ለሚፈልግ ሁሉ መመስከር ጀመሩ። ከመሞታቸው ከጥቂት ጊዜ በፊት እንድንመጣ መልእክት ላኩብን። እዚያ ስንደርስ ሞተው ነበር፤ ሆኖም ትራሳቸው ሥር በዚያ ወር በአገልግሎት ያሳለፉትን ሰዓት ያሰፈሩበትን ሪፖርት አገኘን።

በመሉ ጊዜ የስብከት ሥራ ከ25 ዓመታት በላይ ካሳለፍኩ በኋላ በ1970 የሱሪናም ቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብሎ መስራትን ለመልመድ ተቸግሬ ነበር። በየቀኑ ወደ መስክ አገልግሎት ትወጣ ከነበረችው ከክሬ ጋር አብሬ ለማገልገል እመኝ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ክሬም በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ መሥራት የጀመረች ሲሆን ሁለታችንም ዕድሜያችን እየገፋ በሄደበት በአሁኑ ወቅት እዚህ ሆነን የምንሠራው ትርጉም ያለው ሥራ አለን።

በእርግጥም በ1945 በዓለም ዙሪያ የነበሩትን 160,000 የማይሞሉ ንቁ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በዛሬው ጊዜ ከሚገኙት ወደ 6,000,000 የሚጠጉ አስፋፊዎች ጋር ሳወዳድር የተፈጸመው ነገር ከጠበቅሁት በላይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እንዲሁም በሱሪናም በአገልግሎቱ የሚካፈሉት ቁጥር በ1955 ወደዚህ ስንመጣ ከነበረው ወደ 100 የሚጠጋ ቁጥር ተነስቶ ከ19 እጥፍ በላይ በመጨመር በዛሬው ጊዜ ከ1,900 በላይ ሆኗል!

ለአምላክ የታመን ሆነን ከቀጠልን ወደፊት የይሖዋ ዓላማዎች ፍጻሜያቸውን እያገኙ ሲሄዱ ከዚህ የበለጠ እድገት ለማየት እንደምንበቃ እርግጠኛ ነኝ። ግባችንም የታመንን ሆነን መቀጠል ነው።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1955 ወደ ሱሪናም በመጣንበት ጊዜ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለአገልግሎት በጀልባ ስንጠቀም

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ጋር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ