በጥድፊያ ስሜት ማገልገል
በሃንስ ፋን ፈረ እንደተነገረው
በኔዘርላንድ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች ፓውል ኩሽኒር በ1962 አንድ ቀን ጠዋት በሮተርዳም ወደብ አገኘኝ። ደብዛዛ ብርሃን ባለበት በአንድ ቡና ቤት ውስጥ ቁጭ ብለን ስንጫወት ፊት ለፊት እየተመለከተኝ “ሃንስ፣ ይህንን የአገልግሎት ምድብ ብትቀበል አንተና ሚስትህ የአንድ ጉዞ ቲኬት ብቻ እንደምትቀበሉ ገብቶሃል?” አለኝ።
“አዎን፣ ሱዝም በዚህ እንደምትስማማ እርግጠኛ ነኝ።”
“ጥሩ ነው። እንግዲያው ከሱዝ ጋር ተነጋገሩበት። ውሳኔያችሁን ቶሎ ብታስታውቁኝ የተሻለ ነው።”
በማግሥቱ “እንሄዳለን” የሚለውን መልሳችንን ሰማ። ስለዚህ ታህሣሥ 26, 1962 ከዘመዶቻችንና ከጓደኞቻችን ጋር ተቃቅፈን ከተሰነባበትን በኋላ በበረዶ ከተሸፈነው የአምስተርዳም ስኬፖል አውሮፕላን ማረፊያ ተነሥተን ሚስዮናውያን ባልረገጧት የኔዘርላንዷ ኒው ጊኒ (አሁን ምዕራብ ኢሪያን፣ ኢንዶኔዥያ ትባላለች) ወደሆነችው የፓፑዋኖች አገር በረርን።
ይህን ፈታኝ የሆነ የአገልግሎት ምድብ ለመቀበል ተጠራጥረን ነበርን? የለም አልተጠራጠርንም። በሙሉ ልባችን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ራሳችንን ለእርሱ የወሰንን ስለነበርን እርሱ እንደሚረዳን ተማምነንበት ነበር። ወደኋላ መለስ ብለን ያሳለፍነውን ሕይወት ስንመለከት በይሖዋ ላይ የነበረን ትምክህት የተሳሳተ እርምጃ አልነበረም። በኢንዶኔዥያ የሆነውን ነገር ከመተረኬ በፊት ከዚያ በፊት ስላሳለፍነው ሕይወት ልንገራችሁ።
በጦርነት ዘመን የተገኘ ሥልጠና
በ1940 ደፋር ምስክር የነበረው አርተር ቪንክለር ቤተሰቦቼን ለመጀመሪያ ጊዜ አግኝቶ ሲመሰክርላቸው እኔ ገና የአሥር ዓመት ልጅ ነበርኩ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕዝበ ክርስትና የሐሰት ትምህርቶች ምን እንደሚል ወላጆቼ በተረዱ ጊዜ በጣም ደነገጡ። በዚያን ጊዜ ኔዘርላንድ በናዚ ጀርመን ተይዛ ስለነበርና የይሖዋ ምስክሮችም ይሰደዱ ስለነበር ወላጆቼ በሕግ ከታገደ ድርጅት ጋር መቀራረብ ይኖርባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ነበረባቸው። ከድርጅቱ ጋር ለመቀራረብ ወሰኑ።
ከዚያ በኋላ እናቴ ነፃነቷንም ሆነ ሕይወቷን በአደጋ ላይ ለመጣል ያሳየችው ድፍረት ልቤን በጣም ነካው። አንድ ጊዜ 11 ኪሎ ሜትር በብስክሌት ተጉዛ በጨለማ ከጠበቀች በኋላ ሻንጣ ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትራክቶችን ይዛ መጣች። ልዩ ዘመቻው የሚጀመርበት ጊዜ ሲደርስ ብስክሌቷን ይዛ የምትችለውን ያህል በፍጥነት እየበረረች ከቦርሳዋ ውስጥ ትራክቶቹን እያወጣች በየመንገዱ ትረጭ ነበር። ይከተላት የነበረ አንድ ብስክሌተኛ መጨረሻ ላይ ደረሰባትና ትንፋሹ ቁርጥ እስኪል ድረስ እየጮኸ “አንቺ ሴትዮ! አንቺ ሴትዮ! ዕቃ ጥለሻል!” አላት። እናታችን ይህንን ታሪክ ስትነግረን ሳቃችንን ማቆም አልቻልንም ነበር።
ልጅ ብሆንም በሕይወቴ ምን ማድረግ እንደምፈልግ አውቅ ነበር። በ1942 አጋማሽ ላይ ባደረግነው አንድ ስብሰባ ላይ የስብሰባው መሪ “በሚቀጥለው አጋጣሚ መጠመቅ የሚፈልግ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀ። እኔ እጄን አወጣሁ። ወላጆቼ የዚህ ውሳኔ ትርጉም ገብቶት ይሆን በማለት ስለተጠራጠሩ እርስ በርሳቸው ተያዩ። ይሁን እንጂ ምንም እንኳ የ12 ዓመት ልጅ ብሆንም ለአምላክ ራስን መወሰን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ገብቶኝ ነበር።
ናዚዎች በጣም በሚከታተሉን በዚያ ሰዓት ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበኩ ጥንቃቄ ማድረግን ይጠይቅ ነበር። ለናዚዎች አሳልፈው ሊሰጡን የሚችሉትን ሰዎች ቤት ላለማንኳኳት ስንል የናዚ ደጋፊዎች የሆኑትን ሰዎች ቤት መስኮቶቻቸው ላይ መፈክር በሚለጥፉበት ቀን በብስክሌት እየተዘዋወርኩ አድራሻቸውን እመዘግብ ነበር። አንድ ቀን እንደዚህ ሳደርግ አንድ ሰው አየኝና “ጥሩ አድርገሃል ልጄ። ሁሉንም የናዚ ደጋፊዎች ስም መዝግብ፣ አንድም አታስቀር” አለኝ። ቅንዓት ነበረኝ ግን ዘዴኛ አልነበርኩም። በ1945 ጦርነቱ ሲያበቃ ለመስበክ የሚያስችል የተሻለ ነፃነት እናገኛለን በሚለው ተስፋ በጣም ተደሰትን።
ቋሚ ሥራ መጀመር
ኅዳር 1, 1948 ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ አቅኚ በመሆን የመጀመሪያውን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ምድቤን ተቀበልኩ። ከአንድ ወር በኋላ ወንድም ዊንክለር እኖርበት የነበረውን ቤተሰብ ለመጠየቅ መጣ። የመጣው እኔ ምን ዓይነት ሰው እንደሆንኩ ለመገምገም ነበር፤ ምክንያቱም ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አምስተርዳም በሚገኘው የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ እንድሠራ ተጠራሁ።
ቆይቶም የክልል የበላይ ተመልካች በመሆን የይሖዋ ምስክሮችን ጉባኤዎች እንድጎበኝ ተጠየቅሁ። ከዚያም በ1952 የመከር ወራት ኒው ዮርክ በሚገኘው በጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በ21ኛው ክፍል የሚስዮናዊነት ሥልጠና እንድወስድ ተጠራሁ። ስለዚህ በ1952 ማለቂያ ላይ ስምንታችንም ከኒዩ አምስተርዳም ወደብ ተነሥተን ወደ አሜሪካ በመርከብ ተጓዝን።
ወደ ትምህርቱ ማለቂያ አካባቢ ከአስተማሪዎቹ አንዱ የሆነው ማክስዌል ፍሬንድ “እዚህ የተማራችኋቸውን ብዙዎቹን ነገሮች ትረሷቸዋላችሁ። ነገር ግን እነዚህ ሦስት ነገሮች ከእናንተ ጋር ይቆያሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። እነሱም እምነት፣ ተስፋና ፍቅር ናቸው” በማለት ተናገረ። በተጨማሪም በአእምሮዬና በልቤ ውስጥ የተቀረጸው ልዩ ትዝታ የይሖዋ ድርጅት በጥድፊያ ስሜት የመሥራቷ ሁኔታ ነው።
በመጨረሻም ያልጠበቅሁት ነገር አጋጠመኝ። እኔን ጨምሮ ከዳች የመጣነው ግማሾቻችን ወደ ኔዘርላንድ ተመልሰን እንድናገለግል ተመደብን። ነገሩ ያልጠበቅሁትም ቢሆን አልተበሳጨሁም። በውጭ አገር የአገልግሎት ምድብ እስክቀበል ድረስ የጥንቱን ሙሴ ያህል 40 ዓመት መጠበቅ እንደማያስፈልገኝ ተስፋ አድርጌ ነበር። — ሥራ 7:23–30
ውድ ረዳቴ የሆነች የትዳር ጓደኛ
እንደ አባት የሆነው ወዳጄ ፍሪትስ ሃርትስታንግ ለማግባት ማሰቤን ሲያውቅ “ከእርሷ የተሻለ ምርጫ ልታገኝ አትችልም” አለኝ። የሱዝ አባት ካሴ ስቱፋ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚዎችን ግንባር ቀደም ሆኖ የተዋጋቸው ሰው ነበር። በ1946 የይሖዋ ምስክሮች ሲያገኙት ግን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ወዲያውኑ ተቀበለ። ብዙም ሳይቆይ እሱና ከስድስት ልጆቹ ውስጥ ሦስቱ ማለትም ሱዝ፣ ማሪያን የተባለችው እና ኬኔት የተባለው ተጠመቁ። ግንቦት 1, 1947 እነዚህ ሦስቱም ልጆች አቅኚዎች ሆነው የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመሩ። በ1948 ካሴ ሱቁን ሸጠና እሱም አቅኚነትን ጀመረ። በኋላም “እነዚያ ዓመታት በሕይወቴ ውስጥ ከሁሉ ይልቅ የተደሰትኩባቸው ጊዜያት ነበሩ” በማለት ተናግሯል።
ሱዝ በ1949 በአምስተርዳም ቅርንጫፍ ቢሮ እንድታገለግል በተጠራችበት ጊዜ እርስ በርስ ተዋወቅን። በሚቀጥለው ዓመት ግን እሷና እኅቷ ማሪያን የጊልያድ 16ኛ ክፍል ተካፈሉና ወደ አገልግሎት ምድባቸው ኢንዶኔዥያ በመርከብ ተጓዙ። ሱዝ በየካቲት 1957 አምስት ዓመት በሚስዮናዊ አገልግሎት ላይ ካሳለፈች በኋላ ወደ ኔዘርላንድ እኔን ለማግባት ተመልሳ መጣች። በዚህ ጊዜ የክልል የበላይ ተመልካች ሆኜ አገልግል ነበር። በጋብቻ ዘመናችን ሁሉ ለመንግሥቱ አገልግሎት ስትል የግል ጥቅሞቿን መሥዋዕት ለማድረግ ያላትን ፈቃደኝነት በተደጋጋሚ አሳይታለች።
ከሠርጋችን በኋላ በኔዘርላንድ የሚገኙትን የተለያዩ ጉባኤዎች መጎብኘታችንን ቀጠልን። ሱዝ ያሳለፈችው አስቸጋሪ የሚስዮናዊነት ሥራ ከአንዱ ጉባኤ ወደ ሌላው ጉባኤ በብስክሌት ለምናደርገው ጉዞ አዘጋጅቷት ነበር። በዚህ የክልል ሥራ ላይ እያለን ነበር በ1962 ወንድም ኩሽኒር በሮተርዳም ሳለን ሊጠይቀን መጥቶ ወደ ዌስት ኢሪያን ኢንዶኔዥያ እንድንዛወር ጥሪውን ያቀረበልን።
በኢንዶኔዥያ ያከናወንነው ሚስዮናዊ አገልግሎት
ፈጽሞ የተለየ ዓለም ወደሆነው የማኖክዋሪ ከተማ ደረስን። በቆላ ውስጥ ሌሊት የሚሰማው አስፈሪ ድምፅ፣ ሙቀቱና አቧራው፤ እንዲሁም እርቃናቸውን ብቻ የሸፈኑ፣ ቆንጨራ የተሸከሙና ከኋላ ከኋላችን እየተከተሉ ነጩን ቆዳችንን ለመንካት የሚሞክሩትን ገጠሬ ፓፑዋኖችና እነዚህን ሁሉ ነገሮች መልመድ ቀላል አልነበረም።
በደረስን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ቄሶች ከይሖዋ ምስክሮች ተጠበቁ የሚል ማስጠንቀቂያ ያለበትን ደብዳቤ በየሰበካ መድረካቸው ላይ አነበቡላቸውና ለእያንዳንዱ ተሰብሳቢ አንዳንድ ቅጂ አደሉአቸው። የአገሩ ራዲዮ ጣቢያ ሳይቀር ደብዳቤውን በስርጭቱ ውስጥ አነበበው። ከዚያም ሦስት ቄሶች መጡና “አረመኔዎች” ናቸው ብለው ወደሚጠሯቸው ወደ ገጠር ሄደን እንድንሠራ ሊያስገድዱን ሞከሩ። በጣም የታወቀ የፓፑዋ የፖሊስ መኮንንም ቀርቦ አካባቢውን ለቀን እንድንወጣ ወተወተን። አንድ ሰላይ ፖሊስም እኛን ለመግደል ሤራ እየተጠነሰሰ መሆኑን ነገረን።
ይህም ሆኖ ሁሉም ሰው አልተቃወመንም። የደች አገር ዜጋ የሆነ አንድ የፓፑዋኖች የፖለቲካ አማካሪ ወደ ኔዘርላንድ ለመሄድ በሚዘጋጅበት ጊዜ ከሁለትና ከሦስት የፓፑዋ ዜጎች አለቆች ጋር አስተዋወቀን። “የይሖዋ ምስክሮች ካሁን ቀደም ከምታውቁት የተሻለ የክርስትና ሃይማኖት ይዘውላችሁ መጥተዋል። ስለዚህ ልትቀበሏቸው ይገባል” ብሎ ነገራቸው።
በኋላም አንድ የመንግሥት ባለ ሥልጣን ሱዝን መንገድ ላይ አግኝቶ በሹክሹክታ “አዲስ ሥራ እዚህ መክፈታችሁን ሰምተናል፤ ነገር ግን ልናስቀምጣችሁ አንችልም። . . . ብቻ ምን ያደርጋል፣ ቤተ ክርስቲያን ቢኖራችሁ ኖሮ ጥሩ ነበር” አላት። ግሩም ፍንጭ! ወዲያውኑ ቤታችንን አዘገጃጀንና አግዳሚ ወንበሮች ደረደርን፣ የተናጋሪ አትራኖስ አቆምንና ከውጪ በትልቁ የሚታይ “የመንግሥት አዳራሽ” የሚል ጽሕፈት ለጠፍንበት። ከዚያም ባለ ሥልጣኑን እንዲጎበኝልን ጠየቅነው። ሳቀ፣ የራሱን አንድ ጎን በአመልካች ጣቱ አስደግፎ ራሱን እየነቀነቀ ‘ጎበዞች፣ ጎበዞች’ ብሎ የተናገረ ያህል ነበር።
እዚያ ከደረስን ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ሰኔ 26, 1964 ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ውስጥ የመጀመሪያዎቹ 12 ፓፑዋኖች ተጠመቁ። ጥቂት ቆይቶ ሌሎች 10 ተጨመሩና የተሰብሳቢዎቻችን ብዛት በአማካይ 40 ደረሰ። ሁለት የኢንዶኔዥያ ተወላጅ የሆኑ አቅኚዎች እንዲረዱን ተላኩልን። በማኖክዋሪ የሚገኘው ጉባኤ በሚገባ ሲጠናከር የማኅበሩ የኢንዶኔዥያ ቅርንጫፍ ቢሮ በታህሣሥ 1964 ሌላ የስብከት ሥራ ምድብ አዘጋጀልን።
አካባቢውን ለቀን ከመውጣታችን በፊት የመንግሥቱ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ለብቻችን ጠርቶ “በመሄዳችሁ በጣም አዝናለሁ። በየሳምንቱ ቄሶቹ እየመጡ ፍሬዎቻችንን ለቀሙብን እያሉ እንዳስወጣችሁ ይለምኑኝ ነበር። እኔ ግን ‘እናንተ እንደምትሉት ሳይሆን ዛፎቻችሁን ፍሬያማ አደረጉላችሁ’ ብዬ እመልስላቸው ነበር” አለን። ጨምሮም “የትም ብትሄዱ ውጊያችሁን ቀጥሉ። ታሸንፋላችሁ!” አለ።
በመንግሥት ግልበጣ መካከል
በመስከረም ወር 1965 በዋና ከተማዋ በጃካርታ እያገለግልን ሳለን አንድ ሌሊት ላይ ዓማፅያኑ ኮሙኒስቶች ብዙ ወታደሮችን ገደሉ፣ ጃካርታን በእሳት አያያዟት፣ እንዲሁም የአገሪቷ ፕሬዘዳንት የነበሩትን ሱካርኖን ከጊዜ በኋላ የገለበጠ አገር አቀፍ ትግል ተጀመረ። ወደ 400,000 የሚያክሉ ሰዎች በዚሁ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል!
አንድ ጊዜ በአገልግሎት ላይ እያለን በሚቀጥለው መንገድ ላይ ተኩስ ተጀመረ፣ በእሳት ማጋየትም ቀጠለ። በሚቀጥለው ቀን የቤት ባለቤቶች ልናነጋግራቸው ስንቀርብ ፍርሃት የዋጣቸው ይመስሉ ነበር፣ ወታደሮቹም በአቅራቢያው የሚገኘውን የኮሙኒስቶች ንብረት በጠቅላላ ለማውደም ትንሽ ቀርቷቸው እንደ ነበረ ሰማን። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክታችንን ሲሰሙ ዘና ይሉና ወደ ቤት እንድንገባ ይፈቅዱልን ነበር። እኛ ከእነርሱ ጋር በመሆናችን ጥበቃ እንደሚያገኙ ሆኖ ይሰማቸው ነበር። ያ ጊዜ ሁላችንንም በይሖዋ ላይ ተስፋችንን እንድንጥልና በአስጨናቂ ሁኔታዎች ሥር ስንሆን ሚዛናችንን እንድንጠብቅ አስተምሮናል።
ተጨማሪ ተቃውሞ ከሸፈ
በ1966 ማለቂያ ላይ በደቡብ ሞሉካ ደሴቶች ወደምትገኘው አምቦን ወደተባለች ውብ ስፍራ ተዛወርን። እዚያም ተግባቢና እንግዳ ተቀባይ በሆነው ሕዝብ መካከል ብዙ መንፈሳዊ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አገኘን። ትንሹ ጉባኤያችን በፍጥነት አደገና የተሰብሳቢያችን ብዛት አንድ መቶ ደረሰ። በዚህም የተነሣ የሕዝበ ክርስትና የቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣኖች የሃይማኖት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆነውን ሰው ከአምቦን በአስቸኳይ እንዲያባርረን ለመጫን ሄዱ። ነገር ግን እዚያው ኃላፊው ጠረጴዛ ላይ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርን ጽሑፎች በግልጽ ተቀምጠው ተመለከቱ። የኃላፊውን ሐሳብ ማስለወጥ ሲያቅታቸው በጃካርታ ወደሚገኙት የሃይማኖት ጉዳይ ሚኒስትር ባለ ሥልጣኖች ቀርበው ከአምቦን ብቻ ሳይሆን ከጠቅላላው ኢንዶኔዥያ የምንባረርበትን መንገድ ለመፈለግ ሞከሩ።
በዚህ ጊዜ የተሳካላቸው ይመስል ነበር፤ ምክንያቱም የካቲት 1, 1968 እንድንባረር የተወሰነበት ቀን ነበር። ይሁን እንጂ በጃካርታ የሚገኙት ክርስቲያን ወንድሞቻችን በሃይማኖት ጉዳይ ሚኒስትር ውስጥ የሚሠራ እስላም የሆነ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን አገኙ። እርሱም ውሳኔው እንዲሻር በማድረግ ረዳን። በተጨማሪም የቀድሞው ፖሊሲ ተለወጠና ተጨማሪ ሌሎች ሚስዮናውያን እንዲገቡ ተፈቀደ ላቸው።
በዚህ መንገድ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት በሰሜናዊው ሱማትራ ውስጥ በሚገኙት በእነዚያ የሚደነቁ ተራሮች፣ ጫካዎችና ሐይቆች ዙሪያ ከአውስትራሊያ፣ ከኦስትሪያ፣ ከጀርመን፣ ከፊሊፒንስ፣ ከስዊድን እና ከአሜሪካ ከመጡ ሚስዮናውያን ጋር አብረን ሠራን። በተለይ ባታክ በሚባሉት ዋነኛ ጎሣዎች ክልል ውስጥ የስብከቱ ሥራ በጣም ተስፋፋ።
ሆኖም ያልተኙት ሃይማኖታዊ ጠላቶቻችን በመጨረሻ ታህሣሥ 1976 የስብከት ሥራችንን ማሳገዱ ተሳካላቸው። በሚቀጥለው ዓመትም ብዙዎቹ ሚስዮናውያን በሌሎች አገሮች የአገልግሎት ምድባቸውን እየተቀበሉ ወጡ። በመጨረሻ በ1979 እኛም መሄድ ነበረብን።
ወደ ደቡብ አሜሪካ
አሁን ዕድሜያችን ወደ 50 ዓመት ተጠግቷል፤ ወደ ሌላ አገር ሄደን ልንለምድ መቻላችንም ግራ አጋብቶን ነበር። “አዲስ የአገልግሎት ምድብ እንቀበላለን ወይስ አንድ ቦታ ላይ ተረጋግተን መኖር አለብን?” ስትል ሱዝ ጠየቀች።
“አየሽ ሱዝ፣ ይሖዋ ሂዱ ወደሚለን ማንኛውም ቦታ ብንሄድ እሱ ይንከባከበናል። መጪዎቹ ቀኖች ምን ተጨማሪ በረከት ይዘው እንደሚቆዩን ማን ያውቃል?” ብዬ መለስኩላት። ስለዚህ አዲስ የአገልግሎት ምድባችን ወደ ሆነችው በደቡብ አሜሪካ ወደ ምትገኘው ሱሪናም ደረስን። በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ውስጥ ገባንና ለመድነው።
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላይ ያሳለፍናቸውን 45 ዓመታት ወደኋላ መለስ ብለን ስናስታውስ በሚስዮናዊነቱ አገልግሎት እንድንቀጥል ወላጆቻችን ያደረጉልን ድጋፍ ምን ያህል ጠቃሚ እንደነበረ ለመገንዘብ ችለናል። በ1969 ወላጆቼን ለመጠየቅ ከስድስት ዓመት በኋላ በሄድኩበት ጊዜ አባቴ ለብቻዬ ወሰደኝና “ምናልባት እናትህ መጀመሪያ ከሞተች፣ መምጣት አያስፈልግህም። በተመደብክበት አገልግሎትህ ቀጥል። እኔ እወጣዋለሁ። ነገር ግን ሁኔታው የተገላቢጦሽ ከሆነ ስለዚህ ጉዳይ እናትህን መጠየቅ ይኖርብሃል” አለኝ። እናቴም በበኩልዋ እንዲሁ አለችኝ።
የሱዝ ወላጆች ተመሳሳይ የሆነ ከራስ ወዳድነት የራቀ አቋም ነበራቸው። አንድ ጊዜ ሱዝ ከእነርሱ ተለይታ ለ17 ዓመታት ያህል ቆይታ ነበር። ነገር ግን አንድም ቀን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ጽፈውላት አያውቁም። እርግጥ ነው፣ ሌላ የሚረዳቸው ባይኖር ኖሮ ወደ እነርሱ ተመልሰን በመሄድ እንረዳቸው ነበር። ለማለት የተፈለገው ዋናው ቁም ነገር ወላጆቻችን ለሚስዮናዊነቱ አገልግሎት ተመሳሳይ አክብሮት የነበራቸውና እራሳቸውም ቢሆኑ እስከ ሞቱበት ጊዜ ድረስ በእኛ ልብ ውስጥ በተከሉት በጥድፊያ ስሜት ይሖዋን በማገልገል መንፈስ መቀጠላቸው ነው። — ከ1 ሳሙኤል 1:26–28 ጋር አወዳድር።
ደብዳቤ እንደሚጽፉ በታመንባቸው ወዳጆቻችን በብዙው ተበረታትተናል። ከ30 ዓመታት በላይ በሚስዮናዊነት ባገለገልንባቸው ጊዜያት ደብዳቤ ሳይጽፉ አንዲት ወር ያላለፈባቸው ጥቂት ወዳጆቻችን አሉ! ነገር ግን ከሁሉም በላይ በምድር ላይ ያሉትን አገልጋዮቹን እንዴት አድርጎ እንደሚንከባከብ የሚያውቀውን ተወዳጁን የሰማይ አባታችንን ይሖዋን ምን ጊዜም አንረሳውም። ስለዚህ ስንጠባበቃቸው የነበሩት ሁኔታዎች ወደ ከፍተኛ ደረጃቸው እየደረሱ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ ከምንጊዜውም ይበልጥ በጥድፊያ ስሜት ይሖዋን እያገለገልን ሱዝ እና እኔ “የይሖዋን ቀን በአእምሮአችን አቅርበን” ማየታችንን የመቀጠል ምኞት አለን። — 2 ጴጥሮስ 3:12 አዓት
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1957 ተጋባን
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስድስት ወጣቶች አቅኚዎች ሲሆኑ ማየት እንዴት ያስደስታል!