ሎይዳ የሐሳብ ግንኙነት ለመፍጠር ያደረገችው ትግል
የሎይዳ እናት እንደተናገረችው
እንደማንኛዋም ነፍሰ ጡር እናት እኔም ጤነኛ ልጅ እወልድ ይሆን እያልኩ እጨነቅ ነበር። ይሁን እንጂ ሦስተኛዋ ልጄ ሎይዳ ስትወለድ ያሰማችው አንጀት የሚበላ ጩኸት ያልጠበቅሁት ነገር ሆነብኝ። ዶክተሩ በማዋለጃ መሣሪያው ሳያውቅ የሎይዳን አፅመክሳድ (collarbone) ሰብሮት ስለነበር ሎይዳ የማስተካከያ ቀዶ ሕክምና ከተደረገላት ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ወደ ቤት ተላከች። ሆኖም ደስታችን በአጭሩ ተቀጨ።
በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ውስጥ አንድ ዓይነት ከባድ ችግር እንዳለባት በግልጽ ታወቀ። ለሎይዳ የተሰጣት ሕክምና ትኩሳት፣ ተቅማጥና ማንቀጥቀጥን ጨምሮ ሌሎች ጎጂ ውጤቶች አስከተለባት። ለዚህ ተብሎ የተሰጣት ሕክምና ደግሞ ሁኔታዋን ከማባባስ በቀር የፈየደው ነገር አልነበረም። ብዙም ሳይቆይ ሎይዳ የሰውነቷን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ተሳናት። በመጨረሻም ዶክተሮቹ በሎይዳ በደረሰው ጉዳት ሳቢያ ሴረብራል ፓልሲ የሚባል ችግር እንዳለባት ነገሩን። ከዚህ በኋላ መራመድም ሆነ መናገር አልፎ ተርፎም እኛ የምንላትን መረዳት እንኳ እንደማትችል ገለጹልን።
የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ የተደረገ የመጀመሪያ ጥረት
ምንም እንኳ ጤንነቷ እንደሚሻሻል የሚያሳይ የተስፋ ጭላንጭል ባይኖርም ሎይዳ ብዙ ነገሮች መረዳት ትችላለች የሚል እምነት ነበረኝ። በመሆኑም ቀለል ያሉ መጻሕፍት ማንበብና ፊደል መቁጠር ለማስተማር ጥረት ማድረግ ጀመርኩ። ይሁን እንጂ ሎይዳ መናገር የማትችል ከመሆኗም በላይ የምነግራትን ነገር እንደምትረዳ የሚጠቁም ምንም ነገር አይታይባትም ነበር። ምን ነገር መረዳት እንደምትችል (ያውም ካለ) ማወቅ የሚቻልበት መንገድ አልነበረም።
ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ሎይዳን ለማስተማር ያደረግሁት ጥረት ሁሉ ከንቱ ልፋት ብቻ ሆኖ ቀረ። እንደዚያም ሆኖ ብዙ ሰዓት አነብላት ነበር። ከዚህም በላይ ከትንሿ ልጃችን ከኖኤሚ ጋር ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ በተባሉት መጻሕፍት የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስናደርግ ሎይዳም አብራን እንድትገኝ ማድረግ ጀመርን።a ከእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ በርካታ ምዕራፎችን ለሎይዳ ደጋግሜ አነብላት ነበር።
ከምትወዱት ሰው ጋር የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ አለመቻል በእርግጥም የሚያበሳጭ ነው። እንድትጫወት ሎይዳን ወደ መናፈሻ ከወሰድኳት አምርራ ታለቅሳለች። ለምን? እንደ ሌሎቹ ልጆች መሯሯጥና መጫወት አለመቻልዋ ጭንቀት ስለሚፈጥርባት ይመስለኛል። በአንድ ወቅት እህቷ ከምትማርበት መጽሐፍ ላይ የሆነ ነገር ስታነብልኝ ሎይዳ ማልቀስ ጀመረች። አንድ ነገር እንደረበሻት ግልጽ ነው፤ ሆኖም ምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም። ሎይዳ ምግብና ውኃ ለማግኘት፣ ለመተኛት ወይም ወደ መጸዳጃ ቤት ለመሄድ ያላትን መሠረታዊ ፍላጎት ለመግለጽ ብዙም የማይገቡ ጥቂት ድምፆችን ከማውጣት ባሻገር የምትናገረው ምንም ነገር አልነበረም።
ሎይዳ ዘጠኝ ዓመት ሲሞላት ለየት ያለ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ልጆች በተቋቋመ ትምህርት ቤት ውስጥ መማር ጀመረች። ሆኖም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ሁኔታዋ እየተባባሰ ሄደ። ያለ ደጋፊ ጥቂት እርምጃ እንኳ መራመድ እያስፈራት መጣ፤ እንዲሁም ድምፅ ማሰማቷንም አቆመች። እኔና ባለቤቴ ሎይዳን ቤት ውስጥ ማስተማሩ የተሻለ እንደሚሆን ወሰንን።
በቀጣዮቹ ስድስት ዓመታት ውስጥ አቅሜ የፈቀደልኝን ያህል ሎይዳን አስተማርኳት። ሎይዳ ትገለብጣቸዋለች በሚል ተስፋ ጥቁር ሰሌዳ ላይ ፊደሎች እጽፍላት ነበር። ጥረቴ ሁሉ መና ሆኖ ቀረ። የሎይዳ ችግር የመረዳት ችሎታ ማነስ ነው ወይስ የእጆቿን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ስለማትችል መጻፍ ተስኗት ነው?
ሎይዳ 18 ዓመት ሲሞላት እሷን መቆጣጠሩ በጣም አስቸጋሪ ስለሆነብኝ ከልጄ ጋር መነጋገር እንድችል እንዲረዳኝ አጥብቄ ይሖዋን ለመንኩት። ባልጠበቅሁት መንገድ ለጸሎቴ መልስ አገኘሁ።
የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ቻለች
ሴቶች ልጆቼ የመኝታ ክፍላችንን እያስጌጡ በነበረበት ጊዜ አንድ ከፍተኛ ለውጥ ተከሰተ። ኖኤሚ ያረጀውን የግድግዳ ወረቀት ልጣ ከማንሳቷ በፊት ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ፣ የጓደኞቻችንንና የቤተሰባችንን አባላት አንዳንድ ስሞች ግድግዳው ላይ ጻፈች። ልጄ ሩት ካደረባት ጉጉት የተነሳ “ይሖዋ” የሚለው ስም የትኛው እንደሆነ ሎይዳን ጠየቀቻት። የሚያስገርመው ነገር ሎይዳ ወደ ግድግዳው ሄደችና የአምላክ ስም ያለበት አጠገብ ጭንቅላቷን አስነካች። ሩት ተደንቃ ሌሎቹንም ስሞች መለየት ትችል እንደሆነ ለማወቅ ሎይዳን ጠየቀቻት። ሎይዳ እያንዳንዱን ስም ከዚህ በፊት በጽሑፍ አይታ የማታውቃቸውን ስሞች እንኳ ሳይቀር ለይታ በማወቋ ሩትን አስገረማት! ሩት ሁሉም የቤተሰቡ አባላት የሆነውን ነገር እንዲመለከቱ ጠራቻቸው። ሎይዳ ማንበብ ትችላለች!
ከጊዜ በኋላ፣ ሎይዳ ለእኛ “መናገር” እንድትችል የሚረዳት አንድ ዘዴ ቀየስን። በረጅሙ የኮሪደሩ ግድግዳ ላይ የእንግሊዝኛ ፊደሎችን በሙሉ ለጠፍንላት። ሎይዳ እያንዳንዱን ፊደል ለማመልከት እጆቿን በበቂ ሁኔታ መቆጣጠር ስለማትችል በእጅ በሚያዝ ሰሌዳ ላይ አነስ ያሉ ፊደላትን መስቀሉ ዋጋ አልነበረውም። ስለዚህ ሎይዳ ሐሳቧን መግለጽ በምትፈልግበት ጊዜ ግድግዳው ላይ ወዳለው ወደ እያንዳንዱ ፊደል በመሄድ ቃላት ትፈጥራለች። መገመት እንደምትችሉት ይህ በጣም አድካሚ ነው። እንዲያውም ሎይዳ አንድ ገጽ በሚያክል ወረቀት ላይ ሐሳቧን ለማስፈር ብዙ ኪሎ ሜትሮች መራመድ የነበረባት ሲሆን ይህንም ለማጠናቀቅ በርካታ ሰዓት ሊፈጅባት ይችላል!
የሆነ ሆኖ ሎይዳ ለእኛ “መናገር” መቻልዋ በጣም አስደሰታት። እንዲያውም ለመጀመሪያ ጊዜ የገለጸችልን ሐሳብ እንዲህ ይላል:- “ይሖዋ ምስጋና ይድረሰውና አሁን መናገር በመቻሌ በጣም ደስ ብሎኛል።” በነገሩ ከመገረማችን የተነሳ ሎይዳን እንዲህ ስንል ጠየቅናት:- “ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብለሽ ስትውይ ምን ታደርጊ ነበር?” ሎይዳ መናገር ብትችል ኖሮ ለእኛ መንገር የምትፈልገውን ነገር በአእምሮዋ ታውጠነጥን እንደነበረ ነገረችን። በእርግጥም ሎይዳ ለ18 ዓመታት ያህል ሐሳቧን የመግለጽ ከፍተኛ ምኞት እንደነበራት ነግራናለች። “ሩት ወደ ትምህርት ቤት መሄድ በጀመረችበት ጊዜ የትምህርት ቤት መጽሐፏን አነብብ ነበር። አፌን በማንቀሳቀስ የተወሰነ ድምፅ አሰማ የነበረ ቢሆንም እናንተ ግን ልትረዱልኝ አልቻላችሁም። በተደጋጋሚ አለቅስ የነበረውም በዚህ የተነሳ ነው” ስትል ነገረችን።
ስሜቷን በተሻለ ሁኔታ መረዳት ሳልችል በመቅረቴ እያለቀስኩ ይቅርታ ጠየቅኋት። ሎይዳ እንዲህ ስትል መለሰችልኝ:- “አንቺ በጣም ደግ እናት ነሽ፤ ተስፋ ቆርጠሽ አልተውሽኝም። ከአንቺ ጋር በመሆኔ ሁልጊዜ ደስተኛ ነበርኩ። በጣም እወድሻለሁ። ካሁን በኋላ አታልቅሺ፣ እሺ?”
መንፈሳዊ እድገት
ሎይዳ አስቀድሞም የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የነበራት ሲሆን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችንም በቃሏ ይዛ ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ፣ በጥያቄና መልስ በሚሸፈነው በሳምንታዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ማለትም በጉባኤ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ሐሳብ መስጠት እንደምትፈልግ ነገረችን። ይህን እንዴት ማድረግ ትችላለች? አንዳችን የጥናቱን ርዕስ ባጠቃላይ እናነብላታለን። ከዚያም ሎይዳ መመለስ የምትፈልገውን አንድ ጥያቄ ትመርጣለች። ፊደላቱን እርሷ በምትነግረን መሠረት ሐሳቧን እንጽፍላታለን። ከዚያም ስብሰባ ላይ አንዳችን የሎይዳን ሐሳብ እናነባለን። በአንድ ወቅት ሎይዳ እንዲህ ብላናለች:- “የጉባኤው ክፍል እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ስለሚያደርግ ተሳትፎ ማድረግ መቻሌ በጣም ያስደስተኛል።”
ሎይዳ 20 ዓመት ሲሞላት መጠመቅ እንደምትፈልግ ነገረችን። ሎይዳ ራስን ለይሖዋ መወሰን ምን ትርጉም እንዳለው ገብቷት እንደሆነ ስትጠየቅ ራስዋን የወሰነችው ከሰባት ዓመት በፊት ገና የ13 ዓመት ልጅ እያለች እንደነበር ተናገረች። “ወደ ይሖዋ በመጸለይ እሱን ለዘላለም ማገልገል እንደምፈልግ ነገርኩት” አለችን። ሎይዳ ነሐሴ 2, 1997 በውኃ በመጠመቅ ለይሖዋ ያደረገችውን ውሳኔ አሳየች። ሎይዳ እንዲህ ብላናለች:- “ለይሖዋ ምስጋና ይድረሰውና ትልቁ ምኞቴ ተፈጽሞልኛል!”
ሎይዳ ለዘመዶችና ለጎረቤቶች ስለ አምላክ መንግሥት መናገር ያስደስታታል። መንገድ ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች ስንሰብክ አንዳንድ ጊዜ አብራን ትወጣለች። በተጨማሪም ቤት ውስጥ ሰው በማይኖርበት ጊዜ በር ላይ ትተነው የምንሄድ አንድ ደብዳቤም አዘጋጅታለች። ሎይዳ ለአረጋውያንና ለታመሙ ሰዎች ለየት ያለ ትኩረት ትሰጣለች። ለምሳሌ ያህል በጉባኤያችን፣ እግሯ የተቆረጠ አንዲት እህት አለች። ሎይዳ “መራመድ አለመቻል ምን ስሜት እንደሚፈጥር አውቀዋለሁ” ስትል ነገረችን። ከዚህ የተነሳ ለዚህች እህት የማበረታቻ ደብዳቤ ጻፈችላት። ሌላው ደግሞ በሌላ ጉባኤ የሚገኝ ሂሮ የተባለ ልጅ ሲሆን እሱም ከራስ እስከ እግሩ ሙሉ በሙሉ ሽባ ነው። ሎይዳ ያለበትን አሳዛኝ ሁኔታ ስትሰማ ደብዳቤ ጻፈችለት። ደብዳቤው በከፊል እንዲህ ይላል:- “በቅርቡ ይሖዋ ጤናማ ያደርገናል። ገነት ውስጥ ምንም ዓይነት ስቃይ አይኖርም። በዚያን ጊዜ ሩጫ እገጥምሃለሁ። በጣም አስደሳች ጊዜ ስለሚሆን አሁን ሳስበው እንኳ ያስቀኛል። ይሖዋ ሲፈጥረን እንደነበርነው ከበሽታ ነፃ እንደምንሆን ማሰቡ . . . በጣም አስደናቂ አይደለም?”
መጽናት እንድትችል ያገኘችው እርዳታ
በፊት ግራ ያጋባኝ ስለነበረው የሎይዳ ባሕርይ አሁን ብዙ ነገሮች ተረድቻለሁ። ለምሳሌ ያህል ሎይዳ ልጅ እያለች በጣም ያስጨንቃት ስለነበር መታቀፍ እንደማትወድ ነግራኛለች። እንዲህ ብላለች:- “እህቶቼ መናገርና አንዳንድ ነገሮችን መማር ሲችሉ እኔ ግን ሳልችል መቅረቴ እንደተበደልሁ እንዲሰማኝ አድርጓል። በጣም ያናድደኝ ነበር። ሞትን የመረጥኩበት ጊዜ ነበር።”
ሎይዳ ሐሳቧን የመግለጽ ችሎታ ብታገኝም እንኳ ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟታል። ለምሳሌ ያህል በየወሩ ማለት ይቻላል፣ ልክ ታንቆ እንደተያዘ ሰው እግሮቿና እጆችዋ በጣም እየተወራጩ በተከታታይ ትንፈራገጣለች። ከዚህም በላይ ቀላል የሆነ ጉንፋንን ጨምሮ የትኛውም ዓይነት ህመም ክፉኛ ያዳክማታል። አልፎ አልፎ ሎይዳ ካለባት ችግር የተነሳ የመንፈስ ጭንቀት ያድርባታል። በጽናት እንድታሳልፈው የሚረዳት ምንድን ነው? እስቲ በራስዋ አባባል ትንገራችሁ:-
“በጸሎት ከፍተኛ እርዳታ አግኝቻለሁ። ይሖዋን ማነጋገርና የእሱ የቅርብ ወዳጅ መሆን በጣም ያስደስተኛል። በተጨማሪም በመንግሥት አዳራሽ የማገኛቸው የሚያሳዩኝን ፍቅርና አሳቢነት አደንቃለሁ። አካላዊ ችግሮች ቢኖሩብኝም እንኳ በጣም የሚወዱኝ ሁለት ግሩም የሆኑ ወላጆች ስላገኘሁ በጣም ዕድለኛ እንደሆንኩ ይሰማኛል። እህቶቼ ያደረጉልኝን ነገር ፈጽሞ አልረሳውም። በግድግዳው ላይ የተጻፉት እነዚያ የሚያምሩ ቃላት ሕይወቴን አትርፈውልኛል። ይሖዋ እና ቤተሰቦቼ ፍቅር ባያሳዩኝ ኖሮ ሕይወቴ ትርጉም የለሽ ይሆን ነበር።”
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተመ። ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ የተባለው መጽሐፍ በአሁኑ ጊዜ መታተም አቁሟል።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሎይዳ እና ቤተሰቦቿ