“ከዓለም አካባቢ” በትምህርት ቤት ውስጥ
በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው የ15 ዓመቷ ኤደልሚራ በትምህርት ቤቷ የንቁ! መጽሔትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ተጠቅማበታለች። ለመጽሔቱ አዘጋጂዎች በላከችው ደብዳቤ እንዲህ ብላለች:-
“በየሳምንቱ ዓርብ ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮችን የሚመለከት ሪፖርት እናቀርባለን። የሚያዝያ 22, 2000 ንቁ! (እንግሊዝኛ) አነበብኩና ‘ከዓለም አካባቢ’ በሚለው ሥር ከሚገኙት ርዕሶች መካከል ‘ማጨስ ካንሰር እንደሚያስከትል የትንባሆ ኩባንያዎች አመኑ’ የሚለውን ለማቀርበው ሪፖርት ለመጠቀም ወሰንኩ።” ፍሬ ነገሩን በአጭሩ ካሰፈርኩ በኋላ ክፍል ውስጥ አነበብኩ። አስተማሪዋና ተማሪዎቹ በጥሞና ተከታተሉኝ። አንብቤ እንደጨረስኩ አንዲት ተማሪ ይህን መረጃ ለማግኘት ረዥም ጊዜ ወስዶብኝ እንደሆነ እዚያው እንደቆምኩ ጠየቀችኝ። የንቁ! መጽሔቱን ሰጠኋት። መጽሔቱን እንደተቀበለች በጉጉት ማንበብ ጀመረች። በሚቀጥለው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ከልጅቷ ጋር በአንድ ክፍል የሚማር በጉባኤያችን የሚገኝ አንድ ልጅ እርሱም መጽሔቱን ስታነብብ እንዳያት ነገረኝ። ልጅቷም በየጊዜው እየታተሙ የሚወጡትን የንቁ! እና አብሮት የሚታተመውን የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት እትሞች ማግኘት እንደምትፈልግ ነግራኛለች።
“ይህ ተሞክሮ የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ እንድኮራ አድርጎኛል። ስለ ይሖዋ ለመናገር የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎች እንዳሉን አስተምሮኛል።” ኤደልሚራ ደብዳቤዋን ስታጠቃልል እንዲህ በማለት ጽፋለች:- “እነዚህን መጽሔቶች ለማዘጋጀት ለምታከናውኑት ትጋት የተሞላበት ሥራ ላመሰግናችሁ እፈልጋለሁ። እባካችሁ ‘ከዓለም አካባቢ’ የሚለውን ዓምድ ማዘጋጀታችሁን ቀጥሉ!”