‘በይሖዋ የሚታመኑ’ ወጣቶች
ውበት የወጣቶች ብቻ አይደለም፤ ጥበብም በዕድሜ ለገፉት ብቻ አይደለም። (ከምሳሌ 11:22ና ከመክብብ 10:1 ጋር አወዳድር።) ከዚህ ይልቅ ዘላቂ ውበትና እውነተኛ ጥበብ ያላቸው በይሖዋ የሚታመኑትና በሙሉ ልባቸው “አንተ አምላኬ ነህ” የሚሉት ናቸው።—መዝሙር 31:14፤ ምሳሌ 9:10፤ 16:31
አምላክን በማገልገልና የመንግሥቱን ምስራች በመስበክ ያላቸውን ጥበብ የሚያሳዩ ቁጥራቸው እያደገ የመጣ ብዙ ውብ አረጋውያንና ወጣቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል የስምንት ዓመት ዕድሜ ያላትን ሳብሪናን እንውሰድ።
ሳብሪና የምትኖረው በጀርመን አገር ሲሆን የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ናት። ለምትማርበት ትምህርት ቤት የመጀመሪያዋ የይሖዋ ምስክር ነች። የሚያሳዝነው ግን አስተማሪያቸው በጣም የሚወዱትን መጽሐፍ እንዲያመጡ እስከጠየቀችበት ዕለት ድረስ የትምህርት ቤቷ ተማሪዎች የስድብ ዒላማ ነበረች። ሳብሪና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን የያዘው መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ ለመውሰድ ወሰነች። ከዚያ በፊት በነበረው ምሽት ስጋት ቢያድርባትም እንኳ በክፍሏ ለምታቀርበው ገለጻ ግን በደንብ ተዘጋጅታ ነበር። በክፍሏ ውስጥ የሚገኙት ተማሪዎች 26 ስለነበሩ ብዙ ጊዜ ልታገኝ እንደማትችል ተሰምቷት ነበር። ነገር ግን የምታቀርበውን ማብራሪያ ማንም እንዳያቋርጥባት ለማገድ ቁርጥ ውሳኔ አደረገች፤ ይሖዋም እንደሚረዳት እርግጠኛ ነበረች። ማብራሪያቸውን በሚያቀርቡበት ቀን አስተማሪያቸው ከመካከላቸው መጽሐፍ ያመጣና በመጀመሪያ ለተማሪዎቹ ሊነግራቸው የሚፈልግ እንዳለ ጠየቀቻቸው። የሚያስገርም ነበር፤ መጽሐፏን ያመጣችው ሳብሪና ብቻ ነበረች። ተነስታ ከተማሪዎቹ ፊት በመቆም ከመጽሐፉ እያነበበችላቸውና ሥዕሉን እያሳየቻቸው እንዲሁም እያንዳንዱ ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆኑን እያብራራችላቸው መናገር ጀመረች። በመደሚደሚያዋ ላይም “ይህንን መጽሐፍ ለማግኘት የሚፈልግ ማን ነው?” ስትል ጠየቀች። የመጽሐፉን አንድ ቅጂ ለአስተማሪዋ ሰጠቻትና በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ተጨማሪ አሥር መጻሕፍትን ለክፍል ጓደኞቿ ሰጠቻቸው። አስተማሪዋ በአቀራረቧ ላይ የሰጠችው አስተያየት ቢኖር “እንዲህ ያለ ነገር አይቼ አላውቅም” የሚል ብቻ ነበር። ሳብሪና ለሠራችውም ሥራ ከፍተኛ ነጥብ ሰጠቻት።
እንዲያውም ብዙዎቹ ወጣት ምስክሮች ደስተኛ የመንግሥቱ ምስራች አስፋፊዎች ናቸው። ሌላዋ ምሳሌ የምትሆነን በሜክሲኮ የምትገኘው የ11 ዓመት ዕድሜ ያላት አስፋፊ ኤሪካ ናት። ከልጅነቷ ጀምሮ ይሖዋን እንድትወደው ስትማር ቆይታለች። የትምህርት ቤት ውጤቷ በጣም የሚደንቅ ነበር። ከተሰጣት የቤት ሥራ መካከል አንዱ ኤድስን እንዲሁም የትንባሆንና የመጠጥ ሱስን በተመለከተ ጽሑፍ እንድታዘጋጅ ነበር። ንቁ! መጽሔትን በመጠቀም ጽሑፏን በሚገባ በማዘጋጀቷ ከፍተኛ ነጥብ ተሰጣት። አስተማሪዋ ሐሳቡን ከየት እንዳገኘችው ጠየቀችና ያንን ርዕሰ ጉዳይ የያዙ መጽሔቶችን አገኘች። በኋላም አስተማሪዋ በእነዚህ መጽሔቶች በመጠቀም በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ከመላው የክፍሉ ተማሪዎች ጋር ተወያየችበት። ኤሪካ ባላት መልካም ባሕርይ፣ ለአስተማሪዎቿ በምታሳየው አክብሮትና በምታገኘው ከፍተኛ ነጥብ ምክንያት ስጦታዎችንና ዲፕሎማዎችን ስታገኝ በግማሽ ክፍያ ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል የሚያስችላትን አጋጣሚ አግኝታለች። የሆነ ሆኖ ለእርሷ ትልቁ ድል የይሖዋ ምስክር ሆና መታወቋና ብዙ ጽሑፎችን ለማበርከት መቻሏ እንዲሁም የአምላክን ስም ከፍ ለማድረግ መቻሏ እንደሆነ ይሰማታል።
እንዲሁም አሥር ዓመት የሆነውንና በኒው ዚላንድ የሚኖረውን ሻኖንን እንውሰድ። ያለው ጤነኛ ዓይን አንድ ብቻ ነው። አንድ ዓይኑ በካንሰር ምክንያት የጠፋበት ሕጻን ሆኖ ነበር። ሻኖን የሰባት ዓመት ልጅ ሳለ እናቱ ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምራ ነበር። ይሁን እንጂ ጥናት ከጀመረችበት ጊዜ ብዙም ሳይቆይ በትዳር ሳይተሳሰሩ ከአንድ ሰውዬ ጋር አብራ መኖር ጀመረችና ጥናቷን ለማቆም ወሰነች። ሻኖን ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ እንዳይቋረጥበት ለመነ። እንዲያጠናም ተፈቀደለት። ምስክሮቹ እየተመላለሱ መጠየቃቸውን አላቆሙም ነበር፤ በመጨረሻ የቤተሰቡ ሦስቱም አባላት መጽሐፍ ቅዱስን አጠኑና መንፈሳዊ ዕድገት አደረጉ። በሕጋዊ መንገድ ጋብቻቸውን ከፈጸሙ በኋላ የሻኖን እናትና የእንጀራ አባቱ ተጠመቁ።
አንድ ቀን ሻኖንና የክልል የበላይ ተመልካቹ ባለቤት አንድ ላይ በመስክ አገልግሎት ተሰማርተው ነበር። የቤቱ ባለቤት ሻኖንን “ዓይንህን ምን ሆነህ ነው?” ሲል ጠየቀው። እርሱም “ካንሰር ይዞኝ ስለነበር መውጣት ነበረበት በቅርቡ ግን ይሖዋ በገነት ሌላ አዲስ ዓይን ይሰጠኛል፤ እንዲያውም ልንነግርዎ የመጣነውም ስለዚሁ ነው” ሲል መለሰለት።