የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g03 9/8 ገጽ 25
  • ጥርስ መፋቂያ እንጨት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥርስ መፋቂያ እንጨት
  • ንቁ!—2003
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሁለቱ በትሮች አንድ መሆን
    የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ!
  • ወደ ጥርስ ሐኪም መሄድ የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው?
    ንቁ!—2007
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • የድድ በሽታ—አንተን ያሰጋህ ይሆን?
    ንቁ!—2014
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2003
g03 9/8 ገጽ 25

ጥርስ መፋቂያ እንጨት

ዛምቢያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

አፍሪካውያን የጥርስ ብሩሽ እምብዛም ባይጠቀሙም ጥርሶቻቸው ነጫጭና የሚያማምሩ ናቸው። ይህ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? ብዙዎቹ ጥርሳቸውን ለማጽዳት እንጨት ወይም መፋቂያ ስለሚጠቀሙ ነው።

በድሮ ጊዜ ባቢሎናውያን ቆየት ብሎ ደግሞ ግብጻውያን፣ ግሪኮችና ሮማውያን ጥርሳቸውን ለማጽዳት መፋቂያ ይጠቀሙ ነበር። የእስልምና ሃይማኖት ከመመሥረቱ በፊት አረቦችም ከእንጨት ቁራጭ በሚሠሩ “የጥርስ ብሩሾች” ጥርሳቸውን ማጽዳታቸው የተለመደ ነበር። የእንጨት መፋቂያ በአውሮፓ የነበረውን ተወዳጅነት የዛሬ 300 ዓመት ገደማ ቢያጣም በአፍሪካ፣ በእስያና በመካከለኛው ምሥራቅ አሁንም በሰፊው ጥቅም ላይ ይውላል።

በመካከለኛው ምሥራቅ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው የጥርስ መፋቂያ ሶልትቡሽ ወይም የጥርስ ብሩሽ ዛፍ ተብሎ የሚጠራው የዛፍ ዓይነት ነው። በምዕራብ አፍሪካ የሎሚና የብርቱካን ዛፍ ቅርንጫፎችን በመፋቂያነት የሚጠቀሙ ሲሆን በሕንድ ደግሞ በዋነኛነት የኒም ዛፍን ይጠቀማሉ። በምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ ወደ 300 የሚጠጉ የዛፍ ዓይነቶችና ቁጥቋጦዎች ለጥርስ መፋቂያነት ያገለግላሉ። የእንጨት መፋቂያ ጥርስ የሚያጸዳው እንዴት ነው?

የእንጨቱ አንደኛው ጫፍ ሲታኘክ እንደ ጥርስ ብሩሽ ሻካራ ይሆናል። መፋቂያውን ማኘክ በጥርሶች መካከል የቀረውን ምግብ ለማውጣት የሚያስችል ሲሆን በድድ ውስጥ ያለውን የደም ዝውውር ከፍ ያደርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ በአፍ ውስጥ የሚኖረው የምራቅ መጠን እንዲጨምር ያደርጋል። ምራቅ ደግሞ ባክቴሪያዎችን አጥቦ ያስወግዳል፤ እንዳይራቡም ያደርጋል።a

ይሁን እንጂ የመፋቂያ እንጨት ጥርስን ከማጽዳት የበለጠ ጥቅም አለው። የአንዳንድ ተክሎች ቀንበጥና ሥራ ሥሮች በጥርስ ላይ ልማም ወይም የጥርስ ቆሻሻ እንዳይፈጠር የሚከላከሉ ኬሚካሎች አሏቸው። ከአንዳንድ የእንጨት ዓይነቶች የሚወጣው ፈሳሽ የፀረ ባክቴሪያነትና የፀረ ፈንገስነት ጠባይ እንዳለው ተረጋግጧል። ቀደም ብለን የጠቀስነው ሶልትቡሽ የተባለው ዛፍ ቀንበጦች የቆላ ቁስል እንዳይፈጠር ይከላከላሉ። በናሚቢያ ሙታላ ከተባለው ተክል ላይ የሚቆረጥ እንጨት የጥርስ መበስበስን፣ የድድ በሽታንና የጉሮሮ ቁስለትን የሚያስከትሉ ተህዋስያንን እድገት እንደሚቀንስ ይታወቃል። ይህ ተፈጥሯዊ የጥርስ ማጽጃ የጥርስ መቦርቦርን ይከላከላል፤ እንዲሁም የጥርስን ሥርና ድድን ያጠነክራል። በአሁኑ ወቅት አንዳንድ የጥርስ ሳሙና አምራች ኩባንያዎች በምርቶቻቸው ውስጥ የእነዚህን ተክሎች ቃጫና ሙጫ ይጨምራሉ።

እርግጥ አንዳንዶች ዘመናዊውን የጥርስ ብሩሽ ለመጠቀም ይመርጣሉ። አንተ የምትጠቀመው ጥንታዊውን የእንጨት መፋቂያም ይሁን ዘመናዊውን የጥርስ ብሩሽ የጥርስህን ንጽሕና መጠበቅህ ለጤንነትህ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a እርግጥ፣ ለጥርስ ንጽሕና አመጋገብም ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አይካድም። በአፍሪካ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በከተማ ከሚኖሩት የበለጠ ያልተፈተጉ እህሎችንና አትክልቶችን ይመገባሉ። እንዲሁም ስኳርን፣ የፋብሪካ ምግቦችንና ለስላሳ መጠጦችን የመሳሰሉ ለጥርስ መበላሸት በዋነኛነት ምክንያት የሚሆኑትን ነገሮች በብዛት አይጠቀሙም።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለጥርስ መፋቂያነት ከሚያገለግሉት ዛፎች መካከል አንዱ የኒም ዛፍ ነው

[ምንጭ]

William M. Ciesla, Forest Health Management International, www.forestryimages.org

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ