ሴቶችን ሊያሳስብ የሚገባ ቫይረስ
ክርስቲናa ባል ካገባች ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የማኅጸን ምርመራ አደረገች። ሐኪሟ አሳሳቢ ነገር ስላገኘች ክሪስቲና ኮልፖስኮፒ የሚባል ምርመራ እንድታደርግ መከረቻት። በውጤቱም በማኅጸኗ አንገት ላይ ቁስል የመሰለ ነገር ስላገኘች ከቁስሉ ተቆንጥሮ የባዮፕሲ ምርመራ ተደረገ።
ክርስቲና “ከሁለት ሳምንት በኋላ እኔና ባለቤቴ አብረን መጥተን ውጤቱን እንድንሰማ ዶክተሯ ጠራችን። ቁስሉ ሂውማን ፓፒሎማቫይረስ በተባለ ቫይረስ ምክንያት የመጣ እንደሆነና አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ እንደሆነም ነገረችን። ኢንፌክሽኑ የማኅጸን አንገት ካንሰር ሊያመጣ ስለሚችል ወዲያውኑ ሕክምና እንድጀምር አሳሰበችን” ትላለች።
“የምርመራውን ውጤት ስሰማ ማልቀስ ጀመርኩ። ለባለቤቴም ሆነ ለእኔ በጣም አስደንጋጭ ነበር። በማግስቱ ቀላል ቀዶ ሕክምና እንዲደረግልኝ ቀጠሮ ወሰድኩ። ያን ዕለት ከሰዓት በኋላ በጣም አዝኜና ተጨንቄ ዋልኩ። ‘ለምን እንዲህ ያለ ነገር ይደርስብኛል?’ ብዬ አማረርኩ።”
ክርስቲና ቫይረሱ የሚተላለፈው በሩካቤ ሥጋ እንደሆነ አንብባ ስለነበረ እንዴት ሊይዛት እንደቻለ ግራ ገባት። እርሷም ሆነች ባለቤቷ የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ሕግጋት አክብረው የሚኖሩ ናቸው።
በብዛት የተስፋፋ ኢንፌክሽን
በመላው ዓለም በሂውማን ፓፒሎማቫይረስ የተለከፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች ሲኖሩ በጣም ተስፋፍቶ የሚገኝና በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፍ በሽታ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ከሆነ ለማኅጸን አንገት ካንሰር መፈጠር ዋነኛው ምክንያት ይህ ኢንፌክሽን ነው።b
በመላው ዓለም በየዓመቱ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሴቶች በሂውማን ፓፒሎማቫይረስ እንደተያዙ በምርመራ የሚረጋገጥ ሲሆን በየዓመቱ በዚሁ ቫይረስ ምክንያት በሚመጣው የማኅጸን ካንሰር ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ይሞታሉ። በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ብዙ ሴቶች በካንሰር የሚሞቱበት ዋነኛ ምክንያት ይህ ቫይረስ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማኅጸን ካንሰር ዓይነቶች በሁለተኛነት ደረጃ ላይ የሚገኘው የማኅጸን አንገት ካንሰር ነው። የዓለም ጤና ድርጅት ሂውማን ፓፒሎማቫይረስን “ዓለም አቀፍ የሕዝብ ጤና ችግር” ሲል መሰየሙ አያስደንቅም! ስለዚህ ቫይረስ ልናውቅ የሚገባን ምን ተጨማሪ ነገር አለ?
በወንዶችም ሆነ በሴቶች ላይ ኮንዲሎማ አኩሚናታ በሚል ስያሜ የሚታወቀውን የአባለዘር ኪንታሮት ጨምሮ የተለያዩ የኪንታሮት ዓይነቶች እንዲፈጠሩ የሚያደርገው ሂውማን ፓፒሎማቫይረስ ነው። እነዚህ ኪንታሮቶች አብዛኛውን ጊዜ የካንሰርነት ባሕርይ የሌላቸው ናቸው። ከመቶ በላይ የሚሆኑ የሂውማን ፓፒሎማቫይረስ ዓይነቶች ቢኖሩም የካንሰርነት ባሕርይ ያላቸው ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። የማኅጸን አንገት ካንሰር የሚያመጡት ሥር ሰደው የሚቆዩ ጥቂት የሂውማን ፓፒሎማቫይረስ ዓይነቶች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኞቹ በዚህ ቫይረስ ምክንያት የሚፈጠሩ ኢንፌክሽኖች በሰውነት የመከላከያ ኃይል ተሸንፈው በራሳቸው ይጠፋሉ።
ለቫይረሱ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች
ከተለያዩ ወንዶች ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጽሙ ወይም ከተለያዩ ሴቶች ጋር የጾታ ግንኙነት ሲያደርግ ከነበረ ወንድ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሴቶች በሂውማን ፓፒሎማቫይረስ የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ ቫይረሱን ወደ ሴት ጓደኛው የሚያጋባው ምንም ዓይነት ውጪያዊ የሕመም ምልክት የማይታይበት ወንድ ነው።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ የሥነ ምግባር ንጽሕናቸውን ጠብቀው የኖሩ ወይም ከነጭራሹ ሩካቤ ሥጋ ፈጽመው የማያውቁ ሴቶች በዚህ ኢንፌክሽን ሊያዙ የሚችሉበት ሁኔታ ይኖራል። ለምሳሌ በቅርቡ የተደረጉ አንዳንድ ጥናቶች ቫይረሱ በልደት ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ ወይም በሌሎች ምክንያቶች ሊተላለፍ እንደሚችል አመልክተዋል። በሽታው የሚታወቀው ግለሰቡ በቫይረሱ ከተያዘ ከብዙ ዓመታት በኋላ ሊሆን ይችላል።
ኢንፌክሽን መኖሩ እንዴት ሊታወቅ ይችላል?
ሴት ከሆንሽ ‘ሂውማን ፓፒሎማቫይረስ እንዳለብኝ እንዴት ላውቅ እችላለሁ?’ እያልሽ ራስሽን ሳትጠይቂ አትቀሪም። ይህ በጣም አስፈላጊ ጥያቄ ነው። ምክንያቱም በሽታው አብዛኛውን ጊዜ ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት አያሳይም። ስለዚህ የመጀመሪያው መሠረታዊ እርምጃ በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰችው ክርስቲና እንዳደረገችው ፓፕ ስሚር የሚባለውን የሴል ምርመራ ማድረግ ነው።c
ምርመራውን ለማድረግ ሐኪሙ ከማኅጸን አንገት ላይ ጥቂት የሴል ናሙና ፍቆ ከወሰደ በኋላ ወደ ላቦራቶሪ ይልከዋል። በዚህ ምርመራ ኢንፌክሽን፣ መቆጣት ወይም ጤነኛ ያልሆነ ሴል መኖሩን ማረጋገጥ ይቻላል። የፓፕ ስሚር ምርመራ የማኅጸን ካንሰርን ስርጭትም ሆነ ገዳይነት በእጅጉ እንደቀነሰ ተዘግቧል።
የዓለም ጤና ድርጅት “እስካሁን ድረስም ሆነ ምናልባትም ወደፊት ዋነኛው የዚህ በሽታ መከላከያ ዘዴ ወደ ካንሰርነት ሊለወጡ የሚችሉ ሴሎችን አስቀድሞና ከመባባሳቸው በፊት ምርመራ ማድረግ ነው” ይላል። በዚህ ምርመራ የሚገኘው ውጤት በቂ መስሎ ካልታየ ሕመምተኛው የሰውነት ክፍል ለማየት የሚያስችል አጉሊ መነጽር ባለው መሣሪያ አማካኝነት ኮልፖስኮፒ የሚባል ምርመራ ይደረግለታል። በዚህ ዘዴ ቁስለት ያለው ሕዋስ መኖሩን ማረጋገጥ ይቻላል። ቁስል መኖሩ ከተረጋገጠ ባዮፕሲ ወይም ተቆንጥሮ በሚወሰድ ናሙና ምርመራ ይደረግና ሕክምና ይጀመራል።
በአሁኑ ጊዜ ከዚህም የረቀቁ የላቦራቶሪ ምርመራዎች ማድረግ ይቻላል። በእነዚህ ምርመራዎች አማካኝነት በሽታ መኖር አለመኖሩን ይበልጥ በእርግጠኝነት ማወቅ ይቻላል።
ሕክምናና መከላከያ
የሂውማን ፓፒሎማቫይረስ ኢንፌክሽንን መቆጣጠር የሚቻልባቸው በርካታ የሕክምና ዘዴዎች አሉ። ሐኪሞች በሽታው ባለበት ቦታ ላይ ብቻ የሚደረጉ መድኃኒቶችን ይጠቀማሉ። ከእነዚህ መድኃኒቶች አንዳንዶቹ ቫይረሱ የሚገኝባቸውን ሴሎች የሚገድሉ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም የሚያጠናክሩ ናቸው። ኤሌክትሮሰርጀሪ፣ ሌዘር ሰርጀሪ ወይም ክራዮሰርጀሪ በመጠቀም በበሽታ የተለከፈውን የሰውነት ክፍል ቆርጦ ማውጣት ሌላው የሕክምና ዘዴ ነው። ይሁን እንጂ ታሞ በሽታውን ለማዳን ላይ ታች ከማለት ከመጀመሪያ ኢንፌክሽኑን መከላከል ቢቻል ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር። ታዲያ እንዴት መከላከል ይቻላል?
ከሁለት ዓመት በፊት በሜክሲኮ ሲቲ “የማኅጸን አንገት ካንሰርና ሂውማን ፓፒሎማቫይረስ በአዲሱ ሚሊኒየም” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚወያይ ሲምፖዚየም ተካሂዶ ነበር። ተጋባዥ ተናጋሪ የነበሩትና የሂውማን ፓፒሎማቫይረስ ኤክስፐርት የሆኑት ካናዳዊው ዶክተር ቪ ሴሲል ራይት “ከማግባታችሁ በፊት የግብረ ሥጋ ግንኙነት አታድርጉ” ሲሉ መክረዋል። በሞንትሪያል፣ ካናዳ በመጊል ዩኒቨርሲቲ የፓቶሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር አሌክስ ፈሬንሲ በተመሳሳይ “የማኅጸን ካንሰርን ለመከላከል . . . አንድ ለአንድ ተወስኖ መኖር አስፈላጊ ስለመሆኑ ሽንጣችንን ገትረን መከራከር ይገባናል” ብለዋል።
ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ሕግጋት አክብረው የኖሩ ሰዎች በሂውማን ፓፒሎማቫይረስ ኢንፌክሽን ምክንያት በሚመጣ ካንሰር የመያዝ አጋጣሚያቸው አነስተኛ ነው። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ከጋብቻ ውጭ የሚደረገውን ሩካቤ ሥጋ ስለሚያወግዝ፣ ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ሆነው እንዲኖሩ ስለሚያበረታታ እንዲሁም ክርስቲያኖች እነዚህኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚከተልና የሚያከብር ሰው ብቻ እንዲያገቡ ስለሚመክር ነው።—1 ቆሮንቶስ 7:39፤ ዕብራውያን 13:4
ይሁን እንጂ የሂውማን ፓፒሎማቫይረስ ኢንፌክሽን ሊወገድ የሚችል በመሆኑ ትምህርት አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ኢንፌክሽኑ ሥር ከሰደደ በኋላም ቢሆን ታክሞ ሊድን ይችላል። እንዲያውም “የማኅጸን አንገት ካንሰር የሕመም ምልክት ከማሳየቱ በፊት ከታወቀ ሁልጊዜ ማለት ይቻላል፣ አክሞ ማዳን እንደሚቻል” የዓለም ጤና ድርጅት ያምናል።
የሥነ ምግባር ትምህርት ከመስጠት በተጨማሪ ሴቶች ስለበሽታው እንዲያውቁና በየጊዜው እንደ ፓፕ ስሚር የመሰለ ምርመራ ማድረግ ጠቃሚ መሆኑን ማስገንዘብ አስፈላጊ ነው።d ችግር እንዳለ ከታወቀ ሴቲቱ በጊዜው ሕክምና ማግኘት ትችላለች። የኮልፖስኮፒ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ሞንሴራት ፍሎረስ “አንዲት ሴት የችግሯን መጠንና ባሕርይ ካወቀች ወደ ሁለት አደገኛ ተጻራሪ ጽንፎች ከመሄድ ትድናለች። ይኸውም በአንድ በኩል በሽታዋን በመናቅ የሕክምና ክትትል ሳታደርግ ትቀርና ወደ ካንሰርነት ይለወጣል፣ በሌላ በኩል ካንሰር ይዞኛል ብላ ከመጠን በላይ በመፍራት አስፈላጊ ያልሆነ ቀዶ ሕክምና ታደርጋለች” ብለዋል።
ሳይንስ የሂውማን ፓፒሎማቫይረስን መመርመሪያ ዘዴዎች ይበልጥ ውጤታማና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት አላቋረጠም። በተጨማሪም ይህን ኢንፌክሽን ለመከላከልም ሆነ ለማከም የሚያስችሉ ክትባቶች በመሠራት ላይ ናቸው።
ክርስቲና ለመጨረሻ ጊዜ ያደረገችው ምርመራ ውጤት አጥጋቢ ቢሆንም አሁንም በየስድስት ወሩ የኮልፖስኮፒ ምርመራ ማድረጓን አልተወችም። ስለያዛት በሽታ ብዙ ካወቀች በኋላ “በሂውማን ፓፒሎማቫይረስ ብንያዝም እንኳን በጤንነት ለመኖር ልናደርግ የምንችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ” ትላለች።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ስሟ ተለውጧል።
b ሰርቪክስ ወይም የማኅጸን አንገት የሚባለው በሴት ብልትና በማኅጸን መገናኛ ላይ የሚገኝ ጠባብ የአካል ክፍል ነው።
c ይህ ምርመራ ስያሜውን ያገኘው በናሙናነት የተወሰዱትን ሴሎች አቅልሞ የመመርመርን ዘዴ ከፈለሰፉት የግሪክ ተወላጅ ከሆኑት ከጆርጅ ኤን ፓፓኒኮላው ነው።
d የዩናይትድ ስቴትስ የብሔራዊ ካንሰር ተቋም እንደሚለው ከሆነ ይህ ዓይነቱ ምርመራ ከ18 ዓመት ዕድሜ ወይም የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየጊዜው መደረግ አለበት።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሴቶች ሊወስዷቸው የሚገቡ የጥበብ እርምጃዎች
ሴቶች በየጊዜው የፓፕ ስሚር ምርመራ ማድረግ፣ ከትንባሆ መራቅና ጤናማ አመጋገብ መከተል ይኖርባቸዋል። ጤናማ አመጋገብ አትክልቶችን፣ ፍራፍሬዎችንና ጥራጥሬዎችን ማዘውተር ይጠይቃል። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ካሮቲን፣ ቫይታሚን ኤ፣ ሲ እና ኢ እንዲሁም ፎሊክ አሲድ ያለባቸውን ምግቦች መመገብ በማኅጸን አንገት ካንሰር የመያዝ ዕድልን ይቀንሳል።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ለሞት የሚዳርግ ቫይረስ
በመላው ዓለም ከአባለዘር በሽታዎች በስርጭቱ ስፋት ከፍተኛውን ደረጃ የያዘው ሂውማን ፓፒሎማቫይረስ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ዋነኛው የማኅጸን አንገት ካንሰር ምክንያት ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማኅጸን ካንሰር ዓይነቶች በሁለተኛነት ደረጃ ላይ የሚገኘው የማኅጸን አንገት ካንሰር ነው።
[ምንጭ]
© Science VU/NCI/Visuals Unlimited
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የፓፕ ስሚርን ምርመራ ያገኙት ዶክተር ጆርጅ ፓፓኒኮላው