እውነትን ለማግኘት ብቻውን የደከመው ማይክል ሰርቪተስ
ስፔን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ጥቅምት 27, 1553 ማይክል ሰርቪተስ በጄኔቫ ስዊዘርላንድ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ተቃጠለ። የሞት ፍርዱን ያስፈጸመውና የጆን ካልቪን ተተኪ የነበረው ጊዮም ፋሬል፣ ሰርቪተስ ሲገደል የተመለከቱትን ሰዎች “[ሰርቪተስ] እውነትን እንደሚያስተምር የሚያስብ ጠቢብ ሰው እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ይሁን እንጂ በዲያብሎስ እጅ ወድቋል። . . . እናንተም ተመሳሳይ ነገር እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ!” በማለት አሳሰባቸው። ይህ ሰው እንዲህ ያለ አሳዛኝ ቅጣት የተበየነበት ምን ሠርቶ ነው?
ማይክል ሰርቪተስ በ1511 በስፔን አገር ቢላኑኤቫ ዴ ሲጄና በምትባል መንደር ተወለደ። ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በትምህርቱ ጎበዝ ነበር። የሕይወት ታሪክ የሚጽፍ አንድ ሰው እንደገለጸው ከሆነ ሰርቪተስ “በ14 ዓመቱ ግሪክኛ፣ ላቲንና ዕብራይስጥ የተማረ ሲሆን በፍልስፍና፣ በሒሳብ እንዲሁም በመንፈሳዊ ትምህርት ደግሞ ሰፊ እውቀት ነበረው።”
የስፔኑ ንጉሠ ነገሥት የቻርልስ አምስተኛ ንስሐ አባት የነበሩት ሁዋን ደ ኬንታና፣ ሰርቪተስ ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለ ተላላኪያቸው እንዲሆን ቀጠሩት። ሰርቪተስ፣ ሁዋን ዴ ኬንታናን አጅቦ ከቦታ ቦታ በሚጓዝበት ጊዜ አይሁዶችና ሙስሊሞች በግዞት እንዲሰደዱ ወይም የካቶሊክን ሃይማኖት እንዲቀበሉ በሚገደዱበት በስፔን የነበረውን ሥር የሰደደ ሃይማኖታዊ መከፋፈል መታዘብ ችሎ ነበር።a
ሰርቪተስ በ16 ዓመቱ በቱሉዝ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ሕግ ሊያጠና ወደ ፈረንሳይ ሄደ። እዚያ እያለ በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ አየ። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በጥብቅ የተከለከለ ቢሆንም ሰርቪተስ በድብቅ አነበበው። ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ጊዜ አንብቦ ከጨረሰ በኋላም “ሺህ ጊዜ ደጋግሞ” ሊያነበው ቃል ገባ። ሰርቪተስ በቱሉዝ ሳለ ያነበበው መጽሐፍ ቅዱስ፣ የላቲኑን ትርጉም ጨምሮ ቅዱስ ጽሑፉ መጀመሪያ በተጻፈባቸው በዕብራይስጥና በግሪክኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀውን የኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎት የሚባለውን እትም ሳይሆን አይቀርም።b ሰርቪተስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያደረገው ጥናት፣ በስፔን ካየው የቀሳውስቱ የሥነ ምግባር ብልሹነት ጋር ተዳምሮ በካቶሊክ ሃይማኖት ላይ የነበረውን እምነት አናጋው።
ሰርቪተስ የቻርለስ 5ኛን ሥርዓተ ንግሥ በተመለከተ ጊዜ በካቶሊክ ሃይማኖት ላይ የነበረው ጥርጣሬ ይበልጥ ጨመረ። ሊቀ ጳጳስ ክሌመንት 7ኛ የስፔኑን ንጉሥ፣ በቅድስቲቷ የሮም ሥርወ መንግሥት ላይ ንጉሠ ነገሥት ብለው በመሰየም ዘውድ ጫኑለት። ሊቀ ጳጳሱ በተንቀሳቃሽ ዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው ንጉሡን ሲቀበሉት እሱ ደግሞ ተጎንብሶ እግራቸውን ሳመ። ሰርቪተስ “መሳፍንቱ ሊቀ ጳጳሱን በትከሻቸው ተሸክመዋቸው በደመቀ ሥነ ሥርዓት ሲያልፉ በመንገድ ላይ የተኮለኮለው ሕዝብ ደግሞ ከፍተኛ ክብር ሲሰጣቸው በገዛ ዓይኔ ተመልክቻለሁ” በማለት ከጊዜ በኋላ ጽፏል። በዚያን ወቅት ያየው ደማቅና የተንዛዛ ሥነ ሥርዓት በወንጌሎች ላይ ካነበበው ነገር ጋር ሊስማማለት አልቻለም።
ሰርቪተስ ሃይማኖታዊ እውነትን መፈለጉን ተያያዘው
ሰርቪተስ ዘዴ ፈልጎ ከኬንታና ዘንድ የነበረውን ሥራ በመተው እውነትን ብቻውን መፈለጉን ተያያዘው። ክርስቶስ ወንጌሉን የሰበከው ለሃይማኖት ምሁራን ወይም ለፈላስፎች ሳይሆን መልእክቱን ተረድተው በሥራ ለሚያውሉት ተራ ሰዎች እንደሆነ ያምን ነበር። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ለመመርመርና ከቅዱስ ጽሑፉ ጋር የማይስማማውን ማንኛውንም ትምህርት ላለመቀበል ወሰነ። በዚህ ምክንያት ሰርቪተስ ባዘጋጃቸው ጽሑፎች ውስጥ ከማንኛውም ቃል ይበልጥ በብዛት ተጠቅሶ የሚገኘው “እውነት” የሚለው ቃልና ከዚህ ጋር የሚዛመዱ ሌሎች ቃላት መሆናቸውን መመልከት ይቻላል።
ሰርቪተስ በታሪክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያደረገው ጥናት ክርስትና የተበከለው ከክርስቶስ ልደት በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት እንደሆነ አስገነዘበው። በዚህ ጥናቱ ቆስጠንጢኖስና ከዚያ በኋላ የተነሱት ነገሥታት የሐሰት ትምህርቶችን እንዳስፋፉና ይህም የኋላ ኋላ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት በይፋ ተቀባይነት እንዲያገኝ በር እንደከፈተ ተረዳ። ስለዚህም ሰርቪተስ፣ ኢንክዊዚሽን የተባለው የካቶሊክ የፍርድ ሸንጎ ዋነኛ የጥቃት ዒላማ ለመሆን ያበቃውን የሥላሴ ስህተት የሚል መጽሐፍ በ20 ዓመቱ አሳተመ።
ሰርቪተስ ነገሮችን አበጥሮ የመረዳት ችሎታ ነበረው። በጽሑፉ ላይ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሥላሴ የሚል ቃል አልተጠቀሰም። . . . አምላክን ማወቅ የምንችለው በምንመጻደቅበት የፍልስፍና አስተሳሰብ ሳይሆን በክርስቶስ በኩል ነው” በማለት ጽፏል።c በተጨማሪም ሰርቪተስ፣ መንፈስ ቅዱስ ራሱን የቻለ አካል ሳይሆን አምላክ የሚጠቀምበት ኃይል እንደሆነ መገንዘብ ችሎ ነበር።
ሰርቪተስ በአንዳንድ አንባብያኑ ዘንድ ተሰሚነት አግኝቷል። የፕሮቴስታንት ተሐድሶ አራማጅ የነበረው ዜባስቲያን ፍራንክ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ስፔናዊው ሰርቪተስ አምላክ አንድ ብቻ እንደሆነ በመግለጽ በበራሪ ጽሑፉ ላይ መከራከሪያ አቅርቧል። የሮም ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በአንድ አምላክ ውስጥ ሦስት አካሎች አሉ ትላለች። እኔ የምስማማው ከስፔናዊው ጋር ነው።” የሆነ ሆኖ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም ሆነች የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት፣ ሰርቪተስ ከፍተኛ ሥፍራ የሚሰጡትን የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ባለመቀበሉ ቂም ይዘውበት ነበር።
ሰርቪተስ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሠረተ ትምህርቶችም ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሌላቸውና ውድቅ መሆናቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ የተረዳ ሲሆን ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምም ቅዱስ ጽሑፋዊ እንዳልሆነ ተገነዘበ። በመሆኑም ሰርቪተስ የሥላሴ ስህተት የሚለውን መጽሐፍ ካሳተመ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ካቶሊኮችንም ሆነ ፕሮቴስታንቶችን በሚመለከት እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “ከሁለቱም ጋር የምስማማበትም የማልስማማበትም ነጥብ አለ። ሁለቱም ቢሆኑ ጥቂት እውነት ሊኖራቸው ቢችልም የተወሰነ ስህተትም ያላቸው ይመስለኛል፤ ሆኖም አንዱ ወገን የሌላውን ስህተት ማየት ሲችል የራሱን ስህተት ግን አያይም።” እውነትም ሰርቪተስ እውነትን የሚፈልገው ብቻውን ነበር።d
ሰርቪተስ እውነትን ለመፈለግ በቅንነት ቢነሳሳም አንዳንድ የተሳሳቱ ድምዳሜዎች ላይ ከመድረስ ግን አላመለጠም። ለምሳሌ ያህል፣ አርማጌዶን የሚመጣውና ክርስቶስ ለሺህ ዓመት የሚገዛው እሱ በኖረበት ዘመን እንደሆነ አስቦ ነበር።
ሳይንሳዊ እውነትን መፈለግ
ሰርቪተስ ከአሳዳጆቹ ለመሸሽ ስለተገደደ ስሙን ለውጦ ቬያኖቫነስ በመባል በፓሪስ መኖር ጀመረ፤ በዚያም በሥነ ጥበብና በሕክምና የተለያየ ዲግሪ አገኘ። የሳይንሱ መስክ የቀሰቀሰበት የማወቅ ጉጉት የሰውን አካል አሠራር ይበልጥ ለመረዳት የሰውን አካል በመሰነጣጠቅ ጥልቅ ጥናት እንዲያደርግ አነሳሳው። በውጤቱም ሰርቪተስ ከሳንባችን ጋር በተያያዘ በሰውነታችን ውስጥ ስለሚከናወነው የደም ዝውውር ያብራራ የመጀመሪያው አውሮፓዊ ሆነ። ይህን ግኝት የክርስትና መመለስ በሚለው ጽሑፉ ውስጥ አካቶታል። ሰርቪተስ ይህን ማብራሪያ የሰጠው ዊልያም ሃርቪ ስለ ጠቅላላው ሥርዓተ ደም ሙሉ ማብራሪያ ከመስጠቱ ከ75 ዓመት በፊት ነበር።
በተጨማሪም ሰርቪተስ በክላውዲየስ ቶለሚ የተጻፈውን የቶለሚ ጂኦግራፊ የተሰኘ መጽሐፍ አዲስ እትም አዘጋጀ። ይህ እትም በጣም ውጤታማ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንዶች ሰርቪተስን ስለ ጂኦግራፊና ስለ ሰው ልጆች ባሕል ለሚደረገው ንጽጽራዊ ጥናት አባት እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። ሰርቪተስ ከጊዜ በኋላ በጄኔቫ ለፍርድ በቀረበበት ወቅት የጳለስጢና ምድር በጣም አነስተኛ የእርሻ መሬት ያላት በረሃማ አገር መሆኗን በመግለጹ ተወግዞ ነበር። ሰርቪተስ ስለ ጳለስጢና ምድር የሰጠው ማብራሪያ ማርና ወተት ታፈስ የነበረችበትን የሙሴን ዘመን ሳይሆን አሁን ያለችበትን ሁኔታ የሚመለከት እንደሆነ በመናገር ለራሱ መከላከያ አቅርቧል።
ከዚህም ሌላ ሰርቪተስ ስለ መድኃኒት አዲስና ሚዛናዊ አመለካከት የተንጸባረቀበት ዩኒቨርሳል ትሪቲስ ኦን ሲረፕስ የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ ጽፏል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የታመቀው የሕክምና እውቀት ሰርቪተስ በመድኃኒቶች ጥናት (ፋርማኮሎጂ) እና በቪታሚኖች አጠቃቀም ረገድ ፈር ቀዳጅ እንዲሆን አድርጎታል። ሰርቪተስ በብዙ መስኮች ካለው ሙያዊ ችሎታ አንጻር አንድ ታሪክ ጸሐፊ “በሰው ታሪክ ውስጥ ከታዩት ታላቅ የአእምሮ ችሎታ ያላቸው ሰዎች መካከል የሚመደብና የሰው ልጆችን ጠቅላላ እውቀት ለማበልጸግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሰው” በማለት ገልጾታል።
የሰርቪተስ የማይገፋ ባላጋራ
እውነት ፈላጊዎች ምንጊዜም ቢሆን ብዙ ጠላቶች ነበሯቸው። (ሉቃስ 21:15) ከሰርቪተስ በርካታ ባላጋራዎች አንዱ በጄኔቫ የፕሮቴስታንት ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት ያቋቋመው ጆን ካልቪን ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት እንደጻፉት ከሆነ ካልቪን “አምባገነን እንዲሆን ያደረገው በሕግ የሚመራ ወይም ጉልበተኛ መሆኑ ሳይሆን በሌሎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ስለቻለና ኃይለኛ ስለነበረ ነው።” ካልቪን “ሰዎች የራሳቸውን እምነት ለመምረጥ ያላቸውን መብት በመጋፋት ረገድም ቢሆን [ከካቶሊክ] ሊቀ ጳጳሳት የማይለይ ነበር።”
ሰርቪተስና ካልቪን የተገናኙት ሁለቱም ገና ወጣቶች ሳሉ በፓሪስ ሳይሆን አይቀርም። ገና ከመጀመሪያው ባሕሪያቸው የማይጣጣም ስለነበር ካልቪን ለሰርቪተስ የማይተኛ ጠላቱ ሆነ። ካልቪን የፕሮቴስታንት ተሐድሶ አራማጅ ቢሆንም የኋላ ኋላ ሰርቪተስን ለካቶሊክ የፍርድ ሸንጎ አሳልፎ ሰጥቶታል። በፈረንሳይ የሰርቪተስን ምስል ሠርተው ቢያቃጥሉትም እሱ ግን ለጥቂት ማምለጥ ችሎ ነበር። ይሁን እንጂ የካልቪን ቃል እንደ ሕግ በሚቆጠርባትና ከፈረንሳይ ድንበር ብዙም በማትርቀው በጄኔቫ ከተማ ሰርቪተስ ስለታወቀ ተይዞ ታሰረ።
ካልቪን፣ ሰርቪተስ በእስር ቤት በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲሠቃይ በየነበት። ያም ሆኖ ሰርቪተስ ፍርድ ቤት ቀርቦ ከካልቪን ጋር ባካሄደው ክርክር፣ ካልቪን የሚያሳምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ ካቀረበለት ሐሳቡን እንደሚለውጥ ቃል ገብቶ ነበር። ይሁን እንጂ ካልቪን አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ሳይችል ቀረ። የፍርዱ ሂደት ሲያበቃ ሰርቪተስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ እንዲቃጠል ተፈረደበት። አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚሉት ካቶሊኮች ምስሉን ሠርተው ፕሮቴስታንቶች ደግሞ በሕይወት እያለ ያቃጠሉት ሃይማኖታዊ ተቃዋሚ እሱ ብቻ ነበር።
የሃይማኖታዊ ነፃነት አብሳሪ
ካልቪን እንደ ግል ባላንጣው የቆጠረውን ሰርቪተስን ማጥፋት ቢችልም ከዚያ በኋላ በሌሎች ላይ ተጽዕኖ የማሳደር ኃይሉን ግን አጣ። ሰርቪተስ አለበቂ ምክንያት መገደሉ በአውሮፓ የነበሩትን አስተዋይ ሰዎች ሁሉ ከማስቆጣቱም በላይ ማንም ሰው በሃይማኖታዊ እምነቱ ምክንያት መገደል የለበትም የሚል አቋም የነበራቸው የግል ነፃነት አራማጆች ኃይለኛ መከራከሪያ ነጥብ አገኙ። ለሃይማኖታዊ ነፃነት ይታገሉ የነበሩት እነዚህ ሰዎች ከምንጊዜውም ይበልጥ በትግላቸው ለመቀጠል ቆርጠው ተነሱ።
ጣሊያናዊው ገጣሚ ካሚሎ ሬናቶ “አምላክም ሆነ መንፈሱ እንዲህ ያለውን [በሰርቪተስ ላይ የተወሰደውን] እርምጃ አይደግፉም። ክርስቶስ በካዱት ሰዎች ላይ እንዲህ አላደረገም” በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል። የሰብዓዊነት ፍልስፍና አራማጅ የነበረው ፈረንሳዊው ሴባስቲያ ሻቴዮ “በሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርት ላይ የተነሳን ተቃውሞ ለማስቆም ብሎ ሰውን መግደል የሰውየውን ሕይወት ከማጥፋት ያለፈ ጥቅም የለውም” በማለት ጽፏል። ሰርቪተስ ራሱም “አምላክ የመረጣቸውም እንኳ ሊሳሳቱ እንደሚችሉ እያወቅን ሰዎች ቅዱስ ጽሑፉን በሚተረጉሙበት ጊዜ ተሳሳቱ ብሎ መግደል ከባድ ወንጀል እንደሆነ እቆጥረዋለሁ” ብሎ ነበር።
የሰርቪተስ መገደል ያስከተለውን ዘላቂ ውጤት በሚመለከት ማይክል ሰርቪተስ—ታላቅ ምሑር፣ የሰብዓዊነት ፍልስፍና አራማጅና ሰማዕት የተሰኘው መጽሐፍ “የሰርቪተስ ሞት፣ ከአራተኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ሰፍኖ በቆየው አመለካከትና አስተሳሰብ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል” ብሏል። አክሎም “ከታሪክ አንጻር ሲታይ ሰርቪተስ የሞተው በዘመናዊው ኅብረተሰብ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ዜጋ የሕሊና ነፃነቱ እንዲከበርለት ነበር” ብሏል።
በ1908 አንማስ በምትባል የፈረንሳይ ከተማ ሰርቪተስ ከሞተበት ሥፍራ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የመታሰቢያ ሐውልት ቆመለት። በሐውልቱ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍ እንደሚከተለው ይላል:- “ማይክል ሰርቪተስ፣ . . . የጂኦግራፊ ባለሞያ፣ ሐኪም፣ የሰውን አካል ውስጣዊ አሠራር ያጠና ሊቅ እንዲሁም በሳይንሳዊ ግኝቱ፣ የታመሙትንና የተቸገሩትን ለመርዳት ራሱን በመስጠቱና በአመለካከቱ ላይ ተጽዕኖ እንዲደረግበት ባለመፍቀድ በወሰደው ቁርጥ አቋም ለሰው ልጅ ውለታ የዋለ . . . እምነቱ የማይናወጥ ሰው ነበር። ለእውነት ሲል ሕይወቱን ሠውቷል።”
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የስፔን ባለ ሥልጣናት የካቶሊክን ሃይማኖት ለመቀበል ፈቃደኛ ያልነበሩትን 120,000 አይሁዶች በግዞት ከአገር ያስወጡ ሲሆን የአረብና የበርበር ተወላጅ የሆኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በእንጨት ላይ ሰቅለው አቃጥለዋል።
b በሚያዝያ 15, 2004 የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የወጣውን “በርካታ ቋንቋዎችን የያዘው የኮምፕሉቴንስ መጽሐፍ ቅዱስ—ታሪካዊ የትርጉም መሣሪያ” የሚል ርዕስ ተመልከት።
c ሰርቪተስ፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠ መግለጫ በሚለው ጽሑፉ ላይ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት አደናጋሪና ግራ የሚያጋባ እንደሆነ ገልጾ በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ ለሥላሴ ድጋፍ የሚሆን “አንድም ቃል” እንደሌለ ተናግሯል።
d ሰርቪተስ በእስር ቤት ሳለ በጻፈው የመጨረሻ ደብዳቤው ላይ ፊርማውን ያሠፈረው “ብቸኛው፣ ሆኖም እርግጠኛ በሆነው የክርስቶስ ጥበቃ የሚተማመነው ማይክል ሰርቪተስ” በማለት ነበር።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ሰርቪተስና የይሖዋ ስም
ሰርቪተስ እውነትን ለማግኘት የነበረው ፍላጎት ይሖዋ በሚለው ስም እንዲጠቀም አድርጎታል። ዊልያም ቲንደል ይህን ስም ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም ያሉትን መጻሕፍት ሲተረጉም ከተጠቀመበት ከጥቂት ወራት በኋላ ሰርቪተስ የሥላሴ ስህተት የተሰኘውን መጽሐፍ ያሳተመ ሲሆን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ይሖዋ በሚለው ስም ተጠቅሟል። በዚህ መጽሐፍ ላይ እንዲህ የሚል ማብራሪያ ሰጥቷል:- “ከስሞች ሁሉ ይበልጥ ቅዱስ የሆነው יהוה የሚባለው ሌላው ስም . . . እንደሚከተለው ያለ ፍቺ ሊሰጠው ይችላል፤ . . . ‘እንዲሆን የሚያደርግ፣’ ‘ወደ መሆን የሚያመጣ፣’ ‘የሕልውና ምንጭ።’” በተጨማሪም “ይሖዋ የተባለው ስም ሊሠራበት የሚገባው አብን ብቻ ለማመልከት ነው” በማለት ጽፏል።
ከዚህም ሌላ ሰርቪተስ ከታች በሥዕሉ ላይ የሚታየውንና በሳንቴስ ፓኒነስ የተዘጋጀውን እውቅ የላቲን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እርማት አድርጎ በ1542 አሳትሞታል። ሰርቪተስ በሕዳጉ ላይ ባሠፈረው ሰፊ ማብራሪያ ውስጥ መለኮታዊውን ስም በድጋሚ አስገብቶታል። በዋናው ጽሑፍ ውስጥ “ጌታ” የሚለው ቃል ለተተካባቸው እንደ መዝሙር 83:18 ለመሳሰሉ ወሳኝ ጥቅሶች፣ በሕዳጉ ላይ ባሠፈረው ማብራሪያ ይሖዋ የተባለውን ስም አስገብቷል።
ሰርቪተስ የክርስትና መመለስ በተሰኘው የመጨረሻ ጽሑፉ ላይ ይሖዋ የሚባለውን መለኮታዊ ስም በሚመለከት “በጥንት ዘመን ይህን ስም የሚጠሩ ብዙ ሰዎች እንደነበሩ . . . ግልጽ ነው” በማለት ተናግሯል።
[ሥዕል]
ለሰርቪተስ መታሰቢያ በአንማስ፣ ፈረንሳይ የቆመ ሐውልት
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስፔን የሚኖሩ ሙስሊሞች በግዴታ ሲጠመቁ የሚያሳይ የ15ኛው መቶ ዘመን ቅርጽ
[ምንጭ]
Capilla Real, Granada
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የሥላሴ ስህተት” የተሰኘው መጽሐፍ የመጀመሪያ ገጽ
[ምንጭ]
በ1531 በማይክል ሰርቪተስ ከተዘጋጀው ዴ ትሪኒታትስ ኤሮሪበስ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰርቪተስ ከሳንባችን ጋር በተያያዘ በሰውነታችን ውስጥ ስለሚከናወነው የደም ዝውውር ጥናት አካሂዷል
[ምንጭ]
Anatomie descriptive et physiologique, Paris, 1866-7, L. Guérin, Editor
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመድኃኒት ጥናት መስክ “ዩኒቨርሳል ትሪቲስ ኦን ሲረፕስ” የተሰኘው የሰርቪተስ መጽሐፍ ፈር ቀዳጅ ነበር
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጆን ካልቪን የሰርቪተስ ቀንደኛ ጠላት ሆነ
[ምንጭ]
Biblioteca Nacional, Madrid
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Biblioteca Nacional, Madrid