የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 3/07 ገጽ 16-19
  • ካምቻትካ—በፓስፊክ የሩሲያ ውብ ምድር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ካምቻትካ—በፓስፊክ የሩሲያ ውብ ምድር
  • ንቁ!—2007
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እሳተ ገሞራዎችና ፍል ውኃዎች
  • ድቦች፣ ሳልሞንና የባሕር ንስሮች
  • የካምቻትካ ነዋሪዎች
  • የርዕስ ማውጫ
    ንቁ!—2007
  • እሳተ ገሞራ አደጋው ያሰጋሃልን?
    ንቁ!—1997
  • የአትላንቲኩ ሳልሞን—ሕልውናው አደጋ ላይ የወደቀው “ንጉሥ”
    ንቁ!—2005
  • የእሳተ ገሞራ አደጋ ባንዣበበበት አካባቢ መኖር
    ንቁ!—2007
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2007
g 3/07 ገጽ 16-19

ካምቻትካ—በፓስፊክ የሩሲያ ውብ ምድር

ሩሲያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ከሦስት መቶ ዓመታት በፊት የሩሲያ አሳሾች እስያ ውስጥ ወደ ምሥራቅ ሲጓዙ በስተ ደቡብ በኩል ወደ ፓስፊክ ውቅያኖስ ገባ ብሎ የሚታየውንና የኧኮተስክን ባሕር ከቤሪንግ ባሕር የሚከፍለውን ተራራማ ባሕረ ገብ መሬት አገኙ። በስፋት ከጣሊያን ትንሽ የሚበልጠው ይህ ምስጢራዊ ውበት የተጎናጸፈ ምድር አሁንም እንኳ በውጭ አገር ሰዎች ዘንድ እምብዛም አይታወቅም።

ከብሪታንያ ትንንሽ ደሴቶች ጋር በተመሳሳይ የኬንትሮስ መሥመር ላይ የሚገኘው ካምቻትካ ቀዝቀዝ ያለ የአየር ጠባይ አለው። በባሕር ዳርቻ አቅራቢያ የክረምቱ ቅዝቃዜ መካከለኛ ሲሆን በመሃል አገር ባሉት አንዳንድ ቦታዎች ግን መሬቱ ከስድስት ሜትር በላይ ጥልቀት ባለው አመዳይ በረዶ ይሸፈናል፤ እንዲያውም አንዳንዴ ጥልቀቱ እስከ 12 ሜትር ይደርሳል! ይህ ባሕረ ገብ ምድር በበጋው ወራት ብዙውን ጊዜ በጭጋግ የሚሸፈን ሲሆን ኃይለኛ ነፋስም ይነፍስበታል። እሳተ ገሞራ በፈነዳበት አካባቢ ያለው የካምቻትካ አፈር ጥሩ ዝናብ ሲያገኝ እንጆሪን የመሳሰሉ የተለያዩ ተክሎችን፣ በሰው ቁመት ልክ የሚያድጉ ረጃጅም የሣር ዓይነቶችንና የመስክ ንግሥት በመባል እንደምትጠራው ውብ ጽጌረዳ ያሉ የሚያማምሩ የዱር አበቦችን ያበቅላል።

ከኃይለኛው ነፋስና ከአመዳዩ ክብደት የተነሳ ግንዶቻቸውና ቅርንጫፎቻቸው ጎብጠውና ተወለጋግደው የሚታዩት ስቶን ወይም ኧርማን በርች የሚባሉ የዛፍ ዓይነቶች የአገሩን አንድ ሦስተኛ ሸፍነውታል። ችግር የሚችሉትና በቀስታ የሚያድጉት እነዚህ ዛፎች ጠንካሮች ናቸው፤ ሥሮቻቸው ጥብቅና ቆንጥጠው መያዝ የሚችሉ መሆናቸው በማንኛውም ቦታ፣ በገደል አፋፍ ላይም እንኳ ሳይቀር አግድም እንዲያድጉ አስችሏቸዋል! እነዚህ ዛፎች በሰኔ ወር ይኸውም ገና በረዶው ቀልጦ ሳያልቅ ቅጠላቸው ይለመልምና በነሐሴ የክረምቱን መቃረብ ለማብሰር ወደ ቢጫነት ይቀየራሉ።

እሳተ ገሞራዎችና ፍል ውኃዎች

በፓስፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ ከፍተኛ የመሬት ነውጥ ባለበት አካባቢ የሚገኘው ካምቻትካ 30 የሚያህሉ ንቅ እሳተ ገሞራዎች አሉት። “በጣም ውብ” እንደሆነ የሚነገርለት የክላይቼፍስኬያ እሳተ ገሞራ ከፍታው ከባሕር ወለል በላይ 4,750 ሜትር የሚደርስ መሆኑ በአውሮፓም ሆነ በእስያ ከሚገኙት ንቅ እሳተ ገሞራዎች መካከል ትልቁ ያደርገዋል። የሩሲያ አሳሾች እግራቸው ካምቻትካን ከረገጠበት ከ1697 አንስቶ በዚህ ባሕረ ገብ መሬት ላይ ከ600 የሚበልጡ የምድር መናወጦች ተመዝግበዋል።

በ1975/76 በቶልባቺክ አካባቢ የደረሱት የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች ከ2,500 ሜትር በላይ ከፍታ ያለው ነበልባል ፈጥረው ነበር! እየተትጎለጎለ በሚወጣው የአመድ ደመና ውስጥ የመብረቅ ብልጭታ ይታይ ነበር። ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ያለማቋረጥ የቀጠለው ፍንዳታ አራት አዳዲስ የእሳተ ገሞራ ተራሮችን ፈጥሯል። በዚህም ሳቢያ ሐይቆችና ወንዞች የደረቁ ሲሆን ከፍተኛ ግለት የነበረው አመድ ደኑንም ሙሉ በሙሉ አደረቀው። በዚህም ሳቢያ የተንጣለለው ገጠራማ አካባቢ ወደ በረሃነት ተለወጠ።

ደግነቱ ብዙዎቹ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች የደረሱት ሰው ከሚኖርበት አካባቢ ርቀው በመሆኑ በዚህ ሳቢያ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በጣም ጥቂት ነው። ይሁን እንጂ ጎብኚዎች፣ በተለይም በኬክፔነች እሳተ ገሞራ ግርጌ ወደሚገኘው የሞት ሸለቆ ወደሚባለው ቦታ በሚሄዱበት ጊዜ መጠንቀቅ እንዳለባቸው የሚጠቁሙ አንዳንድ ምክንያቶችም አሉ። ነፋስ በማይኖርበትና በተለይም ደግሞ በረዶው ሟምቶ በሚያልቅበት የፀደይ ወራት መርዛማ የሆነ የእሳተ ገሞራ አየር በሸለቆው ውስጥ ስለሚከማች የዱር አራዊቱን ሊፈጃቸው ይችላል። በአንድ ወቅት በሸለቆው ውስጥ አሥር ድቦችና በርካታ ቁጥር ያላቸው ትንንሽ እንስሳት ተረፍርፈው ተገኝተዋል።

ኡዞን ካልዴራ ተብሎ በሚጠራውና እሳተ ገሞራ በፈጠረው ሰፊ ጎድጓዳ ሥፍራ ላይ የሚንተከተክ ጭቃ እንዲሁም የተለያዩ ቀለማት ያላቸው አልጌዎች የሞሉባቸው የሚጨሱ ሐይቆች ይገኛሉ። በዚሁ አካባቢ በ1941 የፍል ውኃ ፊንፊኔዎች (Geysers) ሸለቆም ተገኝቷል። በአንዳንድ አካባቢዎች ፍል ውኃዎች ከመሬት ውስጥ ፊን ፊን እያሉ የሚወጡት በየሁለትና ሦስት ደቂቃው ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በጥቂት ቀናት ልዩነት ነው። ጎብኚዎች ከፔትሮፓቭሎቭስክ ካምቻትስኪ ከተማ በስተ ሰሜን በኩል 180 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኙት ወደነዚህ አስደናቂ ቦታዎች በሄሊኮፕተር ይሄዳሉ። ይሁን እንጂ በቋፍ ላይ ያለውን ሥነ ምሕዳር ላለማዛባት ሲባል የጎብኚዎቹ ቁጥር ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግበታል። ለዚህም ሲባል በካምቻትካ የሚገኙ አምስት አካባቢዎች በዓለም ቅርስነት ተመዝግበው ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው።

በካምቻትካ በርካታ የፍል ውኃ ምንጮች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ፍል ውኃዎች ውስጥ አብዛኞቹ ሙቀታቸው በ30 እና በ40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ መካከል ነው፤ ይህም ጎብኚዎቹን የሚያስደስት ከመሆኑም በላይ ቀዝቃዛ ለሆኑት ረዥም የክረምት ወራት ጥሩ ማካካሻ ነው። የከርሰ ምድር ሙቀት የሚፈጥረው እንፋሎትም የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ያገለግላል። እንዲያውም ሩሲያ የመጀመሪያውን በእንፋሎት የሚሠራ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የገነባችው በዚህ ባሕረ ገብ መሬት ላይ ነበር።

ድቦች፣ ሳልሞንና የባሕር ንስሮች

ቡናማ መልክ ያላቸው 10,000 የሚያህሉ ድቦች አሁንም በካምቻትካ ምድር ይፈነጫሉ። እነዚህ ድቦች አማካይ ክብደታቸው ከ150 እስከ 200 ኪሎ ግራም የሚደርስ ሲሆን ሰው ካልገደላቸው የዚህን ሦስት እጥፍ ክብደት ሊጨምሩ ይችላሉ። ኢተልመን ተብሎ በሚጠራው የአካባቢው ሕዝብ አፈ ታሪክ መሠረት ድብ እንደ ‘ወንድም’ ስለሚታይ እነዚህ እንስሳት በአክብሮት ይታዩ ነበር። ጠመንጃ ከመጣ በኋላ ግን ይህ ወንድማማችነት አከተመ። አሁን የአካባቢ ጥበቃ ባለ ሥልጣናት የእነዚህ እንስሳት የወደፊት ዕጣ እያሳሰባቸው ነው።

ድቦች ሰው ስለሚፈሩ እምብዛም አይታዩም። ይሁን እንጂ የዓሣ ዝርያ የሆኑት ሳልሞኖች በወንዞች ውስጥ ተራብተው መብዛት በሚጀምሩበት በሰኔ ወር ድቦቹ እነዚህን ዓሦች ለመብላት በብዛት ይመጣሉ። አንድ ድብ በአንድ ጊዜ ብዙ ዓሦችን ሊበላ ይችላል! ድቡ ይህን ያህል ብዙ የሚበላው ለምንድን ነው? ድቦች የምግብ እጥረት በሚኖርባቸው ቀዝቃዛ የክረምት ወራት ኃይላቸውን ለመቆጠብ ተኝተው ስለሚያሳልፉ ለዚያ ጊዜ የሚሆናቸውን በቂ ስብ በበጋው ወራት ማጠራቀም ስለሚኖርባቸው ነው።

ሳልሞን ዓሣን መብላት የሚወደው ሌላ እንስሳ ደግሞ ስቴለርስ ሲ ኢግል የተባለው ንስር ነው። በጣም ድንቅ የሆነው ይህ ንስር ሁለቱ ክንፎቹ ከጫፍ ጫፍ ርዝመታቸው 2.5 ሜትር ይደርሳል። መልኩ በአብዛኛው ጥቁር ሲሆን ትከሻው ላይ ነጭ ጣል ጣል አድርጎበታል፤ እንዲሁም ሾል ያለ ነጭ ጭራ አለው። ቁጥሩ እየቀነሰ መጥቶ 5,000 የደረሰው ይህ ንስር የሚገኘው በዚህ አካባቢና አልፎ አልፎም አሉሸን እና ፕሪበሎፍ በተባሉት የአላስካ ደሴቶች ላይ ብቻ ነው። እነዚህ ንስሮች ጎጆ ከሠሩ በኋላ ያንኑ እየጠጋገኑና እያሰፉ ከዓመት ዓመት ይኖሩበታል እንጂ ሌላ አይቀይሩም። መሃል ለመሃል ርዝመቱ 3 ሜትር የሚደርሰው አንድ የንስር ጎጆ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ በርች የሚባለውን ዛፍ ሰንጥቆታል!

የካምቻትካ ነዋሪዎች

በአሁኑ ጊዜ በካምቻትካ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ሩሲያውያን ቢሆኑም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአገሬው ተወላጆችም ይገኛሉ፤ ከእነዚህ መካከል በሕዝብ ብዛት ከፍተኛውን ደረጃ የያዘው በስተ ሰሜን የሚኖረው ከሪያክ የሚባለው ጎሳ ነው። በዚያ ከሚኖሩት ጎሳዎች መካከል የየራሳቸው ቋንቋ ያላቸው ቹክቼ እና ኢተልመን የሚባሉት ይገኙበታል። ብዙዎቹ የካምቻትካ ሕዝቦች የሚኖሩት የአስተዳደር ማዕከል በሆነችው በፔትሮፓቭሎቭስክ ካምቻትስኪ ነው። ቀሪው የአገሩ ክፍል ብዙም ሰው የማይኖርበት ሲሆን በባሕርና በወንዞች ዳርቻ ላይ ወደሚገኙት ወደ አብዛኞቹ መንደሮች መሄድ የሚቻለው በጀልባ ወይም በአውሮፕላን ብቻ ነው።

የካምቻትካ ኢኮኖሚ ዓሣና ሸርጣን በማጥመድ ላይ የተመሠረተ ነው። በተለይም ደግሞ የዚያ አካባቢ ቀይ ሸርጣን በጣም ተወዳጅ ነው። ከአንዱ እግር ጫፍ እስከ ሌላው እግር ጫፍ ድረስ 1.7 ሜትር የሚረዝመው ይህ ሸርጣን በጣም የሚያምር ሲሆን ለሽያጭ ለቀረበበት ጠረጴዛም ድምቀት ይጨምርለታል።

ከ1989 ጀምሮ የይሖዋ ምሥክሮች ሌላ ዓይነት የዓሣ ማጥመድ ሥራ ለማከናወን ወደ ካምቻትካ ሲሄዱ ቆይተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች “ሰዎችን አጥማጆች” እንደመሆናቸው መጠን ተገልለው ለሚኖሩት የካምቻትካ ሕዝቦች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ሲሰብኩ ቆይተዋል። (ማቴዎስ 4:19፤ 24:14) አንዳንዶቹ ለምሥራቹ በጎ ምላሽ የሰጡ ከመሆኑም በላይ ሌሎችም ፍጡርን ሳይሆን ፈጣሪ የሆነውን ይሖዋ አምላክን እንዲያውቁና እንዲያመልኩ እየረዱ ነው። በውጤቱም በአካባቢው የሚኖሩ በርካታ ሰዎች በጣም ተስፋፍቶ ከሚገኘው ክፉ መናፍስትን የመፍራት ልማድ ነፃ እየወጡ ነው። (ያዕቆብ 4:7) በተጨማሪም ወደፊት መላዋ ምድር ከክፋትና ከክፉ አድራጊዎች ጸድታ “ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ” የምትሞላበት ጊዜ እንደሚመጣ እየተማሩ ነው።—ኢሳይያስ 11:9

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ዕጹብ ድንቅ የሆነ ካልዴራ

ኡዞን ካልዴራ በመባል የሚታወቀው እሳተ ገሞራ የፈጠረው ሰፊ ጎድጓዳ ሥፍራ ከጫፍ ጫፍ 10 ኪሎ ሜትር ያህል ርዝመት አለው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ቀጥ ባለ ዳገት ላይ የሚገኘውን ይህን ሥፍራ በሚመለከት “የካምቻትካን ስም የሚያስጠሩ የተለያዩ ነገሮችን” ሰብስቦ ይዟል በማለት ይናገራል። በዚህ ሥፍራ ፍልና ቀዝቃዛ ምንጮች፣ የሚንተከተክ ጭቃ ያለባቸው ድስት መሰል ጉድጓዶች፣ እሳተ ገሞራ የፈጠራቸው የጭቃ ጉብታዎች እንዲሁም ዓሦችና ዳክዬዎች የሚርመሰመሱባቸውና ተክሎች የሞሉባቸው ሐይቆች ይገኛሉ።

ሚራክልስ ኦቭ ካምቻትካ ላንድ የተሰኘው መጽሐፍ፣ የመከር ወቅት በጣም አጭር ቢሆንም በዚህ ጊዜ “በምድር ላይ” ውበት የተርከፈከፈበት “እንዲህ ያለ ቦታ የለም” በማለት ይናገራል። ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ምድር፣ የበርች ዛፎች ካላቸው ደማቅ ቢጫና ወርቃማ መልክ ጋር ሲዋሃድ እንዲሁም ራቅ ራቅ ብለው ከሚገኙት የሚንተከተኩ ጭቃዎች ውስጥ የሚወጣው ነጭ እንፋሎት፣ ደማቅ ሰማያዊ መልክ ካለው ሰማይ ጋር ሲቀናጅ የሚፈጥረው ውበት በጣም ልዩ ነው። በተጨማሪም ጫካው ማለዳ ላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አመዳይ ያዘሉ ቅጠሎች ወደ መሬት ሲወድቁ በሚፈጥሩት የኮሽታ ድምፅ አማካኝነት ግሩም “ጣዕመ ዜማ” ያሰማል፤ ይህም ክረምት መቃረቡን የሚያበስር ክስተት ነው።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ቀሳፊ ሐይቅ!

በ1996፣ ፈንድቶ የወጣለት እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ የነበረ እሳተ ገሞራ ከካሪምስኪ ሐይቅ በታች ፈንድቶ የአካባቢውን ደን እንዳልነበረ ያደረገ 10 ሜትር ከፍታ ያለው ሞገድ አስነስቶ ነበር። በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የሐይቁ ውኃ ሕይወት ያለው ነገር ወደማይኖርበት አሲድነት ተለወጠ። አንድሩ ሎገን የተባሉ ተመራማሪ እንደገለጹት የሐይቁ ዳርቻ እሳተ ገሞራ በተፋቸው ነገሮችና በሞገዱ ተመትቶ የነበረ ቢሆንም በአካባቢው የሞተ እንስሳ አልተገኘም። ተመራማሪው ሲናገሩ “ከፍንዳታው ቀደም ብሎ በካሪምስኪ ሐይቅ ውስጥ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዓሦች (በዋነኝነት ሳልሞን እና ትራውት) እንደሚኖሩ ይታወቅ ነበር። ከፍንዳታው በኋላ ሐይቁ ሕይወት አልባ ሆነ።” ይሁን እንጂ በርካታ ዓሦች ከጥፋቱ ሳይተርፉ አልቀረም። የሳይንስ ሊቃውንት ለዚህ ምክንያቱ የውኃው ኬሚካላዊ ይዘት መለወጡ ዓሦቹን አስበርግጓቸው በአቅራቢያው ወደሚገኘው የካሪምስኪ ወንዝ እንዲሸሹ አድርጓቸው ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሩሲያ

ካምቻትካ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ