እሳተ ገሞራ አደጋው ያሰጋሃልን?
ረመጥ የሆነ አመድና በተለያየ ቀለማት ያሸበረቀ ትፍ ቅላጭ ድንጋይ (lava) የሚተፉ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች በምድር ላይ ያለውን ተፈጥሮአዊ ኃይል ከሚያንጸባርቁ እጅግ አስደናቂ የሆኑ ትዕይንቶች መካከል የሚደመሩ ናቸው። እንዲህ ዓይነቱን ክስተት በዓይንህ አልተመለከትክ ይሆናል፤ ሆኖም በእሳተ ገሞራ ፍል ውኃ ታጥበህ ወይም ደግሞ የእሳተ ገሞራ አመድ በተቀላቀለበት ለም አፈር ላይ ካደገ እህል የተዘጋጀ ምግብ ተመግበህ ረክተህ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም አንዳንዶች እቤታቸው ድረስ በሚመጣው ከውስጠ ምድር ሙቀት (geothermal) የሚመነጭ ኃይል ይገለገላሉ።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ንቅ ገሞራ (active volcano) ባለበት አካባቢ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች እሳተ ገሞራ ባደረሰው አደጋ ያለቁ ሰዎችንና የተከሰተውን ውድመት ተመልክተዋል። ዩ ኤስ ኤ ውስጥ በዋሽንግተን ክፍለ ግዛት ደቡባዊ ምዕራብ በሚገኘው ሴይንት ሄለንስ ተራራ ላይ ግንቦት 18, 1980 ኃይለኛ ፍንዳታ ከደረሰ ወዲህ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የማያቋርጡ የሚመስሉ ቀሳፊ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች በተከታታይ ተከስተዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ቀደም ብለው በነበሩት ሰባት አሥርተ ዓመታት ከሞቱት ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር በልጧል፤ በንብረት ላይ የደረሰው ጥፋትም በብዙ መቶ ሚልዮን ዶላር የሚገመት ነው። በእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች ወቅት ወደ ላይ በተረጨው አመድ ሳቢያ አውሮፕላኖች መብረር ተስኗቸው ያሰቡት ቦታ ሳይደርሱ ለማረፍ ተገደዋል።
ከሁሉ ይበልጥ ከፍተኛ ጥፋት ያደረሱት ፊሊፒንስ ውስጥ በፒናቱቦ ተራራ ላይ እንዲሁም ኮሎምቢያ ውስጥ በኔቫዶ ደል ሩዪዝ የደረሱት ፍንዳታዎችና ጭቃፍሶች (mudflows) ናቸው። በፊሊፒንስ የተከሰተው እሳተ ገሞራ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ቤቶችን እንዳልነበሩ ያደረገ ሲሆን የኮሎምቢያው ደግሞ ከ22,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ሌሎች አደጋዎችም ሊከሰቱ ይችላሉ። በዩ ኤስ የሥነ ምድር ጥናት ውስጥ የሚሠሩት ሮበርት ቲሊንግና ፒተር ሊፕማን የተባሉ የእሳተ ገሞራ ጠበብት “በ2000 ዓመት ለእሳተ ገሞራ አደጋዎች የሚጋለጠው ሕዝብ ቁጥር ቢያንስ ወደ 500 ሚልዮን እንደሚደርስ” ተናግረዋል።
እንግዲያው የሚከተሉትን ጥያቄዎች ማንሳትህ ጥሩ ሊሆን ይችላል:- ‘በምኖርበት አካባቢ ንቅ ወይም ንቅ ሊሆን የሚችል ገሞራ አለን? ይበልጥ አደገኛ የሆኑት የፍንዳታ ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው? ይበልጥ ቀሳፊ የሆኑ ሌሎች የፍንዳታ ዓይነቶችን ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸውን? የምኖርበት ቦታ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ሊከሰትበት የሚችልበት ከሆነ ለአደጋው እንዳልጋለጥ ምን ማድረግ እችላለሁ?’
ንቅ እሳተ ገሞራዎች የሚገኙት የት ነው?
በምትኖርበት አካባቢ ዋልጌ ገሞራ (dormant volcano) እንዳለና ይህ ገሞራ ወደ ንቅ ገሞራነት ቢለወጥ ያለጥርጥር የሆነ ችግር እንደሚያስከትልብህ ስታውቅ ትገረም ይሆናል። እሳተ ገሞራዎችን የሚያጠኑ ሳይንቲስቶች (ቮልኬኖሎጂስቶች ተብለው ይጠራሉ) ከጥቂት አሥርተ ዓመታት ወዲህ ንቅና ዋልጌ የሆኑ ገሞራዎችን ለይቶ በማወቅ ብቻ ሳይሆን እሳተ ገሞራዎች በአንዳንድ ቦታዎች የሚከሰቱት ለምን እንደሆነ በመረዳት ረገድም ተሳክቶላቸዋል።
ንቅ ገሞራዎች ተብለው የተመዘገቡ ከ500 የሚበልጡ እሳተ ገሞራዎች የሚገኙባቸውን ቦታዎች የሚያሳየውን ካርታ (ገጽ 17) ተመልከት። ከእነዚህ መካከል አንተ በምትኖርበት አካባቢ የሚገኝ እሳተ ገሞራ አለን? ፍል ውኃ፣ ውርውር ፍል ውኃ (geysers) እና ጭሳማ ፍል ውኃ (fumaroles) ያለባቸው ሌሎች ቦታዎችም በውስጣቸው ዋልጌ ገሞራዎች እንዳሉ ያመለክታሉ፤ እነዚህም ቢሆኑ ወደፊት ወደ ንቅ ገሞራነት ሊለወጡ ይችላሉ። ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ንቅ ገሞራዎች በሰላማዊ ውቅያኖስ ዳርቻዎች እሳት ቀለበት (Ring of Fire) ተብሎ በሚጠራው ቦታ የሚገኙ ናቸው። ከእነዚህ እሳተ ገሞራዎች መካከል አንዳንዶቹ በአህጉራቱ ውስጥ ይከሰታሉ፤ ለዚህም በሰሜን አሜሪካ በሚገኙት የካስኬድ ተራሮችና በደቡብ አሜሪካ በሚገኙት በአንዲዝ ተራሮች ላይ ያሉትን እሳተ ገሞራዎች እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ሌሎቹ ደግሞ በውቅያኖስ ውስጥ በሚገኙት እንደ አሉሻን፣ ጃፓን፣ ፊሊፒንስና ደቡባዊ ኢንዶኔዥያ ባሉት ደሴቶች ላይ እንደ ሰንሰለት ተቀጣጥለው የሚገኙ ናቸው። እሳተ ገሞራዎች በሜዲትራንያን ውስጥና በአቅራቢያው ባሉ ቦታዎችም በብዛት ይገኛሉ።
ሳይንቲስቶች እነዚህ እሳተ ገሞራዎች የሚገኙት ግዙፍና ተንቀሳቃሽ በሆኑ የምድር ቅርፊት (crust) ጉማጆች ወይም ስፍሃኖች (plates) ጠርዞች ላይ በተለይ ደግሞ የውቅያኖስ ስፍሃን ከአህጉር ስፍሃን ሥር በሚገባባቸው ቦታዎች ላይ እንደሆነ መገንዘብ ችለዋል። ይህ ሂደት ግብተ ምድር (subduction) ይባላል። ይህ ሂደት የሚያስከትለው ሙቀት ወደ ላይኛው የምድር ገጽ የሚወጣ ቅላጭ ድንጋይ (magma) ይፈጥራል። ከዚህም በተጨማሪ በስፍሃኖቹ መካከል የሚፈጠረው ድንገተኛ እንቅስቃሴ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ በሚከሰትባቸው በአብዛኞቹ ቦታዎች ኃይለኛ ርዕደ ምድር ያስከትላል።
በተጨማሪም እሳተ ገሞራዎች የውቅያኖስ ስፍሃኖች በሚለያዩባቸው ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ፍንዳታዎች የሚከሰቱት በውቅያኖስ ወለል ውስጥ በመሆኑ ሰዎች አያዩአቸውም። ይሁን እንጂ አይስላንድ በተባለችው ደሴት ላይ የምትኖር ከሆነ ሰሜንና ደቡብ አሜሪካን አጠቃለው የያዙት ስፍሃኖች አውሮፓንና አፍሪካን አጠቃለው ከያዙት ስፍሃኖች ተለያይተው በሚገኙበት ቦታ ላይ ማለትም በአትላንቲክ ውቅያኖስ መሀል ካለው ሸንተረር ጋር ከተያያዘው ሬኪያንስ ሸንተረር በላይ ነህ ማለት ነው። በሌሎች ጥቂት ሁኔታዎች ደግሞ ነጠል ብለው ከቅርፊተ ዝርጌ (crustal plates) ሥር የሚገኙት ሙቅ ሥፍራዎች በሃዋይና በአፍሪካ አህጉር ትልልቅ እሳተ ገሞራዎች እንዲከሰቱ አድርገዋል።
አደጋዎቹ ምንድን ናቸው?
አንድ እሳተ ገሞራ የሚፈጥረው አደጋ መጠን የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎችንና ከእነዚህ ፍንዳታዎች ጋር የተያያዙ አደጋዎችን ስፋት ጨምሮ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባደረገው እንቅስቃሴ ይወሰናል። የአደጋው መጠን በአደጋው ቀጣና የሚኖረውን ሕዝብ ብዛትና ዝግጁነት የሚያንጸባርቅ ነው። በመጀመሪያ አደጋዎቹን እንመርምር።
አብዛኛውን ጊዜ ይበልጥ አደገኛ የሆኑ ፍንዳታዎችን የሚያስከትለው በውስጡ ከፍተኛ የሲሊካ ክምችት ያለው ቅላጭ ድንጋይ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ቅላጭ ድንጋይ በጣም ጠጣር የሆነ ይዘት ያለው ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ጋዞቹ እሳተ ገሞራው ፈንቅሎ እንዲወጣ የሚያደርግ በቂ ግፊት እስኪያከማቹ ድረስ እሳተ ገሞራውን ለጊዜው ተጭኖ ሊያቆየው ይችላል። በውስጡ ከፍተኛ የሲሊካ ክምችት ያለው ቅላጭ ድንጋይ ወደ ጠጣር ድንጋይ ተለውጦ ግራጫ መልክ ያለው አለት ይሆናል፤ ይህ ደግሞ በስፍሃን ጠርዞች ላይ ባሉ እሳተ ገሞራዎች በብዛት የሚታይ ነገር ነው። በተጨማሪም ወደ ላይ እየወጣ ያለ ቅላጭ ድንጋይ ከውኃ ጋር ተገናኝቶ ውኃውን ወዲያው እንዲተን ሲያደርገው ፍንዳታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። በከፍተኛ ፍንዳታዎች የሚፈጠረው ረመጥ አመድ ሊገድል ይችላል፤ በ1902 በመካከለኛው አሜሪካ በካሪቢያን ክልል የተከሰቱ ሦስት እሳተ ገሞራዎች በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ከ36,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት አጥፍተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በውቅያኖሶች ውስጥ ባሉ ሙቅ ሥፍራዎች እንዲሁም ስፍሃኖች በሚከፈሉባቸውና በሌሎችም ቦታዎች የሚፈጠሩ ብዙ እሳተ ገሞራዎች ባመዛኙ የጥቁር ድንጋይ ክምችት ያለባቸው ናቸው፤ ይህ ጥቁር ድንጋይ የያዘው የሲሊካ መጠን አነስተኛ ቢሆንም ከፍተኛ የብረትና የማግኒዝየም ክምችት አለው። የጥቁር ድንጋይ ቅላጭ ፈሳሽ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ፍንዳታው መጠነኛ ወይም ምንም ኃይል የሌለው ነው። በተጨማሪም የሚተፋው ቅላጭ ድንጋይ ቀስ እያለ የሚፈስ በመሆኑ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ሰዎች በቀላሉ ከአደጋው ሊያመልጡ የሚችሉት ዓይነት ነው። ሆኖም እነዚህ ፍንዳታዎች ለረጅም ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ፤ በሃዋይ ደሴት ውስጥ የተከሰተው የኪላኡኤ እሳተ ገሞራ ከ1983 ጥር ወር አንስቶ ለረጅም ጊዜ ሲፈነዳ ቆይቷል። ምንም እንኳ እንዲህ ዓይነቶቹ ፍንዳታዎች በንብረት ላይ ከፍተኛ ጥፋት ቢያደርሱም በሰው አካልና በሕይወት ላይ እምብዛም ጉዳት አያደርሱም።
አንዳንድ ፍንዳታዎች የተፉትን አመድ በእሳተ ገሞራው ዙሪያ ይቆልሉታል፤ ይህም ሽርትት (landslide) ሊፈጥር ወይም ደግሞ የአመድ ቁልሉ ከፍተኛ መጠን ካለው በረዶ ወይም ውኃ ጋር ሲቀላቀል ወደ ጭቃነት ተለውጦ ወዲያውኑ ወደ ሸለቆዎች ሊወርድ ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ጭቃፍስ (ላሃር ተብሎም ይጠራል፤ ኢንዶኔዥያውያን ትፍ ቅላጭ ድንጋይን ለማመልከት ከሚጠቀሙበት ቃል የተወሰደ ነው) እሳተ ገሞራው ከፈነዳበት ቦታ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ ሊሄድ ይችላል። ምናልባትም ይህ የሚሆነው ፍንዳታዎቹ ከጠፉ ከብዙ ጊዜ በኋላም ሊሆን ይችላል።
በውቅያኖስ ውስጥ በሚከሰት ፍንዳታ ወይም ደግሞ በባሕር ውስጥ በሚገኝና አፉ ከባሕር ወለል ከፍ ብሎ በወጣ እሳተ ገሞራ ዙሪያ ባለ ሽርትት አማካኝነት የሚፈጠረውና ማእበለ ርዕደ ምድር ተብሎ የሚጠራው ኃይለኛ የውቅያኖስ ማዕበል ብዙ ጊዜ የማይከሰት ቢሆንም እንኳ በጣም ሰፊ የሆነ ቦታን የሚያካልል ነው። ይህ ኃይለኛ ማዕበል በሰዓት በመቶ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ሊያቋርጥ ይችላል። ማእበለ ርዕደ ምድር በውቅያኖስ ወለል ውስጥ የሚፈጠር በመሆኑ በዚያ በሚያልፉ መርከቦች ላይ የሚፈጥረው ሥጋት የለም፤ ሆኖም በምድር አጠገብ በሚገኝ የውቅያኖስ ዳርቻ ውስጥ በሚከሰትበት ጊዜ ርዝማኔው ወዲያውኑ ይጨምራል። የዚህ ማዕበል ጫፍ ከቤቶችና ከብዙ ሕንጻዎች በላይ ይሆናል። በ1883 ክራካታኡ ሲፈነዳ ማእበለ ርዕደ ምድር የጃቫንና የሱማትራን የባሕር ዳርቻዎች በመምታቱ 36,000 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በሕይወት ላይ ጉዳት ወይም ጥፋት ሊያደርሱ የሚችሉት ሌሎቹ የእሳተ ገሞራ አደጋዎች ደግሞ እየተፈናጠረ የሚመጣውን የእሳተ ገሞራ አመድና ቁርጥራጭ እንዲሁም በኃይለኛ ፍንዳታዎች፣ በመርዛማ ጭስ፣ አሲድ በተቀላቀለበት ዝናብና በርዕደ ምድር ሳቢያ በከባቢ አየር ውስጥ የሚከሰተውን ክውታዊ ሞገድ (shock wave) ያጠቃልላሉ። በዓለም ዙሪያ ያሉ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ብዙ እሳተ ገሞራዎች ተለይተው የታወቁ ከመሆኑም በላይ እሳተ ገሞራዎች ሊፈጠሩባቸው የሚችሉ ሌሎች በጣም በርካታ የሆኑ ቦታዎች ስላሉ እሳተ ገሞራዎች የሚያስከትሉትን አደጋ አጥንቶ ግልጽ በሆነ መንገድ ማስቀመጥ በእርግጥም በጣም ውስብስብና ፈታኝ የሆነ ሥራ ነው።
ከአደጋው ማምለጥ የምትችልበትን አጋጣሚ ማስፋት ትችላለህን?
የዓለም ሕዝብ ቁጥር እያደገ ሲሄድ አደገኛ እሳተ ገሞራዎች ሊከሰቱባቸው በሚችሉባቸው ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ አይቀርም። ከዚህም በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ዙሪያ የእሳተ ገሞራ እንቅስቃሴ እየጨመረ በመሄዱ ቮልኬኖሎጂስቶች እሳተ ገሞራ የሚያስከትለውን አደጋ ለመቀነስ ጥረታቸውን አጠናክረዋል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ፍንዳታዎች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ ለመተንበይ የተደረጉት ጥረቶች ሰምረው የብዙ ሰዎች ሕይወት ሊተርፍ ችሏል። ለእነዚህ ትንበያዎች መሠረት የሚሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው?
ብዙውን ጊዜ ፍንዳታዎች ከመፈጠራቸው በፊት በእሳተ ገሞራው ውስጥ ወይም ከእሳተ ገሞራው በታች ያለው ቅላጭ ድንጋይ ወደ ላይ እየገፋ በሚመጣበት ቦታ ርዕደ ምድር ይከሰታል። ቅላጭ ድንጋዩ ወደ ላይ መጥቶ እሳተ ገሞራው ውስጥ ሲከማች ግፊቱ እየጨመረ ይሄዳል። ጋዞች ይለቀቃሉ፤ በምድር ውስጥ ያለው ውኃ የሙቀቱና የአሲዱ መጠን ይጨምራል። በተጨማሪም ትልቅ ፍንዳታ ከመፈጠሩ በፊት አነስተኛ ፍንዳታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። እነዚህን እንቅስቃሴዎች ሁሉ መከታተል ይቻላል።
የሥነ ምድር ተመራማሪዎች ፍንዳታ ከመከሰቱ አስቀድሞ የአለት ምርመራውን መዝገብ በመመልከት ሊከሰት የሚችለውን አደጋ በተመለከተ ፍንጭ ሊያገኙ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ የእሳተ ገሞራው ፍሰት ዓይነትና በዚህ ሳቢያ የሚከሰቱት አደጋዎች ከዚህ በፊት ከተከሰቱት ጋር ተመሳሳይ ይሆናሉ፤ ወይም ደግሞ ፍንዳታዎች ቀደም ሲል ጥናት ከተደረገባቸው ሌሎች እሳተ ገሞራዎች ጋር ይመሳሰላሉ። በእንዲህ ዓይነቱ መረጃ ላይ በመመርኮዝ ብዙዎቹ እሳተ ገሞራዎች ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉባቸውን ቦታዎች የሚያመለክቱ ካርታዎች ተሠርተዋል።
ስለዚህ ሕይወትን ከእሳተ ገሞራ አደጋዎች ለማዳን የሚያስችሉት ቁልፍ ነገሮች ቮልኬኖሎጂስቶች በአደጋው መጠንና በእሳተ ገሞራ ሂደት ላይ የሚያደርጉትን ጥናትና ምርምር እንዲሁም የአካባቢ ባለ ሥልጣኖች አስቀድመው የሚሰጡትን የአደጋ ማስጠንቀቂያ ያካትታሉ። ርዕደ ምድርን በተመለከተ እስካሁንም ድረስ በአብዛኛው አስቀድሞ መተንበይ ያልተቻለ ቢሆንም ብዙዎቹን የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች ሂደት ግን በትክክል መከታተልና አደጋው ከመከሰቱ በፊት በዚያ አካባቢ የሚኖሩትን ሰዎች አስቀድሞ ማስወጣት ይቻላል። የአደጋ ቀጣናውን ለቅቆ መውጣቱ በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም በአብዛኛው የሰው ልጅ መዋቅሮች በኃይል ገንፍሎ የሚወጣው የእሳተ ገሞራ ፍሰትና ፍንዳታ ከሚያስከትለው ሙቀት እንዲሁም አውዳሚ ኃይሎች ከሆኑት ከሽርትት፣ ከጭቃፍስና ከማእበለ ርዕደ ምድር ሊጠብቁን የሚችሉ አይደሉም።
ምንም እንኳ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎችና ከዚሁ ጋር የተያያዙ አደጋዎች በሰው ልጅ ላይ የሚያደርሱትን ጉዳትና ጥፋት ለመቀነስ የሚያስችሉ የሚያስመሰግኑ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም የሰው ልጅ ፍንዳታዎችንና ከዚህ ጋር የተያያዙ አውዳሚ ነገሮችን መቶ በመቶ በትክክል አስቀድሞ በመተንበይ ከእሳተ ገሞራ አደጋዎች ሙሉ በሙሉ መጠበቅ የሚችልበት ደረጃ ላይ መድረስ አልቻለም። ሌላው ቀርቶ የእሳተ ገሞራዎችን ሂደት የሚከታተሉ አንዳንድ ሰዎች እንኳ ሳይታሰብ በተከሰተ ፍንዳታ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ይሁን እንጂ ንቅ ገሞራ ሊከሰት በሚችልበት ቦታ አቅራቢያ የምትኖር ከሆነ የአካባቢው ባለ ሥልጣናት የሚሰጡትን ማንኛውንም ማስጠንቀቂያ መከተል ይኖርብሃል። ይህን በማድረግ ከእሳተ ገሞራ አደጋ መትረፍ የምትችልበትን አጋጣሚ በእጅጉ ልታሰፋ ትችላለህ።—በአንድ አስትሮጂኦሎጂስት የተጠናቀረ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎችን ከሕዋ ላይ መተንበይ?
በሰከንድ አምስት ኪሎ ሜትር የሚጓዙና ከምድር 20,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ሳተላይቶች፣ እሳተ ገሞራዎች የሚያደርጉትን እያንዳንዱን ውጫዊ እንቅስቃሴ ቅንጣት ያህል ሳይሳሳቱ በትክክል መለካት መቻላቸው በግርምት የሚያስደምም ነው! ይህን ማድረግ የተቻለው ስትራቴጂያዊ በሆነ መንገድ በምድር ላይ የተተከሉ የሬዲዮ መቀበያዎችን ጨምሮ በርከት ያሉ ሳተላይቶችን ባቀፈው ግሎባል ፖዚሽኒንግ ሲስተም (ጂ ፒ ኤስ) አማካኝነት ነው። እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለመለካት ቢያንስ ቢያንስ አራት ሳተላይቶች ትክክለኛ ቦታቸውን እንዲይዙ ይደረጋል። ጊዜ የሚለካው ፍጹም ትክክል በሆኑ አቶሚክ ሰዓቶች ነው። እነዚህ መለኪያዎች በአብዛኛው የአየር ጠባይ ወቅት ሊሠሩ የሚችሉ ሲሆን በምድር ላይ ለሚካሄዱት ጥናቶች ብዙ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። የጂ ፒ ኤስ መለኪያዎች ከመፈንዳቱ በፊት ለብዙ ዓመታት እየተነፋና እያበጠ ሊሄድ የሚችለውን እሳተ ገሞራ አስቀድሞ ለመተንበይ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ሊያግዙ ይችላሉ። በአሁኑ ጊዜ ይህ ቴክኖሎጂ በአይስላንድ፣ በጣሊያን፣ በጃፓንና በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ እሳተ ገሞራዎች ላይ እየተሠራበት ይገኛል።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(For fully formatted text, see publication)
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንቅ ገሞራዎችንና ቅርፊተ ዝርጌዎችን የሚያሳይ የዓለም ካርታ
ንቅ ገሞራዎች
የስፍሃን ወሰኖች
ከ500 የሚበልጡት ንቅ ገሞራዎች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች መካከል አንዳንዶቹ በካርታው ላይ ምልክት ተደርጎባቸዋል
[ምንጭ]
Mountain High Maps™ copyright © 1993 Digital Wisdom, Inc.
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጃፓን ውስጥ የኡንዜን እሳተ ገሞራ የተፋው አመድ በአንድ መንደር ላይ ሲወርድ
[ምንጭ]
Orion Press-Sipa Press
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሴይንት ሄለንስ ተራራ ሲፈነዳ
[ምንጭ]
USGS, David A. Johnston, Cascades Volcano Observatory
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሲሲሊ ውስጥ የሚገኘው የኤትና ተራራ በቅርቡ ለ15 ወራት ያህል ትፍ ቅላጭ ድንጋይ ሲተፋ ቆይቷል
[ምንጭ]
Jacques Durieux/Sipa Press
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሃዋይ ውስጥ በኪላኡኤ ተራራ ላይ የፈነዳው እሳተ ገሞራ ለደሴቲቷ 200 ሄክታር መሬት ጨምሮላታል
[ምንጭ]
©Soames Summerhays/Photo Researchers