የጥንቃቄ ምክሮች ለአረጋውያን
አንዲት ልጅ የበረዶ ላይ ሸርተቴ እየተጫወተች ሳለ ድንገት አዳልጧት ወደቀች። በሴኮንዶች ውስጥ ብድግ ብላ ጨዋታዋን ቀጠለች፤ ትንሽ የኀፍረት ስሜት ተሰማት እንጂ ምንም አልሆነችም። በሌላ በኩል ደግሞ አንዲት አረጋዊት ቤታቸው ሳሉ ተደናቅፈው በመውደቃቸው የዳሌ አጥንታቸው ተሰበረ። በዚህም የተነሳ ቀዶ ሕክምና የተደረገላቸው ሲሆን እስኪያገግሙም ብዙ ወራት ወሰደባቸው። በአሁኑ ጊዜ እኚህ አረጋዊት እወድቃለሁ የሚለው ነገር ይበልጥ ስለሚያስፈራቸው እምብዛም እንቅስቃሴ አያደርጉም፤ በመሆኑም አቅማቸው እየተዳከመ መጥቷል።
በአውሮፓ ውስጥ ከሚኖሩት 65 ዓመትና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ሰዎች መካከል ከአንድ ሦስተኛ የሚበልጡት በየዓመቱ የመውደቅ አደጋ ያጋጥማቸዋል። ከዚህም በላይ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚያጋጥሙ ለሞት መንስኤ የሚሆኑ አደጋዎች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው መውደቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አረጋውያን ‘ዳገት መውጣት እንደሚያርዳቸውና መንገድም እንደሚያስፈራቸው’ የተናገረው ያለ ምክንያት አይደለም።—መክብብ 12:5
ብዙውን ጊዜ ዕድሜ ሲገፋ አካላዊ ጤንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች ማጋጠማቸው የማይቀር ቢሆንም እርስዎ ግን ደኅንነትዎን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግና በሕይወትዎ የተሻለ ደስታ ለማግኘት አንዳንድ ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላሉ። ሊያደርጉት የሚችሉት አንዱ ነገር የተሻለ ጤንነትና አካላዊ ጥንካሬ እንዲኖርዎ መጣር ነው። ሌላው ደግሞ ቤትዎ ለአደጋ የማያጋልጥ እንዲሆን ማድረግ ነው።
የተሻለ ጤንነትና አካላዊ ጥንካሬ እንዲኖርዎ ራስዎን ይንከባከቡ
በዕድሜ እየገፋን ስንሄድ አእምሯችንና ሰውነታችን ተቀናጅተው መሥራት ሊያቅታቸው እንዲሁም የማየት ችሎታችን ሊዳከምና ሚዛናችንን መጠበቅ ሊያስቸግረን ይችላል። በተጨማሪም ጡንቻችን እየተዳከመና አጥንታችን እየሳሳ ስለሚመጣ አቅመ ቢስ ልንሆን እንችላለን። ይሁን እንጂ ዘወትር አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግና ጥሩ የአመጋገብ ልማድ ማዳበር እያሽቆለቆለ የሚሄደው ይህ ሂደት እንዳይፋጠን ሊያደርጉት ይችላሉ። “ሚዛን የመጠበቅ ችሎታችን፣ አቋማችንና አካላዊ ጥንካሬያችን የተሻለ እንዲሆን አልፎ ተርፎም ሰውነታችን እንደ ልብ እንዲተጣጠፍ የሚረዱ ስፖርቶችን መሥራት በጣም ጠቃሚ ነው” በማለት ኒታ የተባሉ የፊዚዮቴራፒ ባለሙያ ይናገራሉ።
የዩናይትድ ስቴትስ የጤና እና ሰብዓዊ አገልግሎት ቢሮ ያሳተመው አንድ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “አረጋውያን የጤንነታቸው ሁኔታና አካላዊ ጥንካሬያቸው ምንም ያህል ቢሆን ዘወትር እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ከሆነ ብዙ ሊጠቀሙ ይችላሉ። መቆምና መራመድ አስቸጋሪ ቢሆንባችሁም እንኳ የሰውነት እንቅስቃሴ በማድረግ ልትጠቀሙ ትችላላችሁ። እንዲያውም በአብዛኛው እንደሚታየው ይበልጥ የምትጎዱት እንቅስቃሴ የማታደርጉ ከሆነ ነው።”a አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የልብ በሽታን፣ በመገጣጠሚያ አካባቢ የሚሰማ ሕመምን፣ የአጥንት መሳሳትንና የመንፈስ ጭንቀትን ለመዋጋት ሊረዳዎ ይችላል። የሰውነትዎ የደም ዝውውርና የምግብ መፈጨት ሂደት እንዲሻሻል እንዲሁም ከበፊቱ ይልቅ ጥሩ እንቅልፍ እንዲያገኙ ብሎም የበለጠ በራስዎ የሚተማመኑና ንቁ ሰው እንዲሆኑ ሊረዳዎ ይችላል።
ስፖርት የመሥራት ልማድ ከሌለዎት በቅድሚያ ሐኪም ቢያማክሩ ጥሩ ይሆናል። በተጨማሪም ስፖርት በሚሠሩበት ጊዜ የማዞር ስሜት ከተሰማዎ ወይም ደረትዎ አካባቢ ሕመም ካጋጠመዎ ሐኪም ያማክሩ። እንዲያውም እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥምዎት ስልክ በመደወል አምቡላንስ መጥራትዎ የተሻለ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ ምልክቶች አደገኛ ሁኔታ ላይ እንዳሉ የሚጠቁሙ ሊሆኑ ስለሚችሉ አቅልለው አይመልከቷቸው! በተጨማሪም በዓመት አንድ ጊዜ የዓይን ሐኪም ዘንድ በመሄድ ዓይንዎን ቢመረመሩ ጥሩ ነው።
ወደ አመጋገብ ስንመጣ ደግሞ በቀላሉ የሚዘጋጁ ቢሆንም እንኳ በቂ ቪታሚንና ማዕድን የሌላቸውን ምግቦች ከመመገብ ተቆጠቡ። አረጋውያን በተለይ በቪታሚን ዲ እና በካልሲየም የበለጸጉ ምግቦችን መመገብ ያስፈልጋቸዋል፤ እንዲህ ያሉ ምግቦች የአጥንትን ጥንካሬ ጠብቆ ለማቆየት ወይም ደግሞ የመሳሳቱን ሂደት ለመቀነስ ሊረዱ ይችላሉ። ስለዚህ ካልተፈተገ እህል የተዘጋጁ ምግቦችን፣ አነስተኛ ቅባት ያላቸው የወተት ተዋጽኦዎችን እንዲሁም ትኩስ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን ለመመገብ ጥረት ያድርጉ። በአመጋገብ ልማድዎ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ከማድረግዎ በፊት ሐኪም ቢያማክሩ የተሻለ ነው። ሐኪሙ ከጤናዎ አንጻር መመገብ ያለብዎትንና የሌለብዎትን ምግቦች በተመለከተ ምክር ሊሰጥዎ ይችላል።
በተጨማሪም ሰውነትዎ በቂ ፈሳሽ እንዲኖረው ለማድረግ ይጣሩ። የሰውነት ፈሳሽ ማለቅ በአረጋውያን ዘንድ የተለመደ ችግር ሲሆን በተለይ ብቻቸውን ወይም በመጦሪያ ተቋማት ውስጥ በሚኖሩ አረጋውያን ላይ በብዛት ይታያል፤ ይህ ዓይነቱ ችግር ለመውደቅ አደጋ፣ ለግራ መጋባት ስሜት፣ ለሆድ ድርቀት፣ ለቆዳ መሸብሸብና ለኢንፌክሽን አልፎ ተርፎም ለሞት ሊያጋልጥ ይችላል።
ቤትዎ ለአደጋ የማያጋልጥ እንዲሆን ያድርጉ
አብዛኞቹ የመውደቅ አደጋዎች የሚያጋጥሙት በቤት ውስጥ ነው። ሆኖም አንዳንድ ቅድመ ጥንቃቄዎችን በማድረግ ይህንን አደጋ በእጅጉ መቀነስ ይችላሉ። ከዚህ በታች የቀረቡትን ምክሮች በሚያነቡበት ጊዜ ስለ ቤትዎ ሁኔታ አስቡ።
ባኞ ቤት፦
● ወለሉ በሚረጥብበት ጊዜ የማያዳልጥ ዓይነት መሆን ይኖርበታል።
● የቁም መታጠቢያው ወይም የገንዳው ወለል ሻከር ያለ አሠራር ያለው ወይም የማያዳልጥ ምንጣፍ የተነጠፈበት መሆን አለበት፤ እንዲሁም ገላዎን የሚታጠቡት ወንበር ላይ ተቀምጠው ከሆነ የወንበሩ ሁኔታ የቧንቧውን መክፈቻ በቀላሉ እንዲደርሱበት የሚያስችል ሊሆን ይገባል። እንደተቀመጡ መታጠብ እንዲችሉ ሻወሩ ተነቅሎ በእጅ የሚያዝ መሆኑ ተመራጭ ነው።
● ባኞ ቤቱ፣ ወደ መታጠቢያ ገንዳው ሲገቡና ሲወጡ ወይም መጸዳጃ ሲጠቀሙ በእጆችዎ የሚይዟቸው መደገፊያ ዘንጎች የተገጠሙለት ቢሆን ጥሩ ነው። እነዚህ መደገፊያዎች ጠንካራና ጥብቅ ተደርገው የታሰሩ መሆን አለባቸው። በተጨማሪም መጸዳጃ ሲጠቀሙ ብዙ ልፋት ሳይጠይቅብዎ መቀመጥና መነሳት እንዲችሉ የመጸዳጃው መቀመጫ ከፍ ያለ ቢሆን የተሻለ ነው።
● ደብዘዝ ያለ ብርሃን ያላቸውን መብራቶች ሌሊት ሌሊት እንዲበሩ ያድርጉ አሊያም የእጅ ባትሪ ይጠቀሙ።
ደረጃዎች፦
● ደረጃዎቹ በጥሩ ሁኔታ ላይ ያሉና በቂ ብርሃን የሚያገኙ መሆን ይኖርባቸዋል፤ እንዲሁም እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን ከደረጃው ላይ ማስወገድ ይገባል።
● ደረጃዎች አስተማማኝ የእጅ ድጋፍ (ከተቻለ በግራም በቀኝም)፣ የማያዳልጡ መረገጫዎች እና ከላይም ሆነ ከታች ማብሪያ ማጥፊያ ሊኖሯቸው ይገባል።
● ደረጃዎችን መውጣትና መውረድ አረጋውያን እግራቸው ጠንካራ እንዲሆን ሊረዳቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ሚዛንዎን መጠበቅ የሚቸገሩ ከሆነ ደረጃዎቹን ብቻዎን ለመውጣት መዳፈር የለብዎትም።
መኝታ ቤት፦
● በቀላሉ መንቀሳቀስ እንዲችሉ በአልጋዎትም ሆነ በሌሎች ዕቃዎች ዙሪያ በቂ ቦታ እንዲኖር ያድርጉ።
● ልብስዎን ሲለብሱ የሚቀመጡበት ወንበር ይኑርዎት።
● የራስጌ መብራት አሊያም ከአልጋዎ አጠገብ የእጅ ባትሪ እንዲኖር ያድርጉ።
ኩሽና፦
● ከውጭ ገዝተው ያመጧቸውን የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችና ሌሎች ነገሮች በቀላሉ ማስቀመጥ እንዲችሉ የወጥ ቤት ጠረጴዛው ያልተዝረከረከ መሆን ይኖርበታል።
● የኩሽናው ወለል የማያዳልጥና በጣም የማያንጸባርቅ መሆን ይገባዋል።
● ያለ ሰው እርዳታ በቀላሉ ማስቀመጥም ሆነ ማውረድ እንዲችሉ ዕቃዎችን በጣም ከፍ ባለ ወይም ዝቅ ባለ መደርደሪያ ላይ አያስቀምጡ። በመሰላልና በበርጩማ ከመጠቀም ተቆጠቡ፤ እንዲሁም ፈጽሞ ወንበር ላይ ለመውጣት አይሞክሩ!
አጠቃላይ ምክር፦
● ሌሊት ወደ ባኞ ቤትም ሆነ ወደ ሌላ ቦታ ሲሄዱ በደንብ እንዲታይዎ መተላለፊያዎቹ ላይ መብራት እንዲኖር ያድርጉ።
● ሌሊት ከአልጋዎ ተነስተው ሲሄዱ እንቅልፍ በደንብ ካለቀቅዎት ወይም አእምሮዎ ንቁ ካልሆነ ከዘራ ወይም ባለ አራት እግር ምርኩዝ ቢጠቀሙ ጥሩ ነው።
● ወንበሮችዎ መሬት ላይ በደንብ የሚረግጡ (ተሽከርካሪ ያልሆኑ)፣ ክንድ ማሳረፊያ ያላቸውና በቀላሉ መቀመጥም ሆነ መነሳት እንዲችሉ ከመሬት ከፍ ያሉ መሆን ይኖርባቸዋል።
● ተደናቅፈው እንዳይወድቁ የነተቡ ምንጣፎችን፣ የተላቀቁ የፕላስቲክ ንጣፎችን ወይም የተሰበሩ የወለል ሸክላዎችን እንዳስፈላጊነቱ መጠገን፣ በሌላ መተካት ወይም እስከነጭራሹ ማስወገድ ይኖርብዎታል። ማንኛውም የኤሌክትሪክ ሽቦ ግድግዳውን ታክኮ ማለፍ ይኖርበታል እንጂ በመተላለፊያ መንገድ ላይ መዘርጋት የለበትም።
● በምንጣፍ በተሸፈነ ወለል ላይ ትንሽ ምንጣፍ ደርቦ ማስቀመጥ ሊያደናቅፍ ስለሚችል መነሳት ይኖርበታል። ከሸክላ ወይም ከሳንቃ አሊያም ከሌላ ነገር በተሠሩ የሚያንሸራትቱ ወለሎች ላይ የሚቀመጥ ከሆነ ደግሞ ሲረግጡት ሊከዳዎት ስለሚችል ከሥሩ ቆንጥጦ የሚይዝ ነገር ሊደረግለት ይገባል።
● ልክዎ ያልሆኑ፣ ያለቁ፣ ከኋላቸው ክፍት የሆኑ ወይም የሚያንሸራትት ሶል ያላቸው ነጠላ ጫማዎችን ከማድረግ ይቆጠቡ። በተጨማሪም ረዥም ተረከዝ ያላቸውን ጫማዎች አያድርጉ።
● አንዳንድ መድኃኒቶች ራስን የማዞር ወይም ሚዛንን የማሳት ባሕርይ ሊኖራቸው ይችላል። መድኃኒት ከወሰዱ በኋላ እንዲህ ዓይነት ስሜት ከተሰማዎት ለሐኪም ማማከር እንዳለብዎ አይዘንጉ። ሐኪሙ የሚወስዱትን መጠን ወይም የመድኃኒቱን ዓይነት ሊለውጥልዎት ይችላል።
በቤትዎ ውስጥ ትኩረት የሚያሻው ሆኖም በራስዎ ሊወጡት የማይችሉት ጉዳይ ካለ የቤተሰብዎን፣ የወዳጆችዎን ወይም በሕንፃው የጥገና ክፍል ውስጥ የሚሠሩ ሰዎችን እርዳታ ለምን አይጠይቁም? ጉዳዩን ለማስፈጸም ዛሬ ነገ አይበሉ።
ሌሎች ምን ማድረግ ይችላሉ?
በዕድሜ የገፉ ወላጆች፣ አያቶች ወይም ወዳጆች ካሉህ ከባድ ጉዳት የሚያስከትል የመውደቅ አደጋ እንዳይደርስባቸው ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላለህ? አንዱ ልታደርገው የምትችለው ነገር፣ ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች አስመልክተህ ከእነሱ ጋር በዘዴ መወያየትና ችግሮች ካሉ ማስወገድ የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ ነው። ምናልባትም አስፈላጊ ከሆነ በሳምንት አንዴ ወይም ሁለቴ ለጤናቸው ተስማሚ የሆነ ምግብ ልታዘጋጅላቸው ትችል ይሆናል። አረጋውያን ዘወትር አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግም ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ የእግር ጉዞ እንዲያደርጉ ይዘሃቸው ልትሄድ ትችላለህ? ምናልባትም ሌሎች ተግባሮችህን ስታከናውን እግረ መንገድህን ይህን ማድረግ ትችላለህ። ብዙ አረጋውያን አብሯቸው የሚሄድ የሚያምኑት ሰው ካለ ከቤታቸው ወጣ ማለት ደስ ይላቸዋል። በአንዳንድ አገሮች ደግሞ አረጋውያንን ቤታቸው ድረስ እየመጣ የሚንከባከብ፣ አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ አሊያም የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን በራሳቸው ማከናወን እንዲችሉ እገዛ የሚሰጥና ቤታቸው ለአደጋ የማያጋልጥ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የሚረዳቸው ሰው መንግሥት ይቀጥርላቸዋል። እንዲህ ያሉ አገልግሎቶችን ማግኘት ከፈለጉ ሐኪምዎ ሊጽፍልዎ ይችላል።
“ጥንታዌ ጥንቱ” ተብሎ የተጠራው ፈጣሪያችን ለአረጋውያን በተለይ ደግሞ በዕድሜ ለገፉ ወላጆቻችን አክብሮት እንድናሳይ ይጠብቅብናል። (ዳንኤል 7:9) “አባትህንና እናትህን አክብር” በማለት አዞናል። (ዘፀአት 20:12) በተጨማሪም “ዕድሜው ለገፋ ተነሥለት፤ ሽማግሌውን አክብር፤ አምላክህንም ፍራ” የሚል መመሪያ ሰጥቶናል። (ዘሌዋውያን 19:32) አዎን፣ ለአረጋውያን አክብሮት ማሳየት በእርግጥም ለአምላክ ጤናማ ፍርሃት እንዳለን ያመለክታል! በምላሹም አረጋውያን ለተደረገላቸው ነገር ከልባቸው የሚያመሰግኑ ከሆነ ሌሎች ፍቅርና አክብሮት በተሞላበት መንገድ ለእነሱ አሳቢነት ለማሳየት ይነሳሳሉ። አረጋውያንን መርዳት እንደ ግዴታ መታየት የለበትም። እንዲያውም አስደሳች መብት ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የመስከረም 2005 ንቁ! መጽሔት አዘውትሮ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ያሉትን ጥቅሞች ይበልጥ ዝርዝር በሆነ መንገድ ያብራራል።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የድረሱልኝ ጥሪ የሚያሰማ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ
በአንዳንድ አገሮች የሚኖሩ በዕድሜ አንጋፋ የሆኑ አረጋውያን ድንገተኛ አደጋ ሲያጋጥማቸው የሚጠቀሙበት አነስተኛ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ይሰጣቸዋል፣ ለምሳሌ እነዚህ አረጋውያን ወድቀው መነሳት ቢያቅታቸው መሣሪያውን ጫን በማለት የድረሱልኝ ጥሪ ማሰማት ይችላሉ። እነዚህን መሣሪያዎች አንገት ላይ ማንጠልጠል ወይም እጅ ላይ ማሠር ይቻላል። በአካባቢዎ እንዲህ ያለው አገልግሎት የሚሰጥ ከሆነ በዝግጅቱ ለመጠቀም ሊያስቡ ይችላሉ፤ በተለይ ብቻዎትን የሚኖሩ ከሆነ ይህን ጉዳይ በጥሞና ቢያስቡበት ጥሩ ነው።