ስጦታ የሆነው ሙዚቃ
ሕይወት ያለ ሙዚቃ ምን ሊመስል እንደሚችል አስበህ ታውቃለህ? ለሕፃናት የሚዜሙ የእሽሩሩ ዜማዎች፣ የፍቅር ዜማዎች፣ ሞቅ ያሉ ዘፈኖች፣ በመሣሪያ የተቀነባበሩ የሚመስጡ ሙዚቃዎችና ስሜትን የሚኮረኩሩ ጣዕመ ዜማዎች አይኖሩም ነበር። አብዛኞቹ ሰዎች ሕይወት እንደዚህ ቢሆን ኖሮ አሰልቺና የማይጥም ይሆን ነበር በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ።
አዎ፣ ሙዚቃ ከሰው ልጅ ስሜት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። ያረጋጋናል፣ ያስደስተናል፣ ያነቃቃናል እንዲሁም ለሥራ ያነሳሳናል። በደስታ ያስፈነድቀናል፣ በለቅሶ ያንሰቀስቀናል። ከዚህም በላይ ሙዚቃ በልባችን ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ኃይል አለው። ታዲያ ሙዚቃ ስሜታችንን ይህን ያህል የሚኮረኩረው ለምንድን ነው? መልሱ በጣም ቀላል ነው፤ ሙዚቃ ከአምላክ የተገኘ ግሩም ስጦታ ስለሆነ ነው። (ያዕቆብ 1:17) በመሆኑም ሙዚቃ እንደ ውድ ነገር ሊቆጠር የሚገባው ከመሆኑም በላይ በሰዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድርና ወጣት አረጋዊ ሳይል ሁሉም ሰው በቀላሉ ሊያገኘው የሚችል መሆን ይኖርበታል።
ሙዚቃ በጣም ረጅም ታሪክ አለው። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ የአፍሪካ ጎሣዎች በብዙ መቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ከበሮ፣ መለከትና ቃጭል ይጠቀሙ እንደነበረ የሚያሳዩ አርኪኦሎጂያዊ መረጃዎች ተገኝተዋል። የጥንቶቹ ቻይናውያን ሃርሞኒካና ፉንፉ የተባለውን የሙዚቃ መሣሪያ ይጫወቱ ነበር። የግብፅ፣ የሕንድ፣ የእስራኤልና የሜሶጶጣሚያ ሕዝቦች ደግሞ በገና ይጫወቱ ነበር። ስለ ሙዚቃ ለይተው ከሚጠቅሱ ታሪካዊ ማስረጃዎች አንዱ በዘፍጥረት 4:21 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ነው። እዚህ ጥቅስ ላይ ዩባል የተባለ ሰው “የበገና ደርዳሪዎችና የዋሽንት ነፊዎች አባት” እንደነበረ እናነባለን። ከበርካታ ምዕተ ዓመታት በኋላ ደግሞ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰለሞን ለሙዚቃ ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረው በገናዎችንና ሌሎች የአውታር መሣሪያዎችን ለማሠራት ከፍተኛ ጥራት ያለው እንጨት አስመጥቷል።—1 ነገሥት 10:11, 12
እርግጥ ነው፣ በዚያ ዘመን ሙዚቃ ማዳመጥ ከፈለግክ ራስህ መሣሪያውን መጫወት አለዚያም የሙዚቃ መሣሪያ የሚጫወት ሌላ ሰው ማግኘት ይኖርብህ ነበር። ዛሬ ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጥቂት ቁልፎችን በመጫን ብቻ የፈለጉትን ሙዚቃ ማግኘት ይችላሉ። ደግሞም ማንኛውንም ዓይነት ሙዚቃ በመቅዳት ወይም ከኢንተርኔት በመገልበጥ ኪስ ውስጥ ሊያዙ በሚችሉ ቀላል መሣሪያዎች ማዳመጥ ይቻላል። በአንድ ምዕራባዊ አገር በ2009 በተደረገ ጥናት ከ8 እስከ 18 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች ሙዚቃና ሌሎች የተቀዱ ነገሮችን በማዳመጥ በየቀኑ ከሁለት ሰዓት በላይ እንደሚያሳልፉ ተረጋግጧል።
ይህ በእጅጉ እየተስፋፋ የመጣ ልማድ ሙዚቃና ከሙዚቃ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ዋነኛ የንግድ ሸቀጦች እየሆኑ የመጡበትን ምክንያት እንድናውቅ ይረዳናል። በእርግጥም ሙዚቃ ብዙ ትርፍ የሚታፈስበት ንግድ ሆኗል። ይሁን እንጂ እጅግ ተወዳጅ የሆነ ዘፈን ለማውጣት ምን ጥረት እንደሚጠይቅ አስበህ ታውቃለህ?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ሙዚቃ በኢንተርኔት
ዳውንሎድ ማድረግ፦ ብዙውን ጊዜ ተጠቃሚዎች ዳውንሎድ ለሚያደርጉት ለእያንዳንዱ ሙዚቃ ገንዘብ ስለሚከፍሉ ሙዚቃው የግል ንብረታቸው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ኮንትራት ይገባሉ፤ ይህን ኮንትራት አብዛኛውን ጊዜ ከሞባይል መስመር ወይም ከሌሎች ግዢዎች ጋር አጣምሮ ማግኘት ይቻላል፤ ኮንትራቱ እስከሚቆይበት ጊዜ ድረስ ሙዚቃዎችን ዳውንሎድ እያደረጉ ማጫወት ይቻላል።
በቀጥታ ማዳመጥ ወይም ስትሪሚንግ፦ ይህም አድማጮች የሙዚቃ ፋይሉን ዳውንሎድ ሳያደርጉ እዚያው ባለበት ማዳመጥ የሚችሉበት መንገድ ነው። በዚህ መንገድ የሚገኙ ሙዚቃዎች አብዛኛውን ጊዜ ነፃ ሲሆኑ አንዳንድ ልዩ የሆኑ ሙዚቃዎችን ለማግኘት ግን ኮንትራት መግባት ያስፈልጋል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ቻርት/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የሙዚቃ ቀረጻ ታሪካዊ ክንውኖች
በ1880ዎቹ
በሸክላ ላይ መቅረጽ
በ1890ዎቹ
በሽቦ ላይ መቅረጽ
በ1940ዎቹ
በሚጠነጠን የቴፕ ክር ላይ መቅረጽ
በ1960ዎቹ
በካሴት ላይ መቅረጽ
በ1980ዎቹ
በሲዲ ላይ መቅረጽ
በ1990ዎቹ
ዲጂታል የድምፅ ፋይሎች (ኤምፒ3፣ ኤኤሲ፣ ደብልዩኤቪ፣ ወዘተ)