የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 3/13 ገጽ 14-15
  • ሮበርት ቦይል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሮበርት ቦይል
  • ንቁ!—2013
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሳይንስ ሰው
  • የእምነት ሰው
  • የርዕስ ማውጫ
    ንቁ!—2013
  • የበዴል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም—አነስተኛ ግን ጉልህ እመርታ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • የላቀ ጥበብ የሚገኝበት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ምንጭ
    የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? እንዴትስ ልታገኘው ትችላለህ?
  • መቼም የማልረሳው አስደሳች የእረፍት ጊዜ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2013
g 3/13 ገጽ 14-15

የታሪክ መስኮት

ሮበርት ቦይል

የታሪክ አዋቂዎች ሮበርት ቦይልን የሚያስታውሱት የቦይል ሕግ የተባለውን ሕግ በማውጣቱ ነው፤ ይህ የተፈጥሮ ሕግ በጋዞች ግፊትና በሚይዙት የቦታ መጠን መካከል ያለውን ዝምድና ያብራራል። የእሱ አስደናቂ ግኝት ከዚያ በኋላ ለመጡ በርካታ ሳይንሳዊ እድገቶች መሠረት ጥሏል። ይሁን እንጂ ሮበርት ቦይል የሚታወቀው በሳይንስ እውቀቱ ብቻ አልነበረም። በአምላክና በመንፈስ መሪነት በተጻፈው ቃሉ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ታላቅ እምነት የነበረው ሰው በመሆኑም ይታወቃል።

ቦይል የተወለደው በ1627 ሊዝሞር ካስል፣ አየርላንድ ውስጥ ከአንድ ባለጸጋ ቤተሰብ ነው። ወቅቱ የታሪክ ምሁራን በምክንያት የማመን ዘመን ብለው የሚጠሩት ጊዜ ማለትም የማስተዋል ችሎታቸው ከፍተኛ የሆኑ ሰዎች የሰውን ዘር ለብዙ ዘመናት ጠፍረው ከያዙት ጭፍን አመለካከቶች ነፃ ለማውጣት ሙከራ ማድረግ የጀመሩበት ዘመን ነበር። ቦይልም ይህ አመለካከት እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርጓል። ስለ ልጅነት ዘመኑ በጻፈው ጽሑፍ ላይ “የጽድቅ አፍቃሪ” የሚል ትርጉም ያለውን ፊላሪተስ የሚል ስም ለራሱ አውጥቶ ነበር።

ቦይል እውነትን ለመማር ይጓጓ የነበረውን ያህል ያወቀውን ነገር ሁሉ ለሌሎች ለማካፈልም ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ቦይል በርካታ ጽሑፎችን ያዘጋጀ ሲሆን ጽሑፎቹም እውቁን የሳይንስ ሊቅ ሰር አይዛክ ኒውተንን ጨምሮ በእሱ ዘመን በኖሩ ብዙ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። በ1660 ሮያል ሶሳይቲ የሚባለውንና አሁንም ድረስ በለንደን፣ እንግሊዝ የሚገኘውን የሳይንስ ተቋም ከመሠረቱት ሰዎች መካከል አንዱ ነው።

የሳይንስ ሰው

ቦይል የኬሚስትሪ አባት እየተባለ ይጠራል። በወቅቱ ከነበሩት የመካከለኛው ዘመን የኬሚስትሪ ተመራማሪዎች ፍጹም የተለየ አመለካከት ነበረው። እነዚህ ሰዎች የምርምር ውጤታቸውን ሚስጥር አድርገው ይይዙት ነበር፤ አለዚያም ከቡድናቸው ውጭ ያሉ ሰዎች ሊገባቸው በማይችል አገላለጽ ተጠቅመው ይጽፉ ነበር። በአንጻሩ ግን ቦይል ስለ ሥራው በዝርዝር ጽሑፎችን ያሳትም ነበር። በተጨማሪም ለረጅም ጊዜ ሲታመንባቸው የኖሩ መላ ምቶችን እንዲሁ ከመቀበል ይልቅ እውነቱን ለማወቅ ሳይንሳዊ ሙከራ ማድረግን አጥብቆ ይደግፍ ነበር።

የቦይል ሳይንሳዊ ሙከራዎች ቁስ አካል የተገነባው እሱ ኮርፐስል ብሎ ከጠራቸው ቅንጣቶች እንደሆነና እነዚህ ቅንጣቶች ደግሞ በተለያዩ መንገዶች ሲቀመጡ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን እንደሚያስገኙ የሚገልጸውን ሐሳብ የሚደግፉ ነበሩ።

ቦይል አንድ ሰው ሳይንሳዊ ምርምር ሲያደርግ ሊኖረው የሚገባውን አመለካከት ዘ ስኬፕቲካል ኬሚስት (ተጠራጣሪው የኬሚስትሪ ሊቅ) በተሰኘው ዝነኛ መጽሐፉ ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ገልጾታል። በመጽሐፉ ውስጥ የሳይንስ ሊቃውንት እብሪተኛ ወይም ሐሳበ ግትር መሆን እንደሌለባቸውና ስህተቶቻቸውን አምነው ለመቀበል ፈቃደኞች መሆን እንዳለባቸው ሐሳብ ሰጥቷል። ቦይል ስለ አንድ ነገር ጠንካራ አቋም ያላቸው ሰዎች እውነት እንደሆኑ በሚያውቋቸውና እውነት ይሆናሉ ብለው በሚያስቧቸው ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት በጥንቃቄ መመዘን እንዳለባቸው አጥብቆ ይናገር ነበር።

ቦይል ስለ አንድ ነገር ጠንካራ አቋም ያላቸው ሰዎች እውነት እንደሆኑ በሚያውቋቸውና እውነት ይሆናሉ ብለው በሚያስቧቸው ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት በጥንቃቄ መመዘን እንዳለባቸው አጥብቆ ይናገር ነበር

የእምነት ሰው

ቦይል ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች የነበረው አመለካከትም ተመሳሳይ ነው። ስለ አጽናፈ ዓለምና ሕያዋን ፍጥረታት ስላላቸው አስደናቂ አሠራር ያገኘው ግንዛቤ አንድ ንድፍ አውጪና ፈጣሪ መኖር እንዳለበት አሳምኖታል። ስለዚህ በእሱ ዘመን በነበሩት ምሁራን መካከል እየተስፋፋ የመጣውን አምላክ የለሽነት አይቀበልም ነበር። የማሰብ ችሎታውን ተጠቅሞ ነገሮችን በሐቀኝነት የሚመረምር ማንኛውም ሰው በአምላክ የማያምንበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ገልጿል።

ይሁን እንጂ ቦይል ሰዎች የማመዛዘን ችሎታቸውን ስለተጠቀሙ ብቻ እውነተኛ መንፈሳዊ ማስተዋል ያገኛሉ የሚል እምነት አልነበረውም። ከአምላክ የሚገኝ እውቀት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ይህ እውቀት ደግሞ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል።

ቦይል ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን የማያውቁ መሆናቸውና ሃይማኖታዊ እምነታቸው በጠንካራ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ አለመሆኑ ያሳዝነው ነበር። አንድ ሰው እምነቱን ከወላጆቹ ወይም ከተወለደበት አካባቢ መውረሱ ብቻውን ሃይማኖቱን ትክክል እንደማያደርገው ተናግሯል። ቦይል፣ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታቸውን እንዲያሰፉ የመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው።

ለዚህም ሲል መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቋንቋዎች ተተርጉሞ እንዲሰራጭ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል የቀድሞዎቹ የሰሜን አሜሪካ ተወላጆች የሚጠቀሙባቸው ቋንቋዎች እንዲሁም አረብኛ፣ አይሪሽ፣ ማላይ እና ቱርክኛ ይገኙበታል። በመሆኑም ሮበርት ቦይል ልዩ ተሰጥኦ ቢኖረውም ስለ ሁሉም ጉዳዮች እውነቱን የማወቅ አልፎ ተርፎም ሌሎች እንዲሁ እንዲያደርጉ የመርዳት ከፍተኛ ምኞት ያለው ትሑት ሰው ነበር።

አጭር መረጃ፦

  • የተወለደው በ1627 በአየርላንድ ነው።

  • የኬሚስትሪ አባት ተብሎ ተጠርቷል።

  • ሳይንሳዊ ሙከራዎች ማድረግ ስለሚቻልበት መንገድ በዝርዝር የሚናገር ጽሑፍ ያዘጋጀ የመጀመሪያው እውቅ የሳይንስ ሊቅ ነው።

  • ጽሑፎቹ በእሱ ዘመን በኖረውና በዕድሜ ከእሱ በሚያንሰው ሰር አይዛክ ኒውተን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል።

  • መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቋንቋዎች እንዲተረጎም የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

  • የሞተው በ1691፣ በ64 ዓመቱ እንግሊዝ ውስጥ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ በአይሪሽ ቋንቋ

ሮበርት ቦይል ከ1573 አንስቶ አንድ የምሁራን ቡድን የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በአይሪሽ ቋንቋ መተርጎም እንደ ጀመረ አወቀ። እነዚህ ምሁራን በ1602 በተለምዶ አዲስ ኪዳን እየተባለ የሚጠራውን ክፍል አዘጋጅተው ነበር። በኋላም፣ በተለምዶ ብሉይ ኪዳን ተብለው የሚጠሩትን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በአይሪሽ ቋንቋ የመተርጎሙ ሥራ በ1640 ተጠናቀቀ። ይህ ትርጉም ቦይል ለኅትመቱ የሚያስፈልገውን የገንዘብ ድጋፍ እስካደረገበት እስከ 1685 ድረስ አልታተመም ነበር። የሚገርመው ነገር፣ የአዋልድ መጻሕፍትም በአይሪሽ ቋንቋ ተተርጉመው ነበር። የአዋልድ መጻሕፍት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያልሆኑ ጽሑፎች ስብስብ ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አብረው በአንድ ጥራዝ ውስጥ ይታተማሉ። ይሁን እንጂ ቦይል የእውነት አፍቃሪ ስለሆነ እነዚያን የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ያልሆኑ ጽሑፎች ለማሳተም ፈቃደኛ አልነበረም።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ