የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 12/14 ገጽ 2-6
  • የአእምሮ ሕመም—ምን ማወቅ ይኖርብሃል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአእምሮ ሕመም—ምን ማወቅ ይኖርብሃል?
  • ንቁ!—2014
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአእምሮ ሕመም—ምን ማወቅ ይኖርብሃል?
  • የአእምሮ ጤንነት—አንዳንድ እውነታዎች
  • የአእምሮ ሕመም—ግንዛቤያችንን ማስፋት
  • የአእምሮ ሕመም—ሕክምና
  • መንፈሳዊ ጤንነት አስፈላጊ ነው
  • የቤተሰብህ አባል ወይም በቅርብ የምታውቀው ሰው የአእምሮ ሕመም ቢኖርበትስ?
    ንቁ!—2004
  • የአንባብያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ዓለም አቀፍ የአእምሮ ጤና ቀውስ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2023
  • አምላክ ፍጹም የአእምሮ ጤንነት የምናገኝበት ጊዜ እንደሚመጣ ቃል ገብቷል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2023
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2014
g 12/14 ገጽ 2-6
የተጨነቀች ሴት የታመመ ባሏን እየተመለከተች

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

የአእምሮ ሕመም—ምን ማወቅ ይኖርብሃል?

ክላውዲያ፣ “ባይፖላር ዲስኦርደር” (የስሜት መለዋወጥ) እና “ፖስት ትራውማቲክ ስትረስ ዲስኦርደር” (ከአሠቃቂ ገጠመኝ በኋላ የሚከሰት ጭንቀት) እንዳለባት ሲነገራት “መተንፈስ አቃተኝ። ባለብኝ የአእምሮ ሕመም ምክንያት ሰዎች ያገሉኛል ብዬ ስለፈራሁ ጉዳዩ በጣም አስጨነቀኝ” በማለት የተሰማትን ተናግራለች።

የክላውዲያ ባለቤት የሆነው ማርክ ደግሞ “ያለንበትን ሁኔታ ለመቀበል ረጅም ጊዜ ወስዶብናል። ይሁንና ባለቤቴን መንከባከብ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ” ብሏል።

አንተ ራስህ ወይም አንድ የቤተሰብህ አባል የአእምሮ ሕመም እንዳለባችሁ ቢነገራችሁ ምን ይሰማሃል? እርግጥ ነው፣ የአእምሮ ሕመም በሕክምና መዳን ይችላል። ስለ አእምሮ ሕመም ያለህን ግንዛቤ የሚያሰፉ ጥቂት ነጥቦች እስቲ እንመርምር።a

የአእምሮ ጤንነት—አንዳንድ እውነታዎች

“በሁሉም የዓለም ክፍል የሚኖሩ በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአእምሮ ሕመም ይሠቃያሉ፤ እንዲሁም ችግሩ በቤተሰቦቻቸውና በወዳጆቻቸው ሕይወት ላይ ጫና ይፈጥራል። ከአራት ሰዎች መካከል አንዱ በሕይወቱ ውስጥ በሆነ ወቅት ላይ የአእምሮ ሕመም ያጋጥመዋል። ለዚህ ዓለም አቀፍ ችግር ዋነኛው መንስኤ የመንፈስ ጭንቀት ነው። በጣም ከባድ ከሆኑትና በሰዎች ላይ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩት የአእምሮ ሕመሞች መካከል ስኪትሰፍሪኒያ እና ባይፖላር ዲስኦርደር ይገኙበታል። . . . በጣም ብዙ ሰዎች በአእምሮ ሕመም የሚጠቁ ቢሆንም ችግሩ አሁንም በድብቅ የሚያዝ ከመሆኑም ሌላ ችላ ይባላል፤ በተጨማሪም እንዲህ ዓይነት በሽታ ያለባቸው ሰዎች መድሎ ይፈጸምባቸዋል።”—የዓለም የጤና ድርጅት

የዓለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው በአእምሮ ሕመም የተያዙ ብዙ ሰዎች ከኅብረተሰቡ መገለል ስለሚያስፈራቸው ሕክምና ከማግኘት ወደኋላ ይላሉ።

አብዛኞቹ የአእምሮ ሕመሞች በሕክምና መዳን ይችላሉ፤ ያም ቢሆን በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ባለፈው ዓመት ብቻ የአእምሮ ሕመም ያለባቸው 60 በመቶ ገደማ የሚሆኑ አዋቂዎችና 50 በመቶ የሚሆኑ ከ8 እስከ 15 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ሕክምና እንዳላገኙ በአእምሮ ሕመም ለተያዙ ሰዎች እርዳታ የሚሰጥ አንድ ተቋም ዘግቧል።

የአእምሮ ሕመም—ግንዛቤያችንን ማስፋት

የአእምሮ ሕመም ያለባት ሴት

የአእምሮ ሕመም ምንድን ነው? አንድ ሰው የአእምሮ ሕመም አለበት የሚባለው ከሚያስብበት መንገድ፣ ከስሜቱ እንዲሁም ከባሕርይው ጋር በተያያዘ ጉልህ የሆነ እክል ሲያጋጥመው እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህ ችግር ያለበት ሰው ብዙውን ጊዜ የሌሎችን ስሜት መረዳትና የኑሮ ጫናዎችን መቋቋም ይከብደዋል።

የአእምሮ ሕመም የሚመጣው በግል ድክመት ወይም በባሕርይ ችግር አይደለም

የሕመሙ ምልክት ይኸውም ችግሩ የሚቆይበት የጊዜ ርዝመትም ሆነ የሥቃዩ መጠን ከሰው ሰው ይለያያል፤ ምልክቱ ግለሰቡን በያዘው የበሽታ ዓይነትና ግለሰቡ ባለበት ሁኔታ ላይ የተመካ ነው። ሕመሙ ፆታ፣ ዕድሜ፣ ባሕል፣ ዘር፣ ሃይማኖት ወይም የትምህርት ደረጃና የገቢ መጠን ሳይለይ ማንኛውንም ሰው ሊያጠቃ ይችላል። የአእምሮ ሕመም የሚመጣው በግል ድክመት ወይም በባሕርይ ችግር አይደለም። እንዲህ ዓይነት የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች ተገቢውን የሕክምና ክትትል ካደረጉ ሊድኑ ብሎም ስኬታማና አርኪ ሕይወት ሊመሩ ይችላሉ።

የአእምሮ ሕመም—ሕክምና

የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች የተለያዩ የአእምሮ ችግሮችን በተሳካ መንገድ ማከም ይችላሉ። በመሆኑም የመጀመሪያው ወሳኝ እርምጃ፣ የአእምሮ ሕመምን በማከም ረገድ ተሞክሮ ያካበተ ብቃት ያለው የጤና ባለሙያ ዘንድ ሄዶ የተሟላ ምርመራ ማድረግ ነው።

የአእምሮ ሕመም ያለባት ሴት ብቃት ካለው የሕክምና ባለሙያ ጋር እየተነጋገረች

የአእምሮ ሕመምተኞች እንዲህ ካለው እርዳታ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት የሚሰጣቸውን ሕክምና ለመቀበል ፈቃደኞች ከሆኑ ብቻ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ የአእምሮ ሕመምን በተመለከተ ከሌሎች ጋር ለመነጋገር የሚሰማቸውን ፍርሃት ማሸነፍ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ሕክምናው ከሠለጠኑ የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ጋር መነጋገርን ይጨምራል፤ እነዚህ ባለሙያዎች ታካሚው ስለ ሕመሙ ግንዛቤ እንዲያገኝ፣ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ የሚያጋጥሙትን ችግሮች እንዲወጣና ሕክምናውን ሳያቋርጥ እንዲከታተል ሊረዱት ይችላሉ። ግለሰቡ እንዲህ ያለ ሕክምና በሚከታተልበት ጊዜ አንድ የቤተሰቡ አባል ወይም ወዳጁ ከጎኑ ሆኖ ሊያበረታታውና ድጋፍ ሊሰጠው ይችላል።

ብዙ ሰዎች ስለ ሕመማቸው የተሻለ ግንዛቤ በማግኘታቸውና በአእምሮ ጤና ባለሙያዎች የሚታዘዝላቸውን ሕክምና በመከታተላቸው ሕመሙን ተቋቁመው እየኖሩ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ማርክ እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴ የአእምሮ ሕመም እንዳለባት ከማወቃችን በፊት ስለዚህ ሕመም ምንም የምናውቀው ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል። አሁን ግን ነገሮችን እንዳመጣጣቸው መቀበልና ከሁኔታው ጋር መላመድ ችለናል። በተጨማሪም እምነት ከሚጣልባቸው ባለሙያዎች እንዲሁም ከቤተሰቦቻችንና ከወዳጆቻችን የምናገኘው ድጋፍ ጠቅሞናል።”

የመጀመሪያው ወሳኝ እርምጃ፣ የአእምሮ ሕመምን በማከም ረገድ ተሞክሮ ያካበተ ብቃት ያለው የጤና ባለሙያ ዘንድ ሄዶ የተሟላ ምርመራ ማድረግ ነው

ክላውዲያም ማርክ በተናገረው ትስማማለች። እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ የምርመራው ውጤት ሲነገረኝ እስር ቤት እንደገባሁ ሆኖ ተሰማኝ። ያለብኝ የጤና እክል በሁለታችንም ላይ የአቅም ገደብ ቢያስከትልም በጣም አስቸጋሪ የሚመስሉ መሰናክሎችንም መቋቋም እንደሚቻል ተገንዝቤያለሁ። በመሆኑም ከሕክምና ቡድኑ ጋር ተባብሬ በመሥራት፣ ከሌሎች ጋር ያለኝን ዝምድና በማጠናከርና ሕይወትን እንዳመጣጡ በመቀበል ያለብኝን ሕመም መቋቋም ችያለሁ።”

መንፈሳዊ ጤንነት አስፈላጊ ነው

መጽሐፍ ቅዱስ የምታነብ ሴት

መጽሐፍ ቅዱስ፣ መንፈሳዊነት የጤና እክሎችን እንደሚፈውስ አይናገርም። ያም ሆኖ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙ ቤተሰቦች መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ነገር ማጽናኛና ማበረታቻ አግኝተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አፍቃሪው ፈጣሪያችን ‘ልባቸውና መንፈሳቸው የተሰበረ’ ሰዎችን እንደሚያጽናና ያረጋግጥልናል።—መዝሙር 34:18

መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና መጽሐፍ ባይሆንም ሥቃይ የሚያስከትሉ ስሜቶችንና አስጨናቂ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚረዳ ሐሳብ ይዟል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት በምድር ላይ ከሕመምና ከሥቃይ ነፃ የሆነ ሕይወት የምንመራበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። የአምላክ ቃል የሚከተለውን ተስፋ ይሰጣል፦ “በዚያን ጊዜም የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ፤ የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ። አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል።”—ኢሳይያስ 35:5, 6

a ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል፣ በዚህ ርዕስ ውስጥ “የአእምሮ ሕመም” የሚለው ስያሜ የአእምሮ በሽታዎችን እንዲሁም የባሕርይና የሥነ ልቦና መቃወስን ያካትታል።

ከአእምሮ ሕመም ጋር መታገል

“በጣም ስለምጨነቅ አንዳንድ ነገሮችን ማከናወን እንደማልችል ሆኖ የሚሰማኝ ጊዜ አለ፤ አንዳንድ ጊዜ ለማንበብ እንኳ ትኩረቴን መሰብሰብ አልችልም። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ስለሚኖርብኝ ከሰዎች አልፎ ተርፎም ከጓደኞቼም ጭምር እሸሻለሁ። አንዳንድ ሰዎች ያለብኝ ችግር በቅርቡ መፍትሔ ማግኘቱ እንደማይቀር ወይም እኔን ያስጨነቀኝ ነገር የማስበውን ያህል የከፋ እንዳልሆነ በመናገር ሊያጽናኑኝ ይሞክራሉ። ሌሎች ደግሞ አዎንታዊ እንድሆን ይነግሩኛል። እኔም ይህን ለማድረግ ብዙ ጊዜ ጥሬያለሁ! እርግጥ ነው፣ እንዲህ የሚሉኝ ለእኔ አስበው እንደሆነ ይገባኛል፤ ያም ቢሆን እንዲህ ያሉ አስተያየቶች ያለብኝ የጥፋተኝነትና የከንቱነት እንዲሁም አልረባም የሚል ስሜት እንዲባባስ ከማድረግ ውጭ የሚፈይዱት ነገር የለም።”—ክላውዲያ፣ ደቡብ አፍሪካ

የአእምሮ ሕመምን ተቋቁሞ መኖር

  1. ብቃት ባላቸው የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች የታዘዘላችሁን ሕክምና ተከታተሉ።b

  2. ዕለታዊ ተግባሮቻችሁን የምታከናውኑበት ሚዛናዊና ቋሚ ፕሮግራም ይኑራችሁ።

  3. አካላዊ እንቅስቃሴ አድርጉ።

  4. በቂ እንቅልፍ አግኙ።

  5. በየዕለቱ ዘና የምትሉበት ጊዜ መድቡ።

  6. ገንቢና የተመጣጠነ ምግብ ተመገቡ።

  7. ከአልኮል መጠጥና በሐኪም ካልታዘዙላችሁ መድኃኒቶች ጋር በተያያዘ ገደብ አብጁ።

  8. ብቻችሁን አትሁኑ፤ ከምታምኗቸውና ከሚያስቡላችሁ ሰዎች ጋር ጊዜ አሳልፉ።

  9. ለመንፈሳዊ ፍላጎታችሁ ትኩረት ስጡ።c

b ንቁ! መጽሔት የትኛውንም ዓይነት ሕክምና ደግፎ አይናገርም። ክርስቲያኖች የሚያደርጉት የትኛውም ዓይነት ሕክምና ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የሚጋጭ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።

c በተጨማሪም በግንቦት 2014 ንቁ! ላይ የወጣውን “ውጥረትን መቆጣጠር የሚቻልበት መንገድ” የሚለውን ርዕስ ተመልከቱ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ