የአንባብያን ጥያቄዎች
አንድ ክርስቲያን የአእምሮ ሕክምና ባለሙያ ቢያማክር ጥበብ ነውን?
ከአንዳንድ አገሮች የሚመጡት ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ውስጥ የሚታዩት ስሜታዊና አእምሮአዊ የጤና መታወኮች ጨምረዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ክርስቲያኖች ሌሎች ወንድሞቻቸው በዚህ ችግር ሲጠቁ ማየት ከልብ የሚያሳዝናቸው ቢሆንም ሕክምና የመውሰድና ያለመውሰዱ ጉዳይ እንዲሁም የሕክምናውን ዓይነት በተመለከተ ውሳኔው ለግለሰቡ የተተወ መሆኑን አይዘነጉም።a “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና።” (ገላትያ 6:5) በሐኪሞች ዘንድ ስኪዞፍሬኒያ፣ ማኒክ ዲፕሬሽን፣ ዲፕ ክሊኒካል ዲፕሬሽን፣ ኦብሰሲቭ ኮምፐልሲቭ ዲስኦርደር፣ ሰልፍ ሚውቲሌሽን በመባል በሚታወቁና በሌሎችም ከባድ ሕመሞች የሚሠቃዩ አንዳንድ ሰዎች ትክክለኛውን የባለሙያዎች እርዳታ ካገኙ በኋላ ጤንነታቸው በመጠኑ ተመልሶላቸዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የአእምሮ ሕክምና ፈላጊዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። እንዲህ ያለውን ሕክምና የሚፈልጉት በሽተኞች አብዛኛውን ጊዜ ከባድ የአእምሮ መታወክ ገጥሟቸው ሳይሆን በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን አንዳንድ ችግሮች መወጣት ስላቃታቸው ብቻ ነው። ይሁን እንጂ በሕይወት ውስጥ የሚከሰቱትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለማሸነፍ የሚያስችል ከሁሉ የተሻለ ውጤታማ እርዳታ የሚገኘው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። (መዝሙር 119:28, 143) ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ጥበብ፣ ማስተዋልና እውነተኛ እውቀት ይሰጠናል፤ እነዚህ ነገሮች ደግሞ አእምሮና ስሜታችንን ይጠብቁልናል። (ምሳሌ 2:1-11፤ ዕብራውያን 13:6) የታመኑ የአምላክ አገልጋዮችም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ውስጣዊ ስሜታቸው ሲታወክ ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን ሊናገሩ ይችላሉ። (ኢዮብ 6:2, 3) ያዕቆብ 5:13-16 እንደነዚህ ያሉ ሰዎች እርዳታና ምክር ለማግኘት የጉባኤ ሽማግሌዎችን እንዲጠሩ ያበረታታል። አንድ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ይታመም ይሆናል አለዚያም መፍትሔ በሌላቸው ሁኔታዎች ወይም በደረሰበት ከባድ ውጥረት ምክንያት ይጨነቅ ይሆናል ወይም ደግሞ የፍትሕ መጓደል እንደተፈጸመበት ይሰማው ይሆናል። (መክብብ 7:7፤ ኢሳይያስ 32:2፤ 2 ቆሮንቶስ 12:7-10) እንዲህ ያለው ሰው ‘ዘይት ቀብተው’ ማለትም የሚያጽናኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮችን እያካፈሉ ‘ከሚጸልዩለት’ ሽማግሌዎች እርዳታ ሊያገኝ ይችላል። ውጤቱስ ምን ይሆናል? “የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም [ከሐዘንና ከትካዜው ወይም አምላክ ትቶኛል ከሚለው ስሜቱ] ያስነሣዋል።”
ይሁንና መንፈሳዊ እረኞች በጥበብ ከረዱት በኋላም የአእምሮ ጭንቀቱና አለመረጋጋቱ ቢጸናበትስ? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የገጠማቸው አንዳንዶች ሰፋ ያለ የሕክምና ምርመራ ለማድረግ መርጠዋል። (ከምሳሌ 14:30፤ 16:24፤ 1 ቆሮንቶስ 12:26 ጋር አወዳድር።) የስሜታዊ ወይም አእምሮአዊ ጭንቀቱ መንስኤ የውስጥ ደዌ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለው ደዌ በሕክምና በመዳኑ በስሜት የታወከው ሰው እፎይታ ያገኘባቸው አጋጣሚዎች አሉ።b ምንም ዓይነት የውስጥ ደዌ ካልተገኘበትና ታማሚው ጥያቄ ካቀረበ ሐኪሙ ወደ አእምሮ ሕክምና ባለሙያ ሊመራው ይችላል። ከዚያስ? ከላይ እንደተገለጸው ይህ ለእያንዳንዱ ግለሰብ የተተወ ውሳኔ ነው። በሚያደርገው ውሳኔም ሌሎች ሊነቅፉት ወይም ሊፈርዱበት አይገባም።—ሮሜ 14:4
የሆነ ሆኖ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዳንዘነጋ የጥበብ እርምጃ መውሰድና ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። (ምሳሌ 3:21፤ መክብብ 12:13) የውስጥ ሕመም ሲከሰት የተለመዱትን መድኃኒቶች ከመጠቀም አንስቶ እስከ ኔቸሮፓቲ (ተፈጥሮአዊ ሕክምና)፣ አኩፓንክቸር (የደረቅ መርፌ ሕክምና) እና ሆሚዎፓቲ የመሳሰሉትን ሕክምናዎች የመጠቀም አማራጮች ከፊታቸው ይደቀናሉ። በተጨማሪም የተለያዩ ዓይነት የአእምሮ ሕክምና ባለሙያዎች አሉ። ከእነዚህም መካከል የታመመው ሰው ባሕርይ በየጊዜው የሚለዋወጠውና ስሜታዊ ሥቃይ የሚሰማው ለምን እንደሆነ ለማወቅ ሲሉ በበሽተኛው የግል የሕይወት ታሪክ ውስጥ የሚገቡ አናሊቲክ ሳይኮቴራፒስት የሚባሉና ሌሎችም ይገኙበታል። የባሕርይ ሳይኮቴራፒስት የሚባሉት ደግሞ ታማሚው አዳዲስ ባሕርያትን እንዲማር ሊረዱት ይሞክሩ ይሆናል። አንዳንድ የአእምሮ ሕክምና ባለሙያዎች አብዛኞቹ የአእምሮ ችግሮች በመድኃኒት መታከም ያለባቸው እንደሆነ ያምናሉ።c ሌሎች ደግሞ በተመጣጠነ ምግብና በቫይታሚኖች መታከምን እንደሚደግፉ ሲናገሩ ይሰማል።
ሕሙማኑና ቤተሰቦቻቸው እነዚህን አማራጮች በሚመረምሩበት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። (ምሳሌ 14:15) በጆንስ ሆፕኪንስ የሕክምና ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሥነ አእምሮና የባሕርይ ሳይንስ ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ፖል ማክዩ ስለ አእምሮ ሕክምና ሙያ እንደሚከተለው ብለዋል፦ “ገና ያልዳበረ የሕክምና መስክ ነው። በጣም ውስብስብ የሆኑት የሰው ልጅ ሕይወት ገጽታዎች ማለትም ከአእምሮና ከባሕርይ መታወክ ጋር የተያያዘ መስክ የመሆኑን ያክል አንድን ዓይነት ምርመራም ሆነ ሕክምና ያዘዘበትን ምክንያት ተጨባጭ ማስረጃ ማረጋገጥ አይችልም።” ይህም ሕክምናው መንገዱን እንዲስትና ማጭበርበር እንዲኖር በር ከመክፈቱም በላይ በቅን ልቦና የሚታዘዙ ሕክምናዎችም እንኳ ሳይቀሩ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው እንዲያመዝን ሊያደርግ ይችላል።
የሥነ አእምሮና የሥነ ልቦና ባለሙያዎች በድኅረ ምረቃ ደረጃ በሙያው የሠለጠኑ ቢሆንም ምንም ዓይነት ሙያዊ ብቃት የሌላቸው ሌሎች ሰዎችም እንደ አማካሪዎች ወይም እንደ ሐኪም ሆነው የሚሠሩ መሆናቸው ሳይጠቀስ የማይታለፍ ነው። አንዳንድ ግለሰቦች እንደነዚህ ያሉትን ብቃት የሌላቸው ሰዎች በማማከር ብዙ ገንዘብ አባክነዋል።
ሌላው ቀርቶ የሠለጠነና ብቃት ያለውን የአእምሮ ሕክምና ባለሙያ በተመለከተ እንኳ ግምት ውስጥ የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች አሉ። አንድን ሐኪም ወይም የቀዶ ሕክምና ባለሙያ በምንመርጥበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን አቋማችንን የሚያከብርልን መሆኑን እርግጠኞች መሆን ይኖርብናል። በተመሳሳይም ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ አቋማችንን የማያከብር የአእምሮ ጤና ባለሙያ ማማከር አደገኛ ይሆናል። ብዙ ክርስቲያኖች የአእምሮና የስሜት አለመረጋጋት ቢኖርባቸውም “የክርስቶስ ኢየሱስ ዓይነት የአእምሮ ዝንባሌ” ለመያዝ ጥርሳቸውን ነክሰው እየጣሩ ነው። (ሮሜ 15:5 አዓት) እነዚህ ክርስቲያኖች አስተሳሰባቸውን ወይም ባሕሪያቸውን ሊለውጥባቸው የሚችል ማንኛውም ሰው ያለው ዝንባሌ በሚገባ ያሳስባቸዋል። አንዳንድ የአእምሮ ሕክምና ባለሙያዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆነ እምነት የሚከለክለው ማንኛውም ነገር አላስፈላጊ እንደሆነ አልፎ ተርፎም ለአእምሮ ጤና መቃወስ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አድርገው ይመለከቱታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተወገዙትን እንደ ግብረሰዶም ወይም ለትዳር ጓደኛ ታማኝ አለመሆን የመሰሉትን ድርጊቶች ሊደግፉ አልፎ ተርፎም እነዚህን ነገሮች እንድንፈጽም ሊያዙን ይችላሉ።
እነዚህ ሐሳቦች ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በውሸት እውቀት የተባለ ክርክር’ ሲል ከጠራቸው መካከል የሚመደቡ ናቸው። (1 ጢሞቴዎስ 6:20) ስለ ክርስቶስ የሚናገረውን እውነት የሚቃወሙ ከመሆናቸውም ሌላ የዚህ ዓለም ‘ፍልስፍናና ከንቱ መታለል’ ክፍል ናቸው። (ቆላስይስ 2:8) የመጽሐፍ ቅዱስ አቋም ግልጽ ነው፦ “ከይሖዋ ካልሆነ በቀር ጥበብ፣ ወይም ማስተዋል ወይም ምክር ቢሆን የለም።” (ምሳሌ 21:30 አዓት) “ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ” የሚሉ የአእምሮ ሕክምና ባለሙያዎች ‘ክፉ ባልንጀራ’ ናቸው። የታወከው አእምሮ እንዲድን ከመርዳት ይልቅ ጭራሹኑ ‘መልካሙን ዓመል ያበላሻሉ።’—ኢሳይያስ 5:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33
ስለዚህ የአእምሮ ሕክምና ባለሙያ ማማከር እንዳለበት የሚሰማው አንድ ክርስቲያን የባለሙያውን ብቃት፣ ዝንባሌ እና ያለውን ስም እንዲሁም የሚያዝለት ነገር የሚያስከትለውን ውጤት በጥንቃቄ መመርመር ይኖርበታል። አንድ ከባድ የስሜት ሥቃይ ያለበት ክርስቲያን ይህንን ራሱ ማድረግ ካልቻለ ምናልባት አንድ የሚቀርበው የጎለመሰ ሰው ወይም ዘመዱ ሊረዳው ይችል ይሆናል። አንድን ሕክምና በተመለከተ ምን ቢያደርግ ጥበብ እንደሚሆን እርግጠኛ ያልሆነ ክርስቲያን ምንም እንኳ የመጨረሻው ውሳኔ ለእርሱ (ወይም ለወላጆቹ ወይም ለባልና ሚስቱ በጋራ) የተተወ ቢሆንም እንኳ ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር መወያየቱ ጠቃሚ ሆኖ ሊያገኘው ይችላል።d
ሳይንስ ከቀደሙት ዘመናት ይልቅ ዛሬ ሥቃይን ለማቃለል ብዙ ማድረግ ችሏል። ይሁንና ዛሬም ቢሆን መፍትሔ ሊያገኙ የማይችሉና እስከዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ድረስ ከመጽናት በቀር ሌላ አማራጭ የማይገኝላቸው ብዙ አካላዊና አእምሮአዊ ሕመሞች አሉ። (ያዕቆብ 5:11) እስከዚያው ድረስ ግን “ታማኝና ልባም ባሪያ፣” ሽማግሌዎችና በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎችም የርኅራኄና የድጋፍ ክንዳቸውን ከመዘርጋት ወደኋላ አይሉም። ይህ ሕመም የማይኖርበት አስደሳች ጊዜ እስኪመጣ ድረስ እንዲጸኑም ይሖዋ ራሱ ያበረታቸዋል።—ማቴዎስ 24:45፤ መዝሙር 41:1-3፤ ኢሳይያስ 33:24
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንድ ጊዜ ግለሰቦች ምናልባት ለከፍተኛ የሥራ ደረጃ ሲታጩ የሥነ አእምሮ ግምገማ (ሳይካትሪክ ኢቫሉዌሽን) እንዲደረግላቸው ይጠየቁ ይሆናል። አንድ ሰው ይህን ዓይነቱን ግምገማ የመቀበልና ያለመቀበሉ ጉዳይ የራሱ ውሳኔ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የሥነ አእምሮ ግምገማ ማለት የሥነ አእምሮ ሕክምና ማለት እንዳልሆነ ሊጤን ይገባዋል።
b በመጠበቂያ ግንብ 5-111 ላይ የወጣውን “የመንፈስ ጭንቀትን ለማስወገድ በሚደረገው ውጊያ አሸናፊ መሆን” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c አንዳንድ የአእምሮ ሕመሞች ትክክለኛውን ዓይነት መድኃኒት ካገኙ ጥሩ ለውጥ የሚያሳዩ ይመስላል። ይሁንና እነዚህ መድኃኒቶች በትክክለኛው መጠን ካልተወሰዱ የሚያስከትሉት ጉዳት ስለሚኖር ጥሩ ችሎታና ተሞክሮ ባለው ሐኪም ወይም የሥነ አእምሮ ባለሙያ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት በጥንቃቄ መወሰድ ይኖርባቸዋል።
d በጥቅምት 15, 1988 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “አንድ ክርስቲያን የአእምሮ ጭንቀት ሲገጥመው” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።