የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 4/15 ገጽ 10-11
  • ብቸኝነትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ብቸኝነትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
  • ንቁ!—2015
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ተፈታታኙ ነገር
  • ጓደኛ የሌለኝ ለምንድን ነው?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • የብቸኝነት ስሜት ሕይወትህን እንዲያጨልመው አትፍቀድለት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • የብቸኝነት ስሜት እንዲለቀኝ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች
  • የብቸኝነት ስሜት ስውሩ ሥቃይ
    ንቁ!—1993
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2015
g 4/15 ገጽ 10-11
አንዲት ልጅ ብቻዋን ተቀምጣለች፤ ሌሎች ልጆች እያወሩ ሲሳሳቁ ትመለከታቸዋለች

ለቤተሰብ | ወጣቶች

ብቸኝነትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?

ተፈታታኙ ነገር

“ሁለት ጓደኞች ነበሩኝ፤ እኔን ሳይጨምሩኝ ብዙ ነገሮችን አብረው ያደርጋሉ። ከዚያም ደስ የሚል ጊዜ አብረው እንዳሳለፉ ይነግሩኛል። አንድ ቀን አንደኛዋ ጓደኛዬ ቤት ደወልኩ፤ ሁለቱ ጓደኞቼ አብረው ነበሩ፤ ስልኩን ያነሳው ሌላ ሰው ነበር፤ ሆኖም ሁለቱ ጓደኞቼ እያወሩ ሲሳሳቁ ከጀርባ ሰማኋቸው። እኔ ግን ሲሳሳቁ ከመስማት በቀር የደስታቸው ተካፋይ አለመሆኔ የበለጠ ብቸኝነት እንዲሰማኝ አደረገ!”—ማሪያa

እናንተስ እንደተተዋችሁና ብቸኛ እንደሆናችሁ ተሰምቷችሁ ያውቃል? ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በዚህ ረገድ ሊረዳችሁ ይችላል። በመጀመሪያ ግን ብቸኝነትን በተመለከተ ልታውቋቸው የሚገቡ ጥቂት ነገሮች አሉ።

ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል፣ አልፎ አልፎ ብቸኝነት ይሰማዋል። ይህ ደግሞ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ሰዎችንም ይጨምራል። ለምን? ምክንያቱም የብቸኝነት ስሜት የተመካው አንድ ሰው ምን ያህል ጓደኞች አሉት በሚለው ላይ ሳይሆን ጓደኞቹ እነማን ናቸው በሚለው ላይ ነው። በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሚመስል ሰው ሁልጊዜ በሰው የተከበበ ቢሆንም እውነተኛ ጓደኞች ላይኖሩት ስለሚችል ብቸኝነት ይሰማዋል።

የብቸኝነት ስሜት ለጤንነት አደገኛ ሊሆን ይችላል። ተመራማሪዎች የ148 ጥናታዊ ጽሑፎችን ውጤቶች በጥንቃቄ ካጤኑ በኋላ እንደደረሱበት ከሆነ ከሌሎች ጋር ማኅበራዊ ግንኙነት አለመፍጠር ዕድሜን ሊያሳጥር ይችላል፤ እንዲሁም በጤንነት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት “ከመጠን በላይ መወፈር ከሚያስከትለው ጉዳት እጥፍ” ይሆናል፤ ወይም ደግሞ “በየቀኑ 15 ሲጋራዎች ከማጨስ ጋር የሚተካከል” ጉዳት ያስከትላል።

የብቸኝነት ስሜት ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል። የብቸኝነት ስሜት፣ አንድ ሰው ጓደኛ አድርጎ ሊቀበለው ፈቃደኛ ከሚሆን ማንኛውም ሰው ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት እንዲፈልግ ሊያደርገው ይችላል። አለን የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ብቸኝነት ሲሰማችሁ የሌሎችን ትኩረት ለማግኘት ስትሉ የማታደርጉት ነገር አይኖርም። የማንንም ትኩረት ሳያገኙ ከመቅረት ግለሰቡ ማንም ይሁን ማን የሆነን ሰው ትኩረት ማግኘት እንደሚሻል ማሰብ ልትጀምሩ ትችላላችሁ። ይህ ደግሞ ችግር ውስጥ ሊከትታችሁ ይችላል።”

ቴክኖሎጂ፣ ብቸኝነት እንዳይሰማችሁ የሚያደርገው ሁልጊዜ አይደለም። “በቀን ውስጥ ለመቶ ሰው የሞባይል ወይም የኢሜይል መልእክት ብልክም እንኳ በሚያስገርም መልኩ ብቸኝነት ሊሰማኝ ይችላል” በማለት ናታሊ የምትባል አንዲት ወጣት ተናግራለች። ታይለር የተባለ ወጣትም ተመሳሳይ ስሜት አለው። እንዲህ ብሏል፦ “የጽሑፍ መልእክት መላላክ እንደ መክሰስ ሲሆን ፊት ለፊት እየተያዩ መነጋገር ግን እንደሚያጠግብ ምግብ ነው። መክሰስ አስደሳች ቢሆንም በደንብ ለመጥገብ ግን ደህና ምግብ ያስፈልጋችኋል።”

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ጥሩ ጥሩውን አስቡ። ለምሳሌ ያህል፣ ፎቶግራፍ ለማስቀመጥና ለማየት በተዘጋጀ አንድ ድረ ገጽ ላይ ጓደኞቻችሁ እናንተ ባልተጋበዛችሁበት አንድ ግብዣ ላይ የተነሷቸውን ፎቶግራፎች አያችሁ እንበል። በዚህ ጊዜ ጓደኞቻችሁ ሆን ብለው እንዳገለሏችሁ ይሰማችሁ ይሆናል፤ ሆኖም ስለ ሁኔታው ጥሩ ጥሩውን ማሰብም ትችላላችሁ። በዚያ ግብዣ ላይ ያልተጠራችሁት ለምን እንደሆነ የተሟላ መረጃ ስለሌላችሁ ለምን ክፉ ክፉውን ታስባላችሁ? ከዚህ ይልቅ ያልተጠራችሁበትን ምክንያት በተመለከተ አዎንታዊ የሆነውን ነገር ለማሰብ ሞክሩ። ብዙውን ጊዜ የብቸኝነትን ስሜት የሚያመጣው የተፈጠረው ሁኔታ ሳይሆን ለሁኔታው ያላችሁ አመለካከት ነው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 15:15

ሁኔታውን አጋንናችሁ ከመመልከት ተቆጠቡ። ብቸኝነት ሲሰማችሁ ‘ማንም የሚጋብዘኝ የለም’ ወይም ‘ሰዎች ሁልጊዜ ያገሉኛል’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሁኔታውን እንዲህ አጋንኖ መመልከት የባሰውን ብቸኝነት እንዲሰማችሁ ከማድረግ ውጭ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። እንዲህ ያለው አመለካከት ማቆሚያ የሌለው ሽክርክሪት ይፈጥራል፤ ይኸውም ሰዎች እንዳገለሏችሁ ሲሰማችሁ እናንተም ራሳችሁን ታገልላላችሁ፤ ከዚያም ብቸኝነት ይሰማችኋል፤ ይህ ደግሞ መልሶ ሰዎች እንዳገለሏችሁ እንዲሰማችሁ ያደርጋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 18:1

በዕድሜ ከሚበልጧችሁ ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት ፈቃደኛ ሁኑ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዳዊት በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ሳለ በዕድሜ 30 ዓመት ከሚበልጠው ከዮናታን ጋር ጓደኝነት እንደመሠረተ ይናገራል። ዳዊትና ዮናታን የዕድሜ ልዩነት ቢኖራቸውም የቅርብ ጓደኛሞች ሆነዋል። (1 ሳሙኤል 18:1) እናንተም እንዲህ ዓይነት ጓደኛ ልታገኙ ትችላላችሁ። የ21 ዓመቷ ኪያራ እንዲህ ብላለች፦ “ከእኔ በዕድሜ የሚበልጡ ጓደኞች መያዝ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው መመልከት ችያለሁ። ከሃያ ዓመት በላይ የሚበልጡኝ የምወዳቸው ጓደኞች አሉኝ፤ ብስለታቸውን እንዲሁም የተረጋጉ መሆናቸውን በጣም አደንቃለሁ።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ኢዮብ 12:12

ለብቻ መሆን ያሉትን ጥቅሞች አድንቁ። አንዳንድ ሰዎች ለአንድ አፍታም እንኳ ከሰው ከተለዩ ወዲያውኑ ብቸኝነት ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ለብቻ መሆናችሁ በራሱ ብቸኝነት እንዲሰማችሁ ሊያደርግ አይገባም። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ከሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ የሚወድ ቢሆንም ብቻውን መሆን የሚፈልግበት ጊዜም ነበር። (ማቴዎስ 14:23፤ ማርቆስ 1:35) እናንተም እንዲሁ ማድረግ ትችላላችሁ። ለብቻ መሆንን እንደ ጉዳት ከመመልከት ይልቅ ይህን ጊዜ ተጠቅማችሁ ስላገኛችኋቸው በረከቶች አስቡ። ይህም ሌሎች ጓደኛቸው ለማድረግ የሚመኙት ዓይነት ሰው እንድትሆኑ ያስችላችኋል።—ምሳሌ 13:20

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

ቁልፍ ጥቅሶች

  • “ጎስቋላ ሰው ዘመኑ ሁሉ አስከፊ ነው፤ ደስተኛ ልብ ያለው ሰው ግን ሁልጊዜ ግብዣ ላይ ያለ ያህል ነው።”—ምሳሌ 15:15

  • ‘ራሱን የሚያገል ሰው ጥበብን ሁሉ ይቃወማል።’—ምሳሌ 18:1

  • “በዕድሜ በገፉት መካከል ጥበብ፣ ከረጅም ዕድሜስ ጋር ማስተዋል አይገኝም?”—ኢዮብ 12:12

ቦ

ቦ

“ብዙ ወጣቶች ብቸኝነት ይሰማቸዋል፤ ሆኖም ሌላ ሰው እንዳያውቅባቸው ለማድረግ የሚጥሩ ይመስለኛል። ለምሳሌ ያህል፣ የሞባይል መልእክት የሚልኩላቸው ወይም በማኅበራዊ ድረ ገጾች አማካኝነት የሚያገኟቸው ‘ጓደኞቻቸው’ በአካል ከእነሱ ጋር አይሆኑም፤ ይህ ደግሞ ብቸኝነት እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል።”

አቢጌል

አቢጌል

“ሁላችንም ብንሆን ወደ ሌላ አካባቢ የሄዱ ወይም በሌላ ምክንያት አሁን ከእኛ ጋር የተጠፋፉ ጓደኞች አሉን። የሚኖሩት ሩቅ ቢሆንም እንኳ እንደዚህ ካሉት ጓደኞቻችን ጋር ግንኙነታችንን መቀጠል ጥሩ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ከቀድሞ ጓደኛችሁ ጋር ማውራቱ ብቻ እንኳ ደስ የሚል ስሜት እንዲሰማችሁ ሊያደርግ ይችላል።”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ