የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 11/15 ገጽ 7-9
  • ዓይነ ስውርነት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዓይነ ስውርነት
  • ንቁ!—2015
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዓይነ ስውራን ስለ ይሖዋ እንዲማሩ እርዷቸው
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2015
  • ሕይወት የሚቀይሩ ነጠብጣቦች
    የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
  • በአገልግሎት ረገድ ክህሎታችንን ማዳበር—ለዓይነ ስውራን መመሥከር
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2020
  • ምሥራቹን ለማየት የታወሩ ዓይኖችን መግለጥ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2015
g 11/15 ገጽ 7-9
ፓኪና ባለቤቷ

ዓይነ ስውርነት

“የዓይኔን ብርሃን ያጣሁት ገና እንደተወለድኩ ኃይለኛ የዓይን ጠብታ በተደረገልኝ ጊዜ ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ ሙሉ በሙሉ ዓይነ ስውር ሆንኩ፤ ከዚያም ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ገባሁ።” —ፓኪ፣ ባለቤቷም ዓይነ ስውር የሆነ በጉልምስና ዕድሜ ላይ የምትገኝ ሴት።

ዓይነ ስውርነት ወይም ሥር የሰደደ የማየት እክል አደጋንና በሽታን ጨምሮ ብዙ መንስኤ ሊኖረው ይችላል። እነዚህ ችግሮች ዓይንን፣ የዓይን ነርቮችን ወይም አንጎልን ሊጎዱ ይችላሉ። በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች ሁኔታውን መቀበል ይከብዳቸዋል፤ እንዲሁም በሐዘንና በፍርሃት ይዋጣሉ። ይሁንና ብዙዎች ችግሩን መቋቋምና አርኪ ሕይወት መምራት ችለዋል።

ዓይናችን በዙሪያችን ስላለው ዓለም መረጃ የምናገኝበት ዋነኛው መንገድ እንደሆነ ግልጽ ነው። በመሆኑም አንድ ሰው የዓይኑን ብርሃን ሲያጣ ሌሎች የስሜት ሕዋሳቱን ይኸውም የማዳመጥ፣ የማሽተት፣ የመዳሰስና የመቅመስ ችሎታዎቹን ይበልጥ ለመጠቀም ይገደዳል።

ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተባለው መጽሔት በገለጸው መሠረት፣ በአንጎልና በነርቮች ላይ የተደረገው ምርምር አንጎላችን “አንድ ዓይነት ለውጥ ሲያጋጥመው በሂደት ራሱን ከሁኔታው ጋር እንደሚያስማማ” ያሳያል። መጽሔቱ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “አንጎላችን ከአንድ የስሜት ሕዋስ መረጃ ማግኘት ሲያቅተው ሌሎች የስሜት ሕዋሳትን ለመደገፍና መረጃ እንዲሰጡት ለማስተባበር ሲል ራሱን እንደ አዲስ የማደራጀት ችሎታ አለው።” እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት።

ማዳመጥ፦ ከእግር ኮቴ አንስቶ እስከ ሰው ድምፅ ድረስ፣ የምንሰማው ማንኛውም ድምፅ በዓይነ ሕሊናችን አንድ ምስል እንድንስል ይረዳናል። ፈርናንዶ የተባለ ዓይነ ስውር “ሰዎችን በድምፃቸው ወይም በኮቴያቸው ብቻ መለየት እችላለሁ” በማለት ተናግሯል። ኹዋን የተባለ ሌላ ዓይነ ስውር ደግሞ “ዓይነ ስውራን ሰዎችን የሚለዩት በድምፃቸው ነው” ብሏል። እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ ዓይነ ስውራንም የተለያየ ዓይነት ስሜት ለማስተላለፍ የሚረዳውን የሰዎችን የድምፅ ቃና ያስተውላሉ።

በሚገባ የሠለጠነ ጆሮ ያለው አንድ ዓይነ ስውር ከሚሰማቸው ድምፆች በመነሳት ስለ አካባቢው፣ ለምሳሌ መኪና እየመጣ ስላለበት አቅጣጫ፣ ስለ አንድ ክፍል ስፋት እንዲሁም ሊያደናቅፉት የሚችሉ ነገሮች ስላሉበት ቦታ ብዙ መረጃ ማግኘት ይችላል።

ማሽተት፦ አንድ ዓይነ ስውር በዚህ የስሜት ሕዋስ አማካኝነት የአንድን ነገር ሽታ ከማወቅ ባለፈ ብዙ መረጃ ማግኘት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በመንገድ ላይ እየሄደ ሳለ የማሽተት ችሎታው እንደ ሻይ ቤት፣ ምግብ ቤት፣ የገበያ ስፍራና እነዚህን የመሳሰሉ ቦታዎች የት እንደሚገኙ በዓይነ ሕሊናው መሳል እንዲችል ይረዳዋል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ የተለመዱ ድምፆችም ከሽታው ጋር ተዳምረው መረጃውን ያጠናክሩለታል፤ ከመዳሰስ ችሎታም ጋር በተያያዘ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

መዳሰስ፦ ፍራንሲስኮ “ጣቶቼ ዓይኖቼ ናቸው” በማለት ተናግሯል። ዱላ መጠቀም የእነዚህን “ዓይኖች” “የማየት” ችሎታ ይጨምረዋል። ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የነበረውና ከልጅነቱ ጀምሮ ዱላ ሲጠቀም የኖረው ማናሴስ እንዲህ ብሏል፦ “ሌሎች የስሜት ሕዋሳቴን፣ የማስታወስ ችሎታዬን እንዲሁም የመንገዱን ዓይነት የሚነግረኝን ዱላዬን በመጠቀም ያለሁበትን ቦታ በእርግጠኝነት ማወቅ እችላለሁ።”

አንድ ሰው በብሬይል የተዘጋጀ መጠበቂያ ግንብ ሲያነብ

በብሬይል የተዘጋጀ መጠበቂያ ግንብ ማንበብ

የመዳሰስ ችሎታ በርካታ ዓይነ ስውራን በብሬይል የተዘጋጁ ጽሑፎችን ማንበብ እንዲችሉ ይረዳቸዋል። በአሁኑ ጊዜ አንድ ዓይነ ስውር አእምሮውንም ሆነ መንፈሳዊ ሕይወቱን ሊያጎለብቱለት የሚችሉ የተለያዩ አጋዥ መሣሪያዎችን ማግኘት ይችላል። በብሬይል ከተዘጋጁ ጽሑፎች በተጨማሪ በድምፅ የተቀዱ ነገሮችና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አሉ። ዓይነ ስውራን በእነዚህ መሣሪያዎች በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስንና የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማንበብ ይችላሉ።a

እነዚህ ዝግጅቶች ቀደም ሲል የተጠቀሱት ፓኪና ባለቤቷ ወደር የሌለው መጽናኛና ተስፋ እንዲያገኙ ረድተዋቸዋል። ትልቅ መንፈሳዊ ቤተሰብ የሆነው፣ በአካባቢው የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያን ጉባኤም ድጋፍ አልተለያቸውም። ፓኪ “አሁን በተወሰነ መጠንም ቢሆን የሌሎች እርዳታ ሳያስፈልገን ጥሩ ኑሮ እየመራን ነው” ብላለች።

እርግጥ ነው፣ ዓይነ ስውርነት የራሱ የሆኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉት። እነዚህን ፈታኝ ሁኔታዎች ተጋፍጠው ከሕይወት የሚገኘውን ደስታ እያጣጣሙ ያሉ ሰዎች መኖራቸው፣ የሰው ልጅ ምን ያህል ከሁኔታዎች ጋር የመላመድና ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ እንዳለው ያሳያል!

a የይሖዋ ምሥክሮች ከ25 በሚበልጡ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በብሬይል ያዘጋጃሉ።

ዓይነ ስውር ብሆንም በሕይወቴ ደስተኛ ነኝ

ማርኮ አንቶንዮና ዳንቴ የተባለው የሚመራው ውሻ

ማርኮ አንቶንዮ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ሲሆን ከአንድ ግለሰብ ጋር በሽርክና የሚያስተዳድረው ድርጅት አለው። ማርኮ ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር ነው። ስለሚያስደስቱት ነገሮችና ስላጋጠሙት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ንቁ! መጽሔት ቃለ ምልልስ አድርጎለታል።

አንድ ድርጅት እያስተዳደርክ ነው። ይህን ማድረግ የቻልከው እንዴት ነው?

ሥራዬ የስልክ ጥያቄዎችን ማስተናገድ፣ ከደንበኞችና ከዕቃ አቅራቢዎች ጋር መነጋገር እንዲሁም ከባንክ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ማከናወን ነው።

የምትወደው ምን ዓይነት መዝናኛ ነው?

ሙዚቃ እወዳለሁ። ምክንያቱም ዘና ያደርገኛል። ፒያኖም እጫወታለሁ፤ ይህንን ማድረግ ግን ቀላል አይደለም። ምክንያቱም በብሬይል የተዘጋጀውን ሙዚቃ እያነበብኩ በአንድ ጊዜ በሁለቱም እጆቼ መጫወት አልችልም። አንድን ሙዚቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ስጫወት በቀኝ እጄ ሙዚቃውን እያነበብኩ በግራ እጄ ደግሞ ፒያኖውን እጫወታለሁ። ከዚያም እጆቼን እያለዋወጥኩ ደጋግሜ እጫወተዋለሁ። ሙዚቃውን በደንብ ስችለው ሁለቱንም እጆቼን እጠቀማለሁ።

ያጋጠሙህ ለየት ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉ?

ልጅ ሳለሁ ወላጆቼም ሆኑ ወንድሞቼ ይንከባከቡኝ የነበረ ሲሆን እንደ ዓይነ ስውር አይቆጥሩኝም ነበር። በተደጋጋሚ ጊዜ እጋጭና እወድቅ እንደነበር ባልክድም ማየት የሚችሉ ሰዎች የሚያከናውኗቸውን አብዛኞቹን ነገሮች ውሎ አድሮ ማከናወን ችያለሁ። አዋቂ ከሆንኩ በኋላ ቅር የሚለኝ ነገር ቢኖር መኪና መንዳት አለመቻሌ ብቻ ነው።

አሁን ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ስሆን የምንከባከበውና የሚንከባከበኝ አፍቃሪ ቤተሰብ አለኝ። ልጄ ዴቪድ ከእኔ የወረሰው የዓይን ነርቭ በሽታ አለበት። በተቻለኝ መጠን ለእሱ ጥሩ ምሳሌ ለመሆን እሞክራለሁ። ታጋሽና ቆራጥ ከሆነ ብዙ ነገሮችን ሊያከናውን እንደሚችል ላስተምረው እፈልጋለሁ።

አሁን የሚመራህ የሠለጠነ ውሻ አለህ። ውሻ እንዲመራህ ማድረግ የመረጥከው ለምንድን ነው?

ከውሻዬ ከዳንቴ ጋር ስሆን ያለስጋት በፍጥነት መራመድ እችላለሁ። ወደ አንድ ቦታ ለመጀመሪያ ጊዜ መሄድ ስፈልግ፣ ዓይነ ስውር ያልሆነችው ባለቤቴ ሎሊ አብራን ትመጣለች፤ ይህም እኔና ዳንቴ መንገዱን እንድናውቀው ይረዳናል። መጀመሪያ ላይ በውሻ ተማምኜ መሄድ ከብዶኝ እንደነበር አልክድም። ውሎ አድሮ ግን በዳንቴ ሙሉ በሙሉ መተማመን ችያለሁ። ምክንያቱም በአካባቢው ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠር ዳንቴ ትኩረቱ ሳይከፋፈል ያሰብኩት ቦታ ያደርሰኛል። ማሰሪያውን ስፈታለት ግን ልክ እንደ ማንኛውም ውሻ ይሯሯጣል።

የይሖዋ ምሥክር እንደመሆንህ መጠን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይጠበቅብሃል፤ ታዲያ ይህን የምታደርገው እንዴት ነው?

ለዓይነ ስውራን የሚሆኑ አጋዥ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ባልነበሩበት ወቅት ሎሊ መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ታነብልኝ ነበር። ሎሊ ከፍተኛ እርዳታ አበርክታልኛለች። በዚህም የተነሳ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ንግግሮችን እስከ ማቅረብ ደርሻለሁ። አሁን ግን መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች ጽሑፎችን በብሬይል ስለማገኝ ራሴ ማንበብ እችላለሁ። በተጨማሪም በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን jw.org የተባለውን ድረ ገጽ በመጠቀም በድምፅ የተቀዱ ጽሑፎችን አወርዳለሁ። ኮምፒውተር ስክሪኔ ላይ ያለውን ጽሑፍ ለማንበብ የሚያስችል መሣሪያም አለኝ። ይህ መሣሪያ፣ ወደ ላይ ብቅ ብቅ እያሉ የብሬይል ፊደላት እንዲፈጠሩ የሚያደርጉ ትናንሽ የሚጎረብጡ ነገሮች አሉት። በጣም አስገራሚ መሣሪያ ነው!

በተለይ ደግሞ፣ ስፔን ውስጥ ማድሪድ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የብሬይል ጽሑፎችን በማዘጋጀቱ ሥራ ድጋፍ የመስጠት መብት በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። እነዚህን ጽሑፎች የሚያዘጋጁት ወንድሞች የጽሑፎቹን ጥራት ለማሻሻል ስለሚረዳቸው ዓይነ ስውራን የሚሰጡትን አስተያየት ከፍ አድርገው ይመለከታሉ። ስለዚህ መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ እንደሚወዱኝና እንደሚያደንቁኝ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ።

ከሌሎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስትሃል?

እንዴታ! በተለይ ደግሞ ከቤተሰቤና ከቤት ወደ ቤት አብረውኝ ከሚሰብኩ የእምነት ባልንጀሮቼ ጋር ጊዜ ማሳለፍ በጣም ያስደስተኛል። መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ከሌሎች የተለየሁ እንደሆንኩ አይሰማቸውም። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ዓይነ ስውር መሆኔን እንኳ ይረሱታል!

የስብከቱ ሥራ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ውድ ተስፋ ለሌሎች የማካፈል አጋጣሚ እንደሚሰጠኝም መግለጽ እፈልጋለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ ኢሳይያስ 35:5 በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር “የዓይነ ስውራን ዓይን [እንደሚገለጥ]” ይናገራል። ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ዓይነ ስውራንን መፈወሱ ወደፊት ይህ ትንቢት እንደሚፈጸም የሚያሳይ ናሙና ነው። (ማቴዎስ 15:30, 31) ስለዚህ እንደ ሌሎቹ የጤና ችግሮች ሁሉ ዓይነ ስውርነትም ጊዜያዊ ነው። ወደፊት ምድር ገነት ስትሆን ማንም ሰው ‘ታምሜአለሁ ወይም የአካል ጉዳተኛ ነኝ’ አይልም።—ኢሳይያስ 33:24፤ ሉቃስ 23:43

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ