ዓይነ ስውራን ስለ ይሖዋ እንዲማሩ እርዷቸው
1. ኢየሱስ ለዓይነ ስውራን ርኅራኄ እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?
1 ኢየሱስ የሚገደልበት ጊዜ ቀርቧል። ከኢያሪኮ ከተማ ወጥቶ እየተጓዘ ሳለ ሁለት ዓይነ ስውራን ለማኞች “ጌታ ሆይ፣ . . . ምሕረት አድርግልን!” እያሉ መጮኽ ጀመሩ። ኢየሱስ ከፊቱ ከሚጠብቁት ከባድ ፈተናዎች አንጻር በአእምሮው ውስጥ የሚመላለስ ብዙ ነገር ቢኖርም ቆም ብሎ ዓይነ ስውራኑን ጠራቸውና ፈወሳቸው። (ማቴ. 20:29-34) ኢየሱስ ለዓይነ ስውራን ርኅራኄ በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
2. አንድ ዓይነ ስውር ስናገኝ ልንመሠክርለት የምንችለው እንዴት ነው?
2 እርዳታ ለመስጠት ፈቃደኛ ሁኑ፦ አንድ ዓይነ ስውር ሰው ስታገኙ ራሳችሁን ካስተዋወቃችሁ በኋላ የእናንተ እርዳታ ያስፈልገው እንደሆነ ጠይቁት። ብዙውን ጊዜ ሰዎች እንዲህ ዓይነት የአካል ጉዳት ያለባቸውን ሰዎች መጠቀሚያ ለማድረግ ስለሚሞክሩ ግለሰቡ መጀመሪያ ላይ ጥርጣሬ ሊያድርበት ይችላል። ይሁንና ከልብ በመነጨ ስሜት ከተግባባችሁት እንዲሁም እሱን ለመርዳት ፍላጎት እንዳላችሁ ካሳያችሁ ግለሰቡ ሊረጋጋ ይችላል። በተጨማሪም ዓይነ ስውርነት የተለያየ ደረጃ እንዳለው አትርሱ፤ ይህም ግለሰቡ የሚያስፈልገው እገዛ ምን ያህል እንደሆነ ለመወሰን ያስችላችኋል። ለግለሰቡ እርዳታ ካደረጋችሁለት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ሥራ እንደምትካፈሉ ልትነግሩት ትችሉ ይሆናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ልታነቡለት እንደምትፈልጉ ግለጹለት፤ እንደ መዝሙር 146:8 ወይም ኢሳይያስ 35:5, 6 ያሉ ጥቅሶችን ልታነቡለት ትችላላችሁ። ብሬይል ማንበብ የሚችል ከሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመማር የሚረዱ በብሬይል የተዘጋጁ ጽሑፎችን ብታመጡለት ይፈልግ እንደሆነ ጠይቁት። በተጨማሪም በjw.org ላይ የሚገኙ በድምፅ የተቀዱ ፋይሎችን ማግኘት እንዲችል ልትረዱት ትችላላችሁ። የግለሰቡ ኮምፒውተር ስክሪኑ ላይ የሚታየውን ጽሑፍ ለማንበብ የሚያስችል ፕሮግራም የተጫነለት ከሆነ jw.org ላይ የሚወጡ የሚታተሙ ጽሑፎችን ወይም በRTF ፎርማት የሚዘጋጁ ጽሑፎችን ማንበብ ይችላል።—“ዓይነ ስውር የሆነን ሰው በምትረዱበት ወቅት . . .” የሚለውን ሣጥን ተመልከቱ
3. በክልላችን ውስጥ የሚገኙ ዓይነ ስውራንን መፈለግ የምንችለው እንዴት ነው?
3 ዓይነ ስውራንን መፈለግ፦ ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ብዙውን ጊዜ ዓይነ ስውራንን አናገኝም፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ ዓይነ ስውራን ቤታቸው ከሚመጣ የማያውቁት ሰው ጋር መነጋገር አይፈልጉም። በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ‘ፈልጎ’ ለእነሱ ምሥክርነት መስጠት ብዙ ጥረት ይጠይቃል። (ማቴ. 10:11) ዓይነ ስውር የሆነ የሥራ ባልደረባ ወይም አብሯችሁ የሚማር ሰው አለ? ቅድሚያውን ወስዳችሁ ግለሰቡን አነጋግሩት። በክልላችሁ ውስጥ ለዓይነ ስውራን የተከፈተ ትምህርት ቤት ካለ በብሬይል የተዘጋጁ አንዳንድ ጽሑፎቻችንን ለትምህርት ቤቱ ቤተ መጻሕፍት መስጠት ይቻል እንደሆነ ጠይቁ። ዓይነ ስውር የሆነ የቤተሰብ አባል ያለው ሰው ታውቃላችሁ? በክልላችሁ ውስጥ ለዓይነ ስውራን ጠቃሚ አገልግሎቶች የሚሰጡ ድርጅቶች ወይም ለዓይነ ስውራን የተዘጋጁ መኖሪያ ቤቶች የሚገኙባቸው ተቋማት አሉ? የይሖዋ ምሥክሮች ዓይነ ስውራንን ለመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ለዓይነ ስውሩ የቤተሰብ አባል፣ እንግዳ መቀበያ ክፍል ለሚሠራው ሰው ወይም ለተቋሙ ኃላፊ አስረዱ፤ ከዚያም በብሬይል የተዘጋጁ ጽሑፎችን ወይም በድምፅ የተቀዱ ነገሮችን ይፈልጉ እንደሆነ ጠይቋቸው። አምላክ በቅርቡ ዓይነ ስውርነትን እንደሚያስወግድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ተስፋ አሳዩአቸው። በተጨማሪም በብሬይል የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ በማግኘቱ የተጠቀመን አንድ ዓይነ ስውር ታሪክ የሚናገረውን በjw.org ላይ የወጣውን “ዊዝአውት ኢት አይ ዉድ ፊል ሎስት” የሚል ርዕስ ያለውን ቪዲዮ ልታሳዩአቸው ትችላላችሁ። ወደ ተቋሙ የመጣችሁበትን ዓላማ ማስረዳታችሁ በዚያ የሚገኙ ዓይነ ስውራንን ማነጋገር እንድትችሉ ፈቃድ እንዲሰጣችሁ ሊያደርግ ይችላል።
4. ከጃኔት ተሞክሮ ምን እንማራለን?
4 ጃኔት የተባለች አንዲት ዓይነ ስውር እህት ዓይነ ስውራን ወደሚኖሩበት አንድ ተቋም ሄደች። በዚያም ከአንዲት ወጣት ሴት ጋር ውይይት ጀመረች። ጃኔት “ኢየሱስ ዓይነ ስውራንን መፈወሱ ወደፊት ለዓይነ ስውራን ምን እንደሚያደርግላቸው ያሳያል” አለቻት። ከዚያም ራእይ 21:3, 4ን ካነበቡ በኋላ ጃኔት የአምላክ መንግሥት በጥቅሱ ላይ የሚገኙት ተስፋዎች እንዲፈጸሙ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ አብራራችላት። ወጣቷም ዝም ብላ ከቆየች በኋላ እንዲህ ስትል ተናገረች፦ “ይህን ሐሳብ ዓይነ ስውር ከሆነ ሰው ሰምቼ አላውቅም። ማየት የሚችሉ ብዙ ሰዎች፣ አንድ ሰው ለዓይነ ስውርነት የሚዳረገው ግለሰቡ ወይም የግለሰቡ አያት ቅድመ አያቶች በሠሩት መጥፎ ነገር የተነሳ እንደሆነ ያምናሉ።” ጃኔት ትክክለኛው ወደተባለው መጽሐፍ የሚወስድ ሊንክ ለወጣቷ በኢሜይል የላከችላት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በሳምንት ሁለቴ መጽሐፍ ቅዱስን አብረው ያጠናሉ።
5. ልክ እንደ ኢየሱስ ዓይነ ስውራንን የመፈወስ ችሎታ ባይኖረንም እንኳ ለእነሱ አሳቢነት ማሳየታችን ምን በረከት ሊያስገኝ ይችላል?
5 ኢየሱስ እንዳደረገው ዓይነ ስውራን ዓይናቸው እንዲበራላቸው ማድረግ እንደማንችል የታወቀ ነው፤ ይሁንና ቃል በቃል ዓይነ ስውር የሆኑትን ጨምሮ የዚህ ሥርዓት አምላክ አእምሯቸውን ያሳወረባቸው ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት እንዲገነዘቡ መርዳት እንችላለን። (2 ቆሮ. 4:4) ኢየሱስ በኢያሪኮ አቅራቢያ ያገኛቸውን ሰዎች የፈወሰው ‘በጣም ስላዘነላቸው’ ነው። (ማቴ. 20:34) እኛም ለዓይነ ስውራን እንዲህ ዓይነት ስሜት ካለን ከእነሱ መካከል አንዳንዶች ዓይነ ስውርነትን ከናካቴው ስለሚያስወግደው አምላክ ይኸውም ስለ ይሖዋ እንዲማሩ የመርዳት መብት ልናገኝ እንችላለን።