የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 8/15 ገጽ 3-4
  • ዓይነ ስውራን ምን ተስፋ አላቸው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዓይነ ስውራን ምን ተስፋ አላቸው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በኢየሱስ ዘመን ዓይነ ስውራንን መፈወስ
  • ምሥራቹን ለማየት የታወሩ ዓይኖችን መግለጥ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ዓይነ ስውራን ስለ ይሖዋ እንዲማሩ እርዷቸው
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2015
  • ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የሆነን ሰው ፈወሰ
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • ዓይነ ስውርነት
    ንቁ!—2015
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 8/15 ገጽ 3-4

ዓይነ ስውራን ምን ተስፋ አላቸው?

ጆን ሚልተን ሙሉ በሙሉ ዓይነ ስውር ቢሆንም እንኳ የጠፋችው ገነት እና ተመልሳ የምትመጣዋ ገነት የሚሉ ዕጹብ ድንቅ የሆኑ ልብ ወለድ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ደርሷል። ሄለን ኬለር ዓይነ ስውርና መስማት የተሳናት መሆኗ አካለ ስንኩላንን ለማስተማር ጥረት ከማድረግ አላገዳትም ነበር። አዎን፣ ዓይነ ስውራን የሆኑ ብዙ ሰዎች ችግሩን ተቋቋመው መኖር ችለዋል። ነገር ግን ሰው ሁሉ የዓይን ችግር ባይኖርበት ምንኛ አስደሳች ይሆን ነበር! በተለይም የምታፈቅረው ሰው ወይም ጓደኛህ ዓይነ ስውር ወይም ዓይኑ የደከመ ቢሆን በዚህ ሐሳብ ትስማማለህ።

እውነት ነው፣ በአንዳንድ አገሮች ማየት የተሳናቸው ሰዎች የዕለት ኑሯቸውን እንዲገፉ የሚያስችላቸውን ሙያ የሚማሩበት ፕሮግራም አላቸው። የብሬል ጽሑፍና ዓይነ ስውራንን ለመምራት የሠለጠኑ ውሾች ዓይነ ስውራንን በመርዳት ረገድ ብዙ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ሆኖም ብዙ ሰዎች ዓይነ ስውርነት ከማንኛውም ሌላ አካለ ጎደሎነት ይበልጥ አስፈሪ የሆነ የአካል ጉዳት እንደሆነ ይሰማቸዋል። አንድ ደራሲ “ዓይነ ስውር መሆን በዙሪያችን ያለውን ዓለም ለመገንዘብ የሚረዳንን ዋነኛውን ክፍል ማጣት ማለት ነው” በማለት ይህን አረጋግጠዋል። ከዚህም በላይ ብዙ ዓይነ ስውራን ለብዙ ነገሮች የሌሎችን ድጋፍ ይሻሉ።

በነገሩ በመገረም ዓይነ ስውርነት ይህን ያህል ሊበዛ የቻለው ለምን ይሆን? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ዓይነ ማዝ (ትራኮማ) ስለ ተባለ በሽታ ሰምተህ ታውቃለህን? ይህ በሽታ ወደ ዘጠኝ ሚልዮን የሚጠጉ በሽተኞች ዓይነ ስውር እንዲሆኑ ምክንያት ሆኗል። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ ስለ ዓይነ ማዝ በሽታ እንዲህ ይላል፦ “ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍ ነው። በሽታው የሚያይለው ብዙ ሰዎች ተጨናንቀው በሚኖሩባቸውና ንጽሕና በጎደላቸው አካባቢዎች ነው። ለመተጣጠቢያ የሚሆን በቂ ውኃ አለመኖሩና በሰው ዓይነ ምድር ላይ የሚያርፉት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዝንቦች ለበሽታው መስፋፋት ዓይነተኛ መንስዔዎች ናቸው። በብዙ መንገዶች የዓይነ ማዝ በሽታ በሕክምና እጦት ሳይሆን በማኅበራዊ ኑሮ ችግሮች ምክንያት የሚከሰት ነው። የኑሮ ሁኔታዎች ሊሻሻሉ ቢችሉ፣ በአንድ አካባቢ ተጨናንቆ መኖር ቢቀንስ፣ ዝንቦች የማይራቡበት መንገድ ቢቀየስና በቂ የንጹሕ ውኃ አቅርቦት ቢኖር በበሽታው የሚጠቁት ሰዎች ቁጥር በጣም ይቀንስ ነበር።” ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች የሚሠቃዩበት ሌላው በሽታ ደግሞ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ኦንኮሰርኪያሲስ ወይም ሪቨር ብላይንድነስ በመባል የሚታወቀው ነው። በቪታሚን ኤእጥረት ምክንያት የሚከሰተው በእንግሊዝኛ ዜሮፍታልሚያ ስለሚባለው በሽታስ ምን ማለት ይቻላል? ምንም እንኳ የበሽታው ስም በቀላሉ የሚያዝ ባይሆንም ዓይነ ስውርነትን በማስከተሉ በጣም የታወቀ በሽታ ነው። የስኳር በሽታ፣ ዘጊ አናዳ (ዲፍቴሪያ)፣ ኩፍኝ፣ ስካርለት ፊቨርና የአባለዘር በሽታዎች መታወርን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

በዕድሜ እየገፋን ስንሄድ በእንግሊዝኛ የሎው ስፖት ተብሎ የሚጠራው የዓይናችን ክፍል በመታመሙ ወይም በእንግሊዝኛ ግላኮማ ተብሎ በሚጠራው የዓይን በሽታ በመያዛችን የማየት ኃይላችን ይዳከም ይሆናል። አለዚያም ካታራክት ተብሎ የሚጠራው የዓይናችን ሌንስ በሞራ የመጋረድ ሁኔታ ያጋጥመን ይሆናል። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ “አሁንም በዓለም ላይ በብዙ አገሮች ዓይንን በማሳወር ትልቁን ደረጃ የያዘው ካታራክት ነው። ይህም በጣም ያሳዝናል፤ ምክንያቱም ቀዶ ሕክምና በማድረግ በቀላሉ ሊድን የሚችል ነው” በማለት ዘግቧል።

ምንም እንኳ የዓይን ሕክምናን በተመለከተ ብዙ አዳዲስ ግኝቶች ቢኖሩም ዓይነ ስውርነት በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚወገድ አይመስልም። ያው ኢንሳይክሎፔድያ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ዓይነ ስውርነትን አስቀድሞ መከላከልም ሆነ በሽታውን በመድኃኒት ማከም ወይም ቀዶ ሕክምና በማድረግ መርዳት የሚቻለው በቀላሉ ሕክምና ማግኘት የሚችሉትን ሰዎች ብቻ ነው። ብዛቱ ቀላል ግምት የማይሰጠው የዓለም ሕዝብ ተመጣጣኝ ምግብ እስካላገኘና የአካባቢው ንጽሕና እስካልተሻሻለለት ድረስ መከላከል ይቻል የነበረው የመታወር አጋጣሚ አሁን ባለበት ከፍተኛ መጠን ይቆያል።”

መታወርን በመከላከል በኩል ፀረ ተዋሕስያን መድኃኒቶችና ቀዶ ሕክምና ከፍተኛ ድርሻ ቢያበረክቱም ዘላቂ ፈውስ የማግኘቱ ተስፋ የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ ተከናውኖ ከነበረው ነገር ጋር የተያያዘ ነው።

በኢየሱስ ዘመን ዓይነ ስውራንን መፈወስ

ዕድሜው በ30ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ አንድ ሰው በአቧራማ መንገድ ላይ በእግሩ ሲሄድ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። በመንገድ ዳር ተቀምጠው የነበሩ ሁለት ዕውሮች ይህ ሰው በዚያ መንገድ እያለፈ መሆኑን ሲሰሙ “ማረን” እያሉ ጮኹ። በወቅቱ የነበሩት ተመልካቾች ዕውሮቹን ዝም እንዲሉ ቢያዟቸውም “ማረን” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ሰውዬው ቆም አለና በደግነት “ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ?” አላቸው። ዕውሮቹም በጉጉት “ዓይኖቻችን ይከፈቱ ዘንድ አሉት።” ቀጥሎ የሚያስገርም ነገር ተፈጸመ፤ ሰውዬው ዓይኖቻቸውን ዳሰሰላቸውና ወዲያውኑ ማየት ቻሉ!—ማቴዎስ 20:29–34

ዓይነ ስውር የነበሩት እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ደስ ብሏቸው ይሆን! ሆኖም ዓይነ ስውርነት አሁንም በስፋት ያለ ችግር ነው። ከላይ የተጠቀሰው ሁኔታ አንድ ገጠመኝ ብቻ ነው። ሆኖም ይህ ትኩረት ልትሰጠው የሚገባህ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ለእነዚያ ዓይነ ስውራን በደግነት ተገፋፍቶ እንዲያዩ ያደረገው የናዝሬቱ ኢየሱስ ስለነበር ነው። ኢየሱስ የተላከው ‘ለድሆች ወንጌልን ለመስበክ’ እና ‘ዕውሮች ማየት እንዲችሉ’ ለመርዳት ነው።—ሉቃስ 4:18

ሰዎች በአምላክ መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በተደረጉት በእነዚህ ተአምራዊ ፈውሶች በጣም ተደንቀው ነበር። “ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፣ ጉንድሾችም ሲድኑ፣ አንካሶችም ሲሄዱ፣ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ” የሚል እናነባለን። (ማቴዎስ 15:31) ኢየሱስ ባደረጋቸው ፈውሶች ገንዘብ ከማስከፈል ወይም ችሎታው በሰው ዘንድ እንዲታይለት የይስሙላ ድርጊት ከመፈጸም ወይም የራሱን ክብር ከመፈለግ ይልቅ የይሖዋን ፍቅርና ምሕረት ጎላ አድርጎ ገልጿል። በተጨማሪም ኢየሱስ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም” ለነበሩት በመንፈሳዊ ለታወሩና ረዳት ለሌላቸው ሰዎች ያዝንላቸው ነበር።—ማቴዎስ 9:36

እንዲህ ያለው ታሪክ ሲያነቡት ደስ የሚል ቢሆንም ዛሬ ስላለው ሁኔታስ ምን ማድረግ ይቻል ይሆን? ብለህ ታስብ ይሆናል። ዛሬ እንደ ኢየሱስ ሰዎችን የሚፈውስ ማንም የለም። ታዲያ እነዚህ የፈውስ ታሪኮች ለእኛ ትርጉም አላቸውን? ለዓይነ ስውራን የሚሆን ተስፋስ ይኖር ይሆንን? ቀጥሎ ያለውን ርዕስ አንብብ።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ብዛቱ ቀላል ግምት የማይሰጠው የዓለም ሕዝብ ተመጣጣኝ ምግብ እስካላገኘና የአካባቢው ንጽሕና እስካልተሻሻለለት ድረስ መከላከል ይቻል የነበረው የመታወር አጋጣሚ አሁን ባለበት ከፍተኛ መጠን ይቆያል።”—ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ