የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g18 ቁጥር 3 ገጽ 6-13
  • ሐዘንን መቋቋም—አሁን ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሐዘንን መቋቋም—አሁን ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎች
  • ንቁ!—2018
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • 1. ቤተሰብህና ወዳጆችህ የሚያደርጉልህን ድጋፍ ተቀበል
  • 2. ለአመጋገብህ ትኩረት ስጥ፤ እንዲሁም እንቅስቃሴ አድርግ
  • 3. በቂ እንቅልፍ ለማግኘት ሞክር
  • 4. አመለካከትህን እንደ ሁኔታው አስተካክል
  • 5. ከጎጂ ልማዶች ራቅ
  • 6. ፋታ የምታገኝበት ጊዜ ይኑርህ
  • 7. ቋሚ ፕሮግራም ይኑርህ
  • 8. ትላልቅ ውሳኔዎችን በችኮላ ከማድረግ ተቆጠብ
  • 9. ሟቹን የሚያስታውሱህን ነገሮች አድርግ
  • 10. የሚያዝናናህ ነገር አድርግ
  • 11. ሌሎችን እርዳ
  • 12. ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች ገምግም
  • ከሐዘኔ ልጽናና የምችለው እንዴት ነው?
    የምትወዱት ሰው ሲሞት
  • ሐዘንን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • ሐዘን ለደረሰባቸው የሚሆን እርዳታ
    ንቁ!—2018
  • በሐዘን ለተደቆሱ ሰዎች የሚሆን ምክር
    ንቁ!—2011
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2018
g18 ቁጥር 3 ገጽ 6-13
በባሕር ዳርቻ ላይ ያሉ ሰዎች በወላንዶ ሲጫወቱና ፎቶግራፍ ሲነሱ

ሐዘን ለደረሰባቸው የሚሆን እርዳታ

ሐዘንን መቋቋም—አሁን ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎች

ሐዘንን መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ብዙ ሐሳቦች ይሰነዘራሉ፤ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የበለጠ ጠቃሚ እንደሆኑ ይሰማህ ይሆናል። ምናልባትም ሐዘን በሰዎች ላይ የሚፈጥረው ስሜት የተለያየ መሆኑ ለዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል። አንድን ሰው ለመጽናናት የሚረዳው ሐሳብ፣ ለሌላው ብዙም አይጠቅመው ይሆናል።

ያም ሆኖ ለብዙዎች ጠቃሚ የሆኑ አንዳንድ ምክሮች አሉ። ሐዘንን መቋቋም ስለሚቻልበት መንገድ ምክር የሚሰጡ ባለሙያዎች እነዚህን ሐሳቦች ብዙ ጊዜ ይጠቅሷቸዋል፤ ምክሮቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ዘመን የማይሽራቸው መመሪያዎች ጋር የሚስማሙ ናቸው።

1. ቤተሰብህና ወዳጆችህ የሚያደርጉልህን ድጋፍ ተቀበል

  • በባሕር ዳርቻ ላይ ያሉ ሰዎች በወላንዶ ሲጫወቱና ፎቶግራፍ ሲነሱ

    ሐዘንን ለመቋቋም ከሚረዱ በጣም ጠቃሚ ነገሮች ዋነኛው፣ ቤተሰብና ወዳጆች የሚያደርጉት ድጋፍ እንደሆነ አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ብቻህን መሆን ትፈልግ ይሆናል። እንዲያውም ሊረዱህ በሚፈልጉት ሰዎች ትበሳጭ ይሆናል። ይህ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው።

  • ሁልጊዜ ከሌሎች ጋር መሆን እንዳለብህ ሊሰማህ አይገባም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሊረዱህ የሚፈልጉ ሰዎችን አትግፋቸው። ወደፊት የእነሱ ድጋፍ የሚያስፈልግህ ጊዜ ይመጣ ይሆናል። አሁን የምትፈልገውና የማትፈልገው ነገር ምን እንደሆነ በደግነት ንገራቸው።

  • እንደ አስፈላጊነቱ፣ ከሌሎች ጋር የምትሆንበትና ለብቻህ የምታሳልፈው ጊዜ ይኑርህ።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል፤ . . . አንዱ ቢወድቅ ሁለተኛው ባልንጀራውን ደግፎ ሊያነሳው ይችላልና።”—መክብብ 4:9, 10

2. ለአመጋገብህ ትኩረት ስጥ፤ እንዲሁም እንቅስቃሴ አድርግ

  • የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ ከሐዘን ጋር ተያይዞ የሚመጣ ውጥረትን ለመቋቋም ሊረዳ ይችላል። የተለያዩ ፍራፍሬዎችን፣ አትክልቶችንና ቅባት ያልበዛባቸው ምግቦችን ለመመገብ ጥረት አድርግ።

  • ውኃና ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ሌሎች ፈሳሾችን በብዛት ጠጣ።

  • የምግብ ፍላጎትህ ከቀነሰ በትንሽ በትንሹ እያደረግክ ብዙ ጊዜ ለመብላት ሞክር። እንዲሁም እንደ ቫይታሚን ያሉ ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን እንዲያዙልህ ሐኪሞችን መጠየቅ ትችል ይሆናል።a

  • የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ለምሳሌ ፈጠን ፈጠን ባለ እርምጃ መሄድ ወይም በሌሎች እንቅስቃሴዎች መካፈል አሉታዊ ስሜቶችን ሊቀንስ ይችላል። አንዳንዶች የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረጋቸው በሕይወታቸው ውስጥ ስላጋጠማቸው ለውጥ ለማሰላሰል ያስችላቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ስለ ሐዘኑ እንዳያስቡ ይረዳቸዋል።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል።”—ኤፌሶን 5:29 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

3. በቂ እንቅልፍ ለማግኘት ሞክር

  • አልጋ

    እንቅልፍ ምንጊዜም አስፈላጊ ቢሆንም በተለይ ሐዘን ለደረሰባቸው ሰዎች የበለጠ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ሐዘኑ ከወትሮው የተለየ ድካም እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል።

  • እንደ ቡናና ሻይ እንዲሁም አልኮል ያሉ መጠጦችን እንዳታበዛ ተጠንቀቅ፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ጥሩ እንቅልፍ እንዳትተኛ እንቅፋት ይሆናሉ።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብዙ በመልፋትና ነፋስን በማሳደድ ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ ጥቂት እረፍት በማድረግ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል።”—መክብብ 4:6

4. አመለካከትህን እንደ ሁኔታው አስተካክል

  • ሐዘን የደረሰባት ሴት ስሜቷን ለወዳጇ ስትናገር

    እያንዳንዱ ሰው ሐዘኑን የሚገልጸው በተለያየ መንገድ እንደሆነ አስታውስ። ሐዘንህ እንዲወጣልህ የሚረዳህ ምን እንደሆነ የምታውቀው አንተ ራስህ ነህ።

  • ብዙ ሰዎች ስሜታቸውን ለሌሎች መናገራቸው ሐዘናቸውን ለመቋቋም እንደሚረዳቸው ይሰማቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ ስለ ሐዘናቸው አለማውራትን ይመርጣሉ። ስሜትን አውጥቶ መናገር ሐዘንን ለመቋቋም ጠቃሚ ስለመሆኑ ባለሙያዎች የተለያየ አስተያየት ይሰነዝራሉ። አንተም የልብህን አውጥተህ መናገር ብትፈልግም እያመነታህ ሊሆን ይችላል፤ ከሆነ ለቅርብ ወዳጅህ የተወሰኑ ነገሮችን ቀስ በቀስ መናገርህ ይጠቅምህ ይሆናል።

  • አንዳንድ ሰዎች ማልቀስ ሐዘናቸውን ለመቋቋም እንደረዳቸው ይሰማቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ ብዙ ባያለቅሱም ሐዘናቸውን መቋቋም የቻሉ ይመስላል።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እያንዳንዱ ልብ የራሱን መራራ ሐዘን ያውቃል።”—ምሳሌ 14:10 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

5. ከጎጂ ልማዶች ራቅ

  • የአልኮል መጠጥ የሚጠጣ ሰው

    ሐዘን የደረሰባቸው አንዳንድ ሰዎች አልኮል ከመጠን በላይ በመጠጣት ወይም ዕፅ በመውሰድ ስሜታዊ ሥቃያቸውን ለማስታገሥ ይሞክራሉ። ይሁንና እንዲህ ያለው የሐዘን “ማስረሻ” ጎጂ ነው። ግለሰቡ በዚህ መንገድ የሚያገኘው እፎይታ ጊዜያዊ ከመሆኑም ሌላ ብዙ መዘዞች ሊያስከትል ይችላል። ጭንቀትህን ለማረጋጋት፣ ጎጂ ያልሆኑ ዘዴዎችን ለመጠቀም ሞክር።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።”—2 ቆሮንቶስ 7:1

6. ፋታ የምታገኝበት ጊዜ ይኑርህ

  • ብዙዎች፣ ሁልጊዜ በሐዘን ከመዋጥ ይልቅ ሐዘናቸውን ለጊዜውም ቢሆን ለመርሳት በሚረዷቸው እንቅስቃሴዎች አልፎ አልፎ መካፈሉ ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

  • አዳዲስ ወዳጆች ለማፍራት ወይም የነበረህን ወዳጅነት ለማጠናከር ጥረት ማድረግ፣ አዳዲስ ሙያዎችን መማር አሊያም ደግሞ መዝናናት ከሐዘንህ ጊዜያዊ ፋታ ለማግኘት ሊረዳህ ይችላል።

  • በሐዘን የምትቆዝምበት ጊዜ ውሎ አድሮ እየቀነሰ ይሄዳል። ስለደረሰብህ ሐዘን ብቻ ከማሰብ ይልቅ በሌሎች እንቅስቃሴዎች የምትጠመድበት ጊዜ እያደር እየጨመረ እንደሄደ ታስተውል ይሆናል፤ ይህ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ . . . ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ለዋይታ ጊዜ አለው፤ ለጭፈራም ጊዜ አለው።”—መክብብ 3:1, 4

7. ቋሚ ፕሮግራም ይኑርህ

  • አንዲት ሴት በቀን መቁጠሪያ ተጠቅማ ፕሮግራም ስታወጣ

    ከሐዘኑ በኋላ ብዙም ሳትቆይ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችህ መካፈልህን ቀጥል።

  • የምትተኛበት፣ ሥራህን የምታከናውንበት እንዲሁም ሌሎች እንቅስቃሴዎችህን የምትፈጽምበት ቋሚ ፕሮግራም መከተልህ ሕይወትህ እንዲረጋጋ ሊረዳህ ይችላል።

  • ጠቃሚ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ራስህን ማስጠመድህ ሐዘኑ ያስከተለብህ ሥቃይ እንዲቀንስ ይረዳሃል።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እውነተኛው አምላክ ልቡን ደስ በሚያሰኙ ነገሮች እንዲጠመድ ስለሚያደርገው [ሰው] የሚያልፈውን የሕይወት ዘመኑን ፈጽሞ ልብ አይለውም።”—መክብብ 5:20

8. ትላልቅ ውሳኔዎችን በችኮላ ከማድረግ ተቆጠብ

  • የሚወዱት ሰው ከሞተ ብዙም ሳይቆይ ትላልቅ ውሳኔዎችን የሚያደርጉ ሰዎች ከጊዜ በኋላ በውሳኔያቸው ይቆጫሉ።

  • የሚቻል ከሆነ፣ ቤት ከመቀየርህ ወይም ሥራህን ከመለወጥህ አሊያም የሟቹን ንብረቶች ከማስወገድህ በፊት የተወሰነ ጊዜ ብትቆይ ጥሩ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል፤ ችኩሎች ሁሉ ግን ለድህነት ይዳረጋሉ።”—ምሳሌ 21:5

9. ሟቹን የሚያስታውሱህን ነገሮች አድርግ

  • አንድ ሰው በሞት ያጣትን ሚስቱን ፎቶግራፍ ለጓደኞቹ ሲያሳያቸው

    የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ብዙዎች፣ ሟቹን የሚያስታውሷቸውን ነገሮች ማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

  • ፎቶግራፎችን ወይም ሟቹን የሚያስታውሱህን ነገሮች መሰብሰብህ አሊያም ከሟቹ ጋር የተያያዙ ክንውኖችንና ታሪኮችን የምትመዘግብበት ማስታወሻ ደብተር ማዘጋጀትህ ሊያጽናናህ ይችላል።

  • አስደሳች ትዝታዎችን የሚቀሰቅሱ የሟቹን ንብረቶች አስቀምጥ፤ በኋላ ላይ ስሜትህ ሲረጋጋ እያወጣህ ልትመለከታቸው ትችላለህ።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የጥንቱን ዘመን አስታውስ።”—ዘዳግም 32:7

10. የሚያዝናናህ ነገር አድርግ

  • ለተወሰነ ጊዜ እረፍት ወስደህ ወጣ በል።

  • ረጅም እረፍት መውሰድ ካልቻልክ አንድ ወይም ሁለት ቀናት የሚያስደስትህን ነገር በማድረግ ማሳለፍ ትችል ይሆናል፤ ለምሳሌ ሽርሽር መሄድ፣ ሙዚየም መጎብኘት ወይም ተራራ መውጣት ትችላለህ።

  • ለአጭር ጊዜም ቢሆን ከተለመደው እንቅስቃሴህ ለየት ያለ ነገር ማድረግህ ሐዘንህን እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለብቻችን ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ትንሽ አረፍ በሉ።”—ማርቆስ 6:31

11. ሌሎችን እርዳ

  • አንዲት ወጣት፣ በዕድሜ የገፋችን ሴት ገበያ ላይ ስታግዛት

    ሌሎችን የሚጠቅም ነገር በማድረግ የምታሳልፈው ጊዜ አንተም ሐዘንህ ቀለል እንዲልልህ ሊረዳህ እንደሚችል አስታውስ።

  • አንተ በሞት ያጣኸውን ሰው በማጣታቸው በሐዘን የተዋጡ ቤተሰቦችህን ወይም ጓደኞችህን ማጽናናት ትችላለህ፤ እነዚህ ሰዎች ሐዘናቸውን የሚጋራቸውና ስሜታቸውን የሚረዳላቸው ሰው ይፈልጋሉ።

  • ሌሎችን መርዳትና ማጽናናት ደስታ የሚያስገኝልህ ከመሆኑም ሌላ ትርጉም ያለው ነገር ማከናወን በመቻልህ እርካታ ታገኛለህ።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35

12. ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች ገምግም

  • ሐዘን፣ በሕይወት ውስጥ ከሁሉ ይበልጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ እንድታስተውል ሊያደርግህ ይችላል።

  • በሕይወትህ ምን እያደረግክበት እንደሆነ ለመገምገም ይህን አጋጣሚ ተጠቀምበት።

  • ቅድሚያ በምትሰጣቸው ነገሮች ላይ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ አድርግ።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ይልቅ ወደ ሐዘን ቤት መሄድ ይሻላል፤ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ሞት ነውና፤ በሕይወት ያለ ሰውም ይህን ልብ ማለት ይገባዋል።”—መክብብ 7:2

ሐዘንን መቋቋም | ዋና ዋና ነጥቦች

  • 1. ቤተሰብህና ወዳጆችህ የሚያደርጉልህን ድጋፍ ተቀበል

    እንደ አስፈላጊነቱ፣ ከሌሎች ጋር የምትሆንበትና ለብቻህ የምታሳልፈው ጊዜ ይኑርህ።

  • 2. ለአመጋገብህ ትኩረት ስጥ፤ እንዲሁም እንቅስቃሴ አድርግ

    ለጤና ተስማሚ የሆነ ምግብ ተመገብ፤ ውኃ በብዛት ጠጣ እንዲሁም መጠነኛ የሰውነት እንቅስቃሴ አድርግ።

  • 3. በቂ እንቅልፍ ለማግኘት ሞክር

    ሐዘን የሚያስከትለውን ከፍተኛ ድካም ለመቋቋም እንቅልፍ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አስታውስ።

  • 4. አመለካከትህን እንደ ሁኔታው አስተካክል

    እያንዳንዱ ሰው ሐዘኑን የሚገልጸው በተለያየ መንገድ ነው፤ ሐዘንህ እንዲወጣልህ የሚረዳህን ነገር ለማወቅ ጥረት አድርግ።

  • 5. ከጎጂ ልማዶች ራቅ

    አልኮል ከመጠን በላይ ከመጠጣት ወይም ዕፆችን ከመውሰድ ተቆጠብ፤ እነዚህ ነገሮች የባሰ ችግር ይፈጥራሉ።

  • 6. ፋታ የምታገኝበት ጊዜ ይኑርህ

    ሁልጊዜ በሐዘን ከመዋጥ ይልቅ ከሌሎች ጋር በመሆን ወይም በመዝናኛ የምታሳልፈው ጊዜ እንዲኖር አድርግ።

  • 7. ቋሚ ፕሮግራም ይኑርህ

    የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችህን የምታከናውንበት ቋሚ ፕሮግራም ማውጣትህ ሕይወትህ እንዲረጋጋ ይረዳሃል።

  • 8. ትላልቅ ውሳኔዎችን በችኮላ ከማድረግ ተቆጠብ

    የሚቻል ከሆነ፣ ከሐዘኑ በኋላ ለአንድ ዓመት ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ ትላልቅ ውሳኔዎችን አታድርግ፤ ይህም በኋላ ላይ ልትቆጭበት የምትችል ውሳኔ ከማድረግ ይጠብቅሃል።

  • 9. ሟቹን የሚያስታውሱህን ነገሮች አድርግ

    ፎቶግራፎችን ወይም ሟቹን የሚያስታውሱህን ነገሮች ሰብስብ፤ አሊያም ከሟቹ ጋር የተያያዙ ነገሮችን የምትመዘግብበት ማስታወሻ ደብተር አዘጋጅ።

  • 10. የሚያዝናናህ ነገር አድርግ

    ለአንድ ቀን ወይም ለተወሰኑ ሰዓታትም እንኳ ቢሆን ከተለመደው እንቅስቃሴ ወጣ ያለ ነገር ለማከናወን ጊዜ መድብ።

  • 11. ሌሎችን እርዳ

    አንተ በሞት ያጣኸውን ሰው በማጣታቸው በሐዘን የተዋጡ ሌሎች ሰዎችን በማጽናናት፣ ትርጉም ያለው ነገር ማከናወን የሚያስገኘውን ደስታ አጣጥም።

  • 12. ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች ገምግም

    ይህን አጋጣሚ፣ በሕይወት ውስጥ ከሁሉ ይበልጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ ቆም ብለህ ለማሰብ ተጠቀምበት። እንዲሁም ቅድሚያ በምትሰጣቸው ነገሮች ረገድ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ አድርግ።

ሐዘንህን ሙሉ ለሙሉ የሚያስወግድ ነገር እንደሌለ አይካድም። ይሁን እንጂ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ብዙ ሰዎች፣ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንደተጠቀሱት ያሉ ጠቃሚ እርምጃዎችን መውሰዳቸው ለመጽናናት እንደረዳቸው ይናገራሉ። እርግጥ ነው፣ ሐዘንን ለመቋቋም የሚረዱ ሐሳቦች በሙሉ እዚህ ላይ ቀርበዋል ማለት አይደለም። ሆኖም ከእነዚህ ጠቃሚ ሐሳቦች መካከል አንዳንዶቹን ተግባራዊ ብታደርግ በተወሰነ መጠን መጽናናት ትችላለህ።

a ንቁ! አንድን የሕክምና ዘዴ ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ