1. መከራ የሚያመጣብን አምላክ ነው?
ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?
ብዙ ሰዎች መከራ የሚያመጣባቸው አምላክ እንደሆነ ስለሚያምኑ ከእሱ ይርቃሉ።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
ብዙ የሃይማኖት መሪዎች መከራ የሚያመጣብን አምላክ እንደሆነ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ። ለምሳሌ እንደሚከተለው ሲሉ ይሰማል፦
የተፈጥሮ አደጋዎች የአምላክ ቁጣ ናቸው።
ልጆች የሚሞቱት አምላክ ተጨማሪ መልአክ ሲያስፈልገው ነው።
አምላክ በጦርነቶች ላይ አንዱን ወገን ይደግፋል (ጦርነቶች ደግሞ የብዙ መከራ መንስኤ ናቸው)።
ይሁንና የሃይማኖት መሪዎች ስለ አምላክ የሚያስተምሩት ነገር የተሳሳተ ይሆን? ደግሞስ አምላክ እነዚህን የሃይማኖት መሪዎች የማይቀበላቸው ቢሆንስ?
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት
jw.org ላይ የሚገኘውን መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መከራ የሚያመጣብን አምላክ አይደለም።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት የአምላክ ባሕርያት መከራ የሚያመጣብን እሱ እንዳልሆነ ያረጋግጣሉ። አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፦
“[አምላክ] መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸውና። . . . ጻድቅና ትክክለኛ ነው።”—ዘዳግም 32:4
“‘እውነተኛው አምላክ ክፉ ነገር ያደርጋል፤ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በደል ይፈጽማል’ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው!”—ኢዮብ 34:10
“ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ፍትሕን አያዛባም።”—ኢዮብ 34:12
አምላክ ስለ እሱ የተሳሳተ ነገር የሚያስተምሩና በእሱ ስም መጥፎ ነገር የሚያደርጉ ሃይማኖቶችን አይቀበልም።
ይህም አምላክ መከራ እንደሚያመጣ የሚያስተምሩ እንዲሁም በጦርነት ወይም በዓመፅ የሚካፈሉ ሃይማኖቶችን ይጨምራል።
“ነቢያቱ በስሜ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ። እኔ አልላክኋቸውም፤ አላዘዝኳቸውም ወይም አላናገርኳቸውም። የሐሰት ራእይን [እና] የገዛ ልባቸውን ማታለያ ይተነብዩላችኋል።”—ኤርምያስ 14:14
ኢየሱስ ሃይማኖታዊ ግብዝነትን አውግዟል።
“‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ብቻ ነው። በዚያ ቀን ብዙዎች እንዲህ ይሉኛል፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም? በስምህ አጋንንትን አላወጣንም? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንም?’ እኔም በዚያ ጊዜ ‘ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ!’ እላቸዋለሁ።”—ማቴዎስ 7:21-23