ምዕራፍ 22
የአምላክን ቃል በድፍረት መናገርህን ቀጥል
1. (ሀ) በ33 እዘአ ከዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን የሚል ምሥራች ማወጅ ጀመሩ? ነገር ግን የአይሁድ መሪዎችና ሽማግሌዎች ምን ስሜት አሳዩ? (ለ) ይህን በተመለከተ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ አለብን?
በ4, 000 ዓመት የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከማንኛውም ነገር የሚበልጡ ሁኔታዎች ተፈጽመው ነበር። የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደፊት መላዋን ምድር የሚገዛ ንጉሥ ሆኖ ተቀብቷል። ኢየሱስ በሃይማኖታዊ ጠላቶቹ አነሳሽነት ቢገደልም ይሖዋ ከሙታን አስነስቶታል። በእርሱ በኩል የዘላለም ሕይወትን የሚያስገኝ የመዳን ዕድል ተከፍቷል። ይሁን እንጂ ታማኝ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህንን ምስራች ለሕዝብ ሲያውጁ ከባድ ተቃውሞ ተነሳባቸው። በመጀመሪያ ሁለት ሐዋርያት በኋላም ሐዋርያቱ በሙሉ ወደ ወኅኒ ገቡ። እዚያም ተገረፉና ሁለተኛ በኢየሱስ ስም እንዳትናገሩ ተብለው ታዘዙ። (ሥራ 4:1–3, 17፤ 5:17, 18, 40) ታዲያ አሁን ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? አንተ ብትሆን ምን ታደርግ ነበር? በድፍረት መመስከርህን ትቀጥል ነበርን?
2. (ሀ) በጊዜአችን ምን ከዚያ ይበልጥ አስደናቂ የሆነ ዜና መሰበክ ያስፈልገዋል? (ለ) ይህንንስ ለመስበክ ኃላፊነት ያለባቸው እነማን ናቸው?
2 እዘአ በ1914 መላውን ጽንፈ ዓለም የሚነካ ከዚያ ይበልጥ አስገራሚ የሆነ ነገር ተፈጸመ። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት በሰማይ ተቋቋመ። ቀጥሎ ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ምድር ተጣሉ። (ራእይ 12:1–5, 7–12) የአሁኑ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች በዚያን ጊዜ ጀምረው ነበር። በ1914 የተፈጸሙትን ነገሮች በዓይኑ የተመለከተው ትውልድ ሞቶ ከማለቁ በፊት አምላክ መላውን ሰይጣናዊ የነገሮች ሥርዓት ይደመስሰዋል። (ማቴዎስ 24:34) ከዚያ ጥፋት ለሚተርፉት ከፊታቸው የዘላለም ሕይወት ዕድል ይዘረጋል። መላዋ ምድር ገነት ትሆንና የመጀመሪያው የአምላክ ዓላማ ይፈጸማል። ይህንን ምሥራች ሰምተህና ተቀብለህ ከሆነ ለሌሎች የማካፈል ኃላፊነት አለብህ። (ማቴዎስ 24:14) ነገር ግን የሰዎቹ አቀባበል እንዴት ይሆናል ብለህ መጠበቅ ይኖርብሃል?
3. (ሀ) ሰዎች ለመንግሥቱ መልዕክት እንዴት ያለ ምላሽ ይሰጣሉ? (ለ) ስለዚህ ከየትኛው ጥያቄ መሸሽ አንችልም?
3 የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ በመሆንህ አንዳንድ ሰዎች በደስታ ሲቀበሉህ አብዛኞቹ ምንም ፍላጎት አያሳዩም። (ማቴዎስ 24:37–39) ሌሎቹ ግን ሊያፌዙብህ ወይም ክፉ ተቃውሞ ሊያመጡብህ ይችላሉ። ከገዛ ዘመዶችህ ተቃውሞ ሊነሳብህ እንደሚችል ኢየሱስ አስጠንቅቋል። (ሉቃስ 21:16–19) ተቃውሞው በመሥሪያ ቤትህ ወይም በትምህርት ቤትህ ሊነሳ ይችላል። በአያሌ የምድር ክፍሎች የይሖዋ ምስክሮች ፍትሕ የጎደለው መንግሥታዊ ዕገዳ ተደርጎባቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ወይም ሁሉም ዓይነት ተቃውሞዎች ቢደርሱብህ የአምላክን ቃል በድፍረት መናገርህን ትቀጥላለህን?
4. የግል ቆራጥነት ብቻ አምላክን በታማኝነት ማገልገላችንን እንድንቀጥል ዋስትና ይሆናልን?
4 ደፋር የአምላክ አገልጋይ መሆን እንደምትፈልግ አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ ምንም ነገር ሊመልሰኝ አይችልም ብለው ያስቡ የነበሩ አንዳንድ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች አገልግሎታቸውን አቁመዋል። በአንጻሩ ግን ሌሎች አስፋፊዎች፣ የተፈጥሮ ፍርሃት ያለባቸውም ጭምር፣ ሳያቋርጡ ቀናተኛ የአምላክ አልጋይ ሆነው ቀጥለዋል። እንግዲያው ‘በእምነት ጸንተው ከሚቆሙት’ አንዱ ለመሆን የምትችለው እንዴት ነው? — 1 ቆሮንቶስ 16:13 አዓት
በራሳችን ኃይል አንመካ
5. (ሀ) ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች መሆናችንን ለማሳየት የምንችልበት አንዱ መሠረታዊ ነገር ምንድን ነው? (ለ) ስብሰባዎች በጣም አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?
5 ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ለመሆን የሚያስፈልጉ ብዙ ነገሮች አሉ። ሆኖም ከሁሉ በላይ መሠረታዊ የሆነው ነገር በይሖዋና በዝግጅቱ ላይ መታመን ነው። ይህንን የምናሳየው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ በጉባኤ ስብሰባ በመገኘት ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች ስብሰባን እንዳንተው አጥብቀው ይመክሩናል። (ዕብራውያን 10:23–25) ሕዝቡ ለመልዕክቱ ፍላጎት በማያሳይበት ቦታ የሚኖሩትም ይሁኑ ስደት የሚደርስባቸው ወንድሞች፣ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው የቀጠሉት ከአምልኮ መሰሎቻቸው ጋር ዘወትር ይሰበሰቡ የነበሩት ናቸው። በእነዚህ ስብሰባዎች ስንገኝ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታችን ይጨምራል፤ ሆኖም ወደ ስብሰባ እንድንሄድ የሚገፋፋን ለአዳዲስ ነገሮች ያለን ጉጉት ብቻ አይደለም። (ከሥራ 17:21 ጋር አወዳድር) በደንብ ለታወቁት እውነቶች የነበረን አድናቆት ይጨምራል፤ በምን መንገድ ልንሠራባቸው እንደምንችልም የበለጠ እያወቅን እንሄዳለን። ኢየሱስ የተወልን ምሳሌ በአእምሮአችንና በልባችን ውስጥ የበለጠ ጠልቆ ይቀረጻል። (ኤፌሶን 4:20–24) ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር በአምልኮ አንድነት በይበልጥ እንተሳሰራለን፤ እኛም ራሳችን የአምላክን ፈቃድ ማድረጋችንን እንድንቀጥል ኃይል እናገኛለን። የይሖዋ መንፈስ በጉባኤው በኩል መመሪያ ይሰጠናል። በስሙ ስንሰበሰብ ኢየሱስ በዚያ መንፈስ አማካኝነት በመሃከላችን ይሆናል። — ራእይ 3:6፤ ማቴዎስ 18:20
6. የይሖዋ ምስክሮች በሚታገዱባቸው አገሮች በስብሰባዎች በኩል ምን ይደረጋል?
6 በሁሉም ስብሰባዎች ዘወትር ትገኛለህን? በዚያ የምትማረውንስ በግልህ ትሠራበታለህን? ዕገዳ ባለባቸው ስፍራዎች ጥቂት ጥቂት ሆኖ በመኖሪያ ቤቶች መሰብሰብ አስፈላጊ ሆኗል። ቦታውና ቀኑ በየጊዜው ሊለዋወጥ ይችላል፤ ለእኛም ሁልጊዜ ምቹ ላይሆንልን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ስብሰባው ሌሊት ይደረግ ይሆናል። ሁኔታው የማያመች ወይም አደገኛ ቢሆንም ታማኝ ወንድሞችና እህቶች በእያንዳንዱ ስብሰባ ለመገኘት ከልብ ይጥራሉ።
7. (ሀ) በይሖዋ ላይ እንደምንተማመን የምናሳይበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው? (ለ) ይህስ በድፍረት መናገራችንን ለመቀጠል እንዴት ሊረዳን ይችላል?
7 ዘወትር ወደ ይሖዋ በጸሎት በመቅረብም በእርሱ ላይ ተማምነን እንደምንኖር ልናሳይ እንችላለን። ይሁን እንጂ ጸሎት ማድረግ ያለብን እንዲሁ እንደ ልማድ አድርገን ሳይሆን የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገን ከልብ ተሰምቶን መሆን ይኖርበታል። እንደዚህ ታደርጋለህን? ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ደጋግሞ ይጸልይ ነበር። (ሉቃስ 3:21፤ 6:12, 13፤ 9:18, 28፤ 11:1፤ 22:39–44) ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት ላይም ደቀ መዛሙርቱን “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ዘወትር ንቁ፣ ጸልዩም” ብሎ አጥብቆ መክሯቸዋል። (ማርቆስ 14:38 አዓት) የምንሰብክላቸው አብዛኞቹ ሰዎች ለመንግሥቱ መልዕክት ፍላጎት የሌላቸው ከሆኑ አገልግሎታችንን እንድንቀንስ ልንፈተን እንችላለን። ሰዎች ቢዘብቱብን ወይም ከባድ ስደት ቢያመጡብን ከዚህ ለመዳን ዝም እንድንል ልንፈተን እንችላለን። ነገር ግን በድፍረት መናገራችንን እንድንቀጥል የአምላክ መንፈስ እንዲረዳን አጥብቀን ብንጸልይ በዚያ ፈተና እንዳንሸነፍ ይረዳናል። — ሉቃስ 11:13፤ ኤፌሶን 6:18–20
ድፍረት ያለበት ምሥክርነት የተሰጠበት የታሪክ መዝገብ
8. (ሀ) በሐዋርያት ሥራ የተመዘገበው ታሪክ ሁላችንም በልዩ ትኩረት ልናነበው የሚገባን ለምንድን ነው? (ለ) ሐሳቡ እንዴት ሊጠቅመን እንደሚችል እያጎላህ ከአንቀጹ ቀጥሎ ያሉትን ጥያቄዎች መልስ።
8 በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው ታሪክ ሁላችንም ልዩ ትኩረት ሰጥተን ልናነበው ይገባናል። የእኛው ዓይነት ስሜት የነበራቸው ሰዎች፤ ይኸውም ሐዋርያትና ሌሎች የጥንት ክርስቲያኖች ልዩ ልዩ መሰናክሎች የማይበግሯቸው ደፋርና ታማኝ የይሖዋ ምስክሮች እንደሆኑ ይነግረናል። እስቲ ከዚህ ቀጥሎ ባሉት ጥያቄዎችና ጥቅሶች አማካኝነት ከፊሉን ታሪክ እንመርምረው። የምታነበው እንዴት ሊጠቅምህ እንደሚችል አስብበት።
ሐዋርያት ከፍተኛ ትምህርት ያላቸው ሰዎች ነበሩን? በተፈጥሮአቸው የመጣ ቢመጣ የማይፈሩ ሰዎች ነበሩን? (ሥራ 4:13፤ ዮሐንስ 18:17, 25–27፤ 20:19)
ጴጥሮስ ከጥቂት ሣምንታት በፊት በአምላክ ልጅ ላይ ፈርዶ በነበረው ሸንጎ ፊት በድፍረት ለመናገር ያስቻለው ምንድን ነው? (ሥራ 4:8፤ ማቴዎስ 10:19, 20)
ሐዋርያት ሳንሔድሪን ወደተባለው የፍርድ ሸንጎ ከመቅረባቸው በፊት በነበሩት ሣምንታት ምን ሲያደርጉ ነበር? (ሥራ 1:14፤ 2:1, 42)
የሕዝቡ መሪዎች በኢየሱስ ስም መናገራቸውን እንዲያቆሙ ሲያዟቸው ጴጥሮስና ዮሐንስ ምን ብለው መለሱ? (ሥራ 4:19, 20)
ከእሥራቱ ከተፈቱ በኋላ ለእርዳታ እንደገና ወደ ማን ዘወር አሉ? የለመኑትስ ስደቱ እንዲቆምላቸው ነው ወይስ ምን? (ሥራ 4:24– 31)
ተቃዋሚዎች የስብከቱን ሥራ ለማቆም በቃጡ ጊዜ ይሖዋ እርዳታ የሰጠው በምን አማካኝነት ነው? (ሥራ 5:17–20, 33–40)
ሐዋርያት ከእሥር ቤት የተለቀቁበት ምክንያት እንደገባቸው ያሳዩት እንዴት ነው? (ሥራ 5:21, 41, 42)
ስደቱ ከመፋፋሙ የተነሳ ብዙዎቹ ደቀ መዛሙርት ወደየቦታው ቢበታተኑም ምን ማድረጋቸውን ቀጥለዋል? (ሥራ 8:3, 4፤ 11:19–21)
9. (ሀ) የእነዚያ የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት አገልግሎት እንዴት ያሉ አስደሳች ውጤቶች አስገኘ? (ለ) ነገሩ እኛን የነካው እንዴት ነው?
9 ምሥራቹን ለማስፋፋት ያደረጉት ድካም ከንቱ አልሆነም። በ33 እዘአ በጴንጠቆስጤ ዕለት 3, 000 የሚያክሉ ደቀ መዛሙርት ተጠምቀዋል። “የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ።” (ሥራ 2:41፤ 4:4፤ 5:14) ምሥራቹን በተቃጠለ ስሜት ይቃወም የነበረው የጠርሴሱ ሳውል ከጊዜ በኋላ ክርስቲያን ሆኖ ለእውነት በድፍረት መመሥከር እንደጀመረ ተገልጿል። እርሱም በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ በመባል ታወቀ። (ገላትያ 1:22–24) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተጀመረው ሥራ ዛሬም አላቆመም። በእነዚህ “መጨረሻ ቀኖች” ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ወደ ሁሉም የምድር ክፍሎች ተስፋፍቷል። በዚህ ሥራ የመሳተፍ መብት አለን። እንደዚህም ስናደርግ ከእኛ በፊት ይሖዋን ያገለገሉት ታማኝ ምሥክሮች ምሳሌ ትምህርት ሊሆነን ይችላል።
10. (ሀ) ጳውሎስ ለመመስከር እንዴት ባሉ አጋጣሚዎች ተጠቅሟል? (ለ) አንተስ የመንግሥቱን መልዕክት ለሌሎች የምታዳርሰው በምን መንገዶች ነው?
10 ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረውን እውነት በሰማ ጊዜ እርምጃ ለመውሰድ ዛሬ ነገ እያለ አላመነታም። “ወዲያውም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በምኩራቦች ሰበከ።” (ሥራ 9:20) ጳውሎስ አምላክ ያሳየውን የማይገባ ደግነት አድንቋል፤ እርሱ ያገኘው ምሥራች ለእያንዳንዱ ሰው እንደሚያስፈልግም ተገነዘበ። አይሁዳዊ ስለነበረ በዘመኑ ልማድ መሠረት ምኩራብ ተብለው ወደሚጠሩት የአይሁድ መሰብሰቢያዎች ሄዶ መሰከረ። ከቤት ወደ ቤት እየሄደ ሰበከ፣ በገበያም ከሰዎች ጋር በመነጋገር ምክንያቶችን እያቀረበ ያስረዳቸው ነበር። ምሥራቹን ለማስፋፋት ወደ አዳዲስ የግዛት ክልሎች ለመሄድም ፈቃደኛ ነበር። — ሥራ 17:17፤ 20:20፤ ሮሜ 15:23, 24
11. (ሀ) ጳውሎስ በሚመሠክርበት ጊዜ ደፋር ቢሆንም አስተዋይነትን ያሳያው እንዴት ነው? (ለ) ለዘመዶች፣ ለሥራ ባልደረቦችና አብረውን ለሚማሩት ልጆች ስንመሰክር ይህንን ጠባይ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
11 ጳውሎስ ደፋር ነበር፤ ነገር ግን አስተዋይም ነበር። እኛም እንደ እርሱ መሆን አለብን። አይሁዶችን ሲያገኝ አምላክ ለአባቶቻቸው በሰጠው ተስፋ መሠረት ያነጋግራቸው ነበር። ከግሪኮች ጋር ሲገናኝ ደግሞ እነርሱ በሚያውቁት መሠረት ያነጋግራቸው ነበር። አንዳንድ ጊዜም ራሱ ወደ እውነት የመጣበትን ሁኔታ ምሥክርነት ለመስጠት እንደ መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምበት ነበር። ራሱ “ምሥራቹን ማካፈል እንድችል ስለ ምሥራቹ ሁሉን አደርጋለሁ” ብሏል። — 1 ቆሮንቶስ 9:20–23 አዓት፤ ሥራ 22:3–21
12. (ሀ) ጳውሎስ ደፋር ቢሆንም ተቃዋሚዎችን ሁልጊዜ ላለመጋፈጥ ምን ያደርግ ነበር? (ለ) ይህንን ምሳሌ ብንከተል ጥሩ የሚሆነው መቼ ነው? እንዴትስ? (ሐ) በድፍረት መናገራችንን ለመቀጠል የሚያስችለን ኃይል ከየት ይመጣል?
12 በምሥራቹ ላይ ስደት በመነሳቱ በሌላ ስፍራ መስበክ ወይም ለትንሽ ጊዜ ወደ ሌላ አካባቢ መሄድ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ጳውሎስ የእውነት ተቃዋሚዎችን ሁልጊዜ ከመጋፈጥ ይልቅ እንደዚያ ያደርግ ነበር። (ሥራ 14:5–7፤ 18:5–7፤ ሮሜ 12:18) ይሁን እንጂ በምሥራቹ ፈጽሞ አፍሮ አያውቅም። (ሮሜ 1:16) ጳውሎስ ምንም እንኳን የተቃዋሚዎቹ ድንዳኔ ወይም ድብደባ ደስ የማይል ቢሆንበትም ስብከቱን እንዲቀጥል ‘ከአምላካችን ድፍረት አግኝቷል።’ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢደርሱበትም “የስብከቱ ሥራ በእኔ እንዲፈጸም አሕዛብም ሁሉ እንዲሰሙት ጌታ በእኔ አጠገብ ቆሞ አበረታኝ” ብሏል። (1 ተሰሎንቄ 2:2፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:17) የክርስቲያን ጉባኤ ራስ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ትንቢት የተናገረለትን ሥራ ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል መስጠቱን ቀጥሏል። — ማርቆስ 13:10
13. ክርስቲያናዊ ድፍረት እንዳለን የምናሳየው እንዴት ነው? ድፍረታችንስ በምን ላይ የተመሠረተ ነው?
13 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች እንዳደረጉት ሁሉ እኛም የአምላክን ቃል በድፍረት መናገራችንን ለመቀጠል ብዙ ምክንያቶች አሉን። እንደዚህም ሲባል ኃይለ ቃል መናገር ወይም ሰዎቹን መናቅ አለብን ማለት አይደለም። ለሰዎቹ ስሜት ግድ የለሽ የምንሆንበት ወይም መልዕክቱን ካልፈለጉ የግድ ካልተቀበላችሁ ብለን የምናስጨንቅበት ምክንያት የለም። ሆኖም ሰዎች ፍላጎት የላቸውም ብለን አገልግሎታችንን አናቆምም፤ ተቃውሞ ሲመጣም ፈርተን ዝም አንልም። ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም መላዋን ምድር ለመግዛት ትክክለኛ መብት ያለው የአምላክ መንግሥት መሆኑን እናሳውቃለን። የጽንፈ ዓለሙን የበላይ ገዥ ይሖዋን ስለምንወክልና የምናውጀው መልዕክት ከእርሱ እንጂ ከራሳችን የመነጨ ስላልሆነ በድፍረት እንናገራለን። — ፊልጵስዩስ 1:27, 28፤ 1 ተሰሎንቄ 2:13
የክለሣ ውይይት
● የመንግሥቱን መልዕክት በተቻለን መጠን ከእያንዳንዱ ሰው ጋር ልንካፈለው የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ይሁን እንጂ የሰዎቹ ስሜት እንዴት ይሆናል ብለን መጠበቅ አለብን?
● ይሖዋን ስናገለግል በራሳችን ኃይል እንደማንመካ የምናሳየው እንዴት ነው?
● ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ምን ምን ጠቃሚ ትምህርቶች እናገኛለን?