በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ተገኝቶ መደሰትና አምላክን ማወደስ
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በየአካባቢው ከሚያደርጉት ስብሰባዎች በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎች ከሚኖሩ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር ቢተዋወቁ ጠቃሚ እንደሚሆን ገና ከ1880ዎቹ ዓመታት መግቢያ ጀምሮ ተገንዝበው ነበር። በዚህም ምክንያት በዩናይትድ ስቴትስ በሙሉና በኋላም በካናዳ ዓመታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስብሰባ ማዘጋጀት ጀመሩ። እነዚህ ስብሰባዎች መንፈሳዊ ማነቃቂያና ኃይል የሚገኝባቸው ወቅቶች ነበሩ። ለበርካታ ቀናት ጥልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይሰጥ ነበር። ሁሉም እርስ በርሳቸው ይጽናኑና ይበረታቱ ነበር። በተጨማሪም በእነዚህ ዓመታዊ ስብሰባዎች ላይ አዳዲስ አማኞች ይጠመቃሉ። ትልልቆቹ ስብሰባዎች ሠፊ ምሥክርነት ለሕዝብ የሚሰጥባቸውን አጋጣሚዎች ከፍተዋል። — ሮሜ 1:11, 12
በአሁኑ ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች አዘውትረው ትልልቅ ስብሰባዎች ያደርጋሉ። አብዛኛውን ጊዜ ከ18 እስከ 25 የሚደርሱ በአንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች የሚጎበኙ ጉባኤዎች ክልል ተብሎ በሚጠራ አንድ ምድብ ውስጥ ይጠቃለላሉ። በክልሉ ውስጥ ያሉት ጉባኤዎች በሙሉ ወይም በከፊል አንድ ጊዜ ቅዳሜና እሁድ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ቅዳሜ ወይም እሑድ አንድ ላይ የሚሰበሰቡበት ትልቅ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜ ይዘጋጃል።
በዓመት አንድ ጊዜ በየአገሩ የወረዳ ስብሰባ ተብሎ የሚጠራ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በአንድ ቦታ የሚሰበሰቡበት የሦስት ወይም የአራት ቀን ስብሰባ ይዘጋጃል። እነዚህ ትልልቅ ስብሰባዎች ለይሖዋ ምሥክሮችና ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ለማወቅ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች መንፈሳዊ መታነጽ የሚያስገኙ ከመሆናቸውም በላይ ለሕዝብም ምሥክርነት የሚሰጥበትን ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራሉ።
የእነዚህ የክልልና የወረዳ ስብሰባዎች ፕሮግራም የሚዘጋጀው በይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል ሲሆን በዓለም ዙሪያ ያሉ ምሥክሮች በሚያስፈልጋቸው ነገር ላይ የተመሠረተ ትምህርት ይዘጋጃል። ፕሮግራሞቹም ንግግሮችን፣ ውይይቶችንና በሕይወት ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሁኔታዎችን የሚያሳዩ ትዕይንቶችን ያጠቃልላሉ። የሚቀርቡትም በተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና በጉባኤዎች ውስጥ በሚገኙ ብቃት ያላቸው ምሥክሮች ነው። የተለያዩ ምሥክሮች በአምላክ የለሹ ዓለም ውስጥ ክርስቲያናዊ አቋም ጠብቆ በመኖር ረገድ የሚያጋጥማቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዴት እንደሚቋቋሙት ወይም በአገልግሎታቸው ምን ውጤት እያገኙ እንዳሉ የሚገልጹ ተሞክሮዎችን ይናገራሉ። በወረዳ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርብ ሌላ ተጨማሪ ፕሮግራም አለ። ክርስቲያኖች በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዴት እንደሚቋቋሙ የሚያሳዩ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ወይም በዘመናዊ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረቱ ድራማዎች ይቀርባሉ።
በተጨማሪም ቀላል ምግቦችና መጠጦች ይቀርባሉ። ይህም ተሰብሳቢዎቹ በእረፍት ጊዜያት በአንድነት እንዲዝናኑና እንዲጫወቱ አስችሏል። ይህን ሁሉ ዝግጅት ለማደራጀት የሚያስፈልገው ሥራ የሚከናወነው ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል በተውጣጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች ነው። ለስብሰባው የሚያስፈልጉት ወጪዎች በሙሉ የሚሸፈኑት በበጐ ፈቃድ በሚሰጥ እርዳታ ነው። ወደ ስብሰባው ለመግባት ክፍያ አይጠየቅም። ተሰብሳቢዎቹ ገንዘብ እንዲሰጡ አይጠየቁም።
እነዚህ ስብሰባዎች በአካባቢህ መቼና የት እንደሚደረጉ ባካባቢህ ካለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ልትጠይቅ ትችላለህ። ወደ ሩቅ ቦታ መሄድ የሚያስፈልግህ ከሆነ መጓጓዣና የማረፊያ ቦታ እንዴት ልታገኝ እንደምትችል የሚገልጽ መረጃ ልታገኝ ትችላለህ።
እነዚህ የክልልና የወረዳ ስብሰባዎች የይሖዋ ምሥክሮችና ከእነሱም ጋር የሚተባበሩ ሰዎች ሁሉ በአካባቢያቸው ከሚገኘው ጉባኤ አልፈው ዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበር እንዲያውቁና እንዲወዱ ይረዱአቸዋል። — 1 ጴጥሮስ 2:17
● የቀድሞዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ካደረጉአቸው ታላላቅ ስብሰባዎች ምን ጥቅም አግኝተዋል?
● በክልልና በወረዳ ስብሰባዎች ላይ ምን ዓይነት ዝግጅትና ፕሮግራም እንደሚደረግ ግለጽ።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በወረዳ ስብሰባ ላይ የቀረበ የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ብሔራት አቀፍ ስብሰባ፣ ፖላንድ
ብሔራት አቀፍ ስብሰባ፣ አርጀንቲና
የክልል ስብሰባ፣ ጃፓን
የስብሰባው ተካፋዮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ሲወስዱ፣ ስዊዘርላንድ
በብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ የተከናወነ ጥምቀት፣ ደቡብ አፍሪካ
አዲስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ መውጣቱ ሲነገር፣ ካናዳ
ለትልቅ ስብሰባ የመጡ በአንድነት ሲዘምሩ፣ ስፔይን