የይሖዋ ምሥክሮች ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባዎች ያደርጋሉ
የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል በ1998 ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎችን ለማድረግ አቅዷል። የፔንሲልቫኒያው የመጠበቂያ ግንብ፣ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ቅዳሜ ጥቅምት 5, 1996 በጀርሲ ሲቲ የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ ባደረገው ዓመታዊ ስብሰባ ይህን ማስታወቂያ በከፍተኛ ደስታ ተቀብሎታል።
በ1998 አጋማሽ ላይ በየዓመቱ ከሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ በተጨማሪ በሰሜን አሜሪካ በዛ ያሉ ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ይደረጋሉ። ይህ ስብሰባ ከተለያዩ የምድር ክፍሎች የመጡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ላይ የሚሰባሰቡበት እንደሚሆን ይጠበቃል። በተቻለ መጠን ከብዙ አገር የተውጣጡ ተወካዮች እንዲገኙ ለማድረግ ከ100 በላይ የሚሆኑት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮዎች እያንዳንዳቸው በሰሜን አሜሪካ ከተሞች በሚደረጉት ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ የተወሰኑ ልዑካን እንዲልኩ ይደረጋል።
ወደ ሰሜን አሜሪካ መጓዝ ከሚፈልጉ መካከል እንዲህ ማድረግ የማይችሉ እንደሚኖሩ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ብዙዎች ለሚኖሩበት አገር ቅርብ በሆኑ አገሮች በሚደረጉት ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይችላሉ። አውሮፓ በሚገኙ ሁለት ወይም ሦስት አገሮች ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ለማድረግ ዝግጅት በመደረግ ላይ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በደቡብ ፓስፊክና በካሪቢያን አገሮች ይደረጋሉ።
ጊዜው ሲቃረብ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በክልላቸው ለሚገኙት ጉባኤዎች ስብሰባዎቹ የሚደረጉባቸውን ከተሞች ወይም የተጋበዙበትን ከተማ ያሳውቋቸዋል። ስብሰባዎቹ የሚደረጉበትን ቀናትና ዝግጅቶቹን አስመልክቶ ወደ ስብሰባው ለሚሄዱት ልዑካን ማብራሪያ ይላካል። ልዑክ ሆነው በስብሰባዎቹ ላይ ለመገኘት ማመልከቻ ለማስገባት የሚፈልጉ ሁሉ በእነዚህ ልዩ ወቅቶች ላይ ለመገኘት ከአሁኑ ገንዘብ ማጠራቀም ይፈልጉ ይሆናል።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ በ1998 በሚደረገው በእነዚህ ዓለም አቀፍ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የሚከናወኑትን ነገሮች በጉጉት ይጠባበቃሉ። በሁሉም አገሮች በሚደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ተመሳሳይ የሆነ ፕሮግራም ይቀርባል።