የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • pe ምዕ. 5 ገጽ 47-56
  • መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ከአምላክ የመጣ ነውን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ከአምላክ የመጣ ነውን?
  • በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ሌላ መጽሐፍ የለም
  • መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ተጻፈ?
  • መጽሐፍ ቅዱስን ሁሉም ሰው በቀላሉ እንዲያገኘው ማድረግ
  • መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጦአልን?
  • መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ እውነተኛ ነውን?
  • መጽሐፍ ቅዱስ ምንድን ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • አምላክን የሚያስደስቱ እውነተኛ ትምህርቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የበዙት ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017
  • መጽሐፍ ቅዱስ—ከአምላክ ያገኘነው ስጦታ
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
ለተጨማሪ መረጃ
በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
pe ምዕ. 5 ገጽ 47-56

ምዕራፍ 5

መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ከአምላክ የመጣ ነውን?

1. አምላክ ስለ ራሱ አንዳንድ መግለጫዎችን ይሰጠናል ብሎ ማመኑ ለምን ምክንያታዊ ነው?

ይሖዋ አምላክ ስለ ራሱ የሚያስረዱ መግለጫዎች ሰጥቶናልን? ከአሁን በፊት ምን እንዳደረገና ወደፊት ምን ለማድረግ ዓላማ እንዳለው ነግሮናልን? ልጆቹን የሚያፈቅር አባት ብዙ ነገሮች ይነግራቸዋል። እስከ አሁን በተመለከትናቸው ነገሮች መሠረት ደግሞ ይሖዋ በእርግጥ አፍቃሪ አባት ነው።

2. (ሀ) ይሖዋ ስለ ራሱ ለእኛ ለመንገር ሊጠቀምበት የሚችል አንዱ ጥሩ መንገድ ምንድን ነው? (ለ) ይህስ ምን ጥያቄዎችን ያስነሳል?

2 ይሖዋ በብዙ የምድር ክፍሎች ለሚገኙትና በተለያዩ ዘመናት ለኖሩት ሰዎች ትምህርታዊ መግለጫዎችን እንዴት ለመስጠት ይችላል? አንዱ ጥሩ መንገድ መጽሐፍ እንዲጻፍላቸውና ለሁሉም እንዲዳረስ ማድረግ ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተገኘ እንደዚህ ያለ መጽሐፍ ነውን? እንደዚያ መሆኑን እንዴት ለማወቅ እንችላለን?

እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ሌላ መጽሐፍ የለም

3. መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ መጽሐፍ የሆነበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

3 መጽሐፍ ቅዱስ የመጣው በእርግጥ ከአምላክ ከሆነ እስከ ዛሬ ድረስ ከተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ መብለጥ አለበት ብለን ብንጠብቅ ትክክል ነው። ታዲያ እንደዚያ ነውን? አዎን ነው! እንደዚህም ለማለት የሚያበቁ ብዙ ምክንያቶች አሉ። አንደኛ በጣም የቆየ መጽሐፍ ነው። ለሁሉም የሰው ልጆች የታሰበ የአምላክ ቃል ከአጭር ጊዜ በፊት ተጽፎ ይሆናል ብለህ አትጠብቅም። ትጠብቃለህ እንዴ? ጽሑፉ የተጀመረው ከ3, 500 ዓመታት በፊት በዕብራይስጥ ቋንቋ ነው። በኋላም ከ2, 200 ዓመታት በፊት ወደ ሌሎች ቋንቋዎች መተርጐም ተጀመረ። ዛሬ ከጥቂቶች በስተቀር በምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በገዛ ቋንቋው ለማንበብ ይችላል።

4. በብዛት በመታተም በኩል መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት ጋር እንዴት ይወዳደራል?

4 በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በምን ያህል ቅጂዎች እንደታተመ ሲታይ ወደዚህ ቁጥር አንድም መጽሐፍ አይጠጋም። አንድ መጽሐፍ በሺህ በሚቆጠሩ ቅጂዎች ስለታተመ ብቻ በጣም ጥሩ ተሸጠ ተብሎ ይነገርለት ይሆናል። ይሁን እንጂ በእያንዳንዱ ዓመት በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶች ይታተማሉ። ባለፉት መቶ ዓመታት ደግሞ ብዙ ሺህ ሚልዮን ቅጂዎች ታትመዋል። የቱንም ያህል ሩቅ ይሁን በምድር ላይ መጽሐፍ ቅዱስን የማታገኝበት አንድም ሥፍራ አይኖርም። በእርግጥ ከአምላክ የመጣ መጽሐፍ እንደዚህ መሆን ይኖርበታል ብለህ አትጠብቅምን?

5. መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት ምን ጥረቶች ተደርገዋል?

5 ይህንን ታላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ስርጭት ከዚያ ይበልጥ አስደናቂ የሚያደርገው ጠላቶች ሊያጠፉት ያደረጉት ሙከራ ነው። ይሁን እንጂ የዲያብሎስ ወኪሎች ከአምላክ በመጣ መጽሐፍ ላይ ጥቃት ማድረሳቸው ልንጠብቀው የሚገባው አይደለምን? ይህ ነገር ደርሶአል። መጽሐፍ ቅዱሶችን ማቃጠል በአንድ ዘመን ላይ የተለመደ ነገር ሆኖ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነቡ የተያዙትም በሞት ይቀጡ ነበር።

6. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ለየትኞቹ ትልልቅ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ያንን ሐሳብ ከየት እንዳገኙት ይናገራሉ?

6 ከአምላክ የመጣ መጽሐፍ ሁላችንም ለማወቅ ስለምንፈልጋቸው ትልልቅ ጉዳዮች ማብራሪያ ይሰጣል ብለህ ትጠብቅበታለህ። ‘ሕይወት ከየት መጣ?’ ‘ወደዚህ ዓለም የመጣነው ለምን ይሆን?’ ‘የወደፊቱ ጊዜ ምን ያመጣ ይሆን?’ እነዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚመልሳቸው ጥያቄዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። መጽሐፉ በውስጡ ያለው ሀሳብ ከይሖዋ አምላክ የመጣ መሆኑን በግልጥ ይናገራል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “የይሖዋ መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነበረ” ብሎአል። (2 ሳሙኤል 23:2) ሌላው ደግሞ “ቅዱስ ጽሑፍ ሁሉ ሰዎች በአምላክ መንፈስ እየተነዱ ጻፉት” ሲል ጽፎአል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16 አዓት) መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የአምላክ ቃል ነኝ እያለ በጣም ግልጽ አድርጐ ስለሚናገር በእርግጥ እንደዚያ መሆኑን ለማረጋገጥ ብንመረምረው ጥበብ አይደለምን?

መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ተጻፈ?

7. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስን ማን ጻፈው? (ለ) ታዲያ እንዴት የአምላክ ቃል ነው ሊባል ይችላል?

7 ‘ግን መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በሰዎች ከሆነ እንዴት ከአምላክ መጣ ለማለት እንችላለን?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። እውነት ነው፣ አርባ የሚያህሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለመጻፍ በየግላቸው አስተዋጽዖ አድርገዋል። አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት በጽላት ላይ ከጻፋቸው አሥር ትእዛዛት በስተቀር መጽሐፍ ቅዱስን በቀጥታ የጻፉት እነዚህ ሰዎች ናቸው። (ዘፀአት 31:18) ሆኖም ይህ ምክንያት እነርሱ የጻፉትን የአምላክ ቃል ከመሆን ዝቅ አያደርገውም። መጽሐፍ ቅዱስ “በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ” ሲል ይገልጽልናል። (2 ጴጥሮስ 1:21) አዎን፣ አምላክ ኃይለኛውን ቅዱስ መንፈሱን ሰማያትን፣ ምድርንና ሁሉንም ሕያዋን ነገሮች ለመፍጠር እንደተጠቀመበት ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስንም ለማስጻፍ ሰዎችን እንዲመራ ተጠቅሞበታል።

8, 9. አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት አድርጐ እንዳስጻፈ ዛሬ ያሉ የትኞቹ ምሳሌዎች እንዲገባን ሊረዱን ይችላሉ?

8 ይህም መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ጸሐፊ ብቻ አለው ማለት ነው፤ እርሱም ይሖዋ አምላክ ነው። አንድ የመሥሪያ ቤት አለቃ ጸሐፊው ደብዳቤ እንድትጽፍለት እንደሚጠቀምባት ሁሉ አምላክም ሃሳቡን በጽሑፍ ለማስፈር በሰዎች ተጠቅሟል። ጸሐፊዋ ደብዳቤውን ብትጽፍም ደብዳቤው የያዛቸው ሃሳቦች የአለቃዋ ናቸው። ስለዚህ የእርሱ እንጂ የጸሐፊዋ ደብዳቤ አይደለም። እንደዚሁም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ እንዲጽፉት የተጠቀመባቸው ሰዎች ሳይሆን የራሱ መጽሐፍ ነው።

9 አእምሮን የፈጠረው አምላክ እንደመሆኑ መጠን አገልጋዮቹ እንዲጽፉት የፈለገውን ሐሳብ በአእምሮአቸው ውስጥ መክተቱን አዳጋች ሆኖ እንዳላገኘው የተረጋገጠ ነው። ዛሬ አንድ ሰው እቤቱ ቁጭ ብሎ በሬድዮ ወይም በቴሌቪዥን አማካይነት ከሩቅ የሚተላለፉትን መልእክቶች ለመቀበል ይችላል። ድምጾቹና ሥዕሎቹ አምላክ በፈጠራቸው ሕጐች አማካይነት ረጅም ርቀት ይጓዛሉ። ስለዚህ ይሖዋ ሰብዓዊው ቤተሰብ እንዲያውቀው የፈለገውን ነገር ሩቅ ካሉት ሰማያት ሆኖ ሰዎችን እየመራ በጽሑፍ ማስፈር እንደሚችል በቀላሉ ሊገባን ይችላል።

10. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ስንት መጻሕፍትን አጠቃልሎ ይዟል? በምን ያህልስ የጊዜ ርዝመት ላይ ተጽፈው አለቁ? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ የትኛውን ዋና መልእክት ያስተላልፋል?

10 በውጤቱም አንድ አስደናቂ መጽሐፍ ተገኘ። መጽሐፍ ቅዱስ 66 ትንንሽ መጻሕፍትን አጠቃልሎ የያዘ መጽሐፍ ነው። “ባይብል” የሚለውን እንግሊዝኛ ቃል የወለደው ቢብልያ የተባለው ግሪክኛ ቃል “ትንንሽ መጻሕፍት” ማለት ነው። እነዚህ መጻሕፍት ወይም ደብዳቤዎች ከ1513 ከዘአበ ጀምሮ እስከ 98 እዘአ ድረስ 1, 600 ዓመታት በፈጀ ዘመን ውስጥ ተጽፈው አበቁ። ይሁን እንጂ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አንድ ጸሐፊ ብቻ ስላላቸው እርስ በርሳቸው ይስማማሉ። ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ዋነኛው መልእክት አንድ ነው፤ እርሱም ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት የጽድቅ ሁኔታዎችን መልሶ እንደሚያመጣ የሚገልጽ ዋና መልዕክት ነው። ኦሪት ዘፍጥረት የሚባለው የመጀመሪያው መጽሐፍ መኖሪያ የነበረች ገነት በአምላክ ላይ በተነሳሳ ዓመፅ ምክንያት እንዴት እንደታጣች ይነግረናል። የመጨረሻው መጽሐፍ ራዕይም በአምላክ አገዛዝ ምድር እንደገና ገነት እንደምትሆን ይገልጻል። —ዘፍጥረት 3:19, 23፤ ራዕይ 12:10፤ 21:3, 4

11. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ በየትኞቹ ቋንቋዎች ተጻፈ? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ በየትኞቹ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል? ይሁን እንጂ አንድነታቸውን የሚያሳየው ምንድን ነው?

11 የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያዎቹ 39 መጻሕፍት በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲጻፉ በጣም ጥቂት ክፍሎች በአረማይክ ተጽፈዋል። የመጨረሻዎቹ 27 መጻሕፍት ደግሞ ኢየሱስና ክርስቲያን ተከታዮቹ በምድር ላይ ሲያገለግሉ የጋራ መነጋገሪያ በነበረው በግሪክኛ ቋንቋ ተጻፉ። እነዚህ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ዋና ክፍሎች “ዕብራይስጥ ጽሑፎች” እና “ግሪክኛ ጽሑፎች” በሚል በትክክል ይጠራሉ። ግሪክኛ ጽሑፎቹ ከዕብራይስጥ ጽሑፎች ከ365 ጊዜ በላይ በቀጥታ በመጥቀስና ከዚያ በተጨማሪ 375 ጊዜ ያህል እነሱን በማውሳት እርስ በርሳቸው የሚስማሙ መሆናቸውን ያሳያሉ።

መጽሐፍ ቅዱስን ሁሉም ሰው በቀላሉ እንዲያገኘው ማድረግ

12. ይሖዋ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች እንዲዘጋጁ ለምን አደረገ?

12 አሁን ሊገኙ የሚችሉት የመጀመሪያዎቹ ቅጂዎች ብቻ ቢሆን ኖሮ የአምላክን ቃል እያንዳንዱ ሰው እንዴት ለማንበብ ይችል ነበር? እንደዚያ ቢሆን አይቻልም ነበር። ስለዚህ ይሖዋ የዕብራይስጥ በኩረ ጽሑፎቹ በብዙ ቅጂ እንዲዘጋጁ አደረገ። (ዘዳግም 17:18) ለምሳሌ ያህል ዕዝራ የተባለው ሰው “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ በሰጠው በሙሴ ሕግ ፈጣን ጸሐፊ ነበረ።” (ዕዝራ 7:6) የግሪክኛ ጽሑፎቹም ብዙ ሺህ ቅጂ እንዲኖሩ ተደርጓል።

13. (ሀ) አብዛኛው ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዲችል ምን ያስፈልግ ነበር? (ለ) የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የተደረገው መቼ ነው?

13 ዕብራይስጥ ወይም ግሪክኛ ጽሑፍ ማንበብ ትችላለህን? ካልሆነ በድሮ ጊዜ በእጅ የተገለበጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ማንበብ አትችልም። ከእነዚህ የቀድሞ ቅጂዎች መካከል አንዳንዶቹ እስከ ዛሬ ድረስ አሉ። ስለዚህ አንተ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንድትችል ቃሎቹን አንተ ወደምታውቀው ቋንቋ የሚተረጉም ሰው አስፈለገ። ከአንዱ ቋንቋ ወደ ሌላው የተደረገው ይህ የትርጉም ሥራ ብዙ ተጨማሪ ሰዎች የአምላክን ቃል እንዲያነቡ አስችሎአል። ለምሳሌ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከ300 ዓመት በፊት አብዛኛው ሰው ግሪክኛን መናገር ጀመረ፤ ስለዚህ ከ280 ከዘአበ ጀምሮ ዕብራይስጥ ጽሑፎች ወደ ግሪክኛ ቋንቋ መተርጐም ጀመሩ። ይህ ቀደም ባሉት ዘመናት የተዘጋጀ ትርጉም “ሴፕቱጀንት” ተብሎ ይጠራል።

14.(ሀ) አንዳንድ ሃይማኖታዊ መሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይተረጐም በኃይል የታገሉት ለምንድን ነው? (ለ) እነርሱስ በትግሉ እንደተሸነፉ የሚያሳየው ምንድን ነው?

14 በኋላም ላቲን የብዙ ሰዎች የጋራ ቋንቋ ሆነ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ላቲን ተተረጐመ። ይሁን እንጂ አያሌ ክፍለ ዘመናት እያለፉ ሲሄዱ ላቲን የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር እያነሰ መጣ። አብዛኞቹ ሰዎች እንደ አረብኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ስፓንኛ፣ የፖርቹጋል ቋንቋ፣ ጣልያንኛ፣ ጀርመንኛና እንግሊዝኛ የመሳሰሉ ሌሎች ቋንቋዎችን መናገር ጀመሩ። የካቶሊክ ሃይማኖታዊ መሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ተራው ሕዝብ ቋንቋ እንዳይተረጐም ለጥቂት ጊዜ ተከላከሉ። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ በእጃቸው የተገኘ ሰዎችን እንጨት ላይ ሰቅለው በእሳት አቃጠሉ። ይህንንም ያደረጉት መጽሐፍ ቅዱስ የሐሰት ትምህርቶቻቸውንና መጥፎ ድርጊቶቻቸውን ስላጋለጠባቸው ነው። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ እነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች በውጊያው ተሸነፉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ብዙ ቋንቋዎች መተርጐምና በብዙ ቁጥር መሰራጨት ጀመረ። ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ ወይም አንዳንድ ክፍሎቹ በተተረጐመባቸው ከ1, 700 በሚበልጡ ቋንቋዎች ሊነበብ ይችላል።

15. አዲሶቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መያዙ ለምን ጥሩ ነው?

15 ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በአንዱ ቋንቋ ብዙ ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ተዘጋጁ። ለምሳሌ በእንግሊዝኛ ብቻ በደርዘን የሚቆጠሩ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አሉ። ለምን ይሆን? አንድ ትርጉም አይበቃም ነበርን? እንደሚታወቀው ሁሉ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ አንድ ቋንቋ ትልቅ ለውጥ እያደረገ ይሄዳል። ስለዚህ ቀደም ሲል የነበሩትን መጽሐፍ ቅዱሶች ከአዲሶቹ ጋር ብታወዳድር በቋንቋ የተደረጉትን ለውጦች ለመመልከት ትችላለህ። ምንም እንኳን አብዛኛውን ጊዜ የሚያስተላልፉት ሃሳብ አንድ ዓይነት ቢሆንም በቅርብ ዓመታት የተዘጋጁት ትርጉሞች ለመረዳት ቀላል ሆነው ታገኛቸዋለህ። ስለዚህ አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በመኖራቸው አመስጋኝ ለመሆን እንችላለን፤ ምክንያቱም የአምላክን ቃል በተለመደውና በቀላሉ ለመረዳት በሚቻለው ዛሬ ባለው አነጋገር ስለሚያቀርቡት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጦአልን?

16. አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጧል ብለው ለምን ያምናሉ?

16 ሆኖም ‘ዛሬ ያሉት መጽሐፍ ቅዱሶቻችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ያንኑን አሳብ እንደያዙ እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በመቶና በሺህ በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ከአንዱ ወደ አንዱ እየተገለበጡ ሲሄዱ አንዳንድ ስሕተቶች አልገቡበትምን? አዎን ገብተዋል፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ስሕተቶች ተደርሶባቸው በዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ታርመዋል። ዛሬ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለው አሳብ አምላክ በመጀመሪያ ለጻፉት ሰዎች ከሰጠው አሳብ ጋር አንድ ዓይነት ነው። ለዚህስ ምን ማረጋገጫ አለን?

17. መጽሐፍ ቅዱስ እንዳልተለወጠ ምን ማስረጃ አለ?

17 በ1947 እና በ1955 መካከል የሙት ባሕር ጥቅሎች በመባል የሚታወቁ መጻሕፍት ተገኙ። እነዚህ የጥንት ጥቅሎች የዕብራይስጥ ጽሑፎችን መጻሕፍት ጭምር ይይዛሉ። የተጻፉትም ኢየሱስ ሳይወለድ ከ100 እስከ 200 ዓመት ድረስ ቀደም ብሎ ነው። ከጥቅሎቹ አንዱ የኢሳይያስ መጽሐፍ ግልባጭ ነው። ይህ ከመገኘቱ በፊት በእጅ የነበረው በጣም ጥንታዊ ነው የሚባለው የኢሳይያስ መጽሐፍ ቅጂ ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ 1, 000 ዓመት ያህል ቆይቶ የተጻፈው ነበር። ሁለቱ ሲወዳደሩ የተገኙት ልዩነቶች በጣም ጥቂት ነበሩ። አብዛኞቹም ልዩነቶች በፊደላት የተደረጉ ጥቃቅን ለውጦች ናቸው። እንግዲህ ይህ ማለት በአንድ ሺህ ዓመት ውስጥ ከአንዱ ወደ ሌላው ሲገለበጥ ምንም ያህል ለውጦች አልተደረጉም ማለት ነው።

18. (ሀ) ጸሐፊዎች በእጅ ሲገለብጡ ያደረጉአቸው ስሕተቶች የታረሙት እንዴት ነው? (ለ) በግሪክኛ ስለ ተጻፉት ጽሑፎች ትክክለኛነት ምን ለማለት ይቻላል?

18 በአሁኑ ጊዜ የዕብራይስጥ ጽሑፎች የተለያዩ ክፍሎች ከ1, 700 በላይ ጥንታውያን ቅጂዎች ይገኛሉ። እነዚህን በጣም ጥንታውያን የሆኑ ብዙ ቅጂዎች በጥንቃቄ በማወዳደር ጸሐፊዎች ያደረጉአቸውን በጣም ጥቂት ስሕተቶች ማግኘትና ማረም ይቻላል። በተጨማሪም በጣም ጥንታውያን የሆኑና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የግሪክኛ ጽሑፎች ቅጂዎች አሉ። አንዳንዶቹ የተጻፉበት ዘመን ወደ ኢየሱስና ወደ ሐዋርያቱ ዘመን የሚጠጋ ነው። ስለዚህ ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን እንዳሉት “ቅዱሳን ጽሑፎች ልክ በመጀመሪያው እንደተጻፉት ይዘታቸውን ሳይለውጡ ወደ እኛ መምጣታቸውን አጠራጣሪ ሊያደርግ ይችል የነበረው የመጨረሻው መሠረት ተወግዷል።” –መጽሐፍ ቅዱስና በቁፋሮ የሚደረግ ምርምር ገጽ 288, 289

19. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጨማሪ ሐሳብ ለማስገባት ለተደረገው ሙከራ አንዱ ምሳሌ ምንድን ነው? (ለ) በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ በ1 ዮሐንስ 5:7 የሚገኙት ሐሳቦች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መግባት ያልነበረባቸው ለምንድን ነው?

19 ይህም ሲባል ግን የአምላክን ቃል ለመለወጥ ሙከራዎች አልተደረጉም ማለት አይደለም። አንዳንድ ሙከራዎች ተደርገዋል። በጣም የታወቀው ምሳሌ 1 ዮሐንስ 5:7 ነው። በ1611 በተተረጐመው ኪንግ ጄምስ ቨርሽን በተባለው የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉምና በ1879 በተተረጐመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቅሱ እንዲህ ይነበባል “በሰማይ የሚመሰክሩ ሦስት ናቸውና እርሳቸውም አብ ቃልም መንፈስ ቅዱስ። እሌህ ሦስትም አንድ ናቸው።” ይሁን እንጂ እነዚህ ቃላት በጣም ጥንታውያን በሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች በአንዳቸውም ላይ አይገኙም። የሥላሴን ትምህርት ለመደገፍ ይሞክር በነበረ ሰው የተጨመሩ ናቸው። እነዚህ ቃላት የአምላክ ቃል ክፍል ስላልሆኑ እርማት ተደርጐ በአዲሶቹ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ አይገኙም።

20. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራት ተጠብቆ እንደኖረ እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?

20 እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ በተጻፈ ጊዜ ይዞት የነበረውን ሃሳብ ዛሬ አልያዘም የሚል ማንኛውም ሰው እውነተኛውን ሁኔታ አያውቅም። ቃሉ በእጅ የሚገለብጡ ጸሐፊዎች ከሚያደርጓቸው ስሕተቶች ብቻ ሳይሆን ሐሳብ ሊጨምሩበት ከሚፈልጉ ከሌሎች ሰዎች ሙከራዎችም እንዲጠበቅ ይሖዋ አምላክ ተከታትሎአል። ዛሬ ለምንኖረው ቃሉ ንጹሕ ሆኖ እንደሚቆይልን አምላክ ቃል መግባቱን የሚገልጽ ተስፋ መጽሐፍ ቅዱስ ይዟል። — መዝሙር 12:6, 7፤ ዳንኤል 12:4፤ 1 ጴጥሮስ 1:24, 25፤ ራዕይ 22:18, 19

መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ እውነተኛ ነውን?

21. ኢየሱስ የአምላክን ቃል እንዴት ተመለከተው?

21 ኢየሱስ ክርስቶስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ቃልህ እውነት ነው” ብሎአል። (ዮሐንስ 17:17) ይሁን እንጂ ማስረጃዎቹ ይህንን አባባል ይደግፋሉን? መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ብንመረምረው በእርግጥ እውነት ሆኖ እናገኘዋለንን? መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ የታሪክ ተማሪዎች በትክክለኛነቱ ብዙ ጊዜ ይደነቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በመረጃ ሊረጋገጡ የሚችሉ ስሞችና ዝርዝር መግለጫዎችን ይዟል። አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት።

22–25. መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ታሪክ እንደያዘ የሚያሳዩ ጥቂቶቹ ምሳሌዎች ምንድን ናቸው?

22 በግብጽ በካርናክ ከተማ በሚገኝ አንድ ቤተመቅደስ ግድግዳ ላይ ያሉትን ሥዕሎችና ጽሕፈት ተመልከት። ከ3, 000 ዓመት በፊት ሺሻቅ የተባለ ፈርዖን የሰሎሞን ልጅ ሮብአም ሲገዛ በይሁዳ መንግሥት ላይ ስላገኘው ድል ይናገራሉ። መጽሐፍ ቅዱስም ስለዚሁ ታሪክ ይናገራል። — 1 ነገሥት 14:25, 26

23 የሞዓባውያንንም ጽላት ተመልከተው። ዋነኛው ጽላት በፈረንሳይ ሉቭር በተባለ የፓሪስ ሙዚየም ውስጥ ይገኛል። ጽሑፉ ሞሳ የተባለ የሞዓብ ንጉሥ በእስራኤል ላይ ስለ ማመጹ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንንም ታሪክ ይዟል። —2 ነገሥት 1:1፤ 3:4-27

24 በስተቀኝ በኩል ራቅ ብለው የሚታዩት የሰሊሆም ኩሬና በኢየሩሳሌም የሚገኝ ርዝመቱ 553 ሜትር የሆነ የአንድ መስኖ መግቢያ ናቸው። በዚህ ዘመን ብዙ የኢየሩሳሌም ጐብኚዎች ይህንን መስኖ ወደ ውስጥ ገብተው አይተውታል። የመስኖው መኖር መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ለመሆኑ ሌላው ማረጋገጫ ነው። እንዴት ቢባል ከ2, 500 ዓመታት በፊት ንጉሥ ሕዝቅያስ የከተማውን ውኃ ከወራሪ ኃይል ለመጠበቅ ይህንን መስኖ እንደሠራ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚገልጽልን ነው። — 2 ነገሥት 20:20፤ 2 ዜና 32:2-4, 30

25 ብሪትሽ ሙዚየምን የሚጐበኝ ሰው የናቦኒደስን ዜና ታሪክ ለማየት ይችላል። የዚህም አንዱ ግልባጭ በስተቀኝ በኩል ይታያል። ዜና ታሪኩ የጥንቷን ባቢሎን አወዳደቅ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስም ስለዚሁ ታሪክ ይናገራል። (ዳንኤል 5:30, 31) ነገር ግን በዚያን ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የነበረው ብልጣሶር እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። የናቦኒደስ ዜና ታሪክ ግን ብልጣሶር የሚለውን ስም እንኳን አይጠቅስም፤ እንዲያውም በእጅ ሊገኙ የቻሉ የጥንት ጽሑፎች በሙሉ የባቢሎን የመጨረሻው ንጉሥ ናቦኒደስ እንደነበረ ሲናገሩ ነበር። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ አይደለም የሚሉ አንዳንድ ሰዎች ብልጣሶር የሚባል ሰው ፈጽሞ አልነበረም፤ ይህም በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ፈጽሞ ስሕተተኛ ነው ብለው ነበር። ነገር ግን በቅርብ ዓመታት የተገኙ የጥንት ጽሑፎች ብልጣሶር የናቦኒደስ ልጅ እንደነበረና በዚያን ጊዜ በባቢሎን ከአባቱ ጋር አብሮ የሚገዛ እንደነበር ይገልጻሉ። አዎን፣ በጣም ብዙ ብዙ ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡት መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ እውነተኛ ነው።

26. መጽሐፍ ቅዱስ በሳይንሳዊ ሐሳቦች በኩል ትክክለኛ ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለ?

26 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ታሪክን የያዘ ብቻ አይደለም። መጽሐፉ የሚናገረው እያንዳንዱ ነገር እውነተኛ ነው። ሳይንስ ነክ ጉዳዮችን በሚጠቅስበትም ጊዜ በሚያስደንቅ አኳኋን ትክክለኛ ሁኔታዎችን ይገልጻል። ሁለት ምሳሌዎችን ለመጥቀስ ያህል በጥንት ጊዜ ምድር አንድ ግዑዝ ነገር ደግፎ እንዳቆማት ወይም በአንድ ግዙፍ ነገር ላይ እንዳረፈች በሰፊው ይታመን ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ግን አምላክ “ምድሪቱንም በታችዋ አንዳች አልባ ያንጠለጥላል” በማለት ከሳይንሳዊ ማስረጃ ጋር ፍጹም ስምምነት አለው። (ኢዮብ 26:7) በድሮ ዘመን ምድር ለጥ ብላ የተዘረጋች ወይም ጠፍጣፋ ነች ተብሎ ይታመን ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ግን አምላክ “በምድር ክበብ ላይ ይቀመጣል” ይላል። — ኢሳይያስ 40:22

27. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የመጣ ለመሆኑ ከሁሉ ይበልጥ ጠንካራው ማስረጃ ምንድን ነው? (ለ) ዕብራይስጥ ጽሑፎች ስለ አምላክ ልጅ አስቀድመው በትክክል የተናገሯቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

27 ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የመጣ ለመሆኑ ከሁሉም የሚበልጠው ማስረጃ ወደፊት የሚሆነውን በፍጹም ትክክለኛነት አስቀድሞ መመዝገቡ ነው። ወደፊት የሚሆነውን ታሪክ በትክክል የሚተነትን በሰዎች የተጻፈ አንድም መጽሐፍ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንደዚያ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ በትክክለኛ ትንቢቶች ወይም አስቀድሞ በተነገሩ ታሪኮች የተሞላ ነው። ከአስደናቂዎቹ ትንቢቶች መካከል የአምላክ ልጅ ወደ ምድር ስለ መምጣቱ የሚናገሩት ይገኙበታል። ዕብራይስጥ ጽሑፎች በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ይህ ተስፋ የተደረገበት የአምላክ ልጅ በቤተልሔም እንደሚወለድ፣ ድንግል እንደምትወልደው፣ በ30 ብር አልፎ እንደሚሰጥ፣ ከኃጢአተኞች ጋር እንደሚቆጠር፣ ከሰውነቱ አጥንቶች ውስጥ አንዱም እንደማይሠበር፣ ልብሶቹን ዕጣ እንደሚጣጣሉባቸውና ሌሎች ብዙ ብዙ ዝርዝሮች በትክክል አስቀድመው ተናግረዋል። —ሚክያስ 5:2፤ ማቴዎስ 2:3-9፤ ኢሳይያስ 7:14፤ ማቴዎስ 1:22, 23፤ ዘካርያስ 11:12, 13፤ ማቴዎስ 27:3-5፤ ኢሳይያስ 53:12፤ ሉቃስ 22:37, 52፤ 23:32, 33፤ መዝሙር 34:20፤ ዮሐንስ 19:36፤ መዝሙር 22:18፤ ማቴዎስ 27:35

28. (ሀ) ገና ያልተፈጸሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንደሚፈጸሙ ለመተማመን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህን ብትቀጥል ምን እምነት ይጨምርልሃል?

28 በዚህኛው መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ እንደተገለጸው መጽሐፍ ቅዱስ ይህ አሮጌ የነገሮች ሥርዓት በቅርቡ እንደሚፈጸምና በምትኩ ጻድቅ የሆነ አዲስ ሥርዓት እንደሚመጣ አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3-14፤ 2 ጴጥሮስ 3:7, 13) ገና ወደፊት ሊፈጸሙ ባላቸው እንደዚህ ባሉት ትንቢቶች ላይ ትምክህት ለመጣል እንችላለንን? አንድ ሰው መቶ ጊዜ እውነቱን ቢነግርህና ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዲስ ነገር ቢያወራልህ በድንገት እርሱን መጠራጠር ትጀምራለህን? አንድም ቀን ስሕተት አግኝተህበት የማታውቅ ከሆነ አሁን እርሱን መጠራጠር ትጀምራለህን? እንደዚያ ብታደርግ እንዴት ምክንያታዊ አለመሆን ነው! በተመሳሳይም አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚሰጠንን ማንኛውንም ተስፋ ለመጠራጠር ምንም ምክንያት አይኖረንም። ቃሉ ሙሉ እምነት ሊጣልበት ይቻላል። (ቲቶ 1:2) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህን ስትቀጥል በማስረጃዎቹ መሠረት መጽሐፉ በእርግጥ ከአምላክ የመጣ መሆኑን እያመንክበት ትሄዳለህ።

[በገጽ 49 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ የመሥሪያ ቤት አለቃ ደብዳቤ ለመጻፍ በጸሐፊው እንደሚጠቀም ሁሉ አምላክም መጽሐፍ ቅዱስን ለመጻፍ በሰዎች ተጠቀመ

[በገጽ 50 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ተራው ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይደርሰው በኃይል ተዋግተዋል፤ እንዲያውም በእጃቸው መጽሐፉ የተገኘባቸው አንዳንድ ሰዎች በእንጨት ላይ በእሳት ተቃጥለዋል

[በገጽ 52, 53 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሙት ባሕሩ የኢሳይያስ ጥቅል

[በገጽ 54, 55 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በግብጽ፣ በካርናክ የአንድ ቤተመቅደስ ግድግዳ

[በገጽ 55 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሞዓባውያን ጽላት

[በገጽ 55 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የናቦኒደስ ዜና ታሪክ

[በገጽ 55 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወደ ሕዝቅያስ መስኖና ወደ ሰሊሆም ኩሬ የሚያስገባው በር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ