መናፍስት በምድር ላይ ኖረው በኋላ የሞቱ ሰዎች አይደሉም
መናፍስት በእርግጥ አሉ! በዓይን በማይታየው ዓለም ውስጥ ጥሩና መጥፎ መናፍስት አሉ። ታዲያ እነዚህ መናፍስት በምድር ላይ ኖረው የሞቱ ሰዎች ናቸው?
አይደሉም። ብዙ ሰዎች እንደሚያስቡት ሰው ሲሞት ወደ መንፈሳዊ ዓለም አይዛወርም። እንደማይዛወር እንዴት እናውቃለን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚነግረን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስሙ ይሖዋ ከሆነው ብቸኛ እውነተኛ አምላክ የመጣ የእውነት መጽሐፍ ነው። ሰዎችን የፈጠራቸው ይሖዋ ነው፤ ስለዚህ ሲሞቱ ምን እንደሚሆኑ የሚያውቀው እሱ ነው።—መዝሙር 83:18፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16
አዳም ከአፈር ተፈጠረ፤ ወደ አፈርም ተመለሰ
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን “ከምድር አፈር” እንደሠራው ይናገራል። (ዘፍጥረት 2:7) አምላክ አዳምን በኤደን የአትክልት ስፍራ ማለትም በገነት አኖረው። አዳም የይሖዋን ሕግ ታዝዞ ቢሆን ኖሮ አይሞትም ነበር፤ እስከዛሬም በምድር ላይ ሕያው ሆኖ ይኖር ነበር። ይሁን እንጂ አዳም ሆን ብሎ የአምላክን ሕግ በጣሰ ጊዜ አምላክ “ከመሬት ስለተገኘህ ወደ መሬት [ትመለሳለህ]። . . . አፈር ስለሆንክ ወደ አፈር ትመለሳለህ” አለው።—ዘፍጥረት 3:19
ይህ ማለት ምን ማለት ነው? አዳም ከምድር አፈር ከመፈጠሩ በፊት የት ነበረ? የትም አልነበረም። በሰማይ የሚኖር ያልተወለደ መንፈስ አልነበረም። ምንም ዓይነት ሕልውና አልነበረውም። ስለዚህ ይሖዋ አዳም ‘ወደ አፈር እንደሚመለስ’ ሲናገር እንደሚሞት መናገሩ ነበር። ወደ መንፈሳዊ ዓለም አልተሻገረም። አዳም በሞተ ጊዜ ከሕልውና ውጭ ማለትም ሕይወት አልባ ሆነ። ሞት በሕይወት አለመኖር ማለት ነው።
ይሁን እንጂ ሌሎች የሞቱ ሰዎችስ? እነሱም እንደ አዳም ምንም ዓይነት ሕልውና የሌላቸው ሆነዋል? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት መልሱን ይሰጠናል፦
“ሁሉም [ሰዎችም ሆኑ እንስሳት] ወደ አንድ ቦታ ይሄዳሉ። ሁሉም የተገኙት ከአፈር ነው፤ ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳሉ።”—መክብብ 3:20
“ሙታን . . . ምንም አያውቁም።”—መክብብ 9:5
“ፍቅራቸው፣ ጥላቻቸውና ቅናታቸው ጠፍቷል።”—መክብብ 9:6
“አንተ በምትሄድበት በመቃብር ሥራም ሆነ ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ የለም።”—መክብብ 9:10
“ወደ መሬት ይመለሳል፤ በዚያው ቀን ሐሳቡ ሁሉ ይጠፋል።”—መዝሙር 146:4
እነዚህን ነገሮች ሊያደርጉ የሚችሉት ሕያዋን ብቻ ናቸው
እነዚህን ጥቅሶች መቀበል ያዳግትሃል? የሚያዳግትህ ከሆነ የሚከተለውን አስብ፦ በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ ሠርቶ ባመጣው ገንዘብ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ወንዱ ነው። ሰውየው ሲሞት አብዛኛውን ጊዜ ቤተሰቡ ችግር ላይ ይወድቃል። አንዳንድ ጊዜ ሚስቱና ልጆቹ ምግብ መግዣ እንኳ ያጣሉ። ምናልባትም የሰውየው ጠላቶች ያጎሳቁሏቸው ይሆናል። እንግዲህ ‘ሟቹ ሰው በመንፈሳዊ ዓለም ውስጥ በሕይወት የሚኖር ከሆነ ለቤተሰቡ የሚያስፈልጋቸውን ማቅረቡን ለምን አይቀጥልም? ቤተሰቡ በመጥፎ ሰዎች ጥቃት እንዳይደርስበት ለምን አይከላከልም?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ይህ የሆነበት ምክንያት ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች ትክክል ስለሆኑ ነው። ያ ሰው ምንም ነገር ማድረግ የማይችልና ሕይወት አልባ ነው።—መዝሙር 115:17
ሙታን የተራቡትን ቤተሰቦቻቸውን ሊረዱ ወይም የሚደርስባቸውን ጥቃት ሊከላከሉላቸው አይችሉም
ታዲያ ይህ ማለት ሙታን ዳግመኛ ወደ መኖር አይመለሱም ማለት ነው? አይደለም። ስለ ትንሣኤ ቆየት ብለን እንነጋገራለን። አሁን ግን የሞቱ ሰዎች አንተ እያደረግከው ያለውን ነገር አያውቁም ማለታችን ነው። ሊያዩህ፣ ሊሰሙህ፣ ወይም ሊያናግሩህ አይችሉም። እነሱን መፍራት አያስፈልግህም። ሙታን ሊረዱህም ሆነ ሊጎዱህ አይችሉም።—መክብብ 9:4፤ ኢሳይያስ 26:14