የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • we ገጽ 7-13
  • እንዲህ የሚሰማኝ የጤና ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እንዲህ የሚሰማኝ የጤና ነው?
  • የምትወዱት ሰው ሲሞት
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳለቀሱ የተገለጹ ሰዎች
  • ማልቀስ ወይስ አለማልቀስ?
  • አንዳንዶች ምን ተሰምቷቸዋል?
  • ቁጣና የጥፋተኝነት ስሜት ተጽዕኖ ሊያሳድርባችሁ የሚችለው እንዴት ነው?
  • የትዳር ጓደኛ ሲሞትባችሁ
  • “ሌሎች እንዲነግሯችሁ አትፍቀዱ”
  • ከሐዘኔ ልጽናና የምችለው እንዴት ነው?
    የምትወዱት ሰው ሲሞት
  • ሐዘንን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • ይህን ያህል ማዘን የጤና ነውን?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች
  • በሐዘን ለተደቆሱ ሰዎች የሚሆን ምክር
    ንቁ!—2011
ለተጨማሪ መረጃ
የምትወዱት ሰው ሲሞት
we ገጽ 7-13

እንዲህ የሚሰማኝ የጤና ነው?

ሐዘን የደረሰበት አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ያደግሁት እንግሊዝ ውስጥ በመሆኑ በሰዎች ፊት ስሜቴን አውጥቼ እንዳልገልጽ ከልጅነቴ ጀምሮ ይነገረኝ ነበር። ወታደር የነበረው አባቴ አንድ ነገር ባሳመመኝ ጊዜ ኮስተር ብሎ ‘እንዳታለቅስ!’ እንዳለኝ ዛሬም ድረስ ትዝ ይለኛል። እናቴ፣ እኔንም ሆነ ወንድሞቼንና እህቶቼን (በቤታችን ውስጥ አራት ልጆች ነበርን) እቅፍ አድርጋ የሳመችበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። አባቴ ሲሞት 56 ዓመቴ ነበር። አባቴን በማጣቴ በጣም ባዝንም መጀመሪያ ላይ ማልቀስ አልቻልኩም።”

በአንዳንድ ባሕሎች ሰዎች ስሜታቸውን ያላንዳች ገደብ ይገልጻሉ። ማዘናቸውንም ሆነ መደሰታቸውን ሌሎች ሰዎች ማወቅ ይችላሉ። በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ግን (ይበልጥ ደግሞ በሰሜን አውሮፓና በብሪታንያ) ሰዎች፣ በተለይ ወንዶች ስሜታቸውን ዋጥ እንዲያደርጉ፣ ጥርሳቸውን ነክሰው ዝም እንዲሉና ሐዘናቸውንም ሆነ ደስታቸውን እንዲደብቁ ተደርገው ያድጋሉ። ይሁን እንጂ በጣም የምትወዱት ሰው በሞት ቢለያችሁ ሐዘናችሁን መግለጽ ስህተት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳለቀሱ የተገለጹ ሰዎች

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በምሥራቃዊ ሜድትራንያን አካባቢ ይኖሩ በነበሩ ዕብራዊ የሆኑ ሰዎች ነው፤ እነዚህ ሰዎች ውስጣዊ ስሜታቸውን በደንብ ይገልጹ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ሐዘናቸውን በግልጽ ያሳዩ ብዙ ሰዎችን ይጠቅሳል። ንጉሥ ዳዊት፣ ልጁ አምኖን በመገደሉ በእጅጉ አዝኗል። እንዲያውም ‘አምርሮ አልቅሷል።’ (2 ሳሙኤል 13:28-39) ዳዊት፣ ንግሥናውን ሊቀማው ሞክሮ የነበረው ከሃዲ ልጁ አቢሴሎም በሞተ ጊዜ እንኳ አልቅሷል። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንደሚከተለው በማለት ይነግረናል፦ “ይህም ንጉሡን [ዳዊትን] ረበሸው፤ በውጭው በር ሰገነት ላይ ወዳለው ክፍልም ወጥቶ አለቀሰ፤ ወዲያ ወዲህ እያለም ‘ልጄ አቢሴሎም፣ ልጄ፣ ልጄ አቢሴሎም! ምነው በአንተ ፋንታ እኔ በሞትኩ፤ ልጄ አቢሴሎም፣ ልጄ!’ ይል ነበር።” (2 ሳሙኤል 18:33) ዳዊት እንደ ማንኛውም አባት አዝኗል። ወላጆች ‘በልጄ ፋንታ እኔ በሞትኩ’ ብለው መመኘታቸው የተለመደ ነገር ነው። ገና በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ከወላጆቹ ቀድሞ መሞቱን መቀበል በጣም ያዳግታል።

ኢየሱስ፣ ወዳጁ አልዓዛር በሞተ ጊዜ ምን ተሰማው? ወደ መቃብሩ ሲቃረብ አልቅሷል። (ዮሐንስ 11:30-38) ከጊዜ በኋላ ደግሞ መግደላዊት ማርያም ወደ ኢየሱስ መቃብር በቀረበች ጊዜ አልቅሳለች። (ዮሐንስ 20:11-16) በእርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የትንሣኤ ተስፋ የሚያውቅ አንድ ክርስቲያን፣ ሙታን የሚገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ ስለሚያምኑበት ነገር ግልጽ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ እንደሌላቸው ሰዎች መጽናናት እስከማይችል ድረስ አያዝንም። ይሁን እንጂ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን የትንሣኤ ተስፋ ቢኖረውም፣ ሰው እንደመሆኑ መጠን የሚወደው ሰው ሲሞትበት ያዝናል እንዲሁም ያለቅሳል።—1 ተሰሎንቄ 4:13, 14

ማልቀስ ወይስ አለማልቀስ?

በዛሬው ጊዜስ? ስሜታችሁን አውጥታችሁ መግለጽ ያስቸግራችኋል ወይም ያሳፍራችኋል? በዚህ ረገድ አንዳንድ አማካሪዎች ምን ይላሉ? ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሰዎች የሚሰጡት አስተያየት፣ ከዘመናት በፊት በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈውን የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ የሚያስተጋባ ነው። ባለሙያዎች፣ ሐዘናችንን ማውጣት እንጂ ማፈን ወይም ለመደበቅ መሞከር እንደማይገባን ይናገራሉ። ይህም እንዳዘኑና እንዳለቀሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን እንደ ኢዮብ፣ ዳዊትና ኤርምያስ ያሉትን የጥንት ታማኝ ሰዎች ያስታውሰናል። እነዚህ ሰዎች ስሜታቸውን አምቀው አልያዙም። ስለዚህ ራሳችሁን ከሰዎች ማግለል ጥበብ አይደለም። (ምሳሌ 18:1) እርግጥ፣ ሐዘን የሚገለጽበት መንገድ እንደየባሕሉና በአካባቢው ተስፋፍቶ እንደሚገኘው ሃይማኖታዊ እምነት ይለያያል።a

ማልቀስ ካስፈለጋችሁስ? ማልቀስ ተፈጥሯዊ ነገር ነው። አልዓዛር በሞተ ጊዜ ኢየሱስ ‘እጅግ እንዳዘነና እንባውን እንዳፈሰሰ’ እናስታውስ። (ዮሐንስ 11:33, 35) ኢየሱስ ይህን ማድረጉ፣ የሚወዱት ሰው ሲሞት ማልቀስ እንግዳ ነገር አለመሆኑን የሚያሳይ ነው።

ሐዘን ላይ ያሉ ሰዎች

የሚወዱት ሰው ሲሞት ማዘንና ማልቀስ ተፈጥሯዊ ነገር ነው

አን የተባለችው እናት ያጋጠማት ሁኔታ ይህን ሐሳብ ይደግፋል፤ ይህች እናት ሪቸል የተባለች ሕፃን ልጇን በሰደን ኢንፋንት ዴዝ ሲንድሮም (ድንገተኛ የጨቅላ ሕፃናት ሞት) አጥታለች። ባሏ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “የሚያስገርመው ነገር በቀብሩ ላይ እኔም ሆንኩ አን አላለቀስንም። ሌላው ሰው ሁሉ ያለቅስ ነበር።” አንም አክላ እንዲህ ብላለች፦ “አዎ፣ በኋላ ላይ ግን ለሁለታችንም የሚበቃ ለቅሶ አልቅሻለሁ። የሐዘኑ ክብደት በጣም የተሰማኝ፣ ልጄ ከሞተች ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ብቻዬን ቤት ውስጥ በነበርኩበት ቀን ይመስለኛል። የዚያን ዕለት፣ ሙሉ ቀን አለቀስኩ። ማልቀሴ እንደረዳኝ አምናለሁ። ከዚያ በኋላ ቀለል አለኝ። ልጄን በማጣቴ ማልቀስ ነበረብኝ። ልባቸው በሐዘን የተሰበረ ሰዎች እንዲያለቅሱ ሊፈቀድላቸው ይገባል ብዬ አምናለሁ። ሌሎች ‘አታልቅስ’ ማለታቸው የተለመደ ነገር ቢሆንም ይህ በምንም መንገድ አይረዳም።”

አንዳንዶች ምን ተሰምቷቸዋል?

አንዳንዶች የሚወዱትን ሰው በሞት ሲያጡ ምን ተሰምቷቸዋል? ለምሳሌ ያህል፣ የኹዋኒታን ሁኔታ እንመልከት። ሕፃን ልጅን ማጣት ምን ዓይነት ስሜት እንደሚፈጥር ታውቃለች። አምስት ጊዜ አስወርዷት ነበር። አሁን እንደገና አረገዘች። ስለዚህ በመኪና አደጋ ምክንያት ሆስፒታል ስትገባ በጣም ተጨነቀች። ከሁለት ሳምንት በኋላ፣ የመውለጃ ጊዜዋ ከመድረሱ በፊት ምጥ ያዛት። ብዙም ሳይቆይ አንድ ኪሎ ግራም የማትሞላ ቫኔሳ የተባለች ልጅ ተወለደች። “በጣም ተደስቼ ነበር” በማለት ኹዋኒታ ታስታውሳለች። “አሁን በመጨረሻ እናት ሆንኩ!”

ይሁን እንጂ ደስታዋ በአጭሩ ተቀጨ። ከአራት ቀን በኋላ ቫኔሳ ሞተች። ኹዋኒታ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች፦ “የባዶነት ስሜት ተሰማኝ። በድንገት እናትነቴን ተነጠቅኩ። ጎዶሎ እንደሆንኩ ተሰማኝ። ቤት ተመልሼ ለቫኔሳ ያዘጋጀነውን ክፍልና የገዛሁላትን ትናንሽ ካናቴራዎች ስመለከት እጅግ አዘንኩ። ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት፣ የተወለደችበትን ቀን እያሰብኩ እተክዝ ነበር። ከማንም ጋር መገናኘት አልፈለግሁም።”

ይህ ከመጠን ያለፈ ሐዘን ነው? ሌሎች ሁኔታውን መረዳት ያስቸግራቸው ይሆናል፤ ሆኖም እንዲህ ያለ ሐዘን የደረሰባቸው እንደ ኹዋኒታ ያሉ ሰዎች እንደሚናገሩት በሕፃኑ ሞት የተሰማቸው ሐዘን፣ ለተወሰነ ጊዜ በሕይወት ኖሮ ለሞተ ሰው ከሚሰማቸው ሐዘን ያላነሰ ነው። ወላጆች፣ ሕፃን ልጃቸውን መውደድ የሚጀምሩት ገና ከመወለዱ በፊት እንደሆነ ይናገራሉ። ሕፃኑ ከእናቲቱ ጋር ልዩ የሆነ ዝምድና አለው። ሕፃኑ በሚሞትበት ጊዜ እናቲቱ የሚሰማት፣ አንድ ሙሉ ሰው በሞት የተለያት ያህል ነው። ሌሎች መረዳት የሚኖርባቸው ይህንን ነው።

ቁጣና የጥፋተኝነት ስሜት ተጽዕኖ ሊያሳድርባችሁ የሚችለው እንዴት ነው?

አንዲት ሌላ እናት ደግሞ ስድስት ዓመት የሆነው ልጇ፣ ሲወለድ ጀምሮ በነበረበት የልብ ሕመም ምክንያት በድንገት እንደሞተ ሲነገራት ምን እንደተሰማት እንዲህ ስትል ገልጻለች፦ “የተመሰቃቀለ ስሜት ተሰማኝ። የመደንዘዝ፣ ነገሩን ያለማመን፣ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማኝ፤ እንዲሁም የልጄ ሕመም ምን ያህል ከባድ መሆኑን ሳይገነዘቡ በመቅረታቸው በባለቤቴና በዶክተሩ ተናደድኩ።”

ሐዘን የሚገለጽበት አንዱ መንገድ ቁጣ ሊሆን ይችላል። የሚወደውን ሰው በሞት ያጣው ግለሰብ፣ ሐኪሞችና ነርሶች ለሟቹ የሚገባውን እንክብካቤና ሕክምና እንዳላደረጉ በማሰብ ይናደድ ይሆናል። አሊያም ወዳጆችና ዘመዶች አግባብ ያልሆነ ነገር እንደሚናገሩ ወይም እንደሚያደርጉ ስለሚሰማው በእነሱ ላይ ሊቆጣ ይችላል። አንዳንዶች፣ ሟቹ ለጤንነቱ ተገቢ ጥንቃቄ ባለማድረጉ ይናደዳሉ። ስቴላ “ባለቤቴ ይበልጥ ጥንቃቄ ቢያደርግ ኖሮ እንደማይሞት አውቅ ስለነበር በእሱ ላይ አምርሬ መቆጣቴ ትዝ ይለኛል። በጣም ታሞ እያለ ሐኪሞች የሰጡትን ማስጠንቀቂያ አልሰማም ነበር” ብላለች። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሕይወት ያሉት ሰዎች፣ ሟቹ በሞት ማንቀላፋቱ ተጨማሪ ሸክም ስለሚያስከትልባቸው ይናደዳሉ።

አንዳንዶች፣ በመቆጣታቸው ምክንያት የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል፤ በሌላ አባባል የቁጣ ስሜት ስለተሰማቸው ራሳቸውን ይኮንናሉ። ሌሎች ደግሞ የሚወዱት ሰው የሞተው በእነሱ ጥፋት እንደሆነ በማሰብ ራሳቸውን ይወቅሳሉ። “ቶሎ ሐኪም ቤት እንዲሄድ ባደርገው ኖሮ” ወይም “ሌላ ሐኪም እንዲያየው ባደርግ ኖሮ” ወይም “ጤንነቱን በሚገባ እንዲንከባከብ ብረዳው ኖሮ አይሞትም ነበር” እያሉ ራሳቸውን ይወቅሳሉ።

አንዲት እናት ልጇን አቅፋ የነበረችበትን ጊዜ ስታስታውስ

የልጅ ሞት ከፍተኛ የስሜት ቁስል ያስከትላል፤ ለወላጆቹ ልባዊ የሆነ አዘኔታና አሳቢነት ማሳየት ሊረዳቸው ይችላል

አንዳንዶች፣ በተለይ የሚወዱት ሰው የሞተባቸው ሳያስቡት በድንገት ከሆነ የሚሰማቸው የጥፋተኝነት ስሜት ከዚህም አልፎ ይሄዳል። ከሟቹ ጋር የተጨቃጨቁበትን ወይም በእሱ ላይ የተቆጡበትን ጊዜ ማስታወስ ይጀምራሉ። አሊያም ለሟቹ የሚገባውን ሁሉ እንዳላደረጉለት ይሰማቸዋል።

የብዙ እናቶች ሐዘን ለረጅም ጊዜ የሚቆይ መሆኑ፣ የልጅ ሞት በወላጆች ላይ በተለይም በእናቲቱ ላይ የማይሽር ሐዘን ጥሎ እንደሚያልፍ በርካታ ባለሙያዎች የሚናገሩት ሐሳብ እውነት መሆኑን ያረጋግጣል።

የትዳር ጓደኛ ሲሞትባችሁ

የትዳር ጓደኛ በተለይ ብዙ ነገር አብሮ ያሳለፈ የትዳር ጓደኛ ሲሞት ከባድ ሐዘን ያስከትላል። ባለትዳሮቹ አብረው በመጓዝ፣ በመሥራት፣ በመዝናናት ብሎም እርስ በርስ በመረዳዳት የሚያሳልፉት ሕይወት ያበቃል ማለት ነው።

ዩኒስ ባሏ በልብ ድካም ምክንያት በድንገት ሲሞት ምን እንደተሰማት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በመጀመሪያው ሳምንት፣ መላ ሰውነቴ ሥራውን ያቆመ ይመስል ድንዝዝ ብዬ ነበር። መቅመስም ሆነ ማሽተት እንኳ ተስኖኝ ነበር። አእምሮዬ ግን ከቀረው ሰውነቴ እንደተነጠለ ያህል ሆኖ በሐሳብ ይብከነከን ነበር። ሐኪሞች በሲ ፒ አር [ካርዲዮፐልሙነሪ ሪሰሲቴሽን] እና በመድኃኒቶች ሕይወቱን ለማቆየት በሚጥሩበት ጊዜ አብሬው ስለነበርኩ ብዙዎች እንደሚያጋጥማቸው መሞቱን ለማመን አልተቸገርኩም። ያም ቢሆን አንድ መኪና ከገደል አፋፍ ወድቆ ሊከሰከስ ሲል ምንም ማድረግ በማልችልበት ሁኔታ ላይ ሆኜ ብመለከት የሚሰማኝ ዓይነት ከፍተኛ ሐዘንና ብስጭት ተሰምቶኝ ነበር።”

ይህች ሴት አልቅሳ ነበር? “አዎ፣ በደንብ አለቀስኩ። በተለይ የተላኩልኝን በርካታ የሐዘን መግለጫ ካርዶች በማነብበት ጊዜ አለቅስ ነበር። እያንዳንዱን ካርድ ባነበብኩ ቁጥር አለቅስ ነበር። ይህን ማድረጌ በቀሪው ቀን ሐዘኔን መቋቋም እንድችል ረድቶኛል። ሰዎች ‘እንዴት ይሰማሻል?’ እያሉ ያቀርቡልኝ የነበረው ተደጋጋሚ ጥያቄ ግን ምንም የሚፈይድልኝ ነገር አልነበረም። በጣም እንዳዘንኩ ግልጽ ነበር” ብላለች።

ዩኒስ ከሐዘኗ እንድትጽናና የረዳት ምን ነበር? “አስቤበት ባይሆንም፣ ኑሮዬን መቀጠል አለብኝ ብዬ ወሰንኩ” ብላለች። “ይሁን እንጂ ሕይወትን በጣም ይወድ የነበረው ባለቤቴ አብሮኝ አለመሆኑና መኖር የሚያስገኘውን ደስታ ማጣጣም አለመቻሉ አሁንም ቢሆን በእጅጉ ያሳዝነኛል።”

“ሌሎች እንዲነግሯችሁ አትፍቀዱ”

ሊቭቴኪንግ—ዌን ኤንድ ሃው ቱ ሴይ ጉድባይ የተባለው መጽሐፍ ደራሲዎች እንደሚከተለው በማለት ይመክራሉ፦ “ምን ልታደርጉና ምን ሊሰማችሁ እንደሚገባ ሌሎች እንዲነግሯችሁ አትፍቀዱ። አንድ ሰው ሐዘኑን የሚገልጽበት መንገድ ከሌላው ይለያል። አንዳንዶች፣ ሐዘናችሁ ከመጠን ያለፈ እንደሆነ ወይም በተገቢው መንገድ እያዘናችሁ እንዳልሆነ ሊሰማቸውና ይህን ስሜታቸውንም ሊያሳውቋችሁ ይችላሉ። ይህን ስላሏችሁ አትዘኑባቸው፤ የነገሯችሁን ግን እርሱት። ራሳችሁን አስገድዳችሁ፣ ሌሎች ሰዎች ወይም ማኅበረሰቡ በሚፈልገው መንገድ ለማዘን መሞከራችሁ ስሜታችሁን ለማረጋጋት በምታደርጉት ጥረት ረገድ እንቅፋት ይፈጥርባችኋል።”

እርግጥ እያንዳንዱ ሰው ሐዘኑን የሚገልጽበት መንገድ ሊለያይ ይችላል። ለሁሉም ሰው የሚሆን መንገድ ለመጠቆም መሞከራችን አይደለም። ይሁን እንጂ ያዘነው ሰው፣ የተፈጠረውን ሁኔታ መቀበል ሲያቅተው አደገኛ ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ ጊዜ ሩኅሩኅ የሆኑ ወዳጆች እርዳታ ያስፈልገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው” ይላል። ስለዚህ ሐዘን ከደረሰባችሁ የሌሎችን እርዳታ ለመጠየቅ፣ ሰዎችን ለማናገርና ለማልቀስ አትፍሩ።—ምሳሌ 17:17

ሐዘን፣ አንድን ነገር ማጣት የሚያስከትለው ጤናማ ስሜት ስለሆነ ማዘናችሁ ለሌሎች ግልጽ ሆኖ ቢታይ ምንም ስህተት የለውም። ይሁን እንጂ ‘ከሐዘኔ ልጽናና የምችለው እንዴት ነው? የጥፋተኝነትና የብስጭት ስሜት የሚሰማኝ በጤና ነው? እነዚህን ስሜቶች እንዴት ላሸንፍ እችላለሁ? የምወደውን ሰው በሞት ማጣቴ የፈጠረብኝን ስሜትም ሆነ ሐዘኑን ለመቋቋም ምን ሊረዳኝ ይችላል?’ የሚሉት ተጨማሪ ጥያቄዎች መልስ ያስፈልጋቸዋል። የሚቀጥለው ክፍል ለእነዚህና ለሌሎች ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

a ለምሳሌ ያህል፣ በናይጄሪያ የሚኖሩት የዮሩባ ጎሣ አባላት ነፍስ ሌላ ሥጋ ለብሳ ትመለሳለች የሚል ባሕላዊ እምነት አላቸው። በዚህም ምክንያት አንዲት እናት ልጅ ሲሞትባት የመረረ ሐዘን የሚሰማት ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው። “ውኃው ተደፋ እንጂ ቅሉ አልተሰበረም” የሚል የተለመደ የዮሩባዎች አባባል አለ። በዮሩባዎች እምነት መሠረት፣ የውኃ መያዣ የሆነው ቅል ማለትም እናቲቱ ሌላ ልጅ ልትወልድ (ምናልባትም የሞተውን ልጅ በሌላ አካል እንደገና ልትወልደው) ትችላለች። የይሖዋ ምሥክሮች፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌላቸውን ‘ነፍስ አትሞትም’ ወይም ‘ነፍስ ሌላ አካል ለብሳ ትመለሳለች’ ከሚሉ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች የመነጩትን ወጎችና አጉል እምነቶች አይከተሉም።—መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4, 20

የሚታሰብባቸው ጥያቄዎች

  • የአንዳንድ ሰዎች ባሕል፣ ሐዘናቸውን በሚገልጹበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?

  • ሐዘናቸውን በግልጽ በማሳየት ረገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የእነማንን ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል?

  • አንዳንዶች የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ሲያጡ ምን ተሰምቷቸዋል? እናንተስ ተመሳሳይ ሁኔታ ባጋጠማችሁ ጊዜ ምን ተሰማችሁ?

  • የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣት ከሌላው ዓይነት ሐዘን የተለየ የሚሆነው ለምንድን ነው?

  • ሐዘን የሚገለጽበትን መንገድ በተመለከተ ምን ልዩነት ሊኖር ይችላል? ማዘን ስህተት ነው?

  • የሐዘን ሂደት አንዳንድ ገጽታዎች ምንድን ናቸው? (በገጽ 9 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከቱ።)

  • ጨቅላ ሕፃናት በድንገት ሲሞቱ ወላጆች ምን ለየት ያለ ስሜት ይፈጠርባቸዋል? (በገጽ 12 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከቱ።)

  • ብዙ እናቶች፣ ሲያስወርዳቸው ወይም የሞተ ሕፃን ሲወልዱ ምን ይሰማቸዋል? (በገጽ 10 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከቱ።)

የሐዘን ሂደት

“ሂደት” የሚለው ቃል፣ የሚወደውን ሰው በሞት ያጣ ግለሰብ የሚያዝንበት የተወሰነ ፕሮግራም እንዳለው የሚያመለክት አይደለም። በሐዘን ምክንያት የሚፈጠሩ ስሜቶች እንደየግለሰቡ ሁኔታ ለተለያየ ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ፤ በተጨማሪም ግለሰቡ በአንድ ጊዜ የተለያዩ ስሜቶች ይፈጠሩበት ይሆናል። የሚከተለው ዝርዝር፣ ሐዘን የሚያስከትላቸውን ስሜቶች ሁሉ ያካትታል ማለት አይቻልም። ሌሎች ስሜቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። ሊያጋጥሙ ከሚችሉ የሐዘን ምልክቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።

መጀመሪያ ላይ የሚፈጠሩ ስሜቶች፦ ድንጋጤ፣ ነገሩን ማመን አለመቻል፣ እውነታውን አለመቀበል፣ የስሜት መደንዘዝ፣ የጥፋተኝነት ስሜት፣ ቁጣ።

መሪር የሐዘን ስሜቶች የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ፦ ማስታወስ አለመቻልና እንቅልፍ ማጣት፤ ሥር የሰደደ ድካም፤ ድንገተኛ የሆነ የጠባይ መለዋወጥ፤ በትክክል ማሰብና ማመዛዘን አለመቻል፤ ድንገተኛ ለቅሶ፤ የምግብ ፍላጎት መለወጥና በዚህ ምክንያት የሚመጣ የክብደት መቀነስ ወይም መጨመር፤ የተለያዩ የጤና መታወክ ምልክቶች፤ መፍዘዝ፤ የሥራ ችሎታ መቀነስ፤ ሟቹን እንዳዩት ወይም ድምፁን እንደሰሙት አድርጎ ማሰብ፤ የሞተው ልጅ ከሆነ ደግሞ ያለምንም ምክንያት የትዳር ጓደኛን መጥላት።

የመረጋጊያ ጊዜ፦ መተከዝ፤ ከሟቹ ጋር ያሳለፉትን አስደሳች ጊዜ ማስታወስና አንዳንድ ጊዜም ትዝታውን እያሰቡ መሳቅ መቻል።

ውርጃና ሞቶ የተወለደ ሕፃን—በእናቶች ላይ የሚያስከትለው ሐዘን

ሞና ሌሎች ልጆች ቢኖሯትም በማህፀኗ ያለችው ሕፃን የምትወለድበትን ጊዜ በናፍቆት ትጠብቅ ነበር። ከመወለዷ በፊት እንኳ “የምታጫውታት፣ የምታነጋግራትና በሕልሟ የምትታያት ልጅ” እንደነበረች ትናገራለች።

እናቶች በማህፀናቸው ውስጥ ካለው ሕፃን ጋር የሚኖራቸው ትስስር በጣም ጠንካራ ነው። ሞና አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ልጄ ሪቸል አን በማህፀኔ ውስጥ ሆና ስትገላበጥ፣ ሆዴ ላይ አስደግፌ የማነበውን መጽሐፍ የምትጥልና ሌሊት የምታነቃኝ ልጅ ነበረች። ፈርገጥ ስትል በቀስታና በፍቅር የምትረግጠኝ ያህል ይሰማኝ እንደነበረ አሁንም ድረስ ትዝ ይለኛል። በምትንቀሳቀስበት ጊዜ ሁሉ መላ ሰውነቴ በፍቅር ይሞላ ነበር። በደንብ አውቃት ስለነበረ ሕመምና ሥቃይ ሲሰማት እንኳ ይታወቀኝ ነበር።”

ሞና ታሪኳን እንዲህ በማለት ትቀጥላለች፦ “ዶክተሩ፣ ምንም ማድረግ የማይቻልበት ደረጃ ላይ እስክንደርስ ድረስ የምነግረውን ሁሉ አላመነኝም ነበር። ‘አትጨነቂ’ ይለኝ ነበር። ስትሞት እንደተሰማኝ እርግጠኛ ነኝ። በድንገት በኃይል ተገላበጠች። በማግስቱ፣ እንደሞተች አወቅን።”

ብዙዎች ሞና የደረሰባት ዓይነት ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ሰርቫይቪንግ ፕሬግናንሲ ሎስ የተባለው መጽሐፍ ደራሲዎች የሆኑት ፍሪድማንና ግራድስታይን በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ አንድ ሚሊዮን የሚያክሉ ሴቶች በየዓመቱ እርግዝናቸው እንደሚጨናገፍ ገልጸዋል። በመላው ዓለም ደግሞ ቁጥሩ ከዚህ በጣም ከፍ ያለ ነው።

አንዲት ሴት ሲያስወርዳት ወይም የሞተ ሕፃን ስትወልድ በጣም እንደምታዝንና ምናልባትም ሕይወቷን በሙሉ የምታስታውሰው አሳዛኝ ሁኔታ እንዳጋጠማት ብዙ ሰዎች አይገነዘቡም። ለምሳሌ ያህል፣ በአሁኑ ጊዜ በዕድሜ የገፋችው ቬሮኒካ የተጨናገፉባትን እርግዝናዎች አትረሳቸውም፤ በተለይ ደግሞ እስከ ዘጠነኛው ወር ድረስ በሕይወት የቆየችውንና ስትወለድ 6 ኪሎ ግራም ትመዝን የነበረችውን ልጇን መቼም አትረሳትም። ሕፃኗ ከሞተች በኋላም ለሁለት ሳምንታት በማህፀኗ ውስጥ ቆይታለች። ቬሮኒካ “ለአንዲት እናት የሞተ ሕፃን መውለድ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው” ብላለች።

ሌሎች ሴቶችም እንኳ የእነዚህን እናቶች ሐዘንና ብስጭት ብዙ ጊዜ አይረዱላቸውም። ፅንስ የጨነገፈባት አንዲት ሴት እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ይህ ነገር በእኔ ላይ ከመድረሱ በፊት፣ [ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጠማቸው] ጓደኞቼ እንዴት ያለ ሥቃይ እንዳሳለፉ ጨርሶ አልገባኝም ነበር፤ ይህን የተረዳሁት እኔ ራሴ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ካለፍኩ በኋላ ነው። በአሁኑ ጊዜ የሚሰማኝን ስሜት ሰዎች እንደማይረዱልኝ ይሰማኛል፤ እኔም የጓደኞቼን ሥቃይ አልተረዳሁላቸውም ነበር።”

በሐዘን የተዋጡ ባልና ሚስት እርስ በርስ ሲደጋገፉ

ይህ ዓይነቱ ሐዘን የደረሰባት እናት የሚያጋጥማት ሌላው ችግር፣ ሐዘኑ የእሷን ያህል ለባሏ እንዳልተሰማው ማሰቧ ነው። አንዲት ሚስት እንዲህ በማለት ገልጻለች፦ “በዚያን ጊዜ በባለቤቴ ተናድጄ ነበር። ለእሱ፣ እርግዝና የሚባል ነገር ያልነበረ ያህል ነበር። የደረሰብኝ ሐዘን የእኔን ያህል አልተሰማውም። ስጋቴን እንጂ ሐዘኔን አልተረዳልኝም።”

ባል እንዲህ ዓይነት ስሜት ማሳየቱ የሚያስገርም ላይሆን ይችላል፤ ነፍሰ ጡር የነበረችው ሚስቱ ከሕፃኑ ጋር የነበራት ዓይነት አካላዊና ስሜታዊ ትስስር የለውም። ቢሆንም ልጁን በማጣቱ እንደሚሰማው የታወቀ ነው። በተጨማሪም ባልና ሚስቱ፣ ችግሩ በተለያየ መንገድ ቢሆንም ሁለቱንም የሚነካ መሆኑን መገንዘባቸው አስፈላጊ ነው። ሐዘናቸውን መካፈል ይኖርባቸዋል። ባልየው ሐዘኑን ከደበቀ፣ ሚስቱ ምንም እንዳልተሰማው ልታስብ ትችላለች። ስለዚህ አብራችሁ አልቅሱ፣ ሐሳባችሁን ግለጹ እንዲሁም የትዳር ጓደኛችሁን እቅፍ በማድረግ ተበረታቱ። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አንዳችሁ ሌላውን እንደምትፈልጉ አሳዩ። አዎ፣ ባሎች የሚስቶቻችሁን ስሜት እንደምትረዱላቸው አሳዩ።

የጨቅላ ሕፃናት ድንገተኛ ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም

የአንድ ሕፃን ድንገተኛ ሞት፣ ቅስም የሚሰብር ሐዘን ያስከትላል። ምንም ዓይነት የበሽታ ምልክት የማይታይበት ጤነኛ ሕፃን አንድ ቀን እንደተኛ ይቀራል። ይህ ፈጽሞ የማይጠበቅ ነገር ነው፤ አንድ ጨቅላ ሕፃን ከወላጆቹ ቀድሞ ይሞታል ብሎ ማን ያስባል? እናቲቱ፣ ፍቅሯን ስታሳየውና ስትንከባከበው የነበረው ሕፃን በድንገት ሲሞት ለከባድ ሐዘን ትዳረጋለች።

ወላጆች በጥፋተኝነት ስሜት ይዋጣሉ። ሳያደርጉ የቀሩት ነገር ያለ ይመስል ለሕፃኑ ሞት ተጠያቂዎች እንደሆኑ ሊሰማቸው ይችላል። ‘ሕፃኑ እንዳይሞት ምን ማድረግ እንችል ነበር?’ ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ።b በአንዳንድ ሁኔታዎች ባልየው ያለበቂ ምክንያት ሳይታወቀው ሚስቱን ጥፋተኛ አድርጎ መመልከት ሊጀምር ይችላል። ለሥራ ከቤት ሲወጣ ሕፃኑ በሕይወት ያለ ጤነኛ ልጅ ነበር። ወደ ቤቱ ሲመለስ ግን አልጋው ላይ ሞቶ ያገኘዋል! ሚስቱ ምን ታደርግ ነበር? በጊዜው የት ነበረች? በትዳራቸው መካከል ውጥረት እንዳይነግሥ፣ እነዚህን የሚከነክኑ ጥያቄዎች ተወያይቶ መፍታት ያስፈልጋል።

ለደረሰው አሳዛኝ ሁኔታ ምክንያት የሆኑት በቅድሚያ ያልታወቁና ሊታወቁ የማይችሉ ምክንያቶች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እኔም ከፀሐይ በታች ሌላ ነገር ተመለከትኩ፤ ፈጣኖች በውድድር ሁልጊዜ አያሸንፉም፤ ኃያላን በውጊያ ሁልጊዜ ድል አይቀናቸውም፤ ጥበበኞች ሁልጊዜ ምግብ አያገኙም፤ አስተዋዮች ሁልጊዜ ሀብት አያገኙም፤ እውቀት ያላቸው ሰዎችም ሁልጊዜ ስኬታማ አይሆኑም፤ ምክንያቱም ሁሉም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል።”—መክብብ 9:11

አንድ ቤተሰብ፣ ሕፃን ልጁን በሞት ሲያጣ ሌሎች እርዳታ ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት ነው? ይህ ዓይነቱ ሐዘን የደረሰባት አንዲት ሴት እንዲህ የሚል መልስ ሰጥታለች፦ “አንድ ወዳጄ ምንም ነገር ሳልነግራት መጥታ ቤቴን አጸዳችልኝ። ሌሎች ደግሞ ምግብ ሠሩልን። አንዳንዶች ደግሞ አንድም ቃል ሳይተነፍሱ እቅፍ አድርገው በመሳም ብቻ አጽናንተውኛል። ስለደረሰብን ሐዘን መናገር አልፈልግም ነበር። የሆነውን ነገር አሁንም አሁንም ደጋግሜ ማውራት አልፈለግሁም። አደጋው የደረሰው እኔ ሳላደርግ በቀረሁት ነገር ምክንያት ይመስል የምርመራ ጥያቄዎች እንዲቀርቡልኝ አልፈለግሁም። እናቲቱ እኔ ነኝ። ልጄን ለማዳን ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አልልም ነበር።”

b አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ እስከ ስድስት ወር ዕድሜ የሚገኙ ሕፃናትን የሚያጠቃው ሰደን ኢንፋንት ዴዝ ሲንድሮም (ኤስ አይ ዲ ኤስ)፣ ጤነኛ የሆኑ ሕፃናት ባልታወቀ ምክንያት ድንገት መሞታቸውን ለመግለጽ የሚሠራበት ስያሜ ነው። በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ ሕፃኑ በሆዱ ሳይሆን በጀርባው ወይም በጎኑ ቢተኛ ይህ አደጋ እንደማይደርስበት ይታመናል። ይሁን እንጂ ኤስ አይ ዲ ኤስን ሙሉ በሙሉ ሊከላከል የሚችል አስተኛኘት የለም።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ