የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ገጽ 33-ገጽ 38 አን. 4
  • ምርምር ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ምርምር ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ የምርምር መጽሐፋችን ነው
  • ለምርምር የሚረዱ ሌሎች ጽሑፎችን መጠቀም
  • ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች
  • የግል ፋይል ይኑርህ
  • ሰዎችን ጠይቅ
  • የምርምርህን ውጤት ገምግም
  • አዲስ የምርምር መሣሪያ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2014
  • ከስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
  • ቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍት ማደራጀት የሚቻለው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ጥናት ብዙ ጥቅም ያስገኛል
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ገጽ 33-ገጽ 38 አን. 4

ምርምር ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

ንጉሥ ሰሎሞን ‘እውነተኛውን ቃል ለማስፈር’ ስለፈለገ ‘ጥልቅ ምርምርና ፍለጋ በማድረግ ብዙ ምሳሌዎችን አስማምቶ ጽፏል።’ (መክብብ 12:​9, 10) ሉቃስ በክርስቶስ ሕይወት ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች በቅደም ተከተል ለማስቀመጥ ሲል “ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ” ተከትሎ ጽፏል። (ሉቃስ 1:​3 አ.መ.ት ) ሁለቱም የአምላክ አገልጋዮች ምርምር አድርገዋል።

ምርምር ምንድን ነው? ስለ አንድ ጉዳይ መረጃ ለማግኘት በጥንቃቄ የሚደረግ ፍለጋ ነው። ይህም ማንበብን እንዲሁም መሠረታዊ የሆኑትን የአጠናን ዘዴዎች መጠቀምን ይጠይቃል። ከሰዎች መረጃ ማግኘትንም ሊያካትት ይችላል።

ምርምር ልታደርግባቸው የሚገቡ አንዳንድ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት። የግል ጥናት ስታደርግ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብ ያጋጠሙህ መልስ ልታገኝላቸው የምትፈልጋቸው ጥያቄዎች ይኖሩ ይሆናል። አገልግሎት ላይ ያነጋገርከው ሰው ላነሳው ጥያቄ መልስ ማግኘት ትፈልግ ይሆናል። ወይም ደግሞ ንግግር እንድትሰጥ ተመድበህም ሊሆን ይችላል።

ንግግር እንድትሰጥ ተመድበሃል እንበል። የትምህርቱ ይዘት ሰፊ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ለአድማጮችህ እንደሚስማማ አድርገህ ማቅረብ የምትችለው እንዴት ነው? ምርምር በማድረግ ትምህርቱን አዳብረው። በመጀመሪያ ግልጽ ነው ብለህ ያሰብኸውንም ነጥብ አንድ ሁለት አኃዛዊ መረጃ በማከል ወይም የአድማጮችህን ሕይወት የሚነካና ከትምህርቱ ጋር የሚስማማ ምሳሌ በመጨመር ግንዛቤያቸውን የሚያሰፋ አልፎ ተርፎም ቀስቃሽ ልታደርገው ትችላለህ። ምናልባት ትምህርቱ የተመሠረተበት ጽሑፍ በየትኛውም ቦታ ለሚገኙ አንባቢዎች ታስቦ የተዘጋጀ ሊሆን ይችላል። አንተ ግን ነጥቦቹን ለአንድ ጉባኤ ወይም ግለሰብ በሚስማማ መንገድ ማዳበር፣ በምሳሌ አስደግፎ ማቅረብ እንዲሁም እንዴት ሊሠራባቸው እንደሚችል ማብራራት ያስፈልግሃል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

መረጃ ማሰባሰብ ከመጀመርህ በፊት አድማጮችህ እነማን እንደሆኑ አስብ። ስለ ጉዳዩ ያላቸው እውቀት ምንድን ነው? ምንስ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል? ከዚያ በኋላ በንግግርህ ምን ማከናወን እንደምትፈልግ ወስን። ዓላማህ ማብራራት ነው? ማሳመን ነው? ሐሰት መሆኑን ማስረዳት ነው? ወይስ ለሥራ መቀስቀስ? ማብራራት ተጨማሪ መረጃ በማቅረብ ነጥቡን ግልጽ ማድረግን ይጠይቃል። መሠረታዊ የሆነው ሐሳብ የሚታወቅ ሊሆን ቢችልም መቼ ወይም እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል በመግለጽ ነጥቡን ማስፋት ያስፈልግህ ይሆናል። ማሳመን ‘ለምን ’ ለሚለው ጥያቄ በማስረጃ የተደገፈ መልስ ማቅረብን ይጠይቃል። አንድ ነገር ሐሰት መሆኑን ለማስረዳት የጉዳዩን ሁለቱንም ወገን ጠንቅቆ ማወቅና በማስረጃነት የሚቀርቡትን ነጥቦች በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል። እርግጥ አሳማኝ ማስረጃዎችንም ማቅረብ የሚኖርብን በደግነት ነው። ለሥራ ማነሳሳት ከልብ እንዲያምኑበት ማድረግን ይጠይቃል። ይህም አድማጮች የሰሙትን ነገር በሥራ የመተርጎም ፍላጎት እንዲያድርባቸው ማድረግ ማለት ነው። አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያሉም እንኳ ተመሳሳይ እርምጃ የወሰዱ ሰዎችን ተሞክሮ መጥቀስ የአድማጮችን ልብ ለማነሳሳት ሊረዳ ይችላል።

አሁን ምርምር ለማድረግ ዝግጁ ነህ ማለት ነው? የሚቀርህ ነገር አለ። ምን ያህል መረጃ ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግህ አስብ። በዚህ ረገድ ጊዜ ወሳኝ ሊሆን ይችላል። ትምህርቱን ለማቅረብ የሚፈቀድልህ ጊዜ ምን ያህል ነው? አምስት ደቂቃ? ወይስ አርባ አምስት ደቂቃ? በጉባኤ ስብሰባ ላይ እንደሚቀርቡት ክፍሎች በተወሰነ ጊዜ ማለቅ አለበት? ወይስ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና እንደ እረኝነት ጉብኝት እንደ ሁኔታው ሊያጥርም ሊረዝምም ይችላል?

ከዚህ በኋላ የሚነሳው ጥያቄ ለምርምር የሚረዱ ምን መሣሪያዎች አሉህ? የሚል ነው። በመንግሥት አዳራሻችሁ ቤተ መጻሕፍት ውስጥስ ተጨማሪ ምርምር ለማድረግ የሚረዱ ጽሑፎች ይገኛሉ? በይሖዋ ቤት ረዘም ላሉ ዓመታት የቆዩ ወንድሞች እንደነዚህ ያሉትን ጽሑፎቻቸውን እንድትጠቀም ሊፈቅዱልህ ይችላሉ? ሌሎች የማመሳከሪያ መጻሕፍት ቢያስፈልጉህ በአካባቢህ ቤተ መጻሕፍት ማግኘት ትችላለህ?

መጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ የምርምር መጽሐፋችን ነው

ምርምር የምታደርገው የአንድን ጥቅስ ትርጉም ለማወቅ ከሆነ ከራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጀምር።

በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ተመልከት። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ይህ ጥቅስ የተጻፈው ለማን ነበር? ከላይና ከታች ያሉት ቁጥሮች ይህ ሐሳብ ስለተጻፈበት ምክንያት ወይም በታሪኩ ውስጥ ስለተጠቀሱት ሰዎች ዝንባሌ ምን የሚጠቁሙት ነገር አለ?’ ይህን ማወቅህ ብዙውን ጊዜ አንድን ጥቅስ እንድትረዳው ከማገዙም ሌላ ንግግርህን ሕያው ለማድረግ ሊያገለግል ይችላል።

ለምሳሌ ያህል የአምላክ ቃል የሰዎችን ልብ የመንካትና ሕይወታቸውን የመለወጥ ኃይል እንዳለው ለማስረዳት ዕብራውያን 4:​12 ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል። በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ቃሉ የሰዎችን ልብ ሊነካ የሚችለው እንዴት እንደሆነ ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል። ይሖዋ ለአብርሃም ቃል የገባለትን የተስፋይቱን ምድር ከመውረሳቸው በፊት እስራኤላውያን ለ40 ዓመት በበረሃ ስላሳለፉት ጊዜ ይገልጻል። (ዕብ. 3:​7–4:​13) “የእግዚአብሔር ቃል” ማለትም አምላክ ለአብርሃም በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ወደ እረፍት ስፍራ እንደሚያስገባቸው የሰጠው ተስፋ፣ ሕያውና ፍጻሜውን እያገኘ ያለ እንጂ የተረሳ አልነበረም። እስራኤላውያን ይህንን ቃል የሚጠራጠሩበት ምንም ምክንያት አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ ይሖዋ ከግብፅ አውጥቶ ወደ ሲና ተራራና ከዚያም ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲመራቸው በተደጋጋሚ እምነት እንደሚጎድላቸው አሳይተዋል። በመሆኑም አምላክ ቃሉን ለማስፈጸም ሲል ላደረጋቸው ነገሮች የሰጡት ምላሽ በልባቸው ውስጥ ያለውን ዝንባሌ የሚያሳይ ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ አምላክ የሰጠው የተስፋ ቃል በሰዎች ልብ ውስጥ ያለው ዝንባሌ ግልጽ ሆኖ እንዲታይ ያደርጋል።

ማጣቀሻዎቹን ተመልከት። አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ማጣቀሻ አላቸው። አንተ የምትጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ ማጣቀሻ አለው? ካለው ሊረዳህ ይችላል። የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ላይ የሚገኝ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በ⁠አንደኛ1 ጴጥሮስ 3:​6 ላይ ሣራ ክርስቲያን ሚስቶች ሊኮርጁዋት የሚገባ ሴት መሆኗ ተጠቅሷል። በማጣቀሻው ላይ የሚገኘው ዘፍጥረት 18:​12 ሣራ አብርሃምን “በልብዋ” ጌታ ብላ እንደጠራችው በመግለጽ ይህንን ነጥብ ያጠናክራል። በመሆኑም ለባሏ የምትገዛው ከልቧ ነበር ማለት ነው። ማጣቀሻዎቹ በዚህ መንገድ ተጨማሪ ማስተዋል እንድታገኝ ከማገዝም ሌላ የአንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ወይም የሕጉን ቃል ኪዳን አሠራር እንድታስተውል የሚረዱ ጥቅሶችን ይጠቁሙሃል። ይሁን እንጂ የአንዳንድ ማጣቀሻዎች ዓላማ እንዲህ ያለውን ማብራሪያ መስጠት እንዳልሆነ መዘንጋት የለብህም። ሌላ ተመሳሳይ ሐሳብ ወይም የሕይወት ታሪክ ወይም ቦታ የተጠቀሰበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚጠቁሙ ሊሆኑ ይችላሉ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ኮንኮርዳንስ ተጠቀም። የመጽሐፍ ቅዱስ ኮንኮርዳንስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራባቸውን ቃላት በፊደል ቅደም ተከተል ይዘረዝራል። ምርምር እያደረግህበት ካለኸው ርዕሰ ጉዳይ ጋር ተዛምዶ ያላቸውን ጥቅሶች ለማግኘት ሊረዳህ ይችላል። ጥቅሶቹን አውጥተህ ስትመለከት ሌሎች ጠቃሚ ነጥቦችን ታገኛለህ። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የእውነት ቃል እንዴት እርስ በእርሱ እንደሚደጋገፍ ለማስተዋል ይረዳሃል። የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም መጨረሻዎቹ ገጾች ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራባቸው መሠረታዊ የሆኑ ቃላት ማውጫ አለው። ኮምፕሬሄንሲቭ ኮንኮርዳንስ የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ማውጫ ግን ከዚያ እጅግ የሚበልጥ ይዘት አለው። ይህ መጽሐፍ በቋንቋህ የሚገኝ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት እያንዳንዱ ዋና ቃል የሚገኝባቸውን ጥቅሶች በሙሉ ይጠቁምሃል።

ለምርምር የሚረዱ ሌሎች ጽሑፎችን መጠቀም

በገጽ 33 ላይ የሚገኘው ሣጥን “ታማኝና ልባም ባሪያ” ያዘጋጃቸውን ምርምር ለማድረግ የሚረዱ ሌሎች በርካታ ጽሑፎች ይዘረዝራል። (ማቴ. 24:​45-47) ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ የአርዕስት ማውጫ አላቸው። በአንዳንዶቹ መጻሕፍት የመጨረሻ ገጾች ላይ ደግሞ የቃላት ማውጫ ይገኛል። ይህም የፈለግኸውን ነጥብ ነጥለህ ማውጣት እንድትችል ተብሎ የተዘጋጀ ነው። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች በእያንዳንዱ ዓመት መጨረሻ ላይ በዓመቱ ውስጥ የወጡትን ርዕሶች ያካተተ ማውጫ ይኖራቸዋል።

የትኛው ርዕሰ ጉዳይ በየትኛው ጽሑፍ ላይ እንደሚገኝ ማወቅህ የምታደርገውን ምርምር ያቀላጥፍልሃል። ለምሳሌ ያህል ስለ ትንቢት፣ ስለ መሠረተ ትምህርት፣ ስለ ክርስቲያናዊ ባሕርይ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ስለሚሆኑበት መንገድ ማወቅ ፈልገሃል እንበል። እንዲህ የመሳሰሉትን ነጥቦች መጠበቂያ ግንብ ላይ እንደምታገኝ የታወቀ ነው። ንቁ! መጽሔት ደግሞ ወቅታዊ ሁኔታዎችን፣ በጊዜው ያሉ ችግሮችን፣ ሃይማኖትን፣ ሳይንስን እና በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ሰዎችን ሁኔታ የሚዳስሱ ርዕሶች ይዞ ይወጣል። እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው በተባለው መጽሐፍ ላይ በወንጌል ዘገባ ውስጥ ስላለው ስለ እያንዳንዱ ታሪክ የጊዜ ቅደም ተከተሉን የጠበቀ ማብራሪያ ይገኛል። አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር በቁጥር የሚያብራሩ ጽሑፎችም አሉ። ከእነዚህ መካከል ራእይ​—⁠ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!፣ የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባሉት መጻሕፍትና በሁለት ጥራዝ የተዘጋጀው የኢሳይያስ ትንቢት​—⁠ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን የተባለው መጽሐፍ ይገኙበታል። ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ላይ አብዛኛውን ጊዜ በመስክ አገልግሎት ለሚነሡ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች መልስ ታገኛለህ። ስለ ሌሎች ሃይማኖቶች፣ ስለሚያስተምሯቸው ትምህርቶችና ስለ ታሪካዊ አመሠራረታቸው ይበልጥ ሰፋ ያለ መረጃ ለማግኘት የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት። የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ ውስጥ በዚህ ዘመን ስላሉት የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ የሚገልጽ ዝርዝር ዘገባ ይገኛል። በምድር ዙሪያ እየተከናወነ ያለው የምሥራቹ ስብከት ሥራ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚገልጽ መረጃ ለማግኘት በቅርብ የወጣውን የጥር 1 መጠበቂያ ግንብ መመልከት ትችላለህ። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ግንኙነት ስላላቸው ሰዎች፣ ቦታዎች፣ ነገሮች፣ ቋንቋዎች ወይም ታሪካዊ ክንውኖች ዝርዝር መረጃ የያዘ ግሩም መጽሐፍ ነው።

“የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ።” ከ20 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ የሚገኘው ይህ ማውጫ በተለያዩ ጽሑፎቻችን ላይ የሚገኙ መረጃዎችን ይጠቁምሃል። የርዕሰ ጉዳይ ማውጫና የጥቅስ ማውጫ ተብሎ ለሁለት ተከፍሏል። የርዕሰ ጉዳይ ማውጫውን ለመጠቀም ልትመረምረው የምትፈልገውን ርዕሰ ጉዳይ የሚወክል ቃል ምረጥ። የጥቅስ ማውጫውን ለመጠቀም ደግሞ ከተዘረዘሩት ጥቅሶች መካከል ማብራሪያ ማግኘት የምትፈልግበትን ጥቅስ ምረጥ። በማውጫው ውስጥ ከተካተቱት ጽሑፎች መካከል በቋንቋህ የወጡትና ስለዚያ ርዕሰ ጉዳይ ወይም ጥቅስ ማብራሪያ የተሰጠባቸው ጽሑፎች ካሉ በማውጫው ዝርዝር ውስጥ ታገኛቸዋለህ። በማውጫው ላይ ያሉት አኅጽሮታዊ ስያሜዎች የትኞቹን ጽሑፎች እንደሚያመለክቱ ለማወቅ በመጀመሪያዎቹ ገጾች ላይ ያለውን መግለጫ ተመልከት። (በዚህ መሠረት ለምሳሌ w99 3/1 15 ቢል የ1999 መጠበቂያ ግንብ የመጋቢት 1 እትም ገጽ 15 ማለት ይሆናል።) “የመስክ አገልግሎት ተሞክሮዎች” (“Field Ministry Experiences”) እና “የይሖዋ ምሥክሮች የሕይወት ታሪኮች” (“Life Stories of Jehovah’s Witnesses”) የሚሉት ርዕሶች ለጉባኤው ቀስቃሽ ክፍል ለማቅረብ ሊረዱህ ይችላሉ።

ምርምር ስታደርግ ትኩረትህ በሌሎች ነጥቦች እንዳይወሰድ መጠንቀቅ ይኖርብሃል። አሁን የተነሳኸው ምርምር እያደረግህበት ላለኸው ጉዳይ የሚረዳ ነጥብ ለማግኘት መሆኑን አትዘንጋ። ማውጫው ወደ አንድ ጽሑፍ ከመራህ የተጠቀሰውን ገጽ ገልጠህ እዚያ ላይ ያሉትን ንዑስ ርዕሶችና የአንቀጾቹን የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር በመመልከት ከምትፈልገው ነጥብ ጋር የሚዛመደውን ሐሳብ ብቻ ለማግኘት ጥረት አድርግ። የምትፈልገው ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የተሰጠውን ማብራሪያ ከሆነ በማውጫው ላይ በተጠቀሰው ገጽ ላይ ጥቅሱ የሚገኝበትን ቦታ ለማግኘት ሞክር። ከዚያ በኋላ በጥቅሱ ዙሪያ የሚገኘውን ማብራሪያ ተመልከት።

በሲዲ የተዘጋጁ “የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች።” ኮምፒውተር ማግኘት የምትችል ከሆነ በሲዲ የተዘጋጁትን የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች የመጠቀም አጋጣሚ ሊኖርህ ይችላል። በዚህ ሲዲ አማካኝነት ብዙ ጽሑፎችን ማግኘት ይቻላል። ይህ ፕሮግራም የምትፈልገው ቃል ወይም ጥቅስ የሚገኝበትን ጽሑፍ ፈልጎ ሊያገኝልህ ይችላል። ምርምር ለማድረግ የሚያግዘው ይህ ዝግጅት በቋንቋህ የማይገኝ እንኳ ቢሆን በሰፊው ከሚሠራባቸው ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች መካከል አንተ በምታውቀው በአንዱ ልታገኘው ትችላለህ።

ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች

ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት ለጢሞቴዎስ በጻፈው ሁለተኛ መልእክቱ ላይ ወጣቱ ጢሞቴዎስ “ጥቅልል መጻሕፍቱን በተለይም የብራና መጻሕፍቱን” ወደ ሮም ይዞለት እንዲመጣ ጠይቆታል። (2 ጢሞ. 4:13 አ.መ.ት ) ጳውሎስ እንደ ውድ ነገር የሚመለከታቸውና በጥንቃቄ ያስቀመጣቸው ጽሑፎች ነበሩት። አንተም እንደዚያ ማድረግ ትችላለህ። የመጠበቂያ ግንብ፣ የንቁ! እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎታችን የግል ቅጂዎችህን በጉባኤ ከተጠኑ በኋላ ታስቀምጣቸዋለህ? ከሆነ እነዚህና ሌሎች ክርስቲያናዊ ጽሑፎችህ ምርምር ለማድረግ ይረዱሃል። ብዙ ጉባኤዎች በመንግሥት አዳራሻቸው ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አሏቸው። እነዚህ ጽሑፎች ሁሉም የጉባኤው አባላት መንግሥት አዳራሽ በሚመጡበት ጊዜ እንዲጠቀሙባቸው ሲባል የተዘጋጁ ናቸው።

የግል ፋይል ይኑርህ

ንግግር በምትሰጥበት ወይም በምታስተምርበት ጊዜ ልትጠቀምባቸው የምትችላቸውን ጥሩ ጥሩ ነጥቦች አሰባስብ። በጋዜጣ ወይም በመጽሔት ላይ የወጣ ዜና፣ አኃዛዊ መረጃ ወይም ምሳሌ ስታነብብ ለአገልግሎት የሚጠቅም ሆኖ ካገኘኸው ቀድደህ ወይም ሐሳቡን በሌላ ወረቀት ገልብጠህ አስቀምጠው። ቀኑን፣ ጽሑፉን እና ምናልባትም የጸሐፊውን ወይም የአሳታሚውን ስም ጻፍ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተህ ስታዳምጥ እውነትን ለሌሎች ለማስረዳት ልትጠቀምባቸው የምትችላቸውን ማሳመኛ ነጥቦችና ምሳሌዎች በማስታወሻ አስፍር። አንድ ጥሩ ምሳሌ ከሰማህ በወቅቱ የምትጠቀምበት አጋጣሚ ባይኖርም ጽፈህ አስቀምጠው። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለረጅም ጊዜ በተካፈልህ መጠን የዚያኑ ያህል ብዙ ክፍሎችን ተዘጋጅተህ ማቅረብህ አይቀርም። እነዚህን ክፍሎች የተዘጋጀህባቸውን ማስታወሻዎች አትጣላቸው። በዝግጅትህ ወቅት ያደረግኸው ምርምር ከጊዜ በኋላ ሊጠቅምህ ይችላል።

ሰዎችን ጠይቅ

ከሰዎች ብዙ መረጃ ማግኘት ትችላለህ። ሉቃስ የወንጌል ዘገባውን ሲያጠናቅር የዓይን ምሥክሮችን በመጠየቅ ብዙ መረጃዎችን እንዳሰባሰበ ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 1:⁠1-4) ምናልባት ምርምር ለማድረግ እየጣርክ ስላለህበት ርዕሰ ጉዳይ አንድ ክርስቲያን ጠቃሚ መረጃ ሊሰጥህ ይችል ይሆናል። ክርስቶስ ‘ስለ አምላክ ልጅ ትክክለኛ እውቀት በማግኘት’ እንድናድግ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶችን’ እንደሚጠቀም በ⁠ኤፌሶን 4:​8, 11-16 ላይ ተገልጿል። አምላክን በማገልገል ተሞክሮ ያላቸውን ሰዎች መጠየቅ ጥሩ ጥሩ ሐሳቦችን ለማግኘት ሊረዳህ ይችላል። ከሌሎች ጋር ስለ ጉዳዩ አንስቶ መነጋገርም እነርሱ ያላቸውን አመለካከት እንድታስተውል ስለሚረዳህ ተግባራዊ የሆነ ትምህርት ለመዘጋጀት ያስችልሃል።

የምርምርህን ውጤት ገምግም

ስንዴ ከተወቃ በኋላ ምርቱን ከገለባ መለየት እንደሚያስፈልግ ሁሉ የምርምርህንም ውጤት እንዲሁ መለየት ያስፈልጋል። በምርምርህ ካሰባሰብኻቸው ሐሳቦች መካከል ለጊዜው የማያስፈልግህን መለየት ይኖርብሃል።

ያገኘኸውን ሐሳብ በንግግርህ ላይ የምትጠቀምበት ከሆነ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘በእርግጥ ልጠቀምበት ያሰብኩት ነጥብ ለማቀርበው ርዕሰ ጉዳይ የሚጨምረው ጠቃሚ ነገር ይኖራል? ወይስ የአድማጮችን ትኩረት የሚስብ ሊሆን ቢችልም ላብራራው ከሚገባኝ ርዕሰ ጉዳይ ያርቀኛል?’ በቅርቡ ስለተከሰቱ ሁኔታዎች ለመጥቀስ የምታስብ ወይም በየጊዜው ማሻሻያና ለውጥ የሚያደርገውን የሳይንስ ወይም የሕክምና መስክ በተመለከተ የምትናገር ከሆነ የምታቀርበው መረጃ ወቅታዊ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብሃል። በቆዩ ጽሑፎቻችን ላይ የሚገኙ አንዳንድ ነጥቦችም ማስተካከያ ተደርጎባቸው ሊሆን እንደሚችል አትዘንጋ። ስለዚህ ይህን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ በቅርብ የወጣውን ማብራሪያ ማግኘት ይኖርብሃል።

ከዓለማዊ ምንጮች መረጃዎችን ለማጠናቀር ካሰብህ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የአምላክ ቃል እውነት እንደሆነ አትዘንጋ። (ዮሐ. 17:​17) በአምላክ ዓላማ ፍጻሜ ረገድ ኢየሱስ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። በመሆኑም ቆላስይስ 2:​3 “የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነው” ይላል። የምርምርህን ውጤት ከዚህ አንጻር ገምግመው። ዓለማዊ ምንጮችን ተጠቅመህ የምታደርገውን ምርምር በተመለከተ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘የተጋነነ፣ በግምት ላይ የተመሠረተ ወይም መንፈሳዊ ማስተዋል ያልተንጸባረቀበት ሐሳብ ነውን? ከራስ ወዳድነት በመነጨ ስሜት ወይም ከንግድ ጋር የተያያዘ ዓላማን ለማራመድ የተጻፈ ነውን? ተዓማኒነት ያላቸው ሌሎች ምንጮች ከዚህ አባባል ጋር ይስማማሉ? ከሁሉ በላይ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ይስማማልን?’

ምሳሌ 2:​1-5 እውቀትንና ማስተዋልን ‘እንደ ብርና እንደተቀበረ ገንዘብ’ እንድንፈልግ ያበረታታናል። ይህ ተጋድሎ የሚጠይቅ ቢሆንም በረከት አለው። ምርምር ማድረግ ጥረት እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው። ይሁንና አምላክ ስለ ነገሮች ያለውን አመለካከት ለመረዳት፣ የተሳሳቱ ሐሳቦችን ለማረም እንዲሁም በእውነት ጎዳና ለመጽናት ያስችልሃል። ከዚህም በተጨማሪ የምታቀርበው ክፍል ቁምነገር ያዘለና ሕያው እንዲሆን ስለሚያደርግ አንተም ንግግሩን ለማቅረብ ልባዊ ጉጉት ይኖርሃል፤ አድማጮችም ደስ ብሏቸው ያዳምጡሃል።

ምርምር ለማድረግ ከሚረዱት ከእነዚህ ጽሑፎች መካከል የትኞቹ አሉህ?

  • የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም

  • ኮንፕሪሄንሲቭ ኮንኮርዳንስ

  • መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ!

  • ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር

  • የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች

  • ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል

  • የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ

  • በሲዲ የተዘጋጁ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ