ጥናት 10
በጋለ ስሜት መናገር
በጋለ ስሜት መናገር አንድ ንግግር ሕያው እንዲሆን ይረዳል። ንግግርህ ግንዛቤ የሚያሰፋ መሆን እንዳለበት አይካድም። ሆኖም አድማጮችን በትኩረት እንዲከታተሉ የሚያደርገው በጋለ ስሜት መቅረቡ ነው። ያደግህበት ባሕልም ሆነ የተፈጥሮ ባሕርይህ ምንም ይሁን ምን በጋለ ስሜት መናገር ልታዳብረው የምትችለው ነገር ነው።
በስሜት ተናገር። ኢየሱስ ከአንዲት ሳምራዊት ሴት ጋር ሲነጋገር ይሖዋን የሚያመልኩ ሁሉ “በመንፈስና በእውነት” ማምለክ እንደሚኖርባቸው ጠቅሷል። (ዮሐ. 4:24) አምልኮታቸውን የሚያቀርቡት በአድናቆት ተገፋፍተውና በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኘው እውነት ጋር ተስማምተው መሆን ይኖርበታል ማለት ነው። አንድ ሰው ጥልቅ አድናቆት ካለው ይህ አድናቆቱ በአነጋገሩ መንጸባረቁ አይቀርም። ስለ ይሖዋ ፍቅራዊ ዝግጅቶች ለሌሎች ለመናገር ይገፋፋል። በፊቱ ላይ የሚነበበው ስሜት፣ አካላዊ መግለጫውና ድምፁ ውስጣዊ ስሜቱን የሚያንጸባርቅ ይሆናል።
ታዲያ አንድ ሰው ይሖዋን የሚወድና የሚያቀርበውን ትምህርት ከልብ የሚያምንበት ከሆነ በጋለ ስሜት እንዳይናገር ሊያደርገው የሚችለው ምንድን ነው? ምን እንደሚናገር መዘጋጀቱ ብቻውን በቂ አይሆንም። በርዕሰ ጉዳዩ ሊመሰጥና በስሜት ሊናገር ይገባል። የሚያቀርበው ንግግር ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው እንበል። ንግግሩን ሊያቀርብ ሲነሳ ዝርዝር ጉዳዮቹን ጠንቅቆ ማወቁ ብቻ በቂ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የክርስቶስ ቤዛ ለእርሱም ሆነ ለአድማጮቹ ያለውን ጥቅም በተመለከተ ጥልቅ አድናቆት ሊያድርበት ይገባል። ስለዚህ ድንቅ ዝግጅት ሲማር ለይሖዋ አምላክና ለኢየሱስ ክርስቶስ ያደረበትን ጥልቅ የአመስጋኝነት ስሜት እንደገና መለስ ብሎ ማስታወስ ያስፈልገዋል። በዚህ ዝግጅት አማካኝነት ለሰው ልጆች ስለተዘረጋው ታላቅ ተስፋ ማለትም ወደፊት በምትቋቋመው ምድራዊት ገነት ስለሚገኘው ዘላለማዊ ደስታና ፍጹም ጤና ማሰብ ያስፈልገዋል! ልቡ መነካት ይኖርበታል ማለት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ በእስራኤል አስተማሪ ስለነበረው ስለ ጸሐፊው ዕዝራ ሲናገር “የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፣ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር” ይላል። (ዕዝራ 7:10) እኛም ትምህርቱን ከመዘጋጀት በተጨማሪ ልባችንንም ካዘጋጀን በስሜት መናገር እንችላለን። እውነትን ከልብ በመነጨ ስሜት መናገራችን የሚያዳምጡን ሰዎችም ለእውነት ፍቅር እንዲያድርባቸው ይረዳል።
ስለ አድማጮችህ አስብ። የምትናገረው ነገር አድማጮችህን እንደሚጠቅማቸው ከልብ የምታምን ከሆነም በጋለ ስሜት ልትናገር ትችላለህ። ይህም ማለት ንግግርህን ስትዘጋጅ ጥሩ ጥሩ ነጥቦች ከማሰባሰብ በተጨማሪ የአድማጮችህን ልብ በሚነካ መንገድ ማቅረብ እንድትችል ወደ ይሖዋ መጸለይ ያስፈልግሃል ማለት ነው። (መዝ. 32:8፤ ማቴ. 7:7, 8) አድማጮችህ ትምህርቱን መስማት የሚያስፈልጋቸው ለምን እንደሆነ፣ እንዴት ሊጠቅማቸው እንደሚችልና የትምህርቱን ዋጋማነት እንዲገነዘቡ በሚያስችል መንገድ ልታቀርበው የምትችለው እንዴት እንደሆነ አስብ።
ትምህርቱ ሕያው እስኪሆንልህ ድረስ በደንብ አጥናው። ትምህርቱ የግድ አዲስ መሆን አለበት ማለት አይደለም። ሆኖም ለየት ባለ መንገድ ልታቀርበው ትችላለህ። አድማጮችህ ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና እንዲያጠናክሩ፣ ዝግጅቶቹን እንዲያደንቁ፣ በዚህ አሮጌ ሥርዓት ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን የኑሮ ጭንቀቶች እንዲቋቋሙ፣ ወይም በአገልግሎታቸው ፍሬያማ እንዲሆኑ የሚረዳቸው ነገር ከተዘጋጀህ ንግግርህን በጋለ ስሜት የምታቀርብበት በቂ ምክንያት አለህ ማለት ነው።
ክፍልህ ለሌሎች ማንበብን የሚጠይቅ ከሆነስ? በጋለ ስሜት ለማቅረብ ቃሎቹን በትክክል መጥራትና አሰካክቶ ማንበብ ብቻውን በቂ አይሆንም። የሚነበበውን ጽሑፍ በደንብ አጥናው። ንባቡን የምታቀርበው ከመጽሐፍ ቅዱስ ከሆነ የምታነብበውን ክፍል በተመለከተ ምርምር አድርግ። ዋናው መልእክት ምን እንደሆነ መረዳት ይኖርብሃል። ለአንተም ሆነ ለአድማጮችህ ምን ጠቃሚ መልእክት እንዳዘለ ለማጤንና አድማጮችህ ይህንን እንዲገነዘቡ በሚያስችል መንገድ ለማንበብ ጥረት ልታደርግ ይገባል።
ለመስክ አገልግሎት እየተዘጋጀህ ነው? ከሆነ ከሰዎች ጋር የምትወያይበትን ርዕሰ ጉዳይና ልትጠቀምባቸው ያሰብካቸውን ጥቅሶች ከልስ። በተጨማሪም የምታገኛቸው ሰዎች የሚያሳስባቸው ነገር ምን እንደሆነ ግምት ውስጥ አስገባ። የሰሞኑ ዜና ምንድን ነው? ምን ችግሮች አሉባቸው? እነርሱን የሚያሳስባቸውን ችግር በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያቀርበውን መፍትሔ ማስረዳት እንደምትችል ከተሰማህ ሰዎችን ለማነጋገር ስለምትጓጓ በጋለ ስሜት መናገርህ አይቀርም።
ንግግርህን ሕያው አድርገህ አቅርብ። በጋለ ስሜት እንደምትናገር በግልጽ የሚያሳየው ንግግርህን ሕያው አድርገህ ማቅረብህ ነው። ይህም በፊትህ ላይ መነበብ መቻል ይኖርበታል። ትምህርቱን ከልብ እንደምታምንበት በሚያሳይ መንገድ መናገር እንጂ አክራሪ መስለህ መታየት የለብህም።
ሚዛንን መጠበቅ አስፈላጊ ነው። አንዳንድ ተናጋሪዎች ሁሉም ነጥብ ይነካቸዋል። አንድ ሰው ከልክ በላይ ስሜታዊ ሆኖ የሚናገር ከሆነ አድማጮቹ ስለሚያቀርበው መልእክት ማሰብ ትተው ስለ እርሱ ማሰብ ሊጀምሩ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ተናጋሪዎች ካሉ ይህንን ጉዳይ ማስገንዘብ ያስፈልግ ይሆናል። ዓይን አፋር ከሆኑ ደግሞ ስሜታቸውን በደንብ እንዲገልጡ ማበረታታት ያስፈልግ ይሆናል።
በንግግርህ ወቅት ከአድማጮችህ ጋር ጥሩ ግንኙነት ካለህና ንግግርህን በጋለ ስሜት የምታቀርብ ከሆነ ይህ ስሜት በአድማጮችም ላይ ይንጸባረቃል። አጵሎስ ንግግሩን ሕያው አድርጎ ያቀርብ ስለነበረ ጥሩ ችሎታ ያለው ተናጋሪ እንደሆነ ተገልጿል። በአምላክ መንፈስ የምትቃጠል ከሆነ ንግግርህን ሕያው አድርገህ በማቅረብ አድማጮችህን ለተግባር ማነሳሳት ትችላለህ።—ሥራ 18:24, 25፤ ሮሜ 12:11
ለትምህርቱ የሚስማማ። ንግግርህ ተጀምሮ እስኪያልቅ በጋለ ስሜት በመናገር አድማጮችህን እንዳታሰለች መጠንቀቅ ይኖርብሃል። አድማጮችህ ከተሰላቹ ትምህርቱን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የምትሰጠው ማሳሰቢያ ሰሚ ጆሮ አያገኝም። ይህም አቀራረብህን መለዋወጥ በሚያስችል መንገድ መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ ነው። አቀራረብህ ግዴለሽነት የሚንጸባረቅበት እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብህ። ነጥቦችህን በጥንቃቄ ከመረጥህ ንግግሩን ለመስጠት ልባዊ ፍላጎት ያድርብሃል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ነጥቦች ከሌሎቹ የበለጠ በጋለ ስሜት መናገርን የሚጠይቁ ሊሆኑ ስለሚችሉ እነዚህ ነጥቦች በንግግርህ መሃል በጥሩ ሁኔታ ተቀናብረውና ተሰካክተው መቅረብ ይኖርባቸዋል።
በተለይ ዋና ዋና ነጥቦች በዚህ መንገድ መቅረብ ይኖርባቸዋል። ንግግርህ፣ ደረጃ በደረጃ እየገነባህ ወደ መደምደሚያ የምታደርሳቸው ጉልህ ነጥቦች ሊኖሩት ይገባል። አብዛኛውን ጊዜ አድማጮችህን ለመቀስቀስ የምትጠቀመው በእነዚህ የንግግርህ ዋና ዋና ነጥቦች ነው። አድማጮችህን ካሳመንካቸው በኋላ ለሥራ ልታነሳሳቸው ማለትም ትምህርቱን ተግባራዊ ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ ልታስገነዝባቸው ይገባል። በጋለ ስሜት መናገር የአድማጮችህን ልብ ለመንካት ይረዳል። አንድን ንግግር ሕያው አድርጎ ለማቅረብ ለዚያ የሚያነሳሳ ነገር ሊኖር ይገባል። ስለዚህ የትምህርቱ ይዘት ንግግሩን ሕያው አድርጎ በማቅረብ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።